ترجمة سورة الممتحنة

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة الممتحنة باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጠላቶቼንና ጠላቶቻችሁን ወዳጆች አድርገችሁ አትያዙ፡፡ ከእውነቱ የመጣላችሁን ሃይማኖት በእርግጥ የካዱ ሲኾኑ ውዴታን ወደእነርሱ ታደርሳላችሁ፡፡ መልክተኛውንና እናንተን በአላህ በጌታችሁ ስላመናችሁ (ከመካ) ያወጣሉ፡፡ በመንገዴ ለመታገልና ውዴታዬን ለመፈለግ የወጣችሁ እንደኾናችሁ (ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው)፡፡ እኔ የምትደብቁትንና የምትገልጹትን ሁሉ የማውቅ ስኾን ወደእነርሱ በፍቅር ትመሳጠራላችሁ፡፡ ከእናንተም (ይህንን) የሚሠራ ሰው ቀጥተኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ፡፡
ቢያሸንፏችሁ ለእናንተ ጠላቶች ይኾናሉ፡፡ እጆቻቸውንና ምላሶቻቸውንም ወደእናንተ በክፉ ይዘረጋሉ፡፡ ብትክዱም ተመኙ፡፡
ዘመዶቻችሁም፣ ልጆቻችሁም በትንሣኤ ቀን አይጠቅሟችሁም፤ (አላህ) በመካከላችሁ ይለያል፡፡ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡
በኢብራሂምና በእነዚያ ከእርሱ ጋር በነበሩት (ምእምናን) መልካም መከተል አለቻችሁ፡፡ ለሕዝቦቻቸው «እኛ ከእናንተ ከአላህ ሌላ ከምትግገዙትም ንጹሖች ነን፡፡ በእናንተ ካድን፡፡ በአላህ አንድ ብቻ ሲኾን እስከምታምኑ ድረስ በእኛና በእናንተ መካከል ጠብና ጥላቻ ዘወትር ተገለጸ፡፡» ባሉ ጊዜ (መልካም መከተል አለቻችሁ)፡፡ ኢብራሂም ለአባቱ «እኔ ለአንተ ከአላህ (ቅጣት) ምንም የማልጠቅም ስኾን ለአንተ በእርግጥ ምሕረትን እለምንልኻለሁ» ማለቱ ብቻ ሲቀር፡፡ «ጌታችን ሆይ! በአንተ ላይ ተመካን፡፡ ወደ አንተም ተመለስን መመለሻም ወደ አንተ ብቻ ነው፤» (ባለው ተከተሉት)፡፡
ጌታችን ሆይ! ለእነዚያ ለካዱት ሰዎች መሞከሪያ አታድርገን፡፡ ለእኛም ምሕረት አድርግልን፡፡ ጌታችን ሆይ! አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህ፡፡
ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን ለሚፈራ ሰው በእነርሱ መልካም መከተል አልላችሁ፡፡ የሚዞርም ሰው (ራሱን ይጎዳል)፡፡ አላህ ተብቃቂው ምስጉኑ እርሱ ብቻ ነውና፡፡
በናንተና በእነዚያ ከእነርሱ ጋር በተጣላችሁት ሰዎች መካከል አላህ መፋቀርን ሊያደርግ ይቻላል፡፡ አላህም ቻይ ነው፡፡ አላህም በጣም አዛኝ ነው፡፡
ከእነዚያ በሃይማኖት ካልተጋደሏችሁ ከአገሮቻችሁም ካላወጡዋችሁ (ከሓዲዎች) መልካም ብትውሉላቸውና ወደእነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፡፡ አላህ ትክክለኞችን ይወዳልና፡፡
አላህ የሚከለክላችሁ ከእነዚያ በሃይማኖት ከተጋደሉዋችሁ፣ ከቤቶቻችሁም ካወጡዋችሁ፣ እናንተም በማውጣት ላይ ከረዱት (ከሓዲዎች) እንዳትወዳጁዋቸው ብቻ ነው፡፡ ወዳጅ የሚያደርጓቸውም ሰዎች እነዚያ እነርሱ በዳዮቹ ናቸው፡፡
እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ምእምናት ስደተኞች ኾነው በመጧችሁ ጊዜ (ለሃይማኖት መሰደዳቸውን) ፈትኑዋቸው፡፡ አላህ በእምነታቸው ይበልጥ ዐዋቂ ነው፡፡ አማኞችም መኾናቸውን ብትውቁ ወደ ከሓዲዎቹ አትመልሱዋቸው፡፡ እነርሱ (ሴቶቹ) ለእነርሱ የተፈቀዱ አይደሉምና፡፡ እነርሱም (ወንዶቹ) ለእነርሱ አይፈቀዱምና፡፡ ያወጡትንም ገንዘብ ስጧቸው፡፡ መህራቸውንም በሰጣችኋቸው ጊዜ ብታገቡዋቸው በእናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም፡፡ የከሓዲዎቹንም ሴቶች የጋብቻ ቃል ኪዳኖች አትያዙ፤ ያወጣችሁትንም ገንዘብ ጠይቁ፡፡ ያወጡትንም ይጠይቁ፡፡ ይህ የአላህ ፍርድ ነው፡፡ በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ከሚስቶቻችሁም ወደ ከሓዲዎቹ አንዳቸው ቢያመልጧችሁ ቀጥሎም ብትዘምቱባቸው ለእነዚያ ሚስቶቻቸው ለኼዱባቸው (ሰዎች) ያወጡትን ብጤ ስጧቸው፡፡ ያንንም እናንተ በርሱ ያመናችሁበትን አላህን ፍሩ፡፡
አንተ ነቢዩ ሆይ! ምእምናቶቹ በአላህ ምንንም ላያጋሩ፣ ላይሰርቁም ላያመነዝሩም፣ ልጆቻቸውን ላይገድሉም፣ በእጆቻቸውና በእግሮቻቸው መካከልም የሚቀጣጥፉት የኾነን ኃጢኣት ላያመጡ (ላይሠሩ) በበጎም ሥራ ትዕዛዝህን ላይጥሱ ቃል ኪዳን ሊገቡልህ በመጡህ ጊዜ ኪዳን ተጋባቸው፡፡ ለእነርሱም አላህን ምሕረት ለምንላቸው፡፡ አላህ በጣም መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
እላንተ ያመናቸሁ ሆይ! አላህ በእነርሱ ላይ የተቆጣባቸውን ሕዝቦች አትወዳጁ፡፡ ከሓዲዎች ከመቃብር ሰዎች ተስፋ እንደቆረጡ ከመጨረሻይቱ ዓለም (ምንዳ) በእርግጥ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡
Icon