ترجمة سورة التوبة

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة التوبة باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .
(ይህች) ከአላህና ከመልክተኛው ወደእነዚያ ቃል ኪዳን ወደ ተጋባችኋቸው አጋሪዎች የምትደርስ ንጽሕና ናት፡፡
በምድር ላይም አራት ወሮችን (ጸጥተኞች ስትኾኑ) ኺዱ፡፡ እናንተም ከአላህ (ቅጣት) የማታመልጡ መኾናችሁንና አላህም ከሓዲዎችን አዋራጅ መኾኑን ዕወቁ፤ (በሏቸው)፡፡
(ይህ) ከአላህና ከመልክተኛው በታላቁ ሐጅ ቀን የወጣ አላህ ከአጋሪዎቹ ንጹሕ ነው መልክተኛውም (እንደዚሁ)፡፡ (ከክህደት) ብትጸጸቱም እርሱ ለእናንተ በላጭ ነው፡፡ (ከእምነት) ብትሸሹም እናንተ አላህን የማታቅቱት መኾናችሁን ዕወቁ በማለት ወደ ሰዎች የሚደርስ ማስታወቂያ ነው፡፡ እነዚያን የካዱትንም በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡
ከአጋሪዎቹ እነዚያ ቃል ኪዳን የተጋባችኋቸውና ከዚያም ምንም ያላጎደሉባችሁ በናንተ ላይም አንድንም ያልረዱባችሁ ሲቀሩ፤ (እነዚህን) ቃል ኪዳናቸውን እስከጊዜያታቸው (መጨረሻ) ሙሉላቸው፡፡ አላህ ጥንቁቆችን ይወዳልና፡፡
የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ያዙዋቸውም፣ ክበቡዋቸውም፣ ለእነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፡፡ ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ መንገዳቸውን ልቀቁላቸው፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፡፡ ከዚያም ወደ መጠበቂያው ስፍራ አድርሰው፡፡ ይህ እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው ነው፡፡
ለአጋሪዎቹ አላህ ዘንድና እመልክተኛው ዘንድ ቃል ኪዳን እንዴት ይኖራቸዋል እነዚያ በተከበረው መስጊድ ዘንድ ቃል ኪዳን የተጋባችኋቸው ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነዚህ) በቃል ኪዳናቸው ለእናንተ ቀጥ እስካሉላችሁ ድረስ ለነርሱም ቀጥ በሉላቸው፡፡ አላህ ጥንቁቆችን ይወዳልና፡፡
በእናንተ ላይ ቢያይሉም በእናንተ ውስጥ ዝምድናንና ቃል ኪዳንን የማይጠብቁ ሲኾኑ እንዴት (ቃል ኪዳን ይኖራቸዋል)፡፡ በአፎቻቸው ያስወድዷችኋል፡፡ ልቦቻቸውም እንቢ ይላሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም አመጸኞች ናቸው፡፡
በአላህ አንቀጾች ጥቂትን ዋጋ ገዙ፡፡ ከመንገዱም አገዱ፡፡ እነርሱ ይሠሩት የነበሩት ሥራ ከፋ!
በምእምን ነገር ዝምድናንም ኪዳንንም አይጠብቁም፤ እነዚያም እነሱ ወሰን አላፊዎች ናቸው፡፡
ቢጸጸቱም፣ ሶላትንም ቢሰግዱ፣ ዘካንም ቢሰጡ የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦችም አንቀጾችን እናብራራለን፡፡
ከቃል ኪዳናቸው በኋላ መሓላዎቻቸውን ቢያፈርሱ፣ ሃይማኖታችሁንም ቢያነውሩ፣ የክህደት መሪዎችን (ከክህደት) ይከለከሉ ዘንድ ተዋጉዋቸው፡፡ እነርሱ ቃል ኪዳን የላቸውምና፡፡
መሓላዎቻቸውን ያፈረሱትን መልክተኛውንም ለማውጣት ያሰቡትን ሕዝቦች እነሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመሩዋችሁ ሲኾኑ ለምን አትዋጉዋቸውም ትፈሩዋቸዋላችሁን ምእምናን እንደ ኾናችሁም አላህ ይበልጥ ልትፈሩት የተገባው ነው፡፡
ተጋደሉዋቸው፡፡ አላህ በእጆቻችሁ ያሰቃያቸዋል፡፡ ያዋርዳቸዋልም፡፡ በእነሱም ላይ ይረዳችኋል፡፡ የምእምናን ሕዝቦችንም ልቦች ያሽራል፡፡
የልቦቻችሁንም ቁጭት ያስወግዳል፡፡ አላህም ከሚሻው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
እነዚያን ከእናንተ ውስጥ የታገሉትንና ከአላህም ከመልክተኛውም ከምእመናንም ሌላ ምስጢረኛ ወዳጅ ያልያዙትን አላህ ሳይገልጽ ልትተው ታስባላችሁን አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
ለከሓዲዎች በነፍሶቻቸው ላይ በክህደት የሚመሰክሩ ሲኾኑ የአላህን መስጊዶች ሊሠሩ አይገባቸውም፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው ተበላሹ፡፡ እነሱም በእሳት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
የአላህን መስጊዶች የሚሠራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ፣ ሶላትንም በደንቡ የሰገደ፣ ግዴታ ምጽዋትንም የሰጠ ከአላህም ሌላ (ማንንም) ያልፈራ ሰው ብቻ ነው፡፡ እነዚያም ከተመሩት ጭምር መኾናቸው ተረጋገጠ፡፡
ካዕባን ጎብኝዎችን ማጠጣትንና የተከበረውን መስጊድ መሥራትን በአላህና በመጨረሻው ቀን እንዳመነና በአላህ መንገድ እንደታገለ ሰው (እምነትና ትግል) አደረጋችሁን አላህ ዘንድ አይተካከሉም፡፡ አላህም በዳዮች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
እነዚያ ያመኑት፣ ከአገራቸውም የተሰደዱት፣ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸውም በአላህ መንገድ ላይ የታገሉት አላህ ዘንድ በደረጃ በጣም የላቁ ናቸው፡፡ እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
ጌታቸው ከርሱ በኾነው እዝነትና ውዴታ በገነቶችም ለነሱ በውስጥዋ የማያቋርጥ መጠቀሚያ ያለባት ስትኾን ያበስራቸዋል፡፡
በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ (ያበስራቸዋል)፡፡ አላህ እርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አለና፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አባቶቻችሁና ወንድሞቻችሁ ክህደትን ከእምነት አብልጠው ቢወዱ ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ወዳጅ የሚያደርጋቸው እነዚያ እነሱ በዳዮች ናቸው፤
«አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም፣ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣ መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም፣ የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው በርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደኾኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ» በላቸው፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
አላህም በብዙ ስፍራዎች በእርግጥ ረዳችሁ፤ የሑነይንም ቀን ብዛታችሁ በአስደነቀቻችሁና ከእናንተም ምንም ባልጠቀመቻችሁ ጊዜ ምድርም ከስፋቷ ጋር በጠበበቻችሁና ከዚያም ተሸናፊዎች ኾናችሁ በዞራችሁ ጊዜ (ረዳችሁ)፡፡
ከዚያም አላህ እርጋታውን በመልክተኛውና በምእምናኖቹ ላይ አወረደ፡፡ ያላያችኋቸውንም ሰራዊት አወረደ፡፡ እነዚያን የካዱትንም በመገደልና በመማረክ አሰቃየ፡፡ ይህም የከሓዲያን ፍዳ ነው፡፡
ከዚያም ከዚህ በኋላ አላህ በሚሻው ሰው ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህም ዓመታቸው በኋላ የተከበረውን መስጊድ አይቅረቡ፡፡ ድኽነትንም ብትፈሩ አላህ ቢሻ ከችሮታው በእርግጥ ያከብራችኋል፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
ከእነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች እነዚያን በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛው እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እውነተኛውንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ኾነው ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው፡፡
አይሁድ ዑዘይር የአላህ ልጅ ነው አለች፡፡ ክርስቲያኖችም አልመሲሕ የአላህ ልጅ ነው አሉ፡፡ ይህ በአፎቻቸው (የሚናገሩት) ቃላቸው ነው፡፡ የእነዚያን ከነሱ በፊት የካዱትን ሰዎች ቃል ያመሳስላሉ፡፡ አላህ ያጥፋቸው፡፡ (ከእውነት) እንዴት ይመለሳሉ!
ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው፡፡
የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡ አላህም ከሓዲዎች ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን መሙላትን እንጅ ሌላን አይሻም፡፡
እርሱ ያ አጋሪዎቹ ቢጠሉም መልክተኛውን (ሙሐመድን) በቅን መንገድና በእውነተኛ ሃይማኖት ላይ ከሃይማኖት ሁሉ በላይ ይፋ ያደርገው ዘንድ የላከው ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሊቃውንትና ከመነኮሳት ብዙዎቹ የሰዎችን ገንዘቦች በውሸት በእርግጥ ይበላሉ፡፡ ከአላህም መንገድ ያግዳሉ፡፡ እነዚያንም ወርቅንና ብርን የሚያደልቡትን በአላህም መንገድ ላይ የማያወጧትን በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው፡፡
በርሷ ላይ በገሀነም እሳት ውስጥ በሚጋልባትና ግንባሮቻቸውም፣ ጎኖቻቸውም፣ ጀርባዎቻቸውም በርሷ በሚተኮሱ ቀን (አሳማሚ በኾነ ቅጣት አብስራቸው)፡፡ ይህ ለነፍሶቻችሁ ያደለባችሁት ነው፡፡ ታደልቡት የነበራችሁትንም ቅመሱ (ይባላሉ)፡፡
የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው፡፡ ከእነሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው፡፡ በእነርሱ ውስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ፡፡ አጋሪዎችንም በአንድ ላይ ኾነው እንደሚዋጉዋችሁ በአንድ ላይ ኾናችሁ ተጋደሉዋቸው፡፡ አላህም ከሚፈሩት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡
የአንዱን ወር ክብር ወደ ሌላው ማዘግየት በክህደት ላይ (ክህደትን) መጨመር ብቻ ነው፡፡ በእርሱ እነዚያ የካዱት ሰዎች ይሳሳቱበታል፡፡ በአንድ ዓመት የተፈቀደ ያደርጉታል፡፡ በሌላው ዓመትም ያወግዙታል፡፡ (ይህ) አላህ ያከበራቸውን ወሮች ቁጥር ሊያስተካክሉ፣ አላህም እርም ያደረገውን የተፈቀደ ሊያደርጉ ነው፡፡ የሥራዎቻቸው መጥፎው ለነርሱ ተዋበላቸው፡፡ አላህም ከሓዲያን ሕዝቦችን አይመራም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ (ለመታገል) ውጡ በተባላችሁ ጊዜ ወደ ምድር የምትወዘፉት ለእናንተ ምን አላችሁ የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን የቅርቢቱም ሕይወት ጥቅም በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡
ለዘመቻ ባትወጡ (አላህ) አሳማሚን ቅጣት ይቀጣችኋል፡፡ ከእናንተ ሌላ የኾኑንም ሕዝቦች ይለውጣል፡፡ በምንም አትጎዱትምም፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
(ነቢዩን) ባትረዱት እነዚያ የካዱት ሕዝቦች የሁለት (ሰዎች) ሁለተኛ ኾኖ (ከመካ) ባወጡት ጊዜ አላህ በእርግጥ ረድቶታል፡፡ ሁለቱም በዋሻው ሳሉ ለጓደኛው አትዘን አላህ ከእኛ ጋር ነውና ባለ ጊዜ አላህም መረጋጋትን በእርሱ ላይ አወረደ፡፡ ባላያችኋቸውም ሰራዊት አበረታው፡፡ የእነዚያንም የካዱትን ሰዎች ቃል ዝቅተኛ አደረገ፡፡ የአላህም ቃል ለእርሷ ከፍተኛ ናት፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ቀላሎችም ከባዶችም ኾናችሁ ዝመቱ፡፡ በአላህም መንገድ በገንዘቦቻችሁ በነፍሶቻችሁም ታገሉ፡፡ ይህ የምታውቁ ብትኾኑ ለናንተ በጣም የተሻለ ነው፡፡
(የጠራህባቸው ነገር) ቅርብ ጥቅምና መካከለኛ ጉዞ በኾነ ኖሮ በተከተሉህ ነበር፡፡ ግን በነሱ ላይ መንገዲቱ ራቀችባቸው፡፡ «በቻልንም ኖሮ ከእናንተ ጋር በወጣን ነበር» ሲሉ በአላህ ይምላሉ፡፡ ነፍሶቻቸውን ያጠፋሉ፡፡ አላህም እነሱ ውሸታሞች መኾናቸውን በእርግጥ ያውቃል፡፡
አላህ ከአንተ ይቅር አለ፡፡ እነዚያ እውነተኛዎቹ ላንተ እስከሚገለጹልህና ውሸታሞቹንም እስከምታውቅ ድረስ ለነርሱ (እንዲቀሩ) ለምን ፈቀድክላቸው
እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምኑት በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው ከመታገላቸው (ለመቅረት) ፈቃድን አይጠይቁህም፡፡ አላህም የሚፈሩትን ዐዋቂ ነው፡፡
ፈቃድን የሚጠይቁህ እነዚያ በአላህና በመጨረሻው ቀን የማያምኑት ልቦቻቸውም የተጠራጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም በጥርጣሬያቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡
መውጣትንም ባሰቡ ኖሮ ለርሱ ዝግጅትን ባሰናዱ ነበር፡፡ ግን አላህ (ለመውጣት) እንቅስቃሴያቸውን ጠላ (አልሻውም)፡፡ አሰነፋቸውም፡፡ ከተቀማጮቹም ጋር ተቀመጡ ተባሉ፡፡
ከእናንተ ጋር በወጡ ኖሮ ጥፋትን እንጂ አይጨምሩላችሁም ነበር፡፡ ሁከትንም የሚፈልጉላችሁ ሲኾኑ በመካከላችሁ (በማሳበቅ) ይቻኮሉ ነበር፡፡ በናንተም ውስጥ ለነሱ አዳማጮች አሏቸው፡፡ አላህም በዳዮችን ዐዋቂ ነው፡፡
እነርሱ ጠይዎች ሲኾኑ እውነቱ እስከመጣና የአላህም ትዕዛዝ እስከተገለጸ ድረስ ከዚህ በፊት ሁከትን በእርግጥ ፈለጉ፡፡ ነገሮችንም ሁሉ አገላበጡልህ፡፡
ከነሱም ውስጥ «ለእኔ ፍቀድልኝ አትሞክረኝም» የሚል ሰው አልለ፡፡ ንቁ! በመከራ ውስጥ ወደቁ፡፡ ገሀነምም ከሓዲዎችን በእርግጥ ከባቢ ናት፡፡
መልካም ነገር ብታገኝህ ታስከፋቸዋለች፡፡ መከራም ብታገኝህ «ከዚህ በፊት በእርግጥ ጥንቃቄያችንን ይዘናል» ይላሉ፡፡ እነርሱም ተደሳቾች ኾነው ይሸሻሉ፡፡
«አላህ ለኛ የጻፈልን (ጥቅም) እንጂ ሌላ አይነካንም፡፡ እርሱ ረዳታችን ነው፡፡ በአላህ ላይም ምእመናን ይመኩ» በላቸው፡፡
«በእኛ ላይ ከሁለቱ መልካሞች አንደኛዋን እንጂ ሌላን ትጠባበቃላችሁን እኛም አላህ ከእርሱ በኾነው ቅጣት ወይም በእጆቻችን የሚያጠፋችሁ መኾኑን በናንተ ላይ እንጠባበቃለን፡፡ ተጠባበቁም እኛ ከእናንተ ጋር ተጠባባቂዎች ነንና» በላቸው፡፡
«ወዳችሁም ኾነ ጠልታችሁ ለግሱ፡፡ ከእናንተ ተቀባይ የላችሁም፡፡ እናንተ አመጸኞች ሕዝቦች ናችሁና» በላቸው፡፡
ልግስናዎቻቸውን ከነሱ ተቀባይ የሚያገኙ ከመኾን እነሱ በአላህና በመልክተኛው የካዱ፣ ሶላትንም እነሱ ታካቾች ኾነው በስተቀር የማይሰግዱ፣ እነሱም ጠይዎች ኾነው በስተቀር የማይሰጡ መኾናቸው እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም፡፡
ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፡፡ አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ሕይወት በነርሱ (በገንዘቦቻቸውና በልጆቻቸው) ሊቀጣቸው ነፍሶቻቸውም እነሱ ከሓዲዎች ኾነው ሊወጡ ብቻ ነው፡፡
እነሱም በእርግጥ ከእናንተ ለመኾናቸው በአላህ ይምላሉ፡፡ እነርሱም ከናንተ አይደሉም፡፡ ግን እነሱ (አጋሪዎችን ያገኘ እንዳያገኛቸው) የሚፈሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡
መጠጊያን ወይም ዋሻዎችን ወይም መግቢያን (ቀዳዳ) ባገኙ ኖሮ እነርሱ እየገሰገሱ ወደርሱ በሸሹ ነበር፡፡
ከነሱም ውስጥ በምጽዋቶች የሚዘልፉህ ሰዎች አሉ፡፡ ከርሷም (የሚሹትን) ቢስሰጡ ይደሰታሉ፡፡ ከርሷም ባይስሰጡ እነሱ ያን ጊዜ ይጠላሉ፡፡
እነሱም አላህና መልክተኛው የሰጣቸውን በወደዱ፣ «አላህም በቂያችን ነው፤ አላህ ከችሮታው በእርግጥ ይሰጠናል፣ መልክተኛውም (ይሰጠናል)፣ እኛ ወደ አላህ ከጃዮች ነን» ባሉ ኖሮ (ለነሱ በተሻላቸው ነበር)፡፡
ግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በእስልምና) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም (በባርነት ተገዢዎችን) ነጻ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ከእነሱም (ከመናፍቃን) እነዚያ ነቢዩን የሚያሰቃዩ «እርሱም ጆሮ ነው» (ወሬ ሰሚ ነው) የሚሉ አልሉ በላቸው፡፡ ለእናንተ የበጎ (ወሬ) ሰሚ ነው፡፡ በአላህ ያምናል፣ ምእምናንንም ያምናቸዋል፣ ከእናንተም ውስጥ ለነዚያ ላመኑት እዝነት ነው፡፡ እነዚያም የአላህን መልክተኛ የሚያሰቃዩ ለነሱ አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
አላህንና መልክተኛውን ሊያስወድዱ ተገቢያቸው ሲኾን እናንተን ያስወደዷችሁ ዘንድ በአላህ ይምሉላችኋል፡፡ ምእምናኖች ቢኾኑ (አላህንና መልክተኛውን ያስወድዱ)፡፡
አላህንና መልክተኛውን የሚከራከር ሰው ለእርሱ የገሀነም እሳት በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን የተገባቺው መኾኑን አያውቁምን ይህ ታላቅ ውርደት ነው፡፡
መናፍቃን በልቦቻቸው ውስጥ ያለውን ነገር የምትነግራቸው ሱራ በእነርሱ ላይ መውረዷን ይፈራሉ፡፡ «አላግጡ አላህ የምትፈሩትን ሁሉ ገላጭ ነው» በላቸው፡፡
በእርግጥ ብትጠይቃቸው «እኛ የምንዘባርቅና የምንጫወት ብቻ ነበርን» ይላሉ፡፡ «በአላህና በአንቀጾቹ፣ በመልክተኛውም ታላግጡ ነበራችሁን» በላቸው፡፡
አታመካኙ፤ ከእምነታችሁ በኋላ በእርግጥ ካዳችሁ፡፡ ከእናንተ አንዷን ጭፍራ ብንምር (ሌላዋን) ጭፍራ እነሱ ኃጢአተኞች በመኾናቸው እንቀጣለን፡፡
መናፍቃንና መናፍቃት ከፊሎቻቸው ከከፊሉ ናቸው፡፡ በመጥፎ ነገር ያዛሉ ከደግም ነገር ይከለክላሉ፡፡ እጆቻቸውንም (ከልግስና) ይሰበስባሉ፡፡ አላህን ረሱ፡፡፤ ስለዚህ (እርሱ) ዋቸው፡፡ መናፍቃን አመጸኞቹ እነሱ ናቸው፡፡
መናፍቃንንና መናፍቃትን፣ ከሓዲዎችንም አላህ የገሀነምን እሳት በውስጧ ዘውታሪዎች ሲኾኑ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ እርሷ በቂያቸው ናት፡፡ አላህም ረግሟቸዋል፡፡ ለእነርሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡
እንደነዚያ ከናንተ በፊት እንደ ነበሩት ናችሁ፡፡ ከእናንተ ይበልጥ በኃይል የበረቱ በገንዘቦችም በልጆችም ይበልጥ የበዙ ነበሩ፡፡ በዕድላቸውም ተጠቀሙ፡፡ እነዚያም ከእናንተ በፊት የነበሩት በዕድላቸው እንደተጠቀሙ በዕድላችሁ ተጠቀማችሁ፡፡ እንደነዚያም እንደዘባረቁት ዘባረቃችሁ፡፡ እነዚያ ሥራዎቻቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም ዓለም ተበላሹ፡፡ እነዚያም ከሳሪዎቹ እነሱ ናቸው፡፡
የእነዚያ ከእናንተ በፊት የነበሩት የኑሕ ሕዝቦች፣ የዓድና የሰሙድም፣ የኢብራሂምም ሕዝቦች የመድየን ባለቤቶችና የተገልባጮቹም ከተሞች ወሬ አልመጣላቸውምን መልክተኞቻቸው በተዓምራት መጧቸው፡፡ አላህም የሚበድላቸው አልነበረም፡፡ ግን ነፍሶቻቸውን የሚበድሉ ነበሩ፡፡
ምእምንና ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በደግ ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
አላህ ምእምናንንና ምእምናትን ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በመኖሪያ ገነቶችም ውስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ ከአላህም የኾነው ውዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ይህ እርሱ ታላቅ እድል ነው፡፡
አንተ ነቢዩ ሆይ! ከሓዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ገሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡
ምንም ያላሉ ለመኾናቸው በአላህ ይምላሉ፡፡ የክህደትንም ቃል በእርግጥ አሉ፡፡ ከእስልምናቸውም በኋላ ካዱ፡፡ ያላገኙትንም ነገር አሰቡ፡፡ አላህም ከችሮታው መልክተኛውም (እንደዚሁ) ያከበራቸው መኾኑን እንጂ ሌላን አልጠሉም፡፡ ቢጸጸቱም ለእነሱ የተሻለ ይኾናል፡፡ ቢሸሹም አላህ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ለእነሱም በምድር ውስጥ ምንም ወዳጅና ረዳት የላቸውም፡፡
ከእነሱም «አላህን ከችሮታው ቢሰጠን በእርግጥ እንመጸውታለን ከመልካሞቹም በእርግጥ እንኾናለን» ሲል ቃል የተጋባ አልለ፡፡
ከችሮታውም በሰጣቸው ጊዜ በእርሱ ሰሰቱ፡፡ እነሱ (ኪዳናቸውን) የተዉ ኾነውም ዞሩ፡፡
አላህንም ቃል የገቡለትን በማፍረሳቸውና ይዋሹትም በነበሩት ምክንያት እስከሚገናኙት ቀን ድረስ ንፍቅናን አስከተላቸው፡፡
አላህ ምስጢራቸውንና ውይይታቸውን የሚያውቅ መኾኑን አላህም ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ መኾኑን አያውቁምን
እነዚያ ከምእምናን በምጽዋቶች ፈቃደኛ የኾኑትን፣ እነዚያንም የችሎታቸውን ያክል እንጅ የማያገኙትን ሰዎች የሚያነውሩ፣ ከእነሱም የሚስቁ አላህ ከነሱ ይሳለቅባቸዋል፤ (ይቀጣቸዋል)፡፡ ለእነሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
ለእነርሱ ምሕረትን ለምንላቸው፤ ወይም ለእነሱ ምሕረትን አትለምንላቸው (እኩል ነው)፡፡ ለእነሱ ሰባ ጊዜ ምሕረትን ብትለምንላቸው አላህ ለነሱ በፍጹም አይምርም፡፡ ይህ እነርሱ አላህና መልክተኛውን በመካዳቸው ነው፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አያቀናም፡፡
እነዚያ ከዘመቻ የቀሩት ከአላህ መልክተኛ በኋላ በመቀመጣቸው ተደሰቱ፡፡ በአላህም መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው መታገልን ጠሉ፡፡ «በሐሩር አትኺዱ» አሉም፡፡ «የገሀነም እሳት ተኳሳነቱ በጣም የበረታ ነው» በላቸው፡፡ የሚያውቁ ቢኾኑ ኖሮ (አይቀሩም ነበር)፡፡
ጥቂትንም ይሳቁ፡፡ ይሠሩት በነበሩት ዋጋ ብዙን ያለቅሳሉ፡፡
ከእነሱም ወደ ኾነችው ጭፍራ አላህ ቢመልስህ (ከአንተ ጋር) ለመውጣትም ቢያስፈቅዱህ፡-«ከኔ ጋር በፍጹም አትወጡም፡፡ ከእኔም ጋር ጠላትን አትዋጉም፡፡ እናንተ በመጀመሪያ ጊዜ መቀመጥን ወዳችኋልና፡፡ ከተቀማጮቹ ጋርም ተቀመጡ» በላቸው፡፡
ከእነሱም በአንድም በሞተ ሰው ላይ ፈጽሞ አትስገድ፡፡ በመቃብሩም ላይ አትቁም፡፡ እነሱ አላህንና መልክተኛውን ክደዋልና፡፡ እነሱም አመጸኞች ኾነው ሞተዋልና፡፡
ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፡፡ አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ዓለም በነሱ ሊቀጣቸውና ከሓዲዎችም ኾነው ነፍሶቻቸው እንዲወጡ ብቻ ነው፡፡
በአላህ እመኑ፡፡ ከመልክተኛውም ጋር ኾናችሁ ታገሉ፤ በማለት ምዕራፍ በተወረደች ጊዜ ከነሱ የሰፊ ሀብት ባለቤቶች የኾኑት (ለመቅረት) ፈቃድ ይጠይቁሃል፡፡ «ከተቀማጮቹ ጋርም እንኹን ተወን» ይሉሃል፡፡
በቤት ከሚቀሩት ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ በልቦቻቸውም ላይ (ዝገት) ታተመባቸው፡፡ ስለዚህ እነሱ አያውቁም፡፡
ግን መልክተኛው እነዚያም ከርሱ ጋር ያመኑት በገንዘቦቻቸውም በነፍሶቻቸውም ታገሉ፡፡ እነዚያም መልካሞች ሁሉ ለነሱ ናቸው፡፡ እነዚያም እነሱ ምኞታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
ለእነሱም ገነቶችን በሥራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ አላህ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ማግኘት ነው፡፡
ከአዕራቦችም ይቅርታ ፈላጊዎቹ ለእነሱ እንዲፈቀድላቸው መጡ፡፡ እነዚያ አላህንና መልክተኛውን የዋሹትም ተቀመጡ፡፡ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡
በደካሞች ላይ በበሽተኞችም ላይ በነዚያም የሚያወጡት ገንዘብ በማያገኙት ላይ ለአላህና ለመልክተኛው ፍጹም ታዛዦች ከኾኑ (ባይወጡም) ኃጢኣት የለባቸውም፡፡ በበጎ አድራጊዎች ላይ (የወቀሳ) መንገድ ምንም የለባቸውም፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
በእነዚያም ልትጭናቸው በመጡህ ጊዜ «በርሱ ላይ የምጭናችሁ (አጋሰስ) አላገኝም፤» ያልካቸው ስትኾን የሚያወጡት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ለማዘናቸው ዓይኖቻቸው እንባን እያፈሰሱ በዞሩት ላይ (የወቀሳ መንገድ የለባቸውም)፡፡
(የወቀሳ) መንገዱ በእነዚያ እነሱ ባለጸጋዎች ኾነው ሳሉ ለመቅረት ፈቃድ በሚጠይቁህ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከቀሪዎቹ ጋር መኾናቸውን ወደዱ፡፡ አላህም በልቦቻቸው ላይ አተመባቸው፤ ስለዚህ እነሱ አያውቁም፡፡
ወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ ምክንያታቸውን ያቀርቡላችኋል፡፡ አታመካኙ፤ እናንተን ፈጽሞ አናምንም፡፡ አላህ ከወሬዎቻችሁ በእርግጥ ነግሮናልና፡፡ አላህም ሥራችሁን በእርግጥ ያያል፡፡ መልክተኛውም (እንደዚሁ)፤ ከዚያም ሩቅንና ቅርብን ሁሉ ዐዋቂ ወደ ኾነው (አላህ) ትመለሳላችሁ ወዲያውም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል በላቸው፡፡
ወደእነሱ በተመለሳችሁ ጊዜ እንድትተውዋቸው ለእናንተ በእርግጥ በአላህ ይምላሉ፡፡ እነሱንም ተዋቸው፡፡ እነሱ እርኩሶች ናቸውና፡፡ ይሠሩትም በነበሩት ዋጋ መኖሪያቸው ገሀነም ነው፡፡
ከእነሱ ትወዱላቸው ዘንድ ለናንተ ይምሉላችኋል፡፡ ከእነሱ ብትወዱም አላህ አመጸኞች ሕዝቦችን አይወድም፡፡
አዕራቦች በክህደትና በንፍቅና በጣም የበረቱ፤ አላህም በመልክተኛው ላይ ያወረደውን ሕግጋት ባለማወቅ የተገቡ ናቸው፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ከአዕራቦችም (በአላህ መንገድ) የሚወጣውን (ገንዘብ) ዕዳ አድርጎ የሚይዝ በእናንተም ላይ የጊዜን መገለባበጥ የሚጠባበቅ ሰው አልለ፡፡ በእነሱ ላይ ጥፋቱ ይዙርባቸው፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
ከአዕራቦችም በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን የሚሰጣቸውንም (ምጽዋቶች) አላህ ዘንድ መቃረቢያዎችና ወደ መልክተኛው ጸሎቶች መዳረሻ አድርጎ የሚይዝ ሰው አልለ፡፡ ንቁ! እርሷ ለእነሱ በእርግጥ አቃራቢ ናት፡፡ አላህ በችሮታው ውስጥ (በገነቱ) በእርግጥ ያስገባቸዋል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
ከስደተኞቹና ከረዳቶቹም ሲኾኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም በበጎ ሥራ የተከተሏቸው አላህ ከእነሱ ወዷል ከእርሱም ወደዋል፡፡ በሥሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘለዓለም ነዋሪዎች ሲኾኑ ለእነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡
በዙሪያችሁም ካሉት ከዐረብ ዘላኖች መናፍቃን አልሉ፡፡ ከመዲና ሰዎችም በንፍቅና ላይ በማመጽ የዘወተሩ አልሉ፡፡ አታውቃቸውም፡፡ እኛ እናውቃቸዋለን፡፡ ሁለት ጊዜ እንቀጣቸዋለን፡፡ ከዚያም ወደታላቅ ቅጣት ይመለሳሉ፡፡
ሌሎችም በኃጢአቶቻቸው የተናዘዙ መልካም ሥራንና ሌላን መጥፎ ሥራ የቀላቀሉ አልሉ፡፡ አላህ ከእነሱ ጸጸታቸውን ሊቀበል ይከጀላል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፡፡ ለነሱም ጸልይላቸው፡፡ ጸሎትህ ለእነሱ እርጋታ ነውና አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
አላህ እርሱ ከባሮቹ ንስሓን የሚቀበል ምጽዋቶችንም የሚወስድ መኾኑን አላህም እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ መኾኑን አያውቁም
በላቸውም ሥሩ አላህ ሠራችሁን በእርግጥ ያያልና፡፡ መልክተኛውና ምእምናንም (እንደዚሁ ያያሉ)፡፡ ሩቁንና ቅርቡን ሁሉ ዐዋቂ ወደ ኾነውም (አላህ) በእርግጥ ትመለሳላችሁ፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡
ሌሎችም ለአላህ ትዕዛዝ የተቆዩ ሕዝቦች አልሉ፡፡ ወይ ይቀጣቸዋል ወይም ከነሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
እነዚያም (ምእምናንን) ለመጉዳት፣ ክህደትንም ለማበርታት፣ በምእምናንም መካከል ለመለያየት፣ ከአሁን በፊት አላህንና መልክተኛውን የተዋጋውንም ሰው ለመጠባበቅ መስጊድን የሠሩት (ከነሱ ናቸው)፡፡ መልካምን ሥራ እንጂ ሌላ አልሻንም ሲሉም በእርግጥ ይምላሉ፡፡ አላህም እነሱ በእርግጥ ውሸታሞች መኾናቸውን ይመሰክራል፡፡
በእርሱ ውስጥ በፍጹም አትስገድ፡፡ ከመጀመሪያ ቀን ይዞ በአላህ ፍራቻ ላይ የተመሠረተው (የቁባ) መስጊድ በውስጡ ልትሰግድበት ይልቅ የተገባው ነው፡፡ በእሱ ውስጥ መጥራራትን የሚወዱ ወንዶች አልሉ፡፡ አላህም ተጥራሪዎችን ይወዳል፡፡
አላህን በመፍራትና ውዴታውን በመፈለግ ላይ ግንቡን የመሠረተው ሰው ይበልጣልን ወይስ ጎርፍ በሸረሸረው ለመናድ በተቃረበ ገደል አፋፍ ላይ ግንቡን የመሠረተውና በርሱ (ይዞት) በገሀነም እሳት ውስጥ የወደቀ (ይበልጣል)፡፡ አላህም በደለኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
ያ የካቡት ግንባቸው ልቦቻቸው (በሞት) ካልተቆራረጡ በቀር በልቦቻቸው ውስጥ የመጠራጠር ምክንያት ከመኾን አይወገድም፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
አላህ ከምእምናን ነፍሶቻቸውንና ገንዘቦቻቸውን ገነት ለእነሱ ብቻ ያላቸው በመኾን ገዛቸው፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ይጋደላሉ፡፡ ይገድላሉም፤ ይገደላሉም፡፡ በተውራት በኢንጅልና በቁርኣንም (የተነገረውን) ተስፋ በእርሱ ላይ አረጋገጠ፡፡ ከአላህም የበለጠ በኪዳኑ የሚሞላ ማነው በዚያም በእርሱ በተሻሻጣችሁበት ሽያጫችሁ ተደሰቱ፡፡ ይህም እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡
(እነርሱ) ተጸጻቺዎች፣ ተገዢዎች፣ አመስጋኞች፣ ጿሚዎች፣ አጎንባሾች፣ በግንባር ተደፊዎች፣ በበጎ ሥራ አዛዦች ከክፉም ከልካዮች፣ የአላህንም ሕግጋት ጠባቂዎች ናቸው ምእምናንንም አብስር፡፡
ለነቢዩና ለነዚያ ላመኑት ለአጋሪዎቹ የዝምድና ባለቤቶች ቢኾኑም እንኳ እነሱ (ከሓዲዎቹ) የእሳት ጓዶች መኾናቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ምሕረትን ሊለምኑ የሚገባ አልነበረም፡፡
የኢብራሂምም ለአባቱ ምሕረትን መለመን ለእርሱ ገብቶለት ለነበረችው ቃል (ለመሙላት) እንጂ ለሌላ አልነበረም፡፡ እርሱም የአላህ ጠላት መኾኑ ለእርሱ በተገለጸለት ጊዜ ከርሱ ራቀ፤ (ተወው)፡፡ ኢብራሂም በእርግጥ በጣም ርኅሩኅ ታጋሽ ነውና፡፡
አላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለእነሱ እስከሚገልጸላቸው (እስከሚተውትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡
አላህ የሰማያትና የምድር ንግስና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ሕያው ያደርጋል፤ ይገድላልም፡፡ ለእናንተም ከርሱ በቀር ጠባቂም ረዳትም የላችሁም፡፡
በነቢዩ በነዚያም በችግሪቱ ጊዜያት (በተቡክ ዘመቻ) ከእነሱ የከፊሎቹ ልቦች (ለመቅረት) ሊዘነበሉ ከተቃረቡ በኋላ በተከተሉት ስደተኞችና ረዳቶች ላይ አላህ በእርግጥ ጸጸታቸውን ተቀበለ፡፡ ከዚያም ከእነሱ ንስሓ መግባታቸውን ተቀበለ፡፡ እርሱ ለእነሱ ርኅሩኅ አዛኝ ነውና፡፡
በእነዚያም በሦስቱ ሰዎች ላይ ምድር ከስፋትዋ ጋር በእነሱ ላይ እስከ ጠበበች፣ ነፍሶቻቸውም በርሳቸው ላይ እስከተጠበቡ፣ ከአላህም ወደርሱ ቢኾን እንጂ ሌላ መጠጊያ አለመኖሩን እስከ አረጋገጡ ድረስ በተቆዩት ላይ (አላህ ጸጸትን ተቀበለ)፡፡ ከዚያም ይጸጸቱ ዘንድ ወደ ጸጸት መራቸው፡፡ አላህ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ፡፡
ለመዲና ሰዎችና ከአዕራብም በዙሪያቸው ላሉት ሰዎች ከአላህ መልክተኛ ወደኋላ ሊቀሩ ነፍሶቻቸውንም ከነፍሱ አብልጠው ሊወዱ አይገባቸውም ነበር፡፡ ይህ (ከመቅረት መከልከል) ለእነርሱ መልካም ሥራ የሚጻፍላቸው ቢኾን እንጅ፡፡ በአላህ መንገድ ላይ ጥምም፣ ድካምም፣ ረኃብም፣ የማይነካቸው ከሐዲዎችንም የሚያስቆጭን ስፍራ የማይረግጡ፣ ከጠላትም የሚጎዳን ነገር (መግደልን መማረክን መዝረፍን) የማያገኙ በመኾናቸው ነው፡፡ አላህ የመልካም ሠሪዎችን ምንዳ አያጠፋምና፡፡
ትንሽንም ትልቅንም ልግስና አይለግሱም ወንዝንም አያቋርጡም አላህ ይሠሩት ከነበረው የበለጠን ምንዳ ይመነዳቸው ዘንድ ለእነሱ የሚጻፍላቸው ቢሆን እንጅ፡፡
ምእምናንም (ከነቢዩ ጋር ካልኾነ) በሙሉ ሊወጡ አይገባም፡፡ ከእነሱ ውስጥ ከየክፍሉ አንዲት ጭፍራ ለምን አትወጣም፡፡ (ሌሎቹ) ሃይማኖትን እንዲማሩና ወገኖቻቸው ወደነርሱ በተመለሱ ጊዜ እንዲጠነቀቁ ይገስጹዋቸው ዘንድ (ለምን አይቀሩም)፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እነዚያን በአቅራቢያችሁ ያሉትን ከሓዲዎች ተዋጉ፡፡ ከእናንተም ብርታትን ያግኙ፡፡ አላህም ከሚጠነቀቁት ጋር መኾኑን ዕወቁ፡፡
ሱራም (ምዕራፍ) በተወረደች ጊዜ ከእነሱ (ከመናፍቃን) ውስጥ ማንኛችሁ ነው ይህች (ምዕራፍ) እምነትን የጨመረችለት የሚል ሰው አልለ፡፡ እነዚያ ያመኑትማ የሚደሰቱ ሲኾኑ እምነትን ጨመረችላቸው፡፡
እነዚያም በልቦቻቸው ውስጥ በሽታ ያለባቸውማ በርክሰታቸው ላይ ርክሰትን ጨመረችላቸው፡፡ እነርሱም ከሓዲዎች ኾነው ሞቱ፡፡
በየዓመቱ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ እነርሱ የሚሞከሩ መኾናቸውን አያዩምን ከዚያም አይጸጸቱምን እነሱም አይገሰጹምን
(እነሱን የምታነሳ) ምዕራፍም በተወረደች ጊዜ አንድ ሰው ያያችኋልን እያሉ ከፊሎቻቸው ወደ ከፊሉ ይመለከታሉ፡፡ ከዚያም (ተደብቀው) ይኼዳሉ፡፡ እነርሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው አላህ ልቦቻቸውን አዞረ፡፡
ከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡
ቢያፈገፍጉም አላህ በቂዬ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ በእርሱ ላይ ተጠጋሁ እርሱም የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው በላቸው፡፡
Icon