ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተዉት ንብረት ለእነርሱ ልጅ ባይኖራቸው ግማሹ አላችሁ፡፡ ለእነሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተዉት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ፡፡ (ይህም) በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ለናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶች) ከአራት አንድ አላቸው፡፡ ለእናንተም ልጅ ቢኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው (ይህም በርሷ ከምትናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡) ወላጅም ልጅም የሌለው በጎን ወራሾች የሚወርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ ለእርሱም (ለሟቹ) ወንድም ወይም እኅት (ከእናቱ በኩል ብቻ የኾነ) ቢኖር ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ከዚህም (ከአንድ) የበዙ ቢኾኑ እነርሱ በሲሶው ተጋሪዎች ናቸው፡፡ (ይህም ወራሾችን) የማይጎዳ ኾኖ በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ከአላህም የኾነን ኑዛዜ (ያዛችኋል)፡፡ አላህም ዐዋቂ ቻይ ነው፡፡


الصفحة التالية
Icon