ترجمة سورة التغابن

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة التغابن باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


በሰማያት ውስጥ ያለው በምድርም ውስጥ ያለው ሁሉ ለአላህ ያሞግሳል፡፡ ንግሥናው የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ምስጋናም ለእርሱ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

እርሱ ያ የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከእናንተም ከሓዲ አልለ፡፡ ከእናንተም አማኝ አልለ፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ተመልካች ነው፡፡

ሰማያትንና ምድርን በእውነት ፈጠረ፡፡ ቀረጻችሁም ቅርጻችሁንም አሳመረ፡፡ መመለሻችሁም ወደእርሱ ነው፡፡

በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡ የምትደብቁትንም የምትገልጡትንም ያውቃል፡፡ አላህም በልቦች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

የእነዚያ ከአሁን በፊት የካዱትና የክሕደታቸውን ቅጣት ቅመሱ የተባሉት ሕዝቦች ወሬ አልመጣላችሁምን? ለእነሱም አሳማሚ ቅጣት አልላቸው፡፡

ይህ (ቅጣት) እርሱ መልክተኞቻቸው በአስረጂዎች ይመጡባቸው ስለ ነበሩ «ሰዎችም ይመሩናልን?» ስላሉና ስለካዱ (ከእምነት) ስለ ዞሩም ነው፡፡ አላህም (ከእነሱ እምነት) ተብቃቃ፡፡ አላህም ተብቃቂ ምስጉን ነው፡፡

እነዚያ የካዱትን በፍጹም የማይቀሰሱ መኾናቸውን አሰቡ፡፡ «አይደለም በጌታዬ እምላለሁ፡፡ በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ፡፡ ከዚያም በሠራችሁት ሁሉ ትነገራላችሁ፡፡ ይህም በአላህ ላይ ቀላል ነው፡፡» በላቸው፡፡

በአላህና በመልክተኛውም፡፡ በዚያም ባወረድነው ብርሃን እመኑ፡፡ «አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው» (በላቸው)፡፡

ለመሰብሰቢያ ቀን የሚሰበስብባችሁን ቀን (አስታውሱ)፤ ይህ የመጎዳዳት (መግለጫ) ቀን ነው፡፡ በአላህም የሚያምን ሰው መልካምንም የሚሠራ ከርሱ ኃጢአቶቹን ይሰርይለታል፤ (ይፍቅለታል)፤ ከሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘለዓለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባዋል፤ ይህ ታላቅ ማግኘት ነው፡፡

እነዚያም የካዱና በአንቀጾቻችን ያስተባበሉ እነዚያ በውስጡ ዘውታሪዎች ሲኾኑ የእሳት ጓዶች ናቸው፤ መመለሻቸውም ከፋ!

ከመከራም (ማንንም) አይነካም በአላህ ፈቃድ ቢኾን እንጅ፤ በአላህም የሚያምን ሰው ልቡን (ለትዕግስት) ይመራዋል፤ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

አላህንም ተገዙ፤ መልክተኛውንም ታዘዙ፤ ብትዞሩም (መልክተኛውን አትጎዱም)፤ በመልክተኛውም ላይ ያለበት ግልጽ ማድረስ ብቻ ነው፡፡

አላህ ከርሱ በቀር አምላክ የለም፤ በአላህም ላይ አማኞቹ ይመኩ፡፡

እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሚስቶቻችሁና ከልጆቻችሁ (ከአላህ መንገድ በማስተጓጎል) ለናንተ ጠላቶች የኾኑ አልሉ፤ ስለዚህ ተጠንቀቋቸው፤ ይቅርታ ብታደርጉ ብታልፏቸውም ብተምሩዋቸውም አላህ በጣም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁ ለናንተ መፈተኛ ብቻ ናቸው፤ አላህም እርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አልለ፡፡

አላህንም የቻላችሁትን የክል ፍሩት፤ ትዕዛዙን ስሙም፤ ታዘዙም፤ ለግሱም፤ ለነፍሶቻችሁ መልካምን (ይሰጣችኋልና)፤ የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ፍላጎታቸውን የሚያገኙ ናቸው፡፡

ለአላህ መልካም ብድርን ብታበድሩ (ምንዳውን) ለናንተ ይደራርበዋል፤ ለናንተም ይምራል፤ አላህም አመስጋኝ ታጋሽ ነው፡፡

ሩቁን ምስጢር ግልጹንም ሁሉ ዐዋቂው አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
Icon