ﮯ
ترجمة معاني سورة فاطر
باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation
.
ﰡ
ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሶስት ሶስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፡፡ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡
አላህ ለሰዎች ከችሮታ የሚከፍታት ለእርሷ ምንም አጋጅ የላትም፡፡ የሚያግደውም ከእርሱ በኋላ ለእርሱ ምንም ለቃቂ የለውም፡፡ እርሱም አሸነፊው ጥበበኛው ነው፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! በእናንተ ላይ (ያለውን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ ከአላህ ሌላ ፈጣሪ አለን? ከሰማይና ከምድርም ሲሳይን የሚሰጣችሁ አለን? ከእርሱ በስተቀር አምላክ (ሰጪም) የለም፡፡ ታዲያ ወዴት ትዞራላችሁ፡፡
ቢያስተባብሉህም ከአንተ በፊት የነበሩ መልክተኞች በእርግጥ ተስተባብለዋል፡፡ ወደ አላህም ነገሮች ሁሉ ይመለሳሉ፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! የአላህ ቀጠሮ እውነት ነው፡፡ የቅርቢቱም ሕይወት አታታላችሁ፡፡ አታላዩም (ሰይጣን) በአላህ (መታገስ) አያታላችሁ፡፡
ሰይጣን ለናንተ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ጠላት አድርጋችሁ ያዙት፡፡ ተከታዮቹን የሚጠራው ከእሳት ጓዶች እንዲኾኑ ብቻ ነው፡፡
እነዚያ የካዱት ለእነርሱ ብርቱ ቅጣት አልላቸው፡፡ እነዚያም ያመኑትና በጎ ስራዎችን የሠሩት ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አልላቸው፡፡
መጥፎ ሥራው የተሸለመለትና መልካም አድርጎ ያየው ሰው (አላህ እንዳቀናው ሰው ነውን?) አላህም የሚሻውን ሰው ያጠምማል፡፡ የሚሻውንም ያቀናል፡፡ ስለዚህ በእነርሱ ላይ (ባለመቅናታቸው) ስለመቆላጨት ነፍስህ አትጥፋ፡፡ አላህ የሚሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡
አላህም ያ ነፋሶችን የላከ ነው፡፡ ደመናዎችንም ትቀሰቅሳለች፤ ወደ ሙት (ድርቅ) አገርም እንነዳዋለን፡፡ በእርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው እናደርጋታለን፡፡ ሙታንንም መቀስቀስ እንደዚሁ ነው፡፡
ማሸነፍን የሚፈልግ የኾነ ሰው አሸናፊነት ለአላህ ብቻ ነው፤ (እርሱን በመግገዛት ይፈልገው)፡፡ መልካም ንግግር ወደርሱ ይወጣል፡፡ በጎ ሥራም ከፍ ያደርገዋል፡፡ እነዚያም መጥፎ ሥራዎችን የሚዶልቱ ለእነሱ ብርቱ ቅጣት አልላቸው፡፡ የእነዚያም ተንኮል እርሱ ይጠፋል፡፡
አላህም ከዐፈር፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ፈጠራችሁ፡፡ ከዚያም ጎሳዎች አደረጋችሁ፡፡ ሴትም አታረግዝም አትወልድምም በዕውቀቱ ቢኾን እንጂ፡፡ ዕድሜው ከሚረዘምም አንድም አይረዘምም ከዕድሜውም አይጎደልም በመጽሐፉ ውስጥ ያለ ቢኾን እንጂ፡፡ ይህ በአላህ ላይ ገር ነው፡፡
ሁለቱ ባሕሮችም አይተካከሉም! ይህ ጣፋጭ፣ ጥምን ቆራጭ፣ መጠጡ በገር ተዋጭ ነው፡፡ ይህኛውም ጨው መርጋጋ ነው፡፡ እርጥብ ስጋንም ከሁሉም ትበላላችሁ፡፡ (ከጨው ባሕር) የምትለብሷትንም ጌጥ ታወጣላችሁ፡፡ ከችሮታው ልትፈልጉና ልታመሰግኑም መርከቦችን በእርሱ ውስጥ ውሃውን ቀዳጆች ኾነው (ሲንሻለሉ) ታያለህ፡፡
ሌሊትን በቀን ውስጥ ያስገባል፡፡ ቀንንም በሌሊት ውሰጥ ያስገባል፤ ፀሐይንና ጨረቃንም ገራ፡፡ ሁሉም እተወሰነ ጊዜ ድረስ ይሮጣሉ፡፡ ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ንግሥናው የእርሱ ብቻ ነው፡፡ እነዚያም ከእርሱ ሌላ የምትግገዟቸው የተምር ፍሬ ሽፋን እንኳ አይኖራቸውም፡፡
ብትጠሩዋቸው ጥሪያችሁን አይሰሙም፡፡ ቢሰሙም ኖሮ ለእናንተ አይመልሱላችሁም፡፡ በትንሣኤም ቀን (እነርሱን በአላህ) ማጋራታችሁን ይክዳሉ፡፡ እንደ ውስጠ ዐዋቂው ማንም አይነግርህም፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! እናንተ (ሁል ጊዜ) ወደ አላህ ከጃዮች ናችሁ፡፡ አላህም እርሱ ተብቃቂው ምስጉኑ ነው፡፡
ቢሻ ያስወግዳችኋል፡፡ አዲስንም ፍጡር ያመጣል፡፡
ይህም በአላህ ላይ ምንም አስቸጋሪ አይደለም፡፡
ኀጢአትን ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላዋን ሸክም አትሸከምም፡፡ የተከበደችም (ነፍስ) ወደ ሸክሟ ብትጣራ (ተጠሪው) የቅርብ ዝምድና ባለቤት ቢኾንም እንኳ ከእርሷ አንዳችን የሚሸከምላት አታገኝም፡፡ የምታስጠነቅቀው እነዚያን ጌታቸውን በሩቅ የሚፈሩትን፣ ሶላትንም አስተካክለው ያደረሱትን ብቻ ነው፡፡ የተጥራራም ሰው የሚጥራራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ መመለሻም ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡
ዕውሩና የሚያየውም አይስተካከሉም፡፡
ጨለማዎችና ብርሃንም፤ (እንደዚሁ)፡፡
ጥላና ሐሩርም፡፡
ሕያዋንና ሙታንም አይስተካከሉም፡፡ አላህ የሚሻውን ሰው ያሰማል፡፡ አንተም በመቃብር ውስጥ ያሉትን አሰሚ አይደለህም፡፡
አንተ አስጠንቃቂ እንጂ ሌላ አይደለህም፡፡
እኛ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን በእውነቱ (መምሪያ) ላክንህ፡፡ ማንኛይቱም ሕዝብ በውስጧ አስፈራሪ ያላለፈባት የለችም፡፡
ቢያስተባብሉህም እነዚያ ከበፊታቸው የነበሩት በእርግጥ አስተባብለዋል፡፡ መልክተኞቻቸው በግልጽ ማስረጃዎችን፣ በጽሑፎችም፣ አብራሪ በኾነ መጽሐፍም መጥተዋቸዋል፡፡
ከዚያም እነዚያን የካዱትን ያዝኳቸው፡፡ ቅጣቴም እንዴት ነበር! (በስፍራው ነው)፡፡
አላህ ከሰማይ ውሃን ማውረዱን አላየህምን? በእርሱም ዓይነቶቻቸው የተለያዩ ፍሬዎችን አወጣን፡፡ ከጋራዎችም መልኮቻቸው የተለያዩ ነጮች፣ ቀዮችም፣ በጣም ጥቁሮችም የኾኑ መንገዶች አልሉ፡፡
ከሰዎችም፣ ከተንቀሳቃሾችም፣ ከቤት እንሰሳዎችም እንደዚሁ መልኮቻቸው የተለያዩ አልሉ፡፡ አላህን ከባሮቹ ውስጥ የሚፈሩት ዐዋቂዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ አላህ አሸናፊ መሓሪ ነው፡፡
እነዚያ የአላህን መጽሐፍ የሚያነቡ፣ ሶላትንም አስተካክለው ያደረሱ፣ ከሰጠናቸውም ሲሳይ በምስጢርም ኾነ በግልጽ የለገሱ፣ በፍጹም የማትከስርን ንግድ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡
ምንዳዎቻቸውን ሊሞላላቸው፣ ከችሮታውም ሊጨምርላቸው (ተስፋ ያደርጋሉ)፡፡ እርሱ በጣም መሓሪ አመስጋኝ ነውና፡፡
ያም ከመጽሐፉ ወዳንተ ያወረድንልህ ከበፊቱ ላለው አረጋጋጭ ሲኾን እርሱ እውነት ነው፡፡ አላህ በርግጥ በባሮቹ ውስጥ ዐዋቂ ተመልካች ነው፡፡
ከዚያም እነዚያን ከባሮቻችን የመረጥናቸውን መጽሐፉን አወረስናቸው፡፡ ከእነርሱም ነፍሱን በዳይ አልለ፡፡ ከእነርሱም መካከለኛ አልለ፡፡ ከእነሱም በአላህ ፈቃድ በበጎ ሥራዎች ቀዳሚ አልለ፡፡ ያ (ማውረስ)፤ እርሱ ታላቅ ችሮታ ነው፡፡
የመኖሪያ ገነቶችን በውስጧ የወርቅ አንባሮችን፣ ሉልንም የሚሸለሙ ኾነው ይገቡባታል፡፡ በእርሷ ውስጥ አልባሳታቸውም ሐር ነው፡፡
ይላሉም «ምስጋና ለእዚያ ከእኛ ላይ ሐዘንን ላስወገደልን አላህ ይገባው፡፡ ጌታችን በጣም መሓሪ አመስጋኝ ነውና፡፡
(እርሱም) ያ ከችሮታው የዘላለም መኖሪያን አገር ያሰፈረን ነው፡፡ በእርሷ ውስጥ መከራ አይነካንም፡፡ በእርሷም ውስጥ ድካም አይነካንም፡፡»
እነዚያ የካዱትም ለእነርሱ የገሀነም እሳት አልላቸው፡፡ ይሞቱ ዘንድ በእነርሱ ላይ (በሞት) አይፈረድም፡፡ ከቅጣቷም ከእነርሱ አይቀለልላቸውም፡፡ እንደዚሁ ከሓዲን ሁሉ እንመነዳለን፡፡
እነርሱም በርሷ ውስጥ እርዳታን በመፈለግ በኀይል ይጮሃሉ፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእዚያ እንሠራው ከነበርነው ሌላ በጎ ሥራን እንሠራ ዘንድ አውጣን» (ይላሉ)፡፡ «በእርሱ ውስጥ ያስታወሰ ሰው የሚገሰጽበትን ዕድሜ አላቆየናችሁምን? አስጠንቃቂውም መጥቶላችኋል (አስተባብላችኋልም)፡፡ ስለዚህ ቅመሱ፡፡ ለበደለኞችም ምንም ረዳት የላቸውም» (ይባላሉ)፡፡
አላህ የሰማያትንና የምድርን ምስጢር በእርግጥ ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱ በልቦች ውስጥ ያለን ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡
እርሱ ያ በምድር ውስጥ ምትኮች ያደረጋችሁ ነው፡፡ የካደም ሰው ክህደቱ በእርሱው ላይ ብቻ ነው፡፡ ከሓዲዎችንም ክሕደታቸው ከጌታቸው ዘንድ መጠላትን እንጂ ሌላ አይጨመርላቸውም፡፡ ከሓዲዎችንም ክሕደታቸው ከሳራን እንጂ አይጨምርላቸውም፡፡
በላቸው «እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን ተጋሪዎቻችሁን አያችሁን? ከምድር ምንን እንደ ፈጠሩ አሳዩኝ፡፡ ወይስ ለእነርሱ በሰማያት ውስጥ ሽርክና አላቸውን? ወይስ መጽሐፍን ሰጠናቸውና እነርሱ ከርሱ በግልጽ አስረጅ ላይ ናቸውን? አይደለም በደለኞች ከፊላቸው ከፊሉን ማታለልን እንጂ አይቀጥሩም፡፡»
አላህ ሰማያትንና ምድርን እንዳይወገዱ ይይዛቸዋል፡፡ ቢወገዱም ከእርሱ ሌላ አንድም የሚይዛቸው የለም፡፡ እነሆ እርሱ ታጋሽ መሓሪ ነውና፡፡
አስፈራሪም ቢመጣላቸው ከሕዝቦቹ ሁሉ ከአንደኛዋ ይበልጥ የተመሩ ሊኾኑ የመሓላቸውን ድካ አድርሰው በአላህ ማሉ፡፡ አስፈራሪም በመጣላቸው ጊዜ መበርገግን እንጂ ሌላ አልጨመረላቸውም፡፡
በምድር ላይ ኩራትንና በክፉ (ተንኮል) መዶለትንም (እንጂ አልጨመረላቸውም፡፡ ክፉ ተንኮልም በባለቤቱ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይሰፍርም፡፡ የቀድሞዎቹን ደንብ እንጂ ይጠባበቃሉን? ለአላህ ደንብም መልለወጥን አታገኝም፡፡ ለአላህ ደንብም መዛወርን አታገኝም፡፡
በምድር ላይ አይኼዱምና የእነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ አይመለከቱምን? ከእነርሱም በኀይል የበረቱ ነበሩ፡፡ አላህም በሰማያትም ኾነ በምድር ውስጥ ምንም ነገር የሚያቅተው አይደለም፡፡ እርሱ ዐዋቂ ቻይ ነውና፡፡
አላህም ሰዎችን በሠሩት ኀጢአት ቢይዝ ኖሮ በወለሏ (በምድር) ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ ባልተወ ነበር፡፡ ግን እተወሰነ ጊዜ ድረስ ያቆያቸዋል፡፡ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት (በኀጢአታቸው ይቀጣቸዋል)፡፡ አላህ በባሮቹ (ኹኔታ) ተመልካች ነውና፡፡