ترجمة سورة الأحقاف

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة الأحقاف باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡
የመጽሐፉ መወረድ አሸናፊ ጥበበኛ ከኾነው አላህ ነው፡፡
ሰማያትንና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በምርና የተወሰነ ጊዜንም በመለካት እንጅ (ለቀልድ) አልፈጠርናቸውም፡፡ እነዚያ የካዱትም ከተስፈራሩት ነገር (ትተው) ዘዋሪዎች ናቸው፡፡
«ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን አያችሁን? ከምድር ምንን እንደ ፈጠሩ አሳዩኝ፡፡ ወይም በሰማያት ለእነርሱ (ከአላህ ጋር) መጋራት አላቸውን? (ያማልዱናል በማለታችሁ) እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ከዚህ (ቁርኣን) በፊት የኾነን መጽሐፍ ወይም ከዕውቀት የኾነ ቅርስን አምጡልኝ» በላቸው፡፡
እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስም ለእርሱ የማይመልስለትን (ጣዖት) ከአላህ ሌላ ከሚጠራ ሰው ይበልጥ የተሳሳተ ማነው? እነርሱም ከጥሪያቸው ዘንጊዎች ናቸው፡፡
ሰዎችም በተሰበሰቡ ጊዜ (ጣዖቶቹ) ለእነርሱ ጠላቶች ይኾናሉ፡፡ (እነሱን) መገዛታቸውንም ከሓዲዎች ይኾናሉ፡፡
በእነርሱም ላይ አንቀጾቻችን ግልጾች ኾነው በተነበቡ ጊዜ እነዚያ እውነቱን በመጣላቸው ጊዜ የካዱትን «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ፡፡
ይልቁንም ቀጠፈው ይላሉን? «ብቀጥፈው ለእኔ ከአላህ (ቅጣት ለማዳን) ምንንም አትችሉም፡፡ እርሱ ያንን በእርሱ የምትቀባዥሩበትን ዐዋቂ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በእርሱ በቃ፡፡ እርሱም መሓሪው አዛኙ ነው» በላቸው፡፡
«ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም፡፡ በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሥሠራም አላውቅም፡፡ ወደእኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላን አልከተልም፡፡ እኔም ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም» በላቸው፡፡
(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው «እስቲ ንገሩኝ፤ (ቁርኣኑ) ከአላህ ዘንድ ቢኾን፡፡ በእርሱም ብትክዱ፣ ከእስራኤል ልጆችም መስካሪ በብጤው (በእርሱ) ላይ ቢመሰክር፣ ቢያምንም፣ (ከእምነት) ብትኮሩም፣ (በዳይ አትኾኑምን?)» አላህ በእርግጥ በደለኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡
እነዚያንም የካዱት ሰዎች ስለእነዚያ ስለ አመኑት ሰዎች (እምነቱ) «መልካም ነገር በኾነ ኖሮ ወደርሱ ባልቀደሙን ነበር» አሉ፡፡ በእርሱም ባልተመሩ ጊዜ «ይህ (ቁርኣን) ጥንታዊ ቅጥፈት ነው» ይላሉ፡፡
ከበፊቱም የሙሳ መጽሐፍ መሪና ጸጋ ሲኾን አልለ፡፡ ይህም እነዚያን የበደሉትን ሊያስፈራራ በዐረብኛ ቋንቋ ሲኾን (የፊቶቹን መጻሕፍት) አረጋጋጭ መጽሐፍ ነው፡፡ ለበጎ አድራጊዎችም ብስራት ነው፡፡
እነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ያሉ፣ ከዚያም ቀጥ ያሉ በነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፡፡ እነርሱም አያዝኑም፡፡
እነዚያ የገነት ጓዶች ናቸው፡፡ በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ሲኾኑ፡፡ በዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ታላቅን ምንዳ (ይምመነዳሉ)፡፡
ሰውንም በወላጆቹ በጎ መዋልን በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ በችግር ላይ ኾና አረገዘችው፡፡ በችግርም ወለደችው፡፡ እርግዝናውና ከጡት መለያውም ሰላሳ ወር ነው፡፡ ጥንካሬውንም ወቅት በደረሰ ጊዜ (ከዚያ አልፎ) አርባ ዓመትንም በደረሰ ጊዜ «ጌታዬ ሆይ! ያችን በእኔ ላይና በወላጆቼ ላይ የለገስካትን ጸጋህን እንዳመሰግን የምትወደውንም መልካም ሥራ እንድሠራ ምራኝ፡፡ ዘሮቼንም ለእኔ አብጅልኝ፡፡ እኔ ወዳንተ ተመለስኩ፡፡ እኔም ከሙስሊሞ ነኝ» አለ፡፡
እነዚህ (ይህንን ባዮች) በገነት ጓዶች ውስጥ ሲኾኑ እነዚያ ከሠሩት ሥራ መልካሙን ከነሱ የምንቀበላቸውና ከኀጢአቶቻቸውም የምናልፋቸው ናቸው፡፡ ያንን ተስፋ ይስሰጡት የነበሩትን እውነተኛ ቀጠሮ (እንሞላላቸዋለን)፡፡
ያንንም ለወላጆቹ «ፎህ ለእናንተ ከእኔ በፊት የክፍል ዘመናት ሰዎች (ሳይወጡ) በእርግጥ ያለፉ ሲኾኑ (ከመቃብር) እንድወጥጣ ታስፈራሩኛላችሁን?» ያለውን ሁለቱም (ወላጆቹ) አላህን የሚለምኑ ሲኾኑ (ባታምን) «ወዮልህ፡፡ እመን፡፡ የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ ነው፡፡»
እነዚህ እነዚያ ከጋኔንም ከሰውም ከእነርሱ በፊት ካለፉት ሕዝቦች ጋር ቃሉ በእነርሱ ላይ የተረጋገጠባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ ከሳሪዎች ነበሩና፡፡
ለሁሉም ከሠሩት ሥራ ደረጃዎች አልሏቸው፡፡ ሥራዎቻቸውንም ይሞላላቸው ዘንድ (ይህንን መነዳቸው) እነርሱም አይበደሉም፡፡
እነዚያም የካዱት በእሳት ላይ በሚጋፈጡ ቀን «ጣፋጮቻችሁን በአነስተኛይቱ ሕይወታችሁ አሳለፋችሁ፡፡ በእርሷም ተጣቀማችሁ፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ ያለ አግባብ ትኮሩ በነበራችሁትና ታምጹ በነበራችሁት ዛሬ የውርደትን ቅጣት ትምመነዳላችሁ» (ይባላሉ)፡፡
የዓድንም ወንድም (ሁድን) ሕዝቦቹን በአሕቃፍ ባስጠነቀቀ ጊዜ አውሳለቸው፡፡ በስተፊቱና በስተኋላውም ብዙ አስፈራሪዎች በእርግጥ አልፈዋል፡፡ «ከአላህ በስተቀር አትግገዙ እኔ በእናነተ ላይ የከባድ ቀንን ቅጣት እፈራላችኋለሁና» በማለት (ባሰጠነቀቀ ጊዜ)፡፡
«ከአማልክቶቻችን ልታዞረን መጣህብን? ከውነተኞቹም እንደኾንክ የምትዝትብንን (ቅጣት) አምጣው» አሉ፡፡
«ዕውቀቱ አላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ያን በእርሱ የተላክሁበትንም አደርስላችኋለሁ፡፡ ግን እኔ የምትሳሳቱ ሕዝቦች ኾናችሁ አያችኋለሁ» አላቸው፡፡
ሸለቆዎቻቸውን ተቅጣጪ አግዳሚ ደመና ኾኖ ባዩትም ጊዜ «ይህ አዝናቢያችን የኾነ ደመና ነው» አሉ፡፡ (ሁድም) «አይደለም፤ እርሱ ያ በእርሱ የተቻኮላችሁበት መዐት ነው፡፡ በውስጧ አሳማሚ ስቃይ ያለባት ነፋስ ናት፡፡
በጌታዋ ትዕዛዝ አንዳቹን ሁሉ ታጠፋለች» (አላቸው)፡፡ ከመኖሪያዎቻቸውም በስተቀር ምንም የማይታዩ ኾኑ፡፡ እንደዚሁ አመጸኞችን ሕዝቦች ሁሉ እንቀጣለን፡፡
በዚያም እናንተን በእርሱ ባላስመቸንበት (ድሎት) በእርግጥ አስመቸናቸው፡፡ ለእነርሱም መስሚያንና ማያዎችን፣ ልቦችንም አደረግንላቸው፡፡ ግን መስሚያቸውና ማያዎቻቸው፣ ልቦቻቸውም ከእነሱ ምንም አልጠቀሟቸውም፡፡ በአላህ አንቀጾች ይክዱ ነበሩና፡፡ በእነርሱም ላይ ያ በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ቅጣት ወረደባቸው፡፡
ከከተሞችም እነዚያን በአካባቢያችሁ የነበሩትን በእርግጥ አጠፋን (ከክሕደታቸው) ይመለሱም ዘንድ አስረጂዎችን መላለስን፡፡
እነዚያም መቃረቢያ ይኾኑ ዘንድ ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው የያዙዋቸው አይረዷቸውም ኖሯልን? በእርግጥ ከነሱ ራቁ፡፡ ይህም ውሸታቸውና (በልማድ) ይቀጥፉት የነበሩት ነው፡፡
ከጋኔን የኾኑን ጭፍሮች ቁርኣንን የሚያዳምጡ ሲኾኑ ወዳንተ ባዞርን ጊዜም (አስታውስ)፡፡ በተጣዱትም ጊዜ ዝም ብላችሁ አዳምጡ ተባባሉ፡፡ በተጨረሰም ጊዜ አስጠንቃቂዎች ኾነው ወደ ሕዝቦቻቸው ተመለሱ፡፡
አሉም «ሕዝቦቻችን ሆይ! እኛ ከሙሳ በኋላ የተወረደን መጽሐፍ በፊቱ ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ ወደ እውነትና ወደ ቀጥተኛ መንገድ የሚመራ የኾነን ሰማን፡፡
ወገኖቻችን ሆይ! የአላህን ጠሪ ተቀበሉ፡፡ በእርሱም እመኑ፡፡ (አላህ) ከኀጢአቶቻችሁ ለእናንተ ይምራልና፡፡ ከአሳማሚ ቅጣትም ያድናችኋልና፡፡
የአላህንም ጠሪ የማይቀበል ሰው በምድር ውስጥ የሚያመልጥ አይደለም፡፡ ከእርሱም ሌላ ለእርሱ ረዳቶች የሉትም፡፡ እነዚያ በግልጽ ስሕተት ውስጥ ናቸው» (አሉ)፡፡
ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ እነርሱንም በመፍጠሩ ያልደከመው አላህ ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ መኾኑን አላስተዋሉምን? (በማስነሳት) ቻይ ነው፡፡ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡
እነዚያም የካዱት ሰዎች በእሳት ላይ በሚቀረቡ ቀን «ይህ እውነት አይደለምን?» (ይባላሉ)፡፡ «እውነት ነው፤ በጌታችን ይኹንብን» ይላሉ፡፡ (አላህም) «ትክዱ በነበራችሁት ምክንያት ቅጣቱን ቅመሱ» ይላቸዋል፡፡
ከመልክተኞችም የቆራጥነት ባለቤቶች የኾኑት እንደ ታገሱ ሁሉ ታገስ፡፡ ለእነርሱም (ለሕዝቦችህ ቅጣት) አትቻኮል፡፡ ያንን የሚስፈራሩበትን ቅጣት በሚያዩ ቀን እነርሱ ከቀን አንዲትን ሰዓት አንጅ እንዳልቆዩ ይኾናሉ፡፡ (ይህ ቁርኣን) በቂ ግሳጼ ነው አመጸኞችም ሕዝቦች እንጅ (ሌሎች) ይጥጠፋሉን?
Icon