ترجمة سورة الحج

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة الحج باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


እናንተ ሰዎች ሆይ! ጌታችሁን ፍሩ የሰዓቲቱ እንቅጥቃጤ በጣም ከባድ ነገር ነውና፡፡

በምታዩዋት ቀን አጥቢ ሁሉ ከአጠባችው ልጅ ትፈዝዛለች፡፡ የእርግዝና ባለቤት የኾነችም ሁሉ እርጉዟን ትጨነግፋለች፡፡ ሰዎቹንም (በድንጋጤ ብርታት) የሰከሩ ኾነው ታያለህ፡፡ እነርሱም (ከመጠጥ) የሰከሩ አይደሉም፡፡ ግን የአላህ ቅጣት ብርቱ ነው፡፡

ከሰዎቹም ያለ ዕውቀት በአላህ ነገር የሚከራከር፤ ሞገደኛ ሰይጣንንም ሁሉ የሚከተል ሰው አልለ፡፡

እነሆ! የተከተለውን ሰው እርሱ ያጠመዋል፡፡ ወደ ነዳጅ እሳት ስቃይም ይመራዋል ማለት በርሱ ላይ ተጽፏል፡፡

እናንተ ሰዎች ሆይ! ከመቀስቀስ በመጠራጠር ውስጥ እንደ ሆናችሁ (አፈጣጠራችሁን ተመልከቱ)፡፡ እኛም ከዐፈር ፈጠርናችሁ፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ ከዚያም ከረጋ ደም፣ ከዚያም ከቁራጭ ሥጋ፣ ፍጥረትዋ ሙሉ ከሆነችና ሙሉ ካልሆነች (ችሎታችንን) ለናንተ ልንገልጽላችሁ ፈጠርናችሁ፡፡ የምንሻውንም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በማሕፀን ውስጥ እናረጋዋለን፡፡ ከዚያም ሕፃን ሆናችሁ እናወጣችኋለን፡፡ ከዚያም ሙሉ ጥንካሪያችሁን ትደርሱ ዘንድ (እናሳድጋችኋለን)፡፡ ከእናንተም የሚሞት ሰው አልለ፡፡ ከእናንተም ከዕውቀት በኋላ ምንንም እንዳያውቅ ወደ ወራዳ ዕድሜ የሚመለስ ሰው አልለ፡፡ ምድርንም ደረቅ ሆና ታያታለህ፡፡ በእርሷም ላይ ውሃን ባወረድን ጊዜ ትላወሳለች፡፡ ትነፋፋለችም፡፡ ውበት ካለው ጎሳ ሁሉ ታበቅላለችም፡፡

ይህ አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡

ሰዓቲቱም መጪ ፣ በእርሷ ፈጽሞ ጥርጣሬ የሌለባት በመሆኗ፣ አላህም በመቃብሮች ውስጥ ያለን ሁሉ የሚቀሰቅስ በመሆኑ ነው፡፡

ከሰዎችም ውስጥ ያለ ዕውቀት፣ ያለ ማስረጃም፣ ያለ አብራሪ መጽሐፍም በአላህ ነገር የሚከራከር ሰው አልለ፡፡

ጎኑን ያጠፈ ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስት (ይከራከራል)፡፡ በቅርቢቱ ዓለም ለእርሱ ውርደት አልለው፡፡ በትንሳኤ ቀንም አቃጣይን ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡

ይህ እጆችህ ባስቀደሙት ኀጢአት አላህም ለባሮቹ ፈጽሞ በዳይ ባለመሆኑ ነው (ይባላል)፡፡

ከሰዎችም (ከሃይማኖት) በጫፍ ላይ ሆኖ አላህን የሚግገዛ ሰው አልለ፡፡ ታዲያ መልካም ነገር ቢያገኘው በእርሱ ይረጋል፡፡ መከራም ብታገኘው በፊቱ ላይ ይገለበጣል፡፡ የቅርቢቱን ዓለምም የመጨረሻይቱንም ከሰረ፡፡ ይህ እርሱ ግልጽ ከሳራ ነው፡፡

ከአላህ ሌላ የማይጎዳውንና የማይጠቅመውን ይግገዛል፡፡ ይህ እርሱ (ከእውነት) የራቀ ስህተት ነው፡፡

ያንን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚቀርብን ይግገዛል፡፡ ረዳቱ ምንኛ ከፋ!

አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፡፡ አላህ የሚሻውን ነገር በእርግጥ ይሠራል፡፡

አላህ (መልክተኛውን) በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም አይረዳውም ብሎ የሚያስብ ሰው ገመድን ወደ ሰማይ ይዘርጋ፡፡ ከዚያም (ትንፋሹ እስኪቆረጥ) ይታነቅ፡፡ ተንኮሉ የሚያስቆጨውን ነገር ያስወግድለት እንደሆነም ይመልከት፡፡

እንደዚሁም (ቁርኣንን) የተብራሩ አንቀጾች አድርገን አወረድነው፡፡ አላህም የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡

እነዚያ ያመኑት፣ እነዚያም ይሁዳውያን የሆኑ፣ ሳቢያኖችም፣ ክርስቲያኖችም፣ መጁሶችም እነዚያም (ጣዖታትን በአላህ) ያጋሩ አላህ በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው በፍርድ ይለያል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ በእርግጥ ዐዋቂ ነውና፡፡

አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣ በምድርም ያለው ሁሉ፣ ፀሐይና ጨረቃም፣ ከዋክብትም፣ ተራራዎችም፣ ዛፎችም፣ ተንቀሳቃሾችም ከሰዎች ብዙዎችም፣ ለርሱ የሚሰግዱለት መሆኑን አታውቁምን ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፡፡ አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለእርሱ ምንም አክባሪ የለውም፡፡ አላህ የሻውን ይሠራልና፡፡

እነዚህ በጌታቸው የተከራከሩ ሁለት ባላጋራዎች ናቸው፡፡ እነዚያም የካዱት ለእነርሱ የእሳት ልብሶች ተለክተውላቸዋል፡፡ ከራሶቻቸው በላይ የፈላ ውሃ ይምቧቧቸዋል፡፡

በሆዶቻቸው ውስጥ ያሉ ቆዳዎቻቸውም በእርሱ ይቀለጣሉ፡፡

ለእነሱም (መቅጫ) ከብረት የሆኑ መዶሻዎች አልሉ፡፡

ከጭንቀት ብርታት የተነሳ ከእርሷ ለመውጣት በፈለጉ ቁጥር ከእርሷ ውስጥ እንዲመለሱ ይደረጋሉ፡፡ «በጣም የሚያቃጥልንም ቅጣት ቅመሱ» (ይባላሉ)፡፡

አላህ እነዚያን ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን ሰዎች በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈስሱባቸውን ገነቶች ያገባቸዋል፡፡ በእርሷ ውስጥ ከወርቅ የሆኑን አንባሮችና ሉልን ይሸለማሉ፡፡ በእርሷ ውስጥ ልብሶቻቸውም ሐር ናቸው፡፡

ከንግግርም ወደ መልካሙ ተመሩ፡፡ ወደ ምስጉንም መንገድ ተመሩ፡፡

እነዚያ የካዱ ከአላህም መንገድና ከዚያም ለሰዎች በውስጡ ነዋሪ ለሆኑትም፣ ከሩቅ ለሚመጡትም እኩል ካደረግነው ከተከበረው መስጊድ (ሰዎችን) የሚከለክሉ (አሳማሚን ቅጣት እናቀምሳቸዋለን)፡፡ በእርሱም ውስጥ (ከትክክለኛ መንገድ) በመዘንበል በዳይ ሆኖ (ማንኛውንም ነገር) የሚፈልግ ሰው ከአሳማሚ ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡

ለኢብራሂምም የቤቱን (የካዕባን) ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት ጊዜ «በእኔ ምንንም አታጋራ፣ ቤቴንም ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት ለሚያጎነብሱትና በግንባራቸውም ለሚደፉት ንጹሕ አድርግላቸው» (ባልነው ጊዜ አስታውስ)፡፡

(አልነውም)፡- በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትዕዛዝ ጥራ፡፡ እግረኞች ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ሆነው ይመጡሃልና፡፡

ለእነሱ የሆኑ ጥቅሞችን ይጣዱ ዘንድ በታወቁ ቀኖችም ውስጥ ከለማዳ እንስሳዎች በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ (ይመጡሃል)፡፡ ከርሷም ብሉ፡፡ ችግረኛ ድሃንም አብሉ፡፡

ከዚያም (እንደ ጠጉርና ጥፍር ያሉትን) ትርፍ አካላቸውንና ዕድፋቸውን ያስወግዱ፡፡ ስለቶቻቸውንም ይሙሉ፤ በጥንታዊውም ቤት ይዙሩ፡፡

(ነገሩ) ይህ ነው፡፡ የአላህንም ሕግጋት የሚያከብር ሰው እርሱ ጌታው ዘንድ ለእርሱ በጣም የተሻለ ነው፡፡ የቤት እንስሳትም (ግመል ከብት በግና ፍየል) በናንተ ላይ (እርም መሆኑ) ከሚነበብላችሁ በስተቀር ለእናንተ ተፈቅዳላችኋለች፡፡ ከጣዖታትም ርክሰት ተጠንቀቁ፡፡ ሐሰትንም ቃል ራቁ፡፡

ለአላህ ታዛዦች በእርሱ የማታገሩ ሆናችሁ (ከሐሰት ራቁ)፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው፤ ከሰማይ እንደ ወደቀና በራሪ እንደምትነጥቀው፣ ወይም ነፋስ እርሱን በሩቅ ስፍራ እንደምትጥለው ብጤ ነው፡፡

(ነገሩ) ይህ ነው፡፡ የአላህንም የሃይማኖት ምልክቶች የሚያከብር ሰው እርሷ ከልቦች የኾነች ጥንቃቄ ናት፡፡

ለእናንተ በእርሷ እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ጥቅሞች አሏችሁ፡፡ ከዚያም (የማረጃ) ስፍራዋ እጥንታዊው ቤት አጠገብ ነው፡፡

ለሕዝብም ሁሉ (ወደ አላህ) መስዋዕት ማቅረብን ደነገግን፡፡ ከቤት እንስሳት በሰጣቸው ሲሳይ ላይ የአላህን ስም ብቻ ያወሱ ዘንድ (አዘዝናቸው)፡፡ አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱም ብቻ ታዘዙ፡፡ ለአላህ ተዋራጆችንም አብስራቸው፡፡

እነዚያን አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚጨነቁትን፣ በደረሰባቸውም (መከራ) ላይ ታጋሾችን፣ ሶላትንም አስተካክለው ሰጋጆችን፣ ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚለግሱትን (አብስር)፡፡

ግመሎችንም ለእናንተ ከአላህ ሃይማኖት ምልክቶች አደረግናቸው፡፡ በእርሷ ለእናንተ መልካም ጥቅም አላችሁ፡፡ በእርሷም ላይ (ስታርዷት) በሶስት እግሮችዋ ቆማ የተሰለፈች ሆና የአላህን ስም አውሱ፡፡ ጎኖቻቸውም በወደቁ ጊዜ ከእርሷ ብሉ፡፡ ለማኝንም ለልመና የሚያገዳድምንም አብሉ፡፡ እንደዚሁ ታመሰግኑ ዘንድ ለእናንተ ገራናት፡፡

አላህን ሥጋዎቿም ደሞቿም ፈጽሞ አይደርሰውም፡፡ ግን ከእናንተ የሆነው ፍራቻ ይደርሰዋል፡፡ እንደዚሁ አላህን በመራችሁ ላይ ልታከብሩት ለእናንተ ገራት፡፡ በጎ ሠሪዎችንም አብስር፡፡

አላህ ከእነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡ አላህ ከዳተኛን ውለታቢስን ሁሉ አይወድም፡፡

ለእነዚያ ለሚገደሉት (ምእመናን) እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው (መጋደል) ተፈቀደላቸው፡፡ አላህም እነርሱን በመርዳት ላይ በእርግጥ ቻይ ነው፡፡

ለእነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ከማለታቸው በስተቀር ያለ አግባብ ከአገራቸው የተባረሩ ለሆኑት (ተፈቀደ)፡፡ አላህ ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መገፍተሩ ባልነበረ ኖሮ ገዳማት፣ ቤተክርስቲያኖችም፣ ምኩራቦችም በውስጣቸው የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጊዶችም፤ በተፈረሱ ነበር፡፡ አላህም ሃይማኖቱን የሚረዳውን ሰው በእርግጥ ይረዳዋል፡፡ አላህ ብርቱ አሸናፊ ነውና፡፡

(እነርሱም) እነዚያ በምድር ላይ ብናስመቻቸው ሶላትን እንደሚገባ የሚያስተካክሉ፣ ዘካንም የሚሰጡ፣ በደግ ነገርም የሚያዝዙ፣ ከመጥፎ ነገርም የሚከለክሉ ናቸው፡፡ የነገሮቹም ሁሉ መጨረሻ ወደ አላህ ነው፡፡

ቢያስተባብሉህም ከእነሱ በፊት የኑሕ ሕዝቦች ዓድና ሰሙድም በእርግጥ አስተባብለዋል፡፡

የኢብራሂምም ሕዝቦች የሉጥም ሕዝቦች (አስተባብለዋል)፡፡

የመድየንም ሰዎች (አስተባብለዋል)፡፡ ሙሳም ተስተባብሏል፡፡ ለከሓዲዎቹም ጊዜ ሰጠኋቸው፡፡ ከዚያም ያዝቸው፡፡ ጥላቻዬም እንዴት ነበረ!

ከከተማም እርሷ በደለኛ ሆና ያጠፋናትና እርሷ በጣሪያዎቿ ላይ ወዳቂ የሆነችው ብዙ ናት፡፡ ከተራቆተችም የውሃ ጉድጓድ ከተገነባም ሕንፃ (ያጠፋነው ብዙ ነው)፡፡

ለእነርሱም በእነርሱ የሚያውቁባቸው ልቦች ወይም በእነርሱ የሚሰሙባቸው ጆሮች ይኖሯቸው ዘንድ በምድር ላይ አይሄዱምን እነሆ ዓይኖች አይታወሩም ግን እነዚያ በደረቶች ውስጥ ያሉት ልቦች ይታወራሉ፡፡

አላህም ቀጠሮውን በፍጹም የማይጥስ ሲሆን በቅጣት ያቻኩሉሃል፡፡ እጌታህም ዘንድ አንዱ ቀን ከምትቆጥሩት (ቀን) እንደ ሺሕ ዓመት ነው፡፡

ከከተማ እርሷ በዳይ ሆና ለእርሷ ጊዜ የሰጠኋትና ከዚያም የያዝኳት ብዙ ናት፡፡ መመለሻም ወደኔ ብቻ ነው፡፡

«እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ለእናንተ ግልጽ አስጠንቃቂ ብቻ ነኝ» በላቸው፡፡

እነዚያም ያመኑ መልካም ሥራዎችንም የሠሩ ለእነርሱ ምህረትና ያማረ ሲሳይ አላቸው፡፡

እነዚያም የሚያመልጡ መስሏቸው ተዓምራቶቻችንን በመንቀፍ የተጉ እነሱ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡

ከመልክተኛና ከነቢይም ከአንተ በፊት አንድንም አላክንም ባነበበ (እና ዝም ባለ) ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ (ማጥመሚያን ቃል) የሚጥል ቢሆን እንጅ፡፡ ወዲያውም አላህ ሰይጣን የሚጥለውን ያስወግዳል፡፡ ከዚያም አላህ አንቀጾቹን ያጠነክራል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡

ሰይጣን የሚጥለውን ነገር ለእነዚያ በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ላለባቸው ልቦቻቸውም ደረቆች ለሆኑት ፈተና ሊያደርግ (ይጥላል)፡፡ በዳዮችም ከእውነት በራቀ ጭቅጭቅ ውስጥ ናቸው፡፡

እነዚያም ዕውቀትን የተሰጡት እርሱ (ቁርኣን) ከጌታህ የኾነ እውነት መኾኑን እንዲያውቁና በእርሱ እንዲያምኑ ልቦቻቸውም ለእርሱ እንዲረኩ (ያጠነክራል)፡፡ አላህም እነዚያን ያመኑትን ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ መሪ ነው፡፡

እነዚያ የካዱት ሰዎች ሰዓቲቱ በድንገት እስከምትመጣባቸው ወይም (ከደግ ነገር) መካን የሆነው ቀን ቅጣት እስከሚመጣባቸው ድረስ ከእርሱ (ከቁርኣን) በመጠራጠር ውስጥ ከመሆን አይወገዱም፡፡

በዚያ ቀን ንግሥናው የአላህ ብቻ ነው፡፡ በመካከላቸው ይፈርዳል፡፡ እነዚያም ያመኑት መልካም ሥራዎችንም የሠሩት በመደሰቻ ገነቶች ውስጥ ናቸው፡፡

እነዚያም የካዱት በአንቀጾቻችንም ያስተባበሉት እነዚያ ለእነርሱ አዋራጅ ቅጣት አላቸው፡፡

እነዚያም በአላህ ሃይማኖት የተሰደዱ ከዚያም የተገደሉ ወይም የሞቱ አላህ መልካምን ሲሳይ በእርግጥ ይሰጣቸዋል፡፡ አላህም እርሱ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው፡፡

የሚወዱትን መግቢያ (ገነትን) በእርግጥ ያገባቸዋል፡፡ አላህም በእርግጥ ዐዋቂ ታጋሽ ነው፡፡

(ነገሩ) ይህ ነው፡፡ በእሱ በተበደለበትም ብጤ የተበቀለ ሰው ከዚያም በእርሱ ላይ ግፍ የተዋለበት አላህ በእርግጥ ይረዳዋል፡፡ አላህ ይቅር ባይ መሓሪ ነውና፡፡

ይህ አላህ ሌሊትን በቀን ውስጥ የሚያስገባ ቀንንም በሌሊት ውስጥ የሚያስገባ (ቻይ) አላህም ሰሚ ተመልካች በመሆኑ ነው፡፡

ይህ አላህ እርሱ እውነት በመሆኑ ከእርሱም ሌላ የሚግገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሸት በመሆኑ አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመኾኑ ነው፡፡

አላህ ከሰማይ ውሃን ማውረዱንና ምድር የምትለመልም መኾኗን አታይምን አላህ ሩኅሩኅ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡

በሰማያት ውስጥ ያለውና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፡፡ አላህም እርሱ ተብቃቂው ምስጉኑ ነው፡፡

አላህ በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ ለእናንተ የገራላችሁ፣ መርከቦችንም በባሕር ውስጥ በፈቃዱ የሚንሻለሉ ሲኾኑ (የገራላችሁ) መኾኑን፣ ሰማይንም በፈቃዱ ካልኾነ በምድር ላይ እንዳትወድቅ የሚይዛት መኾኑን አላየህምን አላህ ለሰዎች በእርግጥ ሩኅሩኅ አዛኝ ነው፡፡

እርሱም ያ ሕያው ያደረጋችሁ ነው፡፡ ከዚያም ይገድላችኋል፡፡ ከዚያም ሕያው ያደርጋችኋል፡፡ ሰው በእርግጥ በጣም ከሓዲ ነው፡፡

ለየሕዝቡ ሁሉ እነሱ የሚሠሩበት የኾነን ሥርዓተ ሃይማኖት አድርገናል፡፡ ስለዚህ በነገሩ አይከራከሩህ፡፡ ወደ ጌታህ መንገድም ጥራ፡፡ አንተ በእርግጥ በቅኑ መንገድ ላይ ነህና፡፡

ቢከራከሩህም «አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡

አላህ በትንሣኤ ቀን በዚያ በእርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ሁሉ በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡

አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መኾኑን አታውቅምን ይህ በመጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ነው፡፡ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡

ከአላህ ሌላም በእርሱ ማስረጃን ያላወረደበትን ለእነርሱም በእርሱ ዕውቀት የሌላቸውን ነገር ይግገዛሉ፡፡ ለባዳዮችም ምንም ረዳት የላቸውም፡፡

አንቀጾቻችንም የተብራሩ ኾነው በእነሱ ላይ በሚነበቡ ጊዜ በእነዚያ በካዱት ሰዎች ፊቶች ላይ ጥላቻን ታውቃለህ፡፡ በእነዚያ በእነሱ ላይ አንቀጾቻችንን በሚያነቡት ላይ በኃይል ሊዘልሉባቸው ይቃረባሉ፡፡ «ከዚህ ይልቅ የከፋን ነገር ልንገራችሁን» በላቸው፡፡ «(እርሱም) እሳት ናት፡፡ አላህ ለእነዚያ ለካዱት ሰዎች ቀጥሯታል፡፡ ምን ትከፋም መመለሻ!»

እናንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምሳሌ ተገለጸላችሁ፡፡ ለእርሱም አድምጡት፡፡ እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው (ጣዖታት) ዝንብን ፈጽሞ አይፈጥሩም፡፡ እርሱን (ለመፍጠር) ቢሰበሰቡም እንኳን (አይችሉም)፡፡ አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከእርሱ አያስጥሉትም፡፡ ፈላጊውም ተፈላጊውም ደከሙ፡፡

አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡ አላህ በጣም ኃያል አሸናፊ ነው፡፡

አላህ ከመላእክት ውስጥ መልክተኞችን ይመርጣል፡፡ ከሰዎችም (እንደዚሁ)፤ አላህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡

በስተፊታቸው ያለን በስተኋላቸውም ያለን ሁሉ ያውቃል፡፡ ወደ አላህም ነገሮች ሁሉ ይመለሳሉ፡፡

እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! (በስግደታችሁ) አጎንብሱ፣ በግንባራችሁም ተደፉ፣ ጌታችሁንም ተገዙ፣ በጎንም ነገር ሥሩ፣ ልትድኑ ይከጀልላችኋልና፡፡

በአላህም ሃይማኖት ተገቢውን ትግል ታገሉ፡፡ እርሱ መርጧችኋል፡፡ በናንተም ላይ በሃይማኖቱ ውስጥ ምንም ችግር አላደረገባችሁም፡፡ የአባታችሁን የኢብራሂምን ሃይማኖት ተከተሉ፡፡ እርሱ ከዚህ በፊት ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡ በዚህም (ቁርኣን)፤ መልክተኛው በእናንተ ላይ መስካሪ እንዲሆን እናንተም በሰዎቹ ላይ መስካሪዎች እንድትኾኑ (ሙስሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል)፡፡ ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፣ ዘካንም ስጡ፣ በአላህም ተጠበቁ፣ እርሱ ረዳታችሁ ነው፡፡ (እርሱ) ምን ያምር ጠባቂ! ምን ያምርም ረዳት!
Icon