ترجمة سورة غافر

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة غافر باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

ሐ.መ (ሓ.ሚም)፤
የመጽሐፉ መወረድ አሸናፊ ዐዋቂ ከሆነው አላህ ነው፡፡
ኀጢአትን መሓሪ፣ ጸጸትንም ተቀባይ፣ ቅጣተ ብርቱ፣ የልግስና ባለቤት ከኾነው (አላህ የወረደ ነው)፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ መመለሻው ወደርሱ ብቻ ነው፡፡
በአላህ አንቀጾች እነዚያ የካዱት ቢኾኑ እንጅ ማንም (በመዝለፍ) አይከራከርም፡፡ በያገሮችም ውስጥ መዘዋወራቸው አይሸንግልህ፡፡
ከእነርሱ በፊት የኑሕ ሕዝቦች ከኋላቸውም አሕዛቦቹ አስተባባሉ፡፡ ሕዝቦችም ሁሉ መልክተኛቸውን ሊይዙ አሰቡ፡፡ በውሸትም በእርሱ እውነትን ሊያጠፉበት ተከራከሩ፡፡ ያዝኳቸውም፡፡ ታዲያ ቅጣቴ እንዴት ነበር?
እንደዚሁም የጌታህ ቃል በእነዚያ በካዱት ላይ እነርሱ የእሳት ጓዶች ናቸው ማለት ተረጋገጠች፡፡
እነዚያ ዐርሹን የሚሸከሙት እነዚያም በዙሪያው ያሉት በጌታቸው ምስጋና ያወድሳሉ፡፡ በእርሱም ያምናሉ፡፡ «ጌታችን ሆይ! ነገሩን ሁሉ በእዝነትና በዕውቀት ከበሃል፡፡ ስለዚህ ለእነዚያ ለተጸጸቱት መንገድህንም ለተከተሉት ምሕረት አድርግላቸው፡፡ የእሳትንም ቅጣት ጠብቃቸው፡፡» እያሉ ለእነዚያ ላመኑት ምሕረትን ይለምናሉ፡፡
«ጌታችን ሆይ! እነርሱንም፣ ከአባቶቻቸውና ከሚስቶቻቸውም፣ ከዝርዮቻቸውም፣ የበጀውን ሁሉ እነዚያን ቃል የገባህላቸውን የመኖሪያ ገነቶች አግባቸው፡፡ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ነህና፡፡
«ከቅጣቶችም ጠብቃቸው፡፡ በዚያ ቀንም የምትጠብቃውን ሰው በእርግጥ አዘንክለት፡፡» ይህም እርሱ ታላቅ ማግኘት ነው፡፡
እነዚያ የካዱት ሰዎች «ወደ እምነት በምትጠሩና በምትክዱ ጊዜ አላህ (እናንተን) መጥላቱ ነፍሶቻችሁን (ዛሬ) ከመጥላታችሁ የበለጠ ነው» በማለት ይጥጠራሉ፡፡
«ጌታችን ሆይ! ሁለትን ሞት አሞትከን፡፡ ሁለትንም ሕይወት ሕያው አደረግከን፡፡ በኃጢኣቶቻችንም መሰከርን፡፡ ታዲያ (ከእሳት) ወደ መውጣት መንገድ አለን?» ይላሉ፡፡
«ይህ እነሆ አላህ ብቻውን በተጠራ ጊዜ ስለ ካዳችሁ በእርሱም ተጋሪ ቢደረግ የምታምኑ ስለ ኾናችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርዱ ከፍተኛ ታላቅ ለኾነው አላህ ብቻ ነው፡፡»
እርሱ ያ (ለአምላክነቱ) ምልክቶቹን የሚያሳያችሁ ለእናንተም ከሰማይ ሲሳይን የሚያወርድላችሁ ነው፡፡ ወደእርሱም የሚመለስ ሰው ቢኾን እንጂ ሌላው አይገሰጽም፡፡
አላህንም ከሓዲዎች ቢጠሉም ሃይማኖትን ለእርሱ አጥሪዎች ኾናችሁ ተገዙት፡፡
(እርሱ) ደረጃዎችን ከፍ አድራጊ የዐርሹ ባለቤት ነው፡፡ የመገናኛውን ቀን ያስፈራራ ዘንድ ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ ከትዕዛዙ መንፈስን (ራእይን) ያወርዳል፡፡
እነርሱ (ከመቃብር) በሚወጡበት ቀን በአላህ ላይ ከእነርሱ ምንም ነገር አይደበቅም፡፡ «ንግሥናው ዛሬ ለማን ነው?» (ይባላል፤)፡፡ «ለአሸናፊው ለአንዱ አላህ ብቻ ነው» (ይባላል)፡፡
«ዛሬ ነፍስ ሁሉ በሠራችው ሥራ ትምመነዳለች፡፡ ዛሬ በደል የለም፡፡ አላህ በእርግጥ ምርመራው ፈጣን ነው» (ይባላል)፡፡
ቅርቢቱንም (የትንሣኤን) ቀን ልቦች ጭንቀትን የተመሉ ኾነው ላንቃዎች ዘንድ የሚደርሱበትን ጊዜ አስጠንቅቃቸው፡፡ ለበዳዮች ምንም ወዳጅና ተሰሚ አማላጅ የላቸውም፡፡
(አላህ) የዓይኖችን ክዳት ልቦችም የሚደብቁትን ሁሉ ያውቃል፡፡
አላህም በእውነት ይፈርዳል፡፡ እነዚያም ከእርሱ ሌላ የሚግገዟቸው በምንም አይፈርዱም፡፡ አላህ እርሱ ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡
የእነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ሕዝቦች ፍጻሜ እንዴት እንደነበረ ይመለከቱ ዘንድ በምድር ላይ አይኼዱምን? በኀይልና በምድር ላይ በተዋቸው ምልክቶች፤ ከእነርሱ ይበልጥ የበረቱ ነበሩ፡፡ አላህም በኀጢአቶቻቸው ያዛቸው፡፡ ለእነርሱም ከአላህ (ቅጣት) ምንም ጠባቂ አልነበራቸውም፡፡
ይህ (መያዝ) እነርሱ መልክተኞቻቸው በተዓምራቶች ይመጡባቸው ስለነበሩና ስለ ካዱ ነው፡፡ አላህም ያዛቸው፡፡ እርሱ ኀያል ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡
ሙሳንም በተዓምራቶቻችንና በግልጽ ማስረጃ በእርግጥ ላክነው፡፡
ወደ ፈርዖንና ወደ ሃማን፤ ወደ ቃሩንም (ላክነው)፡፡ «ድግምተኛ ውሸታም ነው» አሉም፡፡
ከእኛ ዘንድ እውነትን ይዞ በመጣላቸውም ጊዜ «የእነዚያን ከእርሱ ጋር ያመኑትን ሰዎች ወንዶች ልጆች ግደሉ፤ ሴቶቻቸውንም አስቀሩ» አሉ፡፡ የከሓዲዎችም ተንኮል በጥፋት ውስጥ እንጅ አይደለም፡፡
ፈርዖንም «ተዉኝ፤ ሙሳን ልግደል፡፡ ጌታውንም ይጥራ፡፡ ያድነው እንደኾነ፡፡ እኔ ሃይማኖታችሁን ሊለውጥ፤ ወይም በምድር ውስጥ ጥፋትን ሊያሰራጭ እፈራለሁና» አለ፡፡
ሙሳም «እኔ በምርመራው ቀን ከማያምን ትዕቢተኛ ሁሉ በጌታዬና በጌታችሁ ተጠበቅሁ» አለ፡፡
ከፈርዖንም ቤተሰቦች አንድ እምነቱን የሚደብቅ ምእመን ሰው አለ፡- «ሰውየውን ከጌታችሁ በተዓምራቶች በእርግጥ የመጣለችሁ ሲኾን ‹ጌታዬ አላህ ነው› ስለሚል ትገድላላችሁን? ውሸታምም ቢኾን ውሸቱ በርሱው ላይ ነው፡፡ እውነተኛ ቢኾን ግን የዚያ የሚያሰፈራራችሁ ከፊሉ ያገኛችኋል፡፡ አላህ ያንን እርሱ ድንበር አላፊ ውሸታም የኾነውን አይመራምና፡፡
«ወገኖቼ ሆይ! በምድር ላይ አሸናፊዎች ስትኾኑ ዛሬ መንግስቱ የእናንተ ነው፡፡ ታዲያ ከአላህ ቅጣት ቢመጣብን የሚያድነን ማን ነው?» (አለ)፡፡ ፈርዖን «የማየውን ነገር እንጅ፤ አላመለክታችሁም፡፡ ቅኑንም መንገድ እንጅ አልመራችሁም» አላቸው፡፡
ያም ያመነው ሰው አለ «እኔ በናንተ ላይ የአሕዛቦቹን ቀን ብጤ እፈራላችኋለሁ፡፡
«የኑሕን ሕዝቦች፣ የዓድንና የሰሙድንም፣ የእነዚያንም ከኋላቸው የነበሩትን ልማድ ብጤ (እፈራላችኋለሁ)፡፡ አላህም ለባሮቹ መበደልን የሚሻ አይደለም፡፡
«ወገኖቼ ሆይ! እኔ በእናንተ ላይ የመጠራሪያን ቀን እፈራለሁ፡፡»
ወደ ኋላ ዞራችሁ በምትሸሹበት ቀን፤ ለናንተ ከአላህ (ቅጣት) ምንም ጠባቂ የላችሁም፡፡ አላህም የሚያጠመው ሰው ለርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡
ዩሱፍም ከዚህ በፊት ግልጽ ማስረጃዎችን በእርግጥ አመጣላቸሁ፡፡ ከዚያም እርሱ ካመጣላችሁ ነገር ከመጠራጠር አልተወገዳችሁም፡፡ በጠፋም ጊዜ «አላህ ከእርሱ ኋላ መልክተኛን በጭራሽ አይልክም» አላችሁ፡፡ አላህ እንደዚሁ ድንበር አላፊ ተጠራጣሪ የኾነን ሰው ያሳስታል፡፡
እነዚያ፤ የመጣላቸው አስረጅ ሳይኖር በአላህ ተዓምራቶች የሚከራከሩ (ክርክራቸው) አላህ ዘንድና እነዚያም አመኑት ዘንድ መጠላቱ በጣም ተለቀ፡፡ እንደዚሁ አላህ በኩሩ ጨካኝ (ሰው) ልብ ሁሉ ላይ ያትማል፡፡
ፈርዖንም አለ «ሃማን ሆይ! መንገዶችን እደርስ ዘንድ ረዢም ሕንጻን ለእኔ ካብልኝ፡፡
«የሰማያትን መንገዶች (እደርስ ዘንድ)፣ ወደ ሙሳም አምላክ እመለከት ዘንድ፡፡ እኔም ውሸታም ነው ብዬ በእርግጥ እጠረጥረዋለሁ» (አለ)፡፡ እንደዚሁም ለፈርዖን መጥፎ ሥራው ተሸለመለት፡፡ ከቅን መንገድም ታገደ፡፡ የፈርዖንም ተንኮል በከሳራ ውስጥ እንጅ አይደለም፡፡
ያም ያመነው አለ «ወገኖቼ ሆይ! ተከተሉኝ፡፡ ቀጥታውን መንገድ እመራችኋለሁና፡፡
«ወገኖቼ ሆይ! ይህቺ ቅርቢቱ ሕይወት (ጥቂት) መጣቀሚያ ብቻ ናት፡፡ መጨረሻይቱም ዓለም እርሷ መርጊያ አገር ናት፡፡»
«መጥፎን የሠራ ሰው ብጤዋን እንጅ አይምመነዳም፡፡ እርሱ ምእመን ኾኖ ከወንድ ወይም ከሴት በጎን የሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡ በእርሷ ውስጥ ያለ ቁጥጥር ይመገባሉ፡፡
«ወገኖቼም ሆይ! ወደ መዳን የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳትም የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለኔ ምን አለኝ!
«በአላህ ልክድና በእርሱም ለእኔ ዕውቀት የሌለኝን ነገር በእርሱ እንዳጋራ ትጠሩኛላችሁ፡፡ እኔም ወደ አሸናፊው፤ መሓሪው (አላህ) እጠራችኋለሁ፡፡
«በእርግጥ ወደእርሱ የምትጠሩብኝ (ጣዖት) ለእርሱ በቅርቢቱም ኾነ በመጨረሻይቱ ዓለም (ተሰሚ) ጥሪ የለውም፡፡ መመለሻችንም በእርግጥ ወደ አላህ ነው፡፡ ወሰን አላፊዎቹም እነሱ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡
«ወደ ፊትም ለእናንተ የምላችሁን ምክር (ቅጣትን በምታዩ ጊዜ) ታስታውሳላችሁ፡፡ ነገሬንም ሁሉ ወደ አላህ አስጠጋለሁ፡፡ አላህ ባሮቹን ተመልካች ነውና፡፡»
ከመከሩዋቸውም መጥፎዎች አላህ ጠበቀው፡፡ በፈርዖን ቤተሰቦችም ላይ ክፉ ቅጣት ሰፈረባቸው፡፡
እሳት በጧትና በማታ በእርሷ ላይ ይቀርባሉ፡፡ ሰዓቲቱም በምትኾንበት ቀን «የፈርዖንን ቤተሰቦች ብርቱን ቅጣት (ገሀነምን) አግቡዋቸው» (ይባላል)፡፡
በእሳትም ውስጥ የሚከራከሩበትን ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ደካማዎቹም ለእነዚያ ለኮሩት «እኛ ለእናንተ ተከታዮች ነበርንና እናንተ (አሁን) ከእሳት ከፊሉን ከእኛ ላይ ገፍታሪዎች ናችሁን?» ይላሉ፡፡
እነዚያም የኮሩት «እኛ ሁላችንም በውስጧ ነን፡፡ አላህ በባሮቹ መካከል በእርግጥ ፈረደ» ይላሉ፡፡
እነዚያም በእሳት ውሰጥ ያሉት ለገሀነም ዘበኞች «ጌታችሁን ለምኑልን፤ ከእኛ ላይ ከቅጣቱ አንድን ቀን ያቃልልን» ይላሉ፡፡
(ዘበኞቹም) «መልእክተኞቻችሁ በተዓምራቶች ይመጡላችሁ አልነበሩምን?» ይላሉ፡፡ (ከሓዲዎቹም) «እንዴታ መጥተውናል እንጅ፤ (ግን አስተባበልናቸው)» ይላሉ፡፡
እኛ መልክተኞቻችንን፣ እነዚያንም ያመኑትን በቅርቢቱ ሕይወት ምስክሮችም በሚቆሙበት ቀን በእርግጥ እንረዳለን፡፡
በደለኞችን ምክንያታቸው በማይጠቅማቸው ቀን (እንረዳለን)፡፡ ለእነርሱም ርግማን አልላቸው፡፡ ለእነርሱም መጥፎ አገር አልላቸው፡፡
ሙሳንም መምሪያን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ የእስራኤልንም ልጆች መጽሐፉን አወረስናቸው፡፡
ለባለ አእምሮዎች መሪና ገሳጭ ሲኾን፡፡
(ሙሐመድ ሆይ!) ታገስም የአላህ ተስፋ እውነት ነውና፡፡ ለስህተትህም ምሕረትን ለምን፡፡ ከቀትር በኋላም በማለዳም ጌታሀን ከማመስገን ጋር አጥራው፡፡
እነዚያ የመጣላቸው አስረጅ ሳይኖር በአላህ አንቀጾች የሚከራከሩ በልቦቻቸው ውስጥ እነርሱ ደራሾቹ ያልኾኑት ኩራት ብቻ እንጅ ምንም የለም፡፡ በአላህም ተጠበቅ፡፡ እነሆ እርሱ ሰሚው ተመልካቹ ነውና፡፡
ሰማያትንና ምድርን መፍጠር ሰዎችን ከመፍጠር ይልቅ ታላቅ ነው፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡
ዕውርና የሚያይ እነዚያም አምነው መልካሞችን የሠሩና መጥፎ ሠሪው አይስተካከሉም፡፡ በጣም ጥቂትን ብቻ ትገሰጻላችሁ፡፡
ሰዓቲቱ በእርግጥ መጪ ናት፡፡ በእርሷ ጥርጥር የለም፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያምኑም፡፡
ጌታችሁም አለ «ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ እነዚያ እኔን ከመግገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ኾነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡
አላህ ያ ለእናንተ ሌሊትን በውስጡ ልታርፉበት (ጨለማ) ቀንንም (ልትሠሩበት) የሚያሳይ ያደረገላችሁ ነው፡፡ አላህ በሰዎች ላይ በእርግጥ የችሮታ ባለቤት ነውና፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያመሰግኑም፡፡
ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ትመለሳላችሁ፡፡
እንደዚሁ እነዚያ በአላህ አንቀጾች ይክዱ የነበሩት (ከእምነት) ይመለሳሉ፡፡
አላህ ያ ምድርን መርጊያ ሰማይንም ጣሪያ ያደረገላችሁ ነው፡፡ የቀረጻችኁም ቅርጻችሁንም ያሳመረ ከጣፋጮችም ሲሳዮች የሰጣችሁ ነው፡፡ ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ የዓለማትም ጌታ አላህ ላቀ፡፡
እርሱ ብቻ (ሁል ጊዜ) ሕያው ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ሃይማኖትንም ለእርሱ ያጠራችሁ ስትኾኑ «ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይኹን» የምትሉ ኾናችሁ ተገዙት፡፡
«እኔ ከጌታዬ አስረጂዎች በመጡልኝ ጊዜ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትገዙዋቸውን እንዳልገዛ ተከልክያለሁ፡፡ ለዓለማት ጌታም እንድገዛ ታዝዣለሁ» በላቸው፡፡
እርሱ ያ ከዐፈር ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ከዚያም ከረጋ ደም የፈጠራችሁ ነው፡፡ ከዚያም ሕጻናት አድርጎ ያወጣችኋል፡፡ ከዚያም ጥንካሬያችሁን ትደርሱ ዘንድ፤ ከዚያም ሽማግሌዎች ትኾኑ ዘንድ (ያቆያችኋል)፡፡ ከእናንተም ውስጥ ከዚህ በፊት የሚሞት አልለ፡፡ (ይህንንም ያደረገው ልትኖሩና) የተወሰነ ጊዜንም ልትደርሱ ታውቁም ዘንድ ነው፡፡
እርሱ ያ ሕያው የሚያደርግ የሚገድልም ነው፡፡ አንዳችን ነገር በሻም ጊዜ ለእርሱ የሚለውን «ኹን» ነው፤ ወዲያውም ይኾናል፡፡
ወደእነዚያ በአላህ አንቀጾች ወደሚከራከሩት (ከእምነት) እንዴት እንደሚመለሱ አታይምን?
ወደእነዚያ በመጽሐፉ በዚያም መልክተኞቻችንን በእርሱ በላክንበት ወዳስተባበሉት (አታይምን?) ወደፊትም ያውቃሉ፡፡
እንዛዝላዎቹና ሰንሰለቶቹ በአንገቶቻቸው ላይ በተደረጉ ጊዜ (በእርሷ) ይጎተታሉ፡፡
በገሀነም ውስጥ (ይጎተታሉ)፤ ከዚያም በእሳት ውስጥ ይማገዳሉ፡፡
ከዚያም ለእነርሱ ይባላሉ (በአላህ) «ታጋሯቸው የነበራችሁት የታሉ?»
«ከአላህ ሌላ (የምታጋሩዋቸው)፤ ከኛ ተሰወሩን?» «ከቶ ከዚህ በፊት ምንንም የምንገዛ አልነበርንም» ይላሉ፤ እንደዚሁ አላህ ከሓዲዎችን ያሳስታል፡፡
ይህ (ቅጣት) ያላግባብ በምድር ውሰጥ ትደሰቱ በነበራችሁትና ትንበጣረሩ በነበራችሁት ነው (ይባላሉ)፡፡
የገሀነምን በሮች በውስጧ ዘውታሪዎች ስትኾኑ ግቡ (ይባላሉ)፡፡ የትዕቢተኞችም መኖሪያ (ገሀነም) ምን ትከፋ!
ታገስም የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና፡፡ የዚያንም የምናስፈራራቸውን ከፊሉን (በሕይወትህ) ብናሳይህ (መልካም ነው)፡፡ ወይም ብንገድልህ ወደኛ ይመለሳሉ፡፡
ካንተ በፊትም መልክተኞችን በእርግጥ ልከናል፡፡ ከእነርሱ ባንተ ላይ የተረክንልህ አልለ፡፡ ከእነርሱም ባንተ ላይ ያልተረክነው አልለ፡፡ ለማንኛውም መልክተኛ በአላህ ፈቃድ ካልኾነ ተዓምርን ሊያመጣ አይገባውም፡፡ የአላህም ትእዛዝ በመጣ ጊዜ በእውነት ይፈረዳል፡፡ እዚያ ዘንድም አጥፊዎቹ ይከስራሉ፡፡
አላህ ያ ለእናንተ ግመልን ከብትንና ፍየልን ከእርሷ (ከፊሏን) ልትጋልቡ የፈጠረላችሁ ነው፡፡ ከእርሷም ትበላላችሁ፡፡
ለእናንተም በእርሷ ውስጥ ጥቅሞች አልሏችሁ፡፡ በእርሷም ላይ (እቃን በመጫን) በልቦቻችሁ ያሰባችሁትን ጉዳይ ትደርሱ ዘንድ (ፈጠረላችሁ)፡፡ በእርሷም ላይ በመርከቦችም ላይ ትሳፈራላችሁ፡፡
ተዓምራቱንም ያሳያችኋል፡፡ ታዲያ ከአላህ ተዓምራት የትኛውን ትክዳላችሁ?
የእነዚያን ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ሕዝቦች ፍጻሜ እንዴት እንደነበረ ይመለከቱ ዘንድ በምድር ላይ አይኼዱምን? ከእነርሱ ይበልጥ ብዙዎች በኀይልና በምድር ላይ በተዋቸው ምልክቶችም በጣም ብርቱዎች ነበሩ፡፡ ያም ይሠሩት የነበሩት ከእነርሱ ምንም አልጠቀማቸውም፡፡
መልክተኞቻቸውም ተዓምራቶችን ባመጡላቸው ጊዜ እነርሱ ዘንድ ባለው ዕውቀት ተደሰቱ፡፡ በእርሱ ይሳለቁበት የነበሩት ቅጣትም በእነርሱ ላይ ሰፈረባቸው፡፡
ብርቱ ቅጣታችንንም ባዩ ጊዜ «በአላህ አንድ ሲኾን አምነናል፤ በእርሱም እናጋራ በነበርነው (ጣዖታት) ክደናል» አሉ፡፡
ብርቱ ቅጣታችንን ባዩ ጊዜ ማመናቸውም የሚጠቅማቸው አልነበረም፡፡ የአላህን ደንብ ያችን በባሮቹ ውስጥ ያለፈችውን (ተጠንቀቁ) በዚያ ጊዜም ከሓዲዎች ከሰሩ፡፡
Icon