ترجمة سورة طه

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة طه باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

ጠ.ሀ. (ጣ ሃ)
ቁርኣንን ባንተ ላይ እንድትቸገር አላወረድንም፡፡
ግን አላህን ለሚፈራ ሰው መገሰጫ ይኾን ዘንድ (አወረድነው)፡፡
ምድርንና የላይኛዎቹን ሰማያት ከፈጠረ አምላክ ተወረደ፡፡
(እርሱ) አልረሕማን ነው በዐርሹ ላይ (ለሱ ክብር በሚስማማ መልኩ) ተደላደለ፡፡
በሰማያት ያለው፣ በምድርም ያለው፣ በመካከላቸውም ያለው፣ ከዐፈር በታችም ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፡፡
በንግግር ብትጮህ (አላህ ከጩኸቱ የተብቃቃ ነው)፡፡ እርሱ ምስጢርን በጣም የተደበቀንም ያውቃልና፡፡
አላህ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ለእርሱ መልካሞች የኾኑ ስሞች አልሉት፡፡
የሙሳም ወሬ በእርግጥ መጥቶሃል፡፡
እሳትን ባየና ለቤተሰቦቹ፡- (እዚህ) «ቆዩ፤ እኔ እሳትን አየሁ፡፡ ከእርሷ ችቦን ላመጣላችሁ፤ ወይም እሳቲቱ ዘንድ መሪን ላገኝ እከጅላለሁ» ባለጊዜ (አስታውስ)፡፡
በመጣትም ጊዜ «ሙሳ ሆይ» በማለት ተጠራ፡፡
«እኔ ጌታህ እኔ ነኝ መጫሚያዎችህንም አውልቅ፡፡ አንተ በተቀደሰው ሸለቆ በጡዋ ነህና፡፡
«እኔም መረጥኩህ፤ የሚወረድልህንም ነገር አዳምጥ፡፡
«እኔ አላህ እኔ ነኝ ያለ እኔ አምላክ የለምና ተገዛኝ፡፡ ሶላትንም (በእርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡
«ሰዓቲቱ በእርግጥ መጪናት፡፡ ልደብቃት እቃረባለሁ፡፡ ነፍስ ሁሉ በምትሠራው ነገር ትመነዳ ዘንድ (መጭ ናት)፡፡
«በእርሷ የማያምነውና ዝንባሌውን የተከተለውም ሰው ከእርሷ አያግድህ ትጠፋለህና፡፤
«ሙሳ ሆይ! ይህችም በቀኝ እጅህ ያለችው ምንድን ናት» (ተባለ)፡፡
«እርሷ በትሬ ናት፡፡ በእርሷ ላይ እደገፍባታለሁ፣ በእርሷም ለፍየሎቼ ቅጠልን አረግፍባታለሁ፣ ለእኔም በእርሷ ሌሎች ጉዳዮች አሉኝ» አለ፡፡
(አላህም) «ሙሳ ሆይ! ጣላት» አለው፡፡
ጣላትም፡፡ ወዲያውም እርሷ የምትሮጥ እባብ ኾነች፡፡
«ያዛት፤ አትፍራም፡፡ ወደ መጀመሪያ ጠባይዋ እንመልሳታለን» አለው፡፡
«እጅህንም ወደ ብብትህ አግባ፡፡ ሌላ ተዓምር ስትኾን ያለነውር ነጭ ኾና ትወጣለችና፡፡
«ከተዓምራቶቻችን ታላቋን እናሳይህ ዘንድ (ይህን ሠራን)፡፡
«ወደ ፈርዖን ኺድ፡፡ እርሱ ወሰን አልፏልና፡፡»
(ሙሳም) አለ «ጌታዬ ሆይ! ልቤን አስፋልኝ፡፡
«ነገሬንም ለእኔ አግራልኝ፡፡
«ከምላሴም መኮላተፍን ፍታልኝ፡፡
«ንግግሬን ያውቃሉና፡፡
«ከቤተሰቦቼም ለእኔ ረዳትን አድርግልኝ፡፡
«ሃሩንን ወንድሜን፡፡
«ኅይሌን በእርሱ አበርታልኝ፡፡
«በነገሬም አጋራው፡፡
«በብዙ እናጠራህ ዘንድ፡፡
«በብዙም እንድናወሳህ፡፡
«አንተ በእኛ ነገር ዐዋቂ ነህና፡፡»
(አላህም) አለ «ሙሳ ሆይ! ልመናህን በእርግጥ ተሰጠህ፡፡
«በሌላም ጊዜ ባንተ ላይ በእርግጥ ለግሰናል፡፡
«ወደናትህ በልብ የሚፈስን ነገር ባሳወቅን ጊዜ፡፡
«(ሕፃኑን) በሳጥኑ ውስጥ ጣይው፡፡ እርሱንም (ሳጥኑን) በባሕር ላይ ጣይው፡፡ ባሕሩም በዳርቻው ይጣለው፡፡ ለእኔ ጠላት ለእርሱም ጠላት የኾነ ሰው ይይዘዋልና በማለት (ባሳወቅን ጊዜ ለገስንልህ)፡፡ ባንተ ላይም ከእኔ የኾነን መወደድ ጣልኩብህ፡፡ (ልትወደድና) በእኔም ጥበቃ ታድግ ዘንድ፡፡
«እኅትህም በምትኼድና የሚያሳድገውን ሰው ላመላክታችሁን በምትል ጊዜ (መወደድን ጣልኩብህ)፡፡ ወደ እናትህም ዓይንዋ እንዲረጋ (እርሷ) እንዳታዝንም መለስንህ፡፡ ነፍስንም ገደልክ፡፡ ከጭንቅም አዳንንህ፡፡ ፈተናዎችንም ፈተንህ፡፡ በመድየን ቤተሰቦችም ውስጥ (ብዙ) ዓመታትን ተቀመጥክ፡፡ ከዚያም ሙሳ ሆይ! በተወሰነ ጊዜ ላይ መጣህ፡፡
«ለነፍሴም (በመልእክቴ) መረጥኩህ፡፡
«አንተም ወንድምህም በተዓምራቶቼ ኺዱ፡፡ እኔንም ከማውሳት አትቦዝኑ፡፡
«ወደ ፈርዖን ኺዱ፡፡ እርሱ ወሰን አልፏልና፡፡
«እርሱም ይገሰጽ ወይም ይፈራ ዘንድ፤ ለእርሱ ልዝብን ቃል ተናገሩት፡፡»
«ጌታችን ሆይ! እኛ በእኛ ላይ ክፋት በመሥራት መቸኮሉን ወይም ኩራትን መጨመሩን እንፈራለን» አሉ፡፡
(አላህም) አለ «አትፍሩ፡፡ እኔ በእርግጥ ከእናንተ ጋር ነኝና፡፡ እሰማለሁ፤ አያለሁም፡፡
«ወደርሱም ኺዱ፤ በሉትም፡- ‹እኛ የጌታህ መልክተኞች ነን፡፡› የእስራኤልንም ልጆች ከኛ ጋር ልቀቅ፡፡ አታሰቃያቸውም፡፡ ከጌታህ በኾነው ተዓምር በእርግጥ መጥተንሃልና፡፡ ሰላምም ቀጥታን በተከተለ ሰው ላይ ይኹን፡፡
«እኛ ቅጣቱ ባስተባበለና እምቢ ባለ ሰው ላይ ነው ማለት በእርግጥ ተወረደልን፡፡»
(ፈርዖንም) «ሙሳ ሆይ! ጌታችሁ ማነው» አለ፡፡
«ጌታችን ያ ለፍጥረቱ ነገርን ሁሉ (የሚያስፈልገውን) የሰጠ ከዚያም የመራው ነው» አለው፡፡
(ፈርዖንም) «የመጀመሪያይቱ ዘመናት ሕዝቦች ኹኔታ ምንድን ነው» አለ፡፡
(ሙሳም) «ዕውቀትዋ እጌታዬ ዘንድ በመጽሐፍ የተመዘገበ ነው፡፡ ጌታዬ አይሳሳትም አይረሳምም» አለው፡፡
(እርሱ) ያ ምድርን ለእናንተ ምንጣፍ ያደረገላችሁ፣ በእርሷም ውስጥ ለእናንተ መንገድን ያገራላችሁ፣ ውሃንም ከሰማይ ያወረደ ነው (አለ)፡፡ በርሱም ከተለያየ በቃይ ዓይነቶችን አወጣንላችሁ፡፡
ብሉ እንስሳዎቻችሁንም አግጡ፤ (ባዮች ኾነን አወጣንላችሁ)፡፡ በዚህ ውስጥ ለአእምሮ ባለቤቶች በእርግጥ ተዓምራት አለበት፡፡
ከእርሷ (ከምድር) ፈጠርናችሁ፡፡ በእርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን፡፡ ከእርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን፡፡
ተዓምራቶቻችንንም ሁሏንም (ለፈርዖን) በእርግጥ አሳየነው፡፡ አስተባበለም፡፡ እምቢም አለ፡፡
«ከምድራችን በድግምትህ ልታወጣን መጣህብን ሙሳ ሆይ!» አለ፡፡
«መሰሉንም ድግምት እናመጣብሃለን፡፡ በእኛና ባንተም መካከል እኛም አንተም የማንጥሰው የኾነ ቀጠሮን በመካከለኛ ስፍራ አድርግልን» አለ፡፡
«ቀጠሯችሁ በማጌጫው ቀን ሰዎቹም በረፋድ በሚሰበሰቡበት ነው» አለ፡፡
ፈርዖንም ዞረ፡፡ ተንኮሉንም ሰበሰበ፡፡ ከዚያም መጣ፡፡
ሙሳ ለእነሱ አላቸው «ወዮላችሁ በአላህ ላይ ውሸትን አትቅጠፉ፡፡ በቅጣት ያጠፋችኋልና፡፡ የቀጠፈም ሰው በእርግጥ አፈረ፡፡»
(ድግምተኞቹ) በመካከላቸውም ነገራቸውን ተጨቃጨቁ፡፡ ውይይትንም ደበቁ፡፡
«እነዚህ በእርግጥ ደጋሚዎች ናቸው፡፡ ከምድራችሁ በድግምታቸው ሊያወጧችሁ በላጪቱንም መንገዳችሁን ሊያስወግዱባችሁ ይሻሉ» አሉ፡፡
«ተንኮላችሁንም አጠንክሩ፡፡ ከዚያም ተሰልፋችሁ ኑ፡፡ ዛሬ ያሸነፈም ሰው ምኞቱን አገኘ» (ተባባሉ)፡፡
«ሙሳ ሆይ! ወይ ትጥላለህ ወይም በመጀመሪያ የምንጥል እንኾናለን» (ምረጥ) አሉ፡፡
«አይደለም ጣሉ» አላቸው፡፡ ወዲያውም ገመዶቻቸውና ዘንጎቻቸው ከድግምታቸው የተነሳ እነርሱ የሚሮጡ (እባቦች) ኾነው ወደርሱ ተመለሱ፡፡
ሙሳም በነፍሱ ውስጥ ፍርሃትን አሳደረ፡፡
«አትፍራ አንተ የበላዩ አንተ ነህና» አልነው፡፡
«በቀኝ እጅህ ያለቸውንም በትር ጣል፡፡ ያንን የሠሩትን ትውጣለችና፡፡ ያ የሠሩት ሁሉ የድግምተኛ ተንኮል ነውና፡፡ ድግምተኛም በመጣበት ስፍራ ሁሉ አይቀናውም» (አልን)፡፡
ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ፡፡ «በሃሩንና በሙሳ ጌታ አመንን» አሉ፡፡
(ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ በእርግጥ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ትልቃችሁ ነው፡፡ እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን በማናጋት (ግራናቀኝን በማፈራረቅ) እቆራርጣችኋለሁ፡፡ በዘምባባም ግንዶች ለይ እሰቅላችኋለሁ፡፡ ማንኛችንም ቅጣቱ በጣም ብርቱ የሚቆይም መኾኑን ታውቃላችሁ» አላቸው፡፡
ከመጡልን ታምራቶች ከዚያም ከፈጠረን(አምላክ) ፈጽሞ አንመርጥህም፤ አንተም የምትፈርደውን ፍረድ፤ የምትፈርደው በዚች በአነስተኛይቱ ሕይወት ብቻ ነው አሉ፡፡
«ኃጢአቶቻችንንና ከድግምትም በእርሱ ላይ ያስገደድከንን ለእኛ ይምረን ዘንድ እኛ በጌታችን አምነናል፡፡ አላህም በጣም በላጭ ነው፤ (ቅጣቱም) በጣም የሚዘወትር ነው» አሉ፡፡
እነሆ ከሓዲ ኾኖ ወደ ጌታው የሚመጣ ሰው ለእርሱ ገሀነም አለችው፡፡ በውስጧም አይሞትም ሕያውም አይኾን፡፡
በጎ ሥራዎችን በእርግጥ የሠራ ምእመን ኾኖ የመጣውም ሰው እነዚያ ለእነሱ ከፍተኛ ደረጃዎች አሏቸው፡፡
ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ (አሏቸው)፡፡ ይህም የተጥራራ ሰው ምንዳ ነው፡፡
ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ በሌሊት ኺድ፡፡ ለእነሱም በባሕር ውስጥ ደረቅ መንገድን አድርግላቸው፡፡ መገኘትን አትፍራ፡፡ (ከመስጠም) አትጨነቅም፡፡» ስንል በእርግጥ ላክንበት፡፡
ፈርዖንም ከሰራዊቱ ጋር ኾኖ ተከተላቸው፡፡ ከባህሩም የሚሸፍን ሸፈናቸው፡፡
ፈርዖንም ሕዝቦቹን አሳሳታቸው፡፡ ቅኑንም መንገድ አልመራቸውም፡፡
የእስራኤል ልጆች ሆይ! ከጠላታችሁ በእርግጥ አዳንናችሁ፡፡ በጡርም ቀኝ ጎን ቀጠሮ አደረግንላችሁ፡፡ በእናንተም ላይ መናንና ድርጭትን አወረድንላችሁ፡፡
ከሰጠናችሁ ሲሳይ፤ ከመልካሙ ብሉ፡፡ በእርሱም ወሰንን አትለፉ፡፡ ቁጣዬ በእናንተ ላይ ይወርድባችኋልና፡፡ በእርሱም ላይ ቁጣዬ የሚወርድበት ሰው በእርግጥ ይጠፋል፡፡
እኔም ለተጸጸተ፣ ላመነም፣ መልካምንም ለሠራ፣ ከዚያም ለተመራ ሰው በእርግጥ መሓሪ ነኝ፡፡
«ሙሳ ሆይ! ከሕዝቦችህ ምን አስቸኮለህም» (ተባለ)፡፡
«እነሱ እነዚህ፤ በዱካዬ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ጌታዬ ሆይ! ትወድልንም ዘንድ ወደ አንተ ቸኮልኩ» አለ፡፡
(አላህ) «እኛም ከአንተ በኋላ ሰዎችህን በእርግጥ ፈትተን፡፡ ሳምራዊውም አሳሳታቸው» አለው፡፡
ሙሳም ወደ ሰዎቹ የተቆጣ ያዘነ ኾኖ ተመለሰ፡፡ «ሕዝቦቼ ሆይ! ጌታችሁ መልካም ተስፋን አልቀጠራችሁምን ቀጠሮው በእናንተ ላይ ረዘመባችሁን» ወይስ በእናንተ ላይ ከጌታችሁ ቅጣት ሊወርድባችሁ ፈለጋችሁና ቀጠሮየን አፈረሳችሁን አላቸው፡፡
«ቀጠሮህን በፈቃዳችን አልጣስንም፡፡ ግን እኛ ከሕዝቦቹ ጌጥ ሸክሞችን ተጫን (በእሳት ላይ) ጣልናትም፡፡ ሳምራዊውም እንደዚሁ ጣለ» አሉት፡፡
ለእነሱም አካል የኾነ ጥጃን ለእርሱ መጓጎር ያለውን አወጣላቸው፡፡ (ተከታዮቹ) «ይህ አምላካችሁ የሙሳም አምላክ ነው ግን ረሳው» አሉም፡፡
ወደእነሱ ንግግርን የማይመልስ ለእነሱም ጉዳትንና ጥቅምን የማይችል መኾኑን አያዩምን
ሃሩንም ከዚህ በፊት በእርግጥ አላቸው፡- «ሕዝቦቼ ሆይ! (ይህ) በእርሱ የተሞከራችሁበት ብቻ ነው፡፡ ጌታችሁም አልረሕማን ነው፡፡ ተከተሉኝም፡፡ ትዕዛዜንም ስሙ፡፡»
«ሙሳ ወደእኛ እስከሚመለስ በእርሱ (መገዛት) ላይ ከመቆየት ፈጽሞ አንወገድም» አሉ፡፡
(ሙሳ) አለ፡- «ሃሩን ሆይ! ተሳስተው ባየሃቸው ጊዜ ምን ከለከልህ
«እኔን ከመከተል ትዕዛዜን ጣስክን»
«የእናቴ ልጅ ሆይ! ጢሜንም ራሴንም አትያዝ፡፡ እኔ በእስራኤል ልጆች መካከል ለያየህ፤ ቃሌንም አልጠበቅህም ማለትህን ፈራሁ» አለው፡፡
(ሙሳ) «ሳምራዊው ሆይ! ነገርህም ምንድን ነው» አለ፡፡
ያላዩትን ነገር አየሁ፡፡ ከመልክተኛው (ከፈረሱ ኮቴ) ዱካም ጭብጥ አፈርን ዘገንኩ፡፡ (በቅርጹ ላይ) ጣልኳትም፡፡ እንደዚሁም ነፍሴ ሸለመችልኝ» አለ፡፡
አለው «ኺድ፤ ላንተም በሕይወትህ (ለአየኸው ሰው ሁሉ) መነካካት የለም ማለት አለህ፡፡ ለአንተም ፈጽሞ የማትጣሰው ቀጠሮ አለህ፡፡ ወደዚያም በእርሱ ላይ ተገዢው ኾነህ ወደ ቆየህበት አምላክህ ተመልከት፡፡ በእርግጥ እናቃጥለዋለን፡፡ ከዚያም በባሕሩ ውስጥ መበተንን እንበትነዋለን፡፡»
ጌታችሁ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ የኾነው አላህ ብቻ ነው፡፡ እውቀቱ ነገርን ሁሉ አዳረሰ፡፡
እንደዚሁ በእርግጥ ካለፉት ወሬዎች ባንተ ላይ እንተርካለን፡፡ ከእኛም ዘንድ ቁረኣንን በእርግጥ ሰጠንህ፡፡
ከእርሱ ያፈገፈገ ሰው እርሱ በትንሣኤ ቀን ከባድን ቅጣት ይሸከማል፡፡
በእርሱ ውስጥ ዘውታሪዎች ኾነው (ይሸከማሉ)፡፡ በትንሣኤም ቀን ለእነሱ የኾነው ሸክም ከፋ!
በቀንዱ በሚነፋ ቀን (ሸክማቸው ከፋ)፤ ከሓዲዎችንም በዚያ ቀን (ዓይኖቻቸው) ሰማያዊዎች ሆነው እንሰበስባቸዋለን፡፡
«ዐሥርን (ቀን) እንጂ አልቆያችሁም» በመባባል በመካከላቸው ይንሾካሾካሉ፡፡
በሐሳብ ቀጥተኛው «አንድን ቀን እንጅ አልቆያችሁም» በሚል ጊዜ የሚሉትን ነገር እኛ ዐዋቂዎች ነን፡፡
ከጋራዎችም ይጠይቁሃል፤ በላቸው «ጌታዬ መበተንን ይበትናቸዋል፡፡
«ትክክል ሜዳም ኾና ይተዋታል፡፡
«በርሷ ዝቅታና ከፍታን አታይም፡፡»
በዚያ ቀን (ለመሰብሰብ) ጠሪውን ለእርሱ መጣመም የሌለውን መከተል ይከተላሉ፡፡ ድምጾችም ለአልረሕማን ጸጥ ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሹክሹክታን እንጂ አትሰማም፡፡
በዚያ ቀን ለእርሱ አልረሕማን የፈቀደለትንና ለእርሱም ቃልን የወደደለትን ሰው ቢኾን እንጅ ምልጃ (አንድንም) አትጠቅምም፡፡
በስተፊታቸው ያለውን በስተኋላቸውም ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡ በእርሱም ዕውቀትን አያካብቡም፤ (አያውቁም)፡፡
ፊቶችም ሁሉ ሕያው አስተናባሪ ለኾነው (አላህ) ተዋረዱ፡፡ በደልንም የተሸከመ ሰው በእርግጥ ከሰረ፡፡
እርሱ አማኝ ኾኖ ከመልካም ሥራዎችም የሠራ ሰው በደልንም መጉደልንም አይፈራም፡፡
እንደዚሁም ዐረብኛ ቁርኣን ኾኖ አወረድነው፡፡ አላህንም ይፈሩ ዘንድ ወይም ለእነሱ ግሣጼን ያድስላቸው ዘንድ ከዛቻ ደጋግመን በውስጡ ገለጽን፡፡
እውነተኛው ንጉስ አላህም (ከሓዲዎች ከሚሉት) ላቀ፡፡ ወደ አንተ መወረዱም ከመፈጸሙ በፊት በማንበብ አትቸኩል፡፡ «ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትንም ጨምርልኝ» በል፡፡
ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡ ረሳም፡፡ ለእርሱም ቆራጥነትን አላገኘንለትም፡፡
ለመላእክትም ለአዳም ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ሰገዱም፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፡፡
አልንም «አደም ሆይ! ይህ ላንተም ለሚስትህም በእርግጥ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ከገነት አያውጣችሁ፤ ትለፋለህና፡፡
ለአንተ በእርሷ ውስጥ አለመራብና አለመታረዝ አለህ፡፡
አንተም በርሷ ውስጥ አትጠማም፤ ፀሐይም አትተኮስም፡፡
ሰይጣንም ወደርሱ ጎተጎተ «አደም ሆይ! በመዘውተሪያ ዛፍ በማይጠፋ ንግሥናም ላይ ላመላክትህን አለው፡፡
ከእርሷም በልሉ፡፡ ለእነርሱም ኀፍረተ ገላቸው ተገለጸች፡፡ ከገነትም ቅጠል በላያቸው ላይ ይለጥፉ ጀመር፡፡ አደምም የጌታውን ትእዛዝ (ረስቶ) ጣሰ፡፡ (ከፈለገው መዘውተር) ተሳሳተም፡፡
ከዚያም ጌታው መረጠው ከእርሱም ጸጸቱን ተቀበለው መራውም፡፡
አላቸው «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ሁላችሁም ከእርሷ ውረዱ ከእኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገርምም፡፡
«ከግሣጼዬም የዞረ ሰው ለእርሱ ጠባብ ኑሮ አለው፡፡ በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን፡፡
«ጌታዬ ሆይ! ለምን ዕውር አድርገህ አስነሳኸኝ በእርግጥ የማይ የነበርኩ ስኾን» ይላል፡፡
(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፡፡ «ታምራታችን መጣችልህ፡፡ ተውካትም፡፡ እንደዚሁም ዛሬ ትተዋለህ» ይለዋል፡፡
እንደዚሁም ያጋራንና በጌታው አንቀጾች ያላመነን ሰው እንቀጣዋለን፡፡ የመጨረሻይቱም ዓለም ቅጣት በጣም ብርቱ ሁልጊዜ ዘውታሪም ነው፡፡
(ቁረይሾች) ከእነሱ በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን ያጠፋን መኾናችን በመኖሪያዎቻቸው የሚኼዱ ኾነው ሳሉ ለእነርሱ አልተገለጸላቸውምን በዚህ ውስጥ ለአእምሮ ባለቤቶች በእርግጥ መልክቶች አሉበት፡፡
ከጌታህ ያለፈች ቃልና የተወሰነ ጊዜ ባልነበረ ኖሮ (ቅጣቱ አሁኑኑ) የሚይዛቸው ይኾን ነበር፡፡
በሚሉትም ላይ ታገስ፡፡ ጌታህንም ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት ከመግባትዋም በፊት የምታመሰግን ኾነህ አጥራው፤ (ስገድ)፡፡ ከሌሊት ሰዓቶችም በቀን ጫፎችም አጥራው፡፡ (በሚሰጥህ ምንዳ) ልትወድ ይከጀላልና፡፡
ዓይኖችህንም ከእነርሱ (ከሰዎቹ) ክፍሎችን በእርሱ ልንፈትናቸው ወደ አጣቀምንበት፤ ወደ ቅርቢቱ ሕይወት ጌጦች አትዘርጋ፡፡ የጌታህ ሲሳይም በጣም በላጭ ዘውታሪም ነው፡፡
ቤተሰብህንም በስግደት እዘዝ፡፡ በእርሷም ላይ ዘውትር፤(ጽና)፡፡ ሲሳይን አንጠይቅህም፡፡ እኛ እንሰጥሃለን፡፡ መልካሚቱ መጨረሻም ለጥንቁቆቹ ናት፡፡
«ከጌታውም በኾነ ተዓምር አይመጣንምን» አሉ በመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ውስጥ ያለችው ማስረጃ አልመጣቻቸውምን
እኛም ከእርሱ (ከሙሐመድ መላክ) በፊት በቅጣት ባጠፋናቸው ኖሮ «ጌታችን ሆይ! ከመዋረዳችንና ከማፈራችን በፊት አንቀጾችህን እንከተል ዘንድ ወደኛ መልከተኛን አትልክም ነበርን» ባሉ ነበር፡፡
«ሁሉም ተጠባባቂ ነው፡፡ ተጠባበቁም፡፡ የቀጥታውም መንገድ ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ እነማንም እንደ ተመሩ ወደ ፊት ታውቃላችሁ» በላቸው፡፡
Icon