ترجمة سورة المدّثر

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة المدّثر باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

አንተ (ልብስህን) ደራቢው ሆይ!
ተነሳ አስጠንቅቅም፡፡
ጌታህንም አክብር፡፡
ልብስህንም አጥራ፡፡
ጣዖትንም ራቅ፡፡
ማብዛትንም የምትፈልግ ኾነህ፤ (በረከትን) አትለግስለለ
ለጌታህም (ትዕዛዝ) ታገሥ፡፡
በቀንዱም በተነፋ ጊዜ (ነገሩ ይበረታል)፡፡
ይህም (ጊዜ) ያ ቀን አስቸጋሪ ቀን ነው፡፡
በከሓዲዎች ላይ ገር ያልኾነ ነው፡፡
አንድ ኾኖ ከፈጠርኩት ሰው ጋር ተዎኝ (እኔ እበቃሃለሁ)፡፡
ለእርሱም የተዘረጋን ገንዘብ (በያይነቱ) ያደረግሁለት፡፡
(በያደባባዩ) ተገኝዎች የኾኑ ወንዶች ልጆችንም፡፡
ለእርሱም (ኑሮውን) መዘርጋትን የዘረጋሁለት (ከኾነ ሰው ገር ተዎኝ)፡፡
ከዚያም ልጨምርለት ይከጅላል፡፡
ይከልከል፤ እርሱ ለአንቀጾቻችን በእርግጥ ተቃዋሚ ነበር፡፡
በእርግጥ ችግርን አስገድደዋለሁ፡፡
እርሱ (በቁርኣን ነገር) ሐሰበ፤ ገመተም፡፡
ተረገመም፤ እንዴት ገመተ!
ከዚያም (ከሞት በኋላ) ተረገመ፡፡ እንዴት ገመተ!
ከዚያም እንደ ገና (በቁርኣኑ ነገር) ተመለከተ፡፡
ከዚያም ፊቱን አጨፈገገ፤ አኮማተረም፡፡
ከዚያም (ከማመን) ዞረ፤ ኮራም፡፡
አለም «ይህ (ከሌላ) የሚቀዳ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
«ይህ የሰው ቃል እንጅ ሌላ አይደለም፡፡»
በሰቀር ውስጥ በእርግጥ አገባዋለሁ፡፡
ሰቀር ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ?
(ያገኘችውን ሁሉ) አታስቀርም አትተውምም፡፡
ቆዳን በጣም አክሳይ ናት፡፡
በእርሷም ላይ አሥራ ዘጠኝ (ዘበኞች) አሉባት፡፡
የእሳትንም ዘበኞች መላእክት እንጅ ሌላ አላደረግንም፡፡ ቁጥራቸውንም ለእነዚያ ለካዱት መፈተኛ እንጅ አላደረግንም፡፡ እነዚያ መጽሐፍን የተሰጡት እንዲያረጋግጡ፣ እነዚያም ያመኑት እምነትን እንዲጨምሩ፣ እነዚያም መጽሐፍን የተሰጡትና ምእምናኖቹ እንዳይጠራጠሩ፣ እነዚያም በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸው (መናፍቃን)፣ ከሓዲዎችም አላህ በዚህ (ቁጥር) ምን ምሳሌ ሽቷል? እንዲሉ (እንጅ አላደረግንም)፡፡ እንደዚሁ አላህ የሚሻውን ያጠምማል፡፡ የሚሻውንም ያቀናል፡፡ የጌታህንም ሰራዊት (ልክ) ከርሱ በቀር ማንም አያውቅም፡፡ እርሷም (የሰቀር እሳት) ለሰዎች መገሰጫ እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡
(ከክህደት) ይከልከሉ፡፡ በጨረቃ እምላለሁ፡፡
በሌሊቱም በኼደ ጊዜ፡፡
በንጋቱም ባበራ ጊዜ፡፡
እርሷ (ሰቀር) ከታላላቆቹ (አደጋዎች) አንዷ ናት፡፡
ለሰዎች አስፈራሪ ስትኾን፡፡
ከእናንተ (ወደ በጎ ነገር) መቅደምን ወይም ወደ ኋላ መቅረትን ለሻ ሰው (አስፈራሪ ስትኾኑ)፡፡
ነፍስ ሁሉ በሠራችው ሥራ ተያዥ ናት፡፡
የቀኝ ባለቤቶች ብቻ ሲቀሩ፡፡
(እነርሱስ) በገነቶች ውስጥ ይጠያየቃሉ፡፡
ከአመጸኞቹ ኹነታ፡፡
(ይሏቸዋልም) «በሰቀር ውስጥ ምን አገባችሁ?»
(እነርሱም) ይላሉ «ከሰጋጆቹ አልነበርንም፡፡
«ለድኾችም የምናበላ አልነበርንም፡፡
«ከዘባራቂዎቹም ጋር እንዘባርቅ ነበርን፡፡
«በፍርዱ ቀንም እናስተባብል ነበርን፡፡
«እርግጠኛው (ሞት) እስከ መጣን ድረስ፡፡»
የአማላጆችም ምልጃ አትጠቅማቸውም፡፡
ከግሣጼዬም (ከቁርኣን) የሚያፈገፍጉት ለእነርሱ ምን አልላቸው?
እነርሱ ልክ ደንባሪዎች የሜዳ አህዮች ይመስላሉ፡፡
ከዐንበሳ የሸሹ፡፡
ይልቁንም ከእነርሱ እያንዳንዱ ሰው ሁሉ የተዘረጉ ጽሑፎችን እንዲስሰጥ ይፈልጋል፡፡
ይከልከሉ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻይቱን ዓለም (ቅጣት) አይፈሩም፡፡
ይከልከሉ፡፡ እርሱ (ቁርኣን) መገሠጫ ነው፡፡
ስለዚህ የሻ ሰው ይገሰጽበታል፡፡
አላህም ካልሻ በስተቀር አይገሠጹም፡፡ እርሱ (አላህ) የመፈራት ባለቤት የምሕረትም ባለቤት ነው፡፡
Icon