ترجمة سورة الحجرات

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة الحجرات باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው ፊት (ነፍሶቻችሁን) አታስቀድሙ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ድምጾቻችሁን ከነቢዩ ድምጽ በላይ ከፍ አታድርጉ፡፡ ከፊላችሁም ለከፊሉ እንደሚጮህ በንግግር ለርሱ አትጩሁ፡፡ እናንተ የማታውቁ ስትኾኑ ሥራዎቻችሁ እንዳይበላሹ (ተከልከሉ)፡፡
እነዚያ በአላህ መልክተኛ ዘንድ ድምጾቻቸውን ዝቅ የሚያደርጉ እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ለፍርሃት የፈተናቸው ናቸው፡፡ ለእነርሱም ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡
እነዚያ ከክፍሎቹ ውጭ ኾነው የሚጠሩህ አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡
ወደእነርሱም እስክትወጣ ድረስ እነርሱ በታገሱ ኖሮ ለእነርሱ በላጭ በኾነ ነበር፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬን ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ኾናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተጸጸቾች እንዳትኾኑ አረጋግጡ፡፡
በውስጣችሁም የአላህ መልክተኛ መኖሩን ዕወቁ፡፡ ከነገሩ በብዙው ቢከተላችሁ ኖሮ በእርግጥ በተቸገራችሁ ነበር፡፡ ግን አላህ አምነትን ወደናንተ አስወደደ፡፡ በልቦቻችሁም ውሰጥ አጌጠው፡፡ ክህደትንና አመጽንም እንቢተኛነትንም ወደናንተ የተጠላ አደረገ፡፡ እነዚያ (እምነትን የወደዱና ክሕደተን የጠሉ) እነርሱ ቅኖቹ ናቸው፡፡
ከአላህ በኾነው ችሮታና ጸጋ (ቅኖች ናቸው)፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ከምዕምናንም የኾኑ ሁለት ጭፍሮች ቢጋደሉ በመካከላቸው አስታርቁ፡፡ ከሁለቱ አንደኛይቱም በሌላይቱ ላይ ወሰን ብታልፍ ያችን ወሰን የምታልፈውን ወደ አላህ ትዕዛዝ እስከምትመለስ ድረስ ተጋደሉ፡፡ ብትመለስም በመካከላቸው በትክክል አስታርቁ፡፡ በነገሩ ሁሉ አስተካክሉም፡፡ አላህ አስተካካዮችን ይወዳልና፡፡
ምእመናኖች ወንድማመቾች ናቸው፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ፡፡ ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ፡፡ ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፡፡ ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)፡፡ ከእነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፡፡ ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ፡፡ በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ፡፡ ከእምነት በኋላ የማመጽ ስም ከፋ፡፡ ያልተጸጸተም ሰው እነዚያ እነርሱ በዳዮቹ ናቸው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከጥርጣሬ ብዙውን ራቁ፤ ከጥርጣሬ ከፊሉ ኃጢአት ነውና፡፡ ነውርንም አትከታተሉ፡፡ ከፊላችሁም ከፊሉን አይማ፡፡ አንደኛችሁ የወንድሙን ስጋ የሞተ ኾኖ ሊበላው ይወዳልን? (መብላቱን) ጠላችሁትም፤ (ሐሜቱንም ጥሉት)፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፡፡ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፡፡ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፡፡ አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነው፡፡
የዐረብ ዘላኖች «አምነናል» አሉ፡፡ «አላመናችሁም፤ ግን ሰልመናል በሉ፡፡ «እምነቱም በልቦቻችሁ ውስጥ ገና (ጠልቆ) አልገባም፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ብትታዘዙ ከሥራዎቻችሁ ምንንም አያጎድልባችሁም፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡
(እውነተኛዎቹ) ምእምናን እነዚያ በአላህና በመልእከተኛው ያመኑት ከዚያም ያልተጠራጠሩት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶ ቻቸውም በአላህ መንገድ የታገሉት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚያ እነሱ እውነተኞቹ ናቸው፡፡
«አላህ በሰማያት ውስጥ ያለውንና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅ ሲኾን አላህን በሃይማኖታችሁ ታስታውቁ ታላችሁን?» በላቸው፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
በመስለማቸው በአንተ ላይ ይመጻደቃሉ «በስልምናችሁ በኔ ላይ አትመጻደቁ፤ ይልቁንም አላህ ወደ እምነት ስለ መራችሁ ይመጸደቅባችኋል፤ እውነተኞች ብትኾኑ» (መመጻደቅ ለአላህ ነው) በላቸው፡፡
አላህ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምሰጢር ያውቃል፤ አላህም የምትሰሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡
Icon