ترجمة سورة سبأ

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة سبأ باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ምስጋና ለዚያ በሰማያትም ያለ በምድርም ያለ ሁሉ የርሱ ለኾነው ለአላህ ይገባው፡፡ በመጨረሻይቱም ዓለም ምስጋና ለእርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ብልሃተኛው ውስጠ ዐዋቂው ነው፡፡

በምድር ውስጥ የሚገባውን ሁሉ ከእርሷም የሚወጣውን ከሰማይም የሚወርደውን በእርሷም ውስጥ የሚያርገውን ሁሉ ያውቃል፡፡ እርሱም አዛኙ መሓሪው ነው፡፡

እነዚያ የካዱትም «ሰዓቲቱ አትመጣብንም» አሉ፡፡ በላቸው «አይደለም፤ ሩቁን ሁሉ ዐዋቂ በኾነው ጌታዬ እምላለሁ፡፡ በእርግጥ ትመጣባችኋለች፡፡ የብናኝ ክብደት ያክል እንኳ በሰማያትና በምድር ውስጥ ከእርሱ አይርቅም፡፡ ከዚህ ያነሰም ኾነ የበለጠ የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢኾን እንጅ፡፡»

እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን ሊመነዳ (ሰዓቲቱ ትመጣባችኋለች)፤ እነዚያ ለእነርሱ ምህረትና የከበረ ሲሳይ አላቸው፡፡

እነዚያም የሚያመልጡ መስሏቸው አንቀጾቻችንን ለማፍረስ የጣሩ እነዚያ ለእነርሱ ከመጥፎ ቅጣት የኾነ አሳማሚ ስቃይ አላቸው፡፡

እነዚያም ዕውቀትን የተሰጡት ያንን ከጌታህ ወዳንተ የተወረደውን እርሱ እውነትና አሸናፊ ምስጉን ወደ ኾነው አላህ መንገድ የሚመራ መኾኑን ያውቃሉ፡፡

እነዚያም የካዱት «(ሙታችሁ) መበጣጠስን ሁሉ በተበጣጠሳችሁ ጊዜ እናንተ በአዲስ መፈጠር ውስጥ ትኾናላችሁ ብሎ የሚነግራችሁን ሰው እናሳያችሁን?» አሉ፡፡

በአላህ ላይ ውሸትን ቀጠፈን? ወይስ በእርሱ ዕብደት አለበትን? (አሉ)፡፡ እንዳሉት አይደለም፡፡ እነዚያ በመጨረሻይቱ (ዓለም) የሚያምኑት (በእርሷ) በቅጣት ውስጥ (አሁን) በራቀ ስህተትም ውስጥ ናቸው፡፡

ከሰማይና ከምድር በፊታቸውና በኋላቸው ወዳለው ሁሉ አይመለከቱምን? ብንሻ በእነርሱ ምድርን እንደረባባቸዋለን፡፡ ወይም በእነርሱ ላይ ከሰማይ ቁራጭን እንጥልባቸዋለን፤ በዚህ ውስጥ (ወደ ጌታው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ምልክት አለበት፡፡

ለዳውድም ከእኛ የኾነን ችሮታ በእርግጥ ሰጠነው፡፡ (አልንም)፡-«ተራራዎች ሆይ! ከእርሱ ጋር ውዳሴን መላልሱ፡፡ በራሪዎችንም (ገራንለት)፡፡ ብረትንም ለእርሱ አለዘብንለት፡፡»

ሰፋፊዎችን ጥሩሮች ሥራ፡፡ በአሠራርዋም መጥን፡፡ መልካምንም ሥራ ሥሩ፡፡ እኔ የምትሠሩትን ነገር ሁሉ ተመልካች ነኝና (አልነው)፡፡

ለሱለይማንም ነፋስን የቀትር በፊት ጉዞዋ የወር መንገድ የቀትር በኋላ ጉዞዋም የወር መንገድ ሲኾን ገራንለት፡፡ የነሐስንም ምንጭ ለእርሱ አፈሰስንለት፡፡ ከጋኔኖችም በጌታው ፈቃድ በፊቱ የሚሠሩን (አደረግንለት)፡፡ ከነርሱም ውስጥ ከትእዛዛችን ዝንፍ የሚል ከነዲድ እሳት ቅጣት እናቀምሰዋለን፡፡

ከምኩራቦች፣ ከምስሎችም እንደ ገንዳ ከኾኑ ገበታዎችም፣ ከተደላደሉ ታላላቅ ድስቶችም የሚሻውን ሁሉ ይሠሩለታል፡፡ (አልናቸውም) «የዳውድ ቤተሰቦች ሆይ! አመስጋኞች ኾናችሁ (ለጌታችሁ) ሥሩ፡፡» ከባሮቼ በጣም አመስጋኞቹም ጥቂቶች ናቸው፡፡

በእርሱም ላይ ሞትን በፈጸምንበት ጊዜ መሞቱን በትሩን የምትበላ ተንቀሳቃሽ ምስጥ እንጂ ሌላ አላመለከታቸውም፡፡ በወደቀ ጊዜም ጋኔኖች ሩቅን ምስጢር የሚያወቁ በኾኑ ኖሮ በአዋራጅ ስቃይ ውስጥ የማይቆይ እንደነበሩ ተረዱ፡፡

ለሰበእ በመኖሪያቸው በእውነት አስደናቂ ምልክት ነበራቸው፡፡ ከግራና ከቀኝ ሁለት አትክልቶች (ነበሯቸው)፡፡ «ከጌታችሁ ሲሳይ ብሉ፡፡ ለእርሱም አመስግኑ፡፡ (አገራችሁ) ውብ አገር ናት፡፡ (ጌታችሁ) መሓሪ ጌታም ነው» (ተባሉ)፡፡

(ከማመስገን) ዞሩም፡፡ በእነርሱም ላይ የግድቡን ጎርፍ ለቀቅንባቸው፡፡ በአትክልቶቻቸውም ሁለት አትክልቶች፣ ባለመርጋጋ ፍሬዎችን፣ ባለጠደቻና ከቁርቁራም ባለጥቂት ዛፎችን ለወጥናቸው፡፡

በመካዳቸው ይህንን መነዳናቸው፤ (እንዲህ ያለውን ቅጣት) በጣም ከሓዲን እንጂ ሌላውን እንቀጣለን?

በእነርሱና በዚያች በውስጧ በረከትን ባደረግንባት አገር (በሻም) መካከልም ቅጥልጥል ከተሞችን አደረግን፡፡ በእርሷም ጉዞን ወሰንን፡፡ «ጸጥተኞች ኾናችሁ በሌሊቶችም በቀኖችም ተጓዙ፤» (አልን)፡፡

«ጌታችን ሆይ! በጉዞዎቻችን መካከል አራርቅልን» አሉም፡፡ ነፍሶቻቸውንም በደሉ፡፡ (መገረሚያ) ወሬዎችም አደረግናቸው፡፡ መበታተንንም ሁሉ በታተንናቸው፡፡ በዚህ ውስጥ በጣም ታጋሽና አመስጋኝ ለሆነ ሁሉ መገሰጫዎች አሉበት፡፡

ኢብሊስም በእነርሱ ላይ ምኞቱን በእርግጥ ፈጸመ፤ ከአመኑትም የሆኑት ጭፍሮች በስተቀር ተከተሉት፡፡

በመጨረሻይቱም ዓለም የሚያምነውን ከዚያ እርሱ ከእርሷ በመጠራጠር ውስጥ ከሆነው ሰው ለይተን እንድናውቅ እንጅ በእነርሱ ላይ ለእርሱ ምንም ስልጣን አልነበረውም፡፡ ጌታህም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡

«እነዚያን ከአላህ ሌላ (አማልክት ብላችሁ) የምታስቧቸውን ጥሩ፡፡ በሰማያትም በምድርም ውስጥ የብናኝ ክብደት ያክል ምንንም አይችሉም፡፡ ለእነርሱም በሁለቱም ውስጥ ምንም ሽርክና የላቸውም፡፡ ከእነርሱም ለእርሱ ምንም አጋዥ የለውም፤» በላቸው፡፡

ምልጃም እርሱ ለፈቀደለት ሰው ብቻ ቢሆን እንጂ እርሱ ዘንድ ምንም አትጠቅምም፡፡ ከልቦቻቸው ላይ ድንጋጤው በተገለጸም ጊዜ (ተማላጆቹ) «ጌታችሁ ምን አለ?» ይላሉ፡፡ (አማላጆቹ) «እውነትን አለ፤ እርሱም ከፍተኛው ታላቁ ጌታ ነው» ይላሉ፡፡

«ከሰማያትና ከምድር (ዝናብንና በቃይን) የሚሰጣችሁ ማነው?» በላቸው፡፡ «አላህ ነው፡፡ እኛ ወይም እናንተ በትክክለኛው መንገድ ላይ ወይም በግልጽ መሳሳት ውስጥ ነን» በላቸው፡፡

«ከአጠፋነው ጥፋት አትጠየቁም፡፡ ከምትሠሩትም ሥራ አንጠየቅም» በላቸው፡፡

«ጌታችን በመካከላችን ይሰበስባል፡፡ ከዚያም በመካከላችን በእውነት ይፈርዳል፡፡ እርሱም በትክክል ፈራጁ ዐዋቂው ነው» በላቸው፡፡

«እነዚያን ተጋሪዎች አድርጋችሁ በእርሱ ያስጠጋችኋቸውን (ጣዖታት) አሳዩኝ፡፡ ተዉ (አታጋሩ)፤ በእውነቱ እርሱ አሸናፊው ብልሃተኛው አላህ ነው» በላቸው፡፡

አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡

«እውነተኞችም እንደ ሆናችሁ ይህ ቀጠሮ መቼ ነው?» ይላሉ፡፡

«ለእናንተ ከእርሱ አንዲትንም ሰዓት የማትዘገዩበት የማትቀድሙበትም የቀጠሮ ቀን አላችሁ» በላቸው፡፡

እነዚያ የካዱትም በዚህ ቁርኣን በዚያ ከበፊቱ ባለውም (መጽሐፍ) በጭራሽ አናምንም አሉ፡፡ በዳዮችም ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ንግግርን የሚመላለሱ ሆነው በጌታቸው ዘንድ በሚቆሙ ጊዜ ብታይ ኖሮ፤ (አስደናቂን ነገር ታይ ነበር)፡፡ እነዚያ የተዋረዱት ለእነዚያ ለኮሩት «እናንተ ባልነበራችሁ ኖሮ አማኞች በኾን ነበር» ይላሉ፡፡

እነዚያ የኮሩት ለእነዚያ ለተዋረዱት «ከትክክለኛው እምነት ከመጣላችሁ በኋላ እኛ ከለከልናችሁን? አይደለም (እናንተው) ከሓዲዎች ነበራችሁ» ይሏቸዋል፡፡

እነዚያም የተዋረዱት ለእነዚያ ለኮሩት «አይደለም፤ በአላህ እንድንክድና ለእርሱ ባላንጣዎችን እንድናደርግ ስታዙን (የከለከለን) የሌሊትና የቀን ዱለታችሁ ነው» ይላሉ፡፡ ቅጣቱንም ባዩ ጊዜ ጸጸትን ይገልጻሉ፡፡ በእነዚያም በካዱት አንገቶች ላይ እንዛዝሎችን እናደርጋለን፡፡ ይሠሩት የነበሩትን እንጂ ሌላን ይመነዳሉን?

በከተማም አስፈራሪን አልላክንም፡፡ ነዋሪዎችዋ «እኛ በዚያ በርሱ በተላካችሁበት ከሓዲዎች ነን» ያሉ ቢኾኑ እንጂ፡፡

«እኛም በገንዘቦችና በልጆች ይበልጥ የበዛን ነን፡፡ እኛም የምንቀጣ አይደለንም» አሉ፡፡

በላቸው «ጌታዬ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ ያጠባልም፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡»

ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁም ያች እኛ ዘንድ መቅረብን የምታቀርባችሁ አይደለችም፡፡ ያመነና መልካምን የሠራ ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያ ለእነርሱ በሠሩት መልካም ሥራ እጥፍ ምንዳ አልላቸው፡፡ እነርሱም በገነት ሰገነቶች ውስጥ ጸጥተኞች ናቸው፡፡

እነዚያም የሚያቅቱ መስሏቸው አንቀጾቻችንን ለማበላሸት የሚጥሩት እነዚያ በቅጣቱ ውስጥ የሚጣዱ ናቸው፡፡

«ጌታዬ ሲሳይን ከባሮቹ ለሚሻው ሰው ያሰፋል፡፡ ለእርሱም ያጠብባል፡፡ ከማንኛውም ነገር የምትለግሱትን እርሱ ይተካዋል፡፡ እርሱም ከሲሳይ ሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነው» በላቸው፡፡

ሁሉንም በሚሰበስባቸውና ከዚያም ለመላእክቶቹ «እነዚህ እናንተን ይግገዙ ነበሩን?» በሚላቸው ቀን (የሚኾነውን አስታውስ)፡፡

(መላእክቶቹም) «ጥራት ይገባህ ከእነርሱ ሌላ ረዳታችን አንተ ብቻ ነህ፡፡ (እንደሚሉት) አይደለም ይልቁንም ጋኔንን ይግገዙ ነበሩ፡፡ አብዛኞቻቸው በእነርሱ አማኞች ናቸው» ይላሉ፡፡

ዛሬም ከፊላችሁ ለከፊሉ መጥቀምንም ኾነ መጉዳትን አይችሉም፡፡ ለእነዚያም ለበደሉት «ያችን በእርሷ ታስተባብሉባት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» እንላቸዋለን፡፡

በእነርሱም ላይ አንቀጾቻችን ግልጽ ኾነው በተነበቡላቸው ጊዜ «ይህ አባቶቻችሁ ይግገዙት ከነበሩት ነገር ሊከለክላችሁ የሚፈልግ ሰው እንጂ ሌላ አይደለም» አሉ፡፡ «ይህም (ቁርኣን) የተቀጣጠፈ ውሸት ነው እንጂ ሌላ አይደለም» አሉ፡፡ እነዚያም የካዱት እውነቱ በመጣላቸው ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው እንጂ ሌላ አይደለም» አሉ፡፡

የሚያጠኑዋቸው የኾኑ መጽሐፍቶችንም ምንም አልሰጠናቸውም፡፡ ከአንተ በፊትም አስፈራሪ ነቢይን ወደእነርሱ አልላክንም፡፡

እነዚያም ከእነርሱ በፊት የነበሩት አስተባብለዋል፡፡ የሰጠናቸውንም ከዐስር አንዱን (እነዚህ) አልደረሱም፡፡ መልክተኞቼንም አስተባበሉ፤ (ነቀፍኳቸውም)፡፡ መንቀፌም እንዴት ነበር!

«የምገስጻችሁ ባንዲት ነገር ብቻ ነው፡፡ (እርሷም) ሁለት ሁለት አንድ አንድም ኾናችሁ ለአላህ እንድትነሱ ከዚያም በጓደኛችሁ (በሙሐመድ) ምንም ዕብደት የሌለበት መኾኑን መርምራችሁ እንድትርረዱ ነው፡፡ እርሱ ለእናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም» በላቸው፡፡

«ከዋጋ ማንኛውም የጠየቅኋችሁ ቢኖር እርሱ ለእናንተው ነው፤ ዋጋዬ በአላህ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይደለም፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡

«ጌታዬ እውነትን ያወርዳል፡፡ ሩቅ የኾኑትን ምስጢሮች ሁሉ ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡

«እውነቱ መጣ፡፡ ውሸትም መነሻም መድረሻም የለውም (ተወገደ)» በላቸው፡፡

«ብሳሳት የምሳሳተው በራሴ ላይ ብቻ ነው፡፡ ብመራም ጌታዬ ወደኔ በሚያወርደው ነው፡፡ እርሱ ሰሚ ቅርብ ነውና» በላቸው፡፡

በደነገጡና ማምለጫ በሌላቸው ጊዜ ከቅርብ ስፍራም በተያዙ ጊዜ (ኹኔታቸውን) ብታይ ኖሮ (አስደናቂን ነገር ባየህ ነበር)፡፡

«በእርሱም (አሁን) አመንን» ይላሉ፡፡ ለእነርሱም ከሩቅ ስፍራ (እምነትን) በቀላል ማግኘት ከየታቸው?

በፊትም በእርሱ በእርግጥ ክደዋል፡፡ ከሩቅ ስፍራም በግምት ንግግርን ይጥላሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በመሰሎቻቸው እንደ ተሠራውም ብጤ በእነርሱና በሚፈልጉት መካከል ተጋረደ፡፡ እነርሱ በእርግጥ በአወላዋይ ጥርጣሬ ውስጥ ነበሩና፡፡
Icon