ترجمة سورة البقرة

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة البقرة باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

አ.ለ.መ
ይህ መጽሐፍ (ከአላህ ለመኾኑ) ጥርጥር የለበትም፤ ለፈራህያን መሪ ነው፡፡
ለነዚያ በሩቁ ነገር የሚያምኑ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው የሚሰግዱ ከሰጠናቸውም ሲሳይ የሚቸሩ ለኾኑት፤
ለእነዚያም ወደ አንተ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው የሚያምኑ በመጨረሻይቱም (ዓለም) እነርሱ የሚያረጋግጡ ለኾኑት (መሪ ነው)፡፡
እነዚያ ከጌታቸው በመመራት ላይ ናቸው፤ እነዚያም እነሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
እነዚያ የካዱት (ሰዎች) ብታስፈራራቸውም ባታስፈራራቸውም በነርሱ ላይ እኩል ነው፤ አያምኑም፡፡
አላህ በልቦቻቸው ላይ በመስሚያቸውም ላይ አትሞባቸዋል፤ በዓይኖቻቸውም ላይ መሸፈኛ አልለ፤ ለነሱም ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡
ከሰዎችም «በአላህና በመጨረሻው ቀን አምነናል» የሚሉ አልሉ፤ እነርሱም አማኞች አይደሉም፡፡
አላህንና እነዚያን ያመኑትን (ሰዎች) ያታልላሉ፤ የማያውቁ ሲኾኑ ነፍሶቻቸውን እንጅ ሌላን አያታልሉም፡፡
በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ አለባቸው፡፡ አላህም በሽታን ጨመረባቸው፡፡ ለነርሱም ይዋሹ በነበሩት ምክንያት አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
ለነርሱም «በምድር ላይ አታበላሹ» በተባሉ ጊዜ «እኛ አሳማሪዎች ብቻ ነን» ይላሉ፡፡
ንቁ እነርሱ አጥፊዎቹ እነሱው ናቸው፤ ግን አያውቁም፡፡
ለነሱም «ሰዎቹ እንዳመኑ እመኑ» በተባሉ ጊዜ «ቂሎቹ እንዳመኑ እናምናለን?» ይላሉ፡፡ አዋጅ ንቁ እነርሱ ቂሎቹ እነርሱው ናቸው፤ ግን አያውቁም፡፡
እነዚያንም ያመኑትን በተገናኙ ጊዜ «አምነናል» ይላሉ፡፡ ወደ ሰይጣኖቻቸውም ባገለሉ ጊዜ «እኛ ከናንተ ጋር ነን፤ እኛ (በነሱ) ተሳላቂዎች ብቻ ነን» ይላሉ፡፡
አላህ በነሱ ይሳለቅባቸዋል፤ በጥመታቸውም ውስጥ የሚዋልሉ ሲኾኑ ያዘገያቸዋል፡፡
እነዚህ እነዚያ ስህተትን በቅንነት የገዙ ናቸው፡፡ ንግዳቸውም አላተረፈችም፤ ቀጥተኞችም አልኾኑም፡፡
(በንፍቅና) ምሳሌያቸው እንደዚያ እሳትን እንዳነደደ ሰው በዙሪያው ያለውን ሁሉ ባበራች ጊዜም አላህ ብርሃናቸውን እንደወሰደባቸው በጨለማዎችም ውስጥ የማያዩ ኾነው እንደተዋቸው (ሰዎች) ብጤ ነው፡፡
(እነሱ) ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አይመለሱም፡፡
ወይም (ምሳሌያቸው) ከሰማይ እንደ ወረደ ዝናም (ባለቤቶች) ነው፤ በርሱ (በደመናው) ውስጥ ጨለማዎች፣ ነጎድጓድም፣ ብልጭታም ያሉበት ሲኾን ከመብረቆቹ ሞትን ለመፍራት ጣቶቻቸውን በጆሮቻቸው ውስጥ እንደሚያደርጉ ብጤ ነው፡፡ አላህም ከሓዲዎችን ከባቢ ነው፡፡
ብልጭታው ዓይኖቻቸውን ሊነጥቅ ይቀርባል፡፡ ለነርሱ ባበራላቸው ቁጥር በርሱ ውስጥ ይኼዳሉ፡፡ በነሱም ላይ ባጨለመ ጊዜ ይቆማሉ፡፡ አላህም በሻ ኖሮ መስሚያቸውንና ማያዎቻቸውን በወሰደ ነበር፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡
(እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው፤ ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው፡፡ እናንተም (ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትኾኑ ለአላህ ባላንጣዎችን አታድርጉ፡፡
በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ፡፡ እውነተኞችም እንደኾናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ፡፡
(ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ድንጋዮች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፤ ለከሓዲዎች ተደግሳለች፡፡
እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሠሩትን ለነርሱ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች ያሏቸው መኾኑን አብስራቸው፡፡ ከርሷ ከፍሬ (ዓይነት) ሲሳይን በተመገቡ ቁጥር (ፍሬዎችዋ ስለሚመሳሰሉ) «ይህ ያ ከአሁን በፊት የተገመብነው ነው» ይላሉ፡፡ እርሱንም ተመሳሳይ ኾኖ ተሰጡት፡፡ ለነሱም በውስጧ ንጹህ የተደረጉ ሚስቶች አሏቸው፡፡ እነሱም በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
አላህ ማንኛውንም ነገር ትንኝንም ኾነ (በትንሽነት ወይም በትልቅነት) ከበላይዋ የኾነንም ምሳሌ ለማድረግ አያፍርም፡፡ እነዚያ ያመኑትማ፤ እርሱ (ምሳሌው) ከጌታቸው (የተገኘ) እውነት መኾኑን ያውቃሉ፡፡ እነዚያም የካዱትማ «አላህ በዚህ ምንን ምሳሌ ሻ» ይላሉ፡፡ በርሱ (በምሳሌው) ብዙዎችን ያሳስታል በርሱም ብዙዎችን ያቀናል፡፡ በርሱም አመፀኞችን እንጅ ሌላን አያሳስትም፡፡
እነዚያ የአላህን ቃል ኪዳን ከአጠበቀባቸው በኋላ የሚያፈርሱ እንዲቀጠልም በርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቆርጡ በምድርም ላይ የሚያበላሹ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፡፡
ሙታን የነበራችሁ ስትኾኑ ሕያው ያደረጋችሁ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ሕያው የሚያደርጋችሁ ሲኾን ከዚያም ወደርሱ የምትመለሱ ስትኾኑ በአላህ እንዴት ትክዳለችሁ!
እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡ (አላህ) «እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ» አላቸው፡፡
አደምንም ስሞችን ሁሏንም አስተማረው፡፡ ከዚያም በመላእክት ላይ (ተጠሪዎቹን) አቀረባቸው፡፡ «እውነተኞችም እንደኾናችሁ የነዚህን (ተጠሪዎች) ስሞች ንገሩኝ» አላቸው፡፡
«ጥራት ይገባህ፤ ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፡፡ አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (አሉ)፡፡
፡-«አደም ሆይ ስሞቻቸውን ንገራቸው» አለው፡፡ ስሞቻቸውን በነገራቸውም ጊዜ «እኔ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምስጢር ዐውቃለሁ፤ የምትገልጹትንና ያንንም ትደብቁት የነበራችሁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን?» አላቸው፡፡
ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ (አስታውስ) ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡
«አደም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ በገነት ተቀመጥ፤ ከርሷም በፈለጋችሁት ስፍራ በሰፊው ተመገቡ፤ ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤ ከበደለኞች ትኾናላችሁና» አልንም፡፡
ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡
አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
«ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡
እነዚያም (በመልክተኞቻችን) የካዱ በአንቀጾቻችንም ያስተባበሉ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬን አስታውሱ፡፡ በቃል ኪዳኔም ሙሉ፤ በቃል ኪዳናችሁ እሞላለሁና፤ እኔንም ብቻ ፍሩ፡፡
ከናንተ ጋር ያለውን (መጽሐፍ) የሚያረጋግጥ ሆኖ ባወረድኩትም (ቁርኣን) እመኑ፡፡ በርሱም የመጀመሪያ ከሓዲ አትሁኑ፡፡ በአንቀጾቼም ጥቂትን ዋጋ አትለውጡ፡፡ እኔንም ብቻ ተጠንቀቁ፡
እውነቱንም በውሸት አትቀላቅሉ፡፡ እናንተም የምታውቁ ስትሆኑ እውነትን አትደብቁ፡፡
ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም (ግዴታ ምጽዋትን) ስጡ፡፡ (ለጌታችሁ) ከአጎንባሾች ጋርም አጎንብሱ፡፡
እናንተ መጽሐፉን የምታነቡ ሆናችሁ ሰዎችን በበጎ ሥራ ታዛላችሁን? ነፍሶቻችሁንም ትረሳላችሁን? (የሥራችሁን መጥፎነት) አታውቁምን?
በመታገስና በሶላትም ተረዱ፡፡ እርሷም (ሶላት) በፈሪዎች ላይ እንጅ በሌላው ላይ በእርግጥ ከባድ ናት፡፡
እነዚያ እነርሱ ጌታቸውን የሚገናኙ እነሱም ወደእርሱ ተመላሾች መኾናቸውን የሚያረጋግጡ በኾኑት (ላይ እንጅ ከባድ ናት)፡፡
የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ (አባቶቻችሁን በጊዜያቸው ከነበሩት ዓለማት ያበለጥኩዋቸው) መኾኔን አስታውሱ፡፡
(ማንኛዋ) ነፍስም ከ(ሌላዋ) ነፍስ ምንንም የማትመነዳበትን፣ ከርሷም ምልጃን የማይቀበሉባትን፣ ከርሷም ቤዛ የማይያዝበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡
ከፈርዖንም ቤተሰቦች (ከጎሶቹና ከሰራዊቱ) ብርቱን ቅጣት የሚያቀምሱዋችሁ ወንዶች ልጆቻችሁን የሚያርዱ ሴቶቻችሁንም የሚተው ሲኾኑ ባዳንናችሁ ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ በዚሃችሁም ከጌታችሁ ታላቅ ፈተና አለበት፡፡
በናንተም ምክንያት ባሕሩን በከፈልን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ ወዲያውም አዳንናችሁ፡፡ የፈርዖንንም ቤተሰቦች እናንተ የምትመለከቱ ኾናችሁ አሰጠምናቸው፡፡
ሙሳንም አርባን ሌሊት በቀጠርነው ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ ከዚያም ከርሱ (መኼድ) በኋላ እናንተ በዳዮች ስትኾኑ ወይፈንን (አምላክ አድርጋችሁ) ያዛችሁ፡፡
ከዚያም ከዚህ በኋላ እናንተ ታመሰግኑ ዘንድ ከናንተ ምሕረት አደረግን፡፡
ሙሳንም መጽሐፍንና (እውነትና ውሸትን) መለያንም ትመሩ ዘንድ በሰጠነው ጊዜ (አስታውሱ)፡፡
ሙሳም ለሕዝቦቹ፡- «ሕዝቦቼ ሆይ! እናንተ ወይፈንን (አምላክ አድርጋችሁ) በመያዛችሁ ነፍሶቻችሁን በደላችሁ፡፡ ወደ ፈጣሪያችሁም ተመለሱ፤ ነፍሶቻችሁንም ግደሉ፤ ይሃችሁ በፈጣሪያችሁ ዘንድ ለናንተ በላጭ ነው» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በእናንተም ላይ ጸጸትን በመቀበል ተመለሰላችሁ፡፡ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
«ሙሳ ሆይ! አላህን በግልጽ እስከምናይ ድረስ ላንተ በፍጹም አናምንልህም» በላችሁም ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ እናንተም እየተመለከታችሁ መብረቅ ያዘቻችሁ፡፡
ከዚያም ታመሰግኑ ዘንድ ከሞታችሁ በኋላ አስነሳናችሁ፡፡
በናንተም ላይ ደመናን አጠለልን፡፡ በናተም ላይ (እንደ ነጭ ማር ያለ) መንናን እና ድርጭትን አወረድን፡፡ ከሰጠናችሁም ጣፋጮች «ብሉ (አልን)፡፡» አልበደሉንምም ግን ነፍሶቻቸውን ይበድሉ ነበር፡፡
«ይህችንም ከተማ ግቡ፡፡ ከርሷም በሻችሁት ስፍራ ሰፊን (ምግብ) ተመገቡ፡፡ በሩንም ያጎነበሳችሁ ኾናችሁ ግቡ፤ (ጥያቄያችን የኃጢአታችን መርገፍ ነው) በሉም፡፡ ኃጢአቶቻችሁን ለናንተ እንምራለንና፡፡ በጎ ሠሪዎችንም (ምንዳን) እንጨምርላቸዋለን» ባልን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡
እነዚያም የበደሉት ሰዎች ከዚያ ለነሱ ከተባሉት ሌላ ቃልን ለወጡ፡፡ በነዚያም በበደሉት ላይ ያመጹ በመሆናቸው ምክንያት መቅሠፍትን አወረድንባቸው፡፡
ሙሳም ለሕዝቦቹ መጠጥን በፈለገ ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ «ድንጋዩንም በበትርህ ምታ» አልነው፡፡ (መታውም) ከርሱም ዐሥራሁለት ምንጮች ፈለቁ፡፡ ሰዎቹ ሁሉ መጠጫቸውን በእርግጥ ዐወቁ፡፡ «ከአላህ ሲሳይ ብሉ፤ ጠጡም፤ አመጠኞችም ኾናችሁ በምድር ላይ አታበላሹ» (አልናቸው)፡፡
ሙሳ ሆይ፡- «በአንድ (ዓይነት) ምግብ ላይ በፍጹም አንታገሥም፤ ስለዚህ ጌታህን ከዚያ ምድር ከምታበቅለው ሁሉ ከቅጠላቅጠል ከዱባዋም ከስንዴዋም ከምስርዋም ከሽንኩርቷም ለኛ ያወጣ ዘንድ ለኛ ለምንልን» ባላችሁም ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ፡፡ ሙሳም፡- «ያንን እርሱ ዝቅተኛ የኾነውን በዚያ እርሱ በላጭ በኾነው ነገር ለውጥን ትፈልጋላችሁን? ወደ ከተማ ውረዱ፤ ለናንተም የጠየቃችሁት ነገር አላችሁ» አላቸው፡፡ በነርሱም ላይ ውርደትና ድኽነት ተመታባቸው፡፡ ከአላህም በኾነ ቁጣ ተመለሱ፡፡ ይህ እነርሱ በአላህ ታምራቶች ይክዱና ነቢያትንም ያለ ሕግ ይገድሉ ስለነበሩ ነው፡፡ ይህ በማመጻቸውና ወሰን የሚያልፉ በመኾናቸው ነው፡፡
እነዚያ ያመኑ እነዚያም ይሁዳውያን የኾኑ፣ ክርስቲያኖችም፣ ሳቢያኖችም (ከእነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡
ከበላያችሁም የጡርን ተራራ ያነሳን ኾነን የጠበቀ ቃልኪዳናችሁን በያዝን ጊዜ (የኾነውን አስታውሱ)፡፡ «ያንን የሰጠናችሁን በኀይል ያዙ፤ በውስጡ ያለውንም ነገር (ከእሳት) ትጠበቁ ዘንድ አስታውሱ» (አልን)፡፡
ከዚያም ከዚህ በኋላ (ኪዳኑን) ተዋችሁ፡፡ በናንተም ላይ የአላህ ችሮታና እዝነቱ ባልነበረ ኖሮ በእርግጥ ከጠፊዎቹ በኾናችሁ ነበር፡፡
እነዚያንም ከእናንተ ውስጥ በቅዳሜ ቀን (ዐሣን በማጥመድ) ወሰን ያለፉትንና ለነሱ «ወራዳዎች ስትኾኑ ዝንጀሮዎች ኹኑ» ያልናቸውን በእርግጥ ዐወቃችሁ፡፡
(ቅጣቲቱንም) ለነዚያ በስተፊትዋ ለነበሩትና ለነዚያም ከበኋላዋ ላሉት (ሕዝቦች) መቀጣጫ ለፈራህያንም መገሰጫ አደረግናት፡፡
ሙሳም ለሕዝቦቹ፡- «አላህ ላምን እንድታርዱ ያዛችኋል» ባለ ጊዜ (አስታወሱ)፡፡«መሳለቂያ አድርገህ ትይዘናለህን?» አሉት፡፡ «ከተሳላቂዎች ከመኾን በአላህ እጠበቃለሁ» አላቸው፡፡
«ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤ እርሷ ምን እንደኾነች (ዕድሜዋን) ያብራራልን» አሉ፡፡ «እርሱ እርሷ ያላረጀች ጥጃም ያልኾነች በዚህ መካከል ልከኛ የኾነች ጊደር ናት ይላችኋል፤ የታዘዛችሁትንም ሥሩ» አላቸው፡፡
«ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤ መልኳ ምን እንደኾነ ለኛ ይግለጽልን» አሉ፡፡ «እርሱ እርሷ መልኳ ደማቅ ተመልካቾችን የምታስደስት ዳለቻ ላም ናት ይላችኋል» አላቸው፡፡
«ለኛ ጌታህን ጠይቅልን፤ እርሷ ምን እንደኾነች ይግለጽልን፤ ከብቶች በኛ ላይ ተመሳሰሉብን፡፡ እኛም አላህ የሻ እንደኾነ በእርግጥ ተመሪዎች ነን» አሉ፡፡
«እርሱ እርሷ ያልተገራች ምድርን (በማረስ) የማታስነሳ እርሻንም የማታጠጣ (ከነውር) የተጠበቀች ልዩ ምልክት የሌለባት ናት ይላችኋል» አላቸው፡፡ «አሁን በትክክል መጣህ» አሉ፤ ሊሠሩ ያልተቃረቡም ሲኾኑ አረዷት ፡፡
ነፍስነም በገደላችሁና በርሷም (ገዳይ) በተከራከራችሁ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ አላህም ትደብቁት የነበራችሁትን ሁሉ ገላጭ ነው፡፡
«(በድኑን) በከፊሏም ምቱት» አልን፤ እንደዚሁ አላህ ሙታንን ያስነሳል፤ ታውቁም ዘንድ ታምራቶችን ያሳያችኋል፡፡
ከዚያም ከዚህ በኋላ ልቦቻችሁ ደረቁ፤ እርሷም እንደ ድንጋዮች ወይም በድርቅና ይበልጥ የበረታች ናት፡፡ ከድንጋዮችም ከርሱ ጂረቶች የሚፈሱለት አልለ፡፡ ከነርሱም በእርግጥ የሚሰነጠቅና ከርሱ ውሃ (ምንጭ) የሚወጣው አልለ፡፡ ከነርሱም አላህን ከመፍራት የተነሳ ወደ ታች የሚወርድ አልለ፡፡ አላህም ከምትሠሩት ነገር ዘንጊ አይደለም፡፡
(አይሁዶች) ከነሱ የኾኑ ጭፍሮች የአላህን ቃል የሚሰሙና ከዚያም ከተረዱት በኋላ እነርሱ እያወቁ የሚለውጡት ሲኾኑ ለናንተ ማመናቸውን ትከጅላላችሁን?
እነዚያንም ያመኑትን ባገኙ ጊዜ «አምነናል» ይላሉ፡፡ ከፊላቸውም ወደ ከፊሉ ባገለለ «ጊዜ አላህ በናንተ ላይ በገለጸላቸሁ ነገር እጌታችሁ ዘንድ በርሱ እንዲከራከሩዋችሁ ትነግሩዋቸዋላችሁን? አታውቁምን?» ይላሉ፡፡
አላህ የሚደብቁትንና የሚገልጹትን የሚያውቅ መኾኑን አያውቁምን?
ከነሱም መጽሐፉን የማያውቁ መሃይማናን አሉ፡፡ ግን ከንቱ ምኞቶችን (ይመኛሉ)፤ እነርሱም የሚጠራጠሩ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡
ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡ ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው፡፡ ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው፡፡
«እሳትም የተቆጠሩን ቀኖች እንጂ አትነካንም» አሉ፡፡ «አላህ ዘንድ ቃል ኪዳን ይዛችኋልን? (ይህ ከኾነ) አላህም ኪዳኑን አያፈርስም፤ በእውነቱ በአላህ ላይ የማታውቁትን ትናገራላችሁ» በላቸው፡፡
አይደለም (ትነካችኋለች)፤ መጥፎን (ክሕደትን) የሠራ በርሱም ኃጠኣቱ የከበበችው ሰው እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
እነዚያም ያመኑት በጎ ሥራዎችንም የሠሩት እነዚያ የገነት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘላለም ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
የእስራኤል ልጆችንም ጥብቅ ኪዳን አላህን እንጂ ሌላን አታምልኩ፤ በወላጆችም በጎን ሥራ (አድርጉ)፤ በዝምድና ባለቤቶችም፣ በየቲሞችም (አባት የሌላቸው ልጆች) በምስኪኖችም (በጎ ዋሉ)፤ ለሰዎችም መልካምን ተናገሩ፤ ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፤ ዘካንም ስጡ በማለት በያዝንባቸው ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ ከዚያም ከናንተ ጥቂቶች ሲቀሩ ሸሻችሁ እናንተም (ኪዳንን) የምትተዉ ናችሁ፡፡
ደሞቻችሁን አታፍስሱ ነፍሶቻችሁንም (ከፊላችሁን) ከአገሮቻችሁ አታውጡ የምንል ስንኾን የጠበቀ ቃል ኪዳናችሁን በያዝንባችሁ ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ ከዚያም (በኪዳኑ) አረጋገጣችሁ፤ እናንተም ትመሰክራላችሁ፡፡
ከዚያም እናንተ እነዚያ ነፍሶቻችሁን የምትገድሉ ከናንተም የኾኑ ጭፍሮችን በኃጢአትና በመበደል በነርሱ ላይ የምትረዳዱ ስትኾኑ ከአገሮቻቸው የምታወጡ ምርኮኞችም ኾነው ቢመጡዋችሁ የምትበዡ ናችሁ፡፡ እርሱ (ነገሩ) እነርሱን ማውጣት በእናንተ ላይ የተከለከለ ነው፡፡ በመጽሐፉ ከፊል ታምናላችሁን? በከፊሉም ትክዳላችሁን? ከእናንተም ይህንን የሚሠራ ሰው ቅጣት በቅርቢቱ ሕይወት ውርደት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በትንሣኤ ቀንም ወደ ብርቱ ቅጣት ይመለሳሉ፡፡ አላህም ከምትሠሩት ሥራ ሁሉ ዘንጊ አይደለም፡፡
እነዚህ እነዚያ ቅርቢቱን ሕይወት በመጨረሻይቱ አገር የገዙ ናቸው፡፡ ከነሱም ቅጣቱ አይቀልላቸውም፤ እነሱም አይርረዱም፡፡
ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ ከበኋላውም መልክትኞችን አስከታተልን፡፡ የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው፡፡ ነፍሶቻችሁ በማትወደው ነገር መልክተኛ በመጣላችሁ ቁጥር (ከመከተል) ትኮራላችሁን? ከፊሉን አስተባበላችሁ፤ ከፊሉንም ትገድላላችሁ፡፡
«ልቦቻችንም ሽፍኖች ናቸው» አሉ፤ አይደለም አላህ በክሕደታቸው ምክንያት ረገማቸው ጥቂትንም ብቻ ያምናሉ፡፡
ከነሱም ጋር ያለውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መጽሐፍ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ (ከመምጣቱ) በፊት በነዚያ በካዱት ላይ ይረዱበት የነበሩ ሲኾኑ ያወቁት ነገር በመጣላቸው ጊዜ በርሱ ካዱ፡፡ የአላህም ርግማን በከሓዲዎች ላይ ይኹን፡፡
ነፍሶቻቸውን በርሱ የሸጡበት ነገር ከፋ! (እርሱም) አላህ ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ ከችሮታው (ራእይን) ማውረዱን በመመቅኘት አላህ ባወረደው ነገር መካዳቸው ነው፡፡ በቁጣ ላይም ቁጣ (የተረጋገጠባቸው ሲኾኑ) ተመለሱ፡፡ ለከሓዲዎችም አዋራጅ ቅጣት አላቸው፡፡
አላህም ባወረደው (ሁሉ) ለእነርሱ «እመኑ» በተባሉ ጊዜ «በኛ ላይ በተወረደው (መጽሐፍ ብቻ) እናምናለን» ይላሉ፡፡ ከርሱ ኋላ ባለው (ቁርአን) እርሱ ከነሱ ጋር ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ እውተኛ ሲኾን ይክዳሉ፡፡ «አማኞች ከኾናችሁ ከአሁን በፊት የአላህን ነቢያት ለምን ገደላችሁ?» በላቸው፡፡
ሙሳም በታምራቶች በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ ከዚያም ከበኋላው እናንተ በዳዮች ስትኾኑ ወይፈንን (አምላክ አድርጋችሁ) ያዛችሁ፡፡
የጡርንም ጋራ ከበላያችሁ ያነሳን ስንኾን (በኦሪት ሕግ እንድትሠሩ) ኪዳናችሁን በያዝን ጊዜ (አስታውሱ)፡፡ «የሰጠናችሁን በኀይል ያዙ፤ ስሙም፤» (አልን)፡፡«ሰማን አመጽንም» አሉ፡፡ የወይፈኑንም ውዴታ በክሕደታቸው ምክንያት በልቦቻቸው ውስጥ ተጠጡ፡፡ «አማኞች እንደኾናችሁ እምነታችሁ በርሱ የሚያዛችሁ ነገር ከፋ!» በላቸው፡፡
«የመጨረሻይቱ አገር (ገነት) አላህ ዘንድ ከሰው ሁሉ ሌላ የተለየች ስትኾን ለእናንተ ብቻ እንደኾነች እውነተኞች ከኾናችሁ ሞትን ተመኙ» በላቸው፡፡
እጆቻቸውም ባሳለፉት (በሠሩት) ምክንያት ምን ጊዜም ፈጽሞ አይመኙትም፤ አላህም በዳዮችን ዐዋቂ ነው፡፡
ከሰዎችም ሁሉ ከእነዚያም (ጣዖትን) ከአጋሩት ይበልጥ በሕይወት ላይ የሚጓጉ ኾነው በእርግጥ ታገኛቸዋለህ፡፡ አንዳቸው ሺሕ ዓመት ዕድሜ ቢሰጥ ይወዳል፡፡ እርሱም ዕድሜ መሰጠቱ ከቅጣት የሚያርቀው አይደለም፡፡ አላህም የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡
ለጂብሪል (ለገብርኤል) ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡
ለአላህና ለመላእክቱ ለመልክተኞቹም ለጂብሪልም ለሚካልም (ሚካኤል) ጠላት የኾነ ሰው አላህ ለ(እነዚህ) ከሓዲዎች ጠላት ነው፡፡
ወዳንተም ግልጽ የኾኑትን አንቀጾች በእርግጥ አውርደናል፡፡ በርሷም አመጸኞች እንጂ ሌላው አይክድም፤
ቃል ኪዳንንም ቃል በገቡ ቁጥር ከእነርሱ ከፊሉ ይጥለዋልን? (ያፈርሰዋልን?)፤ ይልቁንም አብዛኞቻቸው አያምኑም፡፡
እነርሱ ጋርም ላለው (መጽሐፍ) አረጋጋጭ የኾነ መልክተኛ ከአላህ ዘንድ በመጣላቸው ጊዜ ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ከፊሉ እነርሱ እንደማያውቁ ኾነው የአላህን መጽሐፍ ከጀርባዎቻቸው ኋላ ጣሉ፡፡
ሰይጣናትም በሱለይማን (ሰሎሞን) ዘመነ መንግስት የሚያነቡትን (ድግምት) ተከተሉ፡፡ ሱለይማንም አልካደም፤ (ድግምተኛ አልነበረም)፤ ግን ሰይጣናት ሰዎችን ድግምትን የሚያስተምሩ ሲኾኑ ካዱ፡፡ ያንንም በባቢል በሁለቱ መላእክት በሃሩትና ማሩት ላይ የተወረደውን ነገር (ያስተምሩዋቸዋል)፡፡ «እኛ መፈተኛ ነንና አትካድ» እስከሚሉም ድረስ አንድንም አያስተምሩም፡፡ ከእነሱም በሰውየውና በሚስቱ መካከል በርሱ የሚለዩበትን ነገር ይማራሉ፡፡ እነርሱም በአላህ ፈቃድ ካልኾነ በርሱ አንድንም ጎጂዎች አይደሉም፡፡ የሚጎዳቸውንና የማይጠቅማቸውንም ይማራሉ፡፡ የገዛውም ሰው ለርሱ በመጨረሻይቱ አገር ምንም እድል የሌለው መኾኑን በእርግጥ ዐወቁ፡፡ ነፍሶቻቸውንም በርሱ የሸጡበት ዋጋ ከፋ! የሚያውቁ በኾኑ ኖሮ (ባልሠሩት ነበር)፡፡
እነርሱም (አይሁዶች) ባመኑና በተጠነቀቁ ኖሮ (በተመነዱ ነበር)፡፡ የሚያውቁ ቢኾኑ ከአላህ ዘንድ የኾነው ምንዳ (ነፍሶቻቸውን ከሚሸጡበት) በላጭ ነው፡፤
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (ለነቢዩ) ራዒና አትበሉ፡፡ ተመለከትን በሉም፡፡ ስሙም፤ ለከሓዲዎችም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
እነዚያ ከመጽሐፉ ባለቤቶችና ከአጋሪዎቹም የካዱት በናንተ ላይ ከጌታችሁ የኾነ መልካም ነገር መወረዱን አይወዱም፡፡ አላህም በችሮታው (በነቢይነት) የሚሻውን ይመርጣል፡፡ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡
ከአንቀጽ ብንለውጥ ወይም እርሷን ብናስረሳህ ከርሷ የሚበልጥን ወይም ብጤዋን እናመጣለን፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ (ቻይ) መኾኑን አታውቅምን?
አላህ የሰማያትና የምድር ንግሥና ለርሱ ብቻ መኾኑን አታውቅምን? ለእናንተም ከአላህ ሌላ ዘመድና ረዳት ምንም የላችሁም፡፡
በእውነቱ ከአሁን በፊት ሙሳ እንደተጠየቀ ብጤ መልክተኛችሁን ልትጠይቁ ትፈልጋላችሁን? በእምነትም ክህደትን የሚለውጥ ሰው ትክክለኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ፡፡
ከመጽሐፉ ባለቤቶች ብዙዎች እውነቱ ከተገለጸላቸው በኋላ ከነፍሶቻቸው በኾነው ምቀኝነት ከእምነታችሁ በኋላ ከሓዲዎች አድርገው ሊመልሱዋችሁ ተመኙ፡፡ አላህም ትዕዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ይቅርታ አድርጉ፤ እለፏቸውም፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ከሃሊ ነውና፡፡
ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፡፡ ዘካንም ስጡ፡፡ ለነፍሶቻችሁም ከበጎ ሥራ የምታስቀድሙትን አላህ ዘንድ ታገኙታላችሁ፡፡ አላህ የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነውና፡፡
«ገነትንም አይሁድን ወይም ክርስቲያኖችን የኾነ ሰው እንጂ ሌላ አይገባትም» አሉ፡፡ ይህቺ (ከንቱ) ምኞታቸው ናት፡፡ «እውነተኞች እንደኾናችሁ አስረጃችሁን አምጡ» በላቸው፡፡
አይደለም (ሌላውም ይገባታል) እርሱ በጎ ሠሪ ኾኖ ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው ለርሱ በጌታው ዘንድ ምንዳው አለው፡፡ በነሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡
እነርሱ መጽሐፉን የሚያነቡ ሲኾኑ አይሁዶች፡- ክርስቲያኖች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ ክርስቲያኖችም፡- አይሁዶች በምንም ላይ አይደሉም አሉ፡፡ እንደዚሁ እነዚያ የማያውቁት (አጋሪዎች) የንግግራቸውን ብጤ አሉ፡፡ አላህም በዚያ በርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር በትንሣኤ ቀን በመካከላቸው ይፈርዳል፡፡
የአላህንም መስጊዶች በውስጣቸው ስሙ እንዳይወሳ ከከለከለና እርሷንም በማበላሸት ከሮጠ ሰው ይበልጥ በዳይ ማነው? እነዚያ ፈሪዎች ኾነው እንጂ ለእነርሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት አላቸው፡፡ ለነርሱም በመጨረሻይቱ አገር ታላቅ ቅጣት አላቸው፡፡
ምሥራቁም ምዕራቡም የአላህ ነው (ፊቶቻችሁን) ወደ የትም ብታዞሩ የአላህ ፊት እዚያ ነው፡፡ አላህ ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነውና፡፡
አላህም ልጅ አለው አሉ፡፡ (ከሚሉት) ጥራት ተገባው፡፡ አይደለም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የርሱ ነው፡፡ ሁሉም ለርሱ ታዛዦች ናቸው፡፡
ሰማያትንና ምድርን ያለብጤ ፈጣሪ ነው፤ ነገርንም (ማስገኘት) በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው፡- «ኹን ነው፤» ወዲያውም ይኾናል፡፡
እነዚያም የማያውቁት (አንተ መልክተኛ ስለመኾንህ) አላህ አያናግረንም ኖሮአልን? ወይም (ለእውነተኛነትህ) ታምር አትመጣልንም ኖሮአልን? አሉ፡፡ እንደዚሁ እነዚያ ከነሱ በፊት የነበሩት እንደ ንግግራቸው ብጤ ብለዋል፡፡ ልቦቻቸው (በክሕደት) ተመሳሰሉ፡፡ ለሚያረጋግጡ ሕዝቦች አንቀጾችን በእርግጥ አብራርተናል፡፡
እኛ አብሳሪና አስፈራሪ ኾነህ በውነት ላክንህ፡፡ ከእሳትም ጓዶች አትጠየቅም፡፡
አይሁዶችና ክርስቲያኖችም ሃይማኖታቸውን እስከምትከተል ድረስ ካንተ ፈጽሞ አይወዱም፡፡ «የአላህ መምራት (ትክክለኛው) መምራት እርሱ ብቻ ነው» በላቸው፡፡ ከዚያም እውቀቱ ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌያቸውን ብትከተል ለአንተ ከአላህ (የሚከለክልልህ) ዘመድና ረዳት ምንም የለህም፡፡
እነዚያ መጽሐፉን የሰጠናቸው ተገቢ ንባቡን ያነቡታል፡፡ እነዚያ በርሱ ያምናሉ፤ በርሱም የሚክዱ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፡፡
የእስራኤል ልጆች ሆይ! ያችን በናንተ ላይ የለገስኳትን ጸጋዬንና እኔም በዓለማት ላይ ያበለጥኳችሁ መኾኔን አስታውሱ፡፡
(አማኝ) ነፍስም ከ(ከሓዲ) ነፍስ ምንንም የማትጠቅምበትን፣ ከርሷም ቤዛ የማይወሰድበትን፣ ምልጃም ለርሷ የማትጠቅምበትን፣ እነርሱም የማይረዱበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡
ኢብራሂምንም ጌታው በቃላት (በሕግጋት) በፈተነውና በፈጸማቸው ጊዜ (አስታውስ)፤ «እኔ ለሰዎች መሪ አድራጊህ ነኝ» አለው፡፡ «ከዘሮቼም (አድርግ)» አለ፡፡ ቃል ኪዳኔ በዳዮቹን አያገኝም አለው፡፡
ቤቱንም ለሰዎች መመለሻና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ከኢብራሂምም መቆሚያ መስገጃን አድርጉ፡፡ ወደ ኢብራሂምና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን ለዘዋሪዎቹና ለተቀማጮቹም ለአጎንባሾች ሰጋጆቹም አጥሩ ስንል ቃል ኪዳን ያዝን፡፡
ኢብራሂም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ጌታዬ ሆይ! ይህንን ጸጥተኛ አገር አድርግ፡፡ ቤተሰቦቹንም ከነሱ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነውን ሰው ከፍሬዎች ስጠው፡፡ (አላህም) የካደውንም ሰው፤ (እሰጠዋለሁ)፡፡ ጥቂትም እጠቅመዋለሁ፤ ከዚያም ወደ እሳት ቅጣት አስጠጋዋለሁ፤ ምን ትከፋም መመለሻ! (አለ)፡፡
ኢብራሂምና ኢስማኢልም «ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል፡፡ አንተ ሰሚውና ዐዋቂው አንተ ነህና» የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡
«ጌታችን ሆይ! ላነተ ታዛዦችም አድርገን፡፡ ከዘሮቻችንም ላንተ ታዛዦች ሕዝቦችን (አድርግ)፡፡ ሕግጋታችንንም አሳየን፤ (አሳውቀን)፡፡ በኛም ላይ ተመለስን፤ አንተ ጸጸትን ተቀባዩ ሩኅሩኅ አንተ ብቻ ነህና፡፡»
«ጌታችን ሆይ! በውስጣቸውም ከነሱው የኾነን መልክተኛ በነርሱ ላይ አንቀጾችህን የሚያነብላቸውን መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራቸውን (ከክህደት) የሚያጠራቸውንም ላክ፤ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና» (የሚሉም ሲኾኑ)፡፡
ከኢብራሂምም ሕግጋት ነፍሱን ያቄለ ሰው ካልኾነ በስተቀር የሚያፈገፍግ ማነው? (የለም)፤ በቅርቢቱም ዓለም በእርግጥ መረጥነው፡፡ በመጨረሻይቱም ዓለም እርሱ ከመልካሞቹ ነው፡፡
ጌታው ለርሱ ታዘዝ ባለው ጊዜ (መረጠው)፡፡ ለዓለማት ጌታ ታዘዝኩ አለ፡፡
በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡ ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)፡፡ «ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ» (አላቸው)፡፡
ያዕቁብን ሞት በመጣበት ጊዜ ለልጆቹ ከኔ በኋላ ማንን ትገዛላችሁ ባለ ጊዜ ቀራቢዎች ነበራችሁን? (እነርሱም) አምላክህንና የአባቶችህን የኢብራሂምን የኢስማዒልንና የኢስሐቅንም አምላክ አንድ የኾነውን አምላክ እኛ ለርሱ ፍፁም ታዛዦች ኾነን እናመልካለን አሉ፡፡
ይህች (የተወሳችው) በእርግጥ ያለፈች ሕዝብ ናት፡፡ ለርሷ የሠራችው (ምንዳ) አላት፡፡ ለናንተም የሠራችሁት (ምንዳ) አላችሁ፡፡ ይሠሩትም ከነበሩት አትጠየቁም፡፡
«አይሁድን ወይም ክርስቲያኖችን ኹኑ፤ (ቅኑን መንገድ) ትመራላችሁና» አሉም፡፡ «አይደለም የኢብራሂምን ሃይማኖት ቀጥተኛ ሲኾን እንከተላለን፤ ከአጋሪዎችም አልነበረም» በላቸው፡፡
«በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡
በርሱ ባመናችሁበት ብጤ ቢያምኑ በእርግጥ ተመሩ፡፡ ቢዞሩም እነርሱ በጭቅጭቅ ውስጥ ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱንም አላህ ይበቃሃል፤ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡
የአላህን (የተፈጥሮ) መንክር (እምነት) ያዙ፡፡ በመንከርም ከአላህ ይበልጥ ያማረ ማነው? (ማንም የለም) እኛም ለርሱ ብቻ ተገዢዎች ነን (በሉ)፡፡
እርሱ (አላህ) ጌታችንና ጌታችሁ ሲኾን ለኛም ሥራችን ያለን ስንኾን ለናንተም ሥራችሁ ያላችሁ ስትኾኑ እኛም ለርሱ ፍጹም ታዛዦች ስንኾን በአላህ (ሃይማኖት) ትከራከሩናላችሁን? በላቸው፡፡
ወይም ኢብራሂም ኢስማዒልም ኢስሐቅም ያዕቁብም ነገዶቹም አይሁዶች ወይም ክርስቲያኖች ነበሩ ትላላችሁን? «እናንተ ታውቃላችሁን? ወይንስ አላህ?» በላቸው፡፡ እርሱም ዘንድ ከአላህ የኾነችን ምስክርነት ከደበቀ ሰው ይበልጥ በዳይ ማነው? አላህም ከምትሠሩት ሁሉ ዘንጊ አይደለም፡፡
ይህቺ በእርግጥ ያለፈች ሕዝብ ናት፤ ለእርሷ የሠራችው አላት፤ ለናንተም የሠራችሁት አላችሁ፤ ይሠሩትም ከነበሩት አትጠየቁም፡፡
ከሰዎቹ ቂሎቹ «ከዚያች በርሷ ላይ ከነበሩባት ቂብላቸው ምን አዞራቸው?» ይላሉ፤ «ምሥራቁም ምዕራቡም የአላህ ነው፤ የሻውን ሰው ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል» በላቸው፡፡
እንደዚሁም (እንደመራናችሁ) በሰዎች ላይ መስካሪዎች ልትሆኑና መልክተኛውም በናንተ ላይ መስካሪ ይሆን ዘንድ ምርጥ ሕዝቦች አደረግናችሁ፡፡ ያችንም በርሷ ላይ የነበርክባትን አቅጣጫ መልክተኛውን የሚከተለውን ሰው ወደ ክህደት ከሚመለሰው ሰው ልናውቅ (ልንገልጽ) እንጅ ቂብላ አላደረግናትም፡፡ እርሷም በነዚያ አላህ በመራቸው ሰዎች ላይ በስተቀር በእርግጥ ከባድ ናት፡፡ አላህም እምነታችሁን (ስግደታችሁን) የሚያጠፋ አይደለም፤ አላህ ለሰዎች በጣም ርኅሩኅ አዛኝ ነውና፡፡
የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን፡፡ ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን፡፡ ስለዚህ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ካዕባ) አግጣጫ አዙር፡፡ የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አግጣጫ አዙሩ፡፡ እነዚያም መጽሐፉን የተሰጡት እርሱ ከጌታቸው ሲኾን እውነት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ አላህም ከምትሠሩት ሥራ ዘንጊ አይደለም፡፡
እነዚያንም መጽሐፍን የተሰጡትን በአስረጅ ሁሉ ብትመጣቸው ቂብላህን አይከተሉም፡፡ አንተም ቂብላቸውን ተከታይ አይደለህም፡፡ ከፊላቸውም የከፊሉን ቂብላ ተከታይ አይደሉም፡፡ ከዕውቀትም (ከራዕይ) ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌያቸውን ብትከተል አንተ ያን ጊዜ ከበዳዮች ነህ፡፡
እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፡፡
(ይህ) ከጌታህ የኾነ እውነት ነው፤ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡
ለሁሉም እርሱ (በስግደት ፊቱን) የሚያዞርባት አግጣጫ አለችው፡፡ ወደ መልካም ሥራዎችም ተሽቀዳደሙ፡፡ የትም ስፍራ ብትኾኑ አላህ እናንተን የተሰበሰባችሁ ኾናችሁ ያመጣችኋል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡
ከየትም (ለጉዞ) ከወጣህበት ስፍራ ፊትሀን ወደ ተከበረው መስጊድ አግጣጫ አዙር፡፡ እርሱም ከጌታህ የኾነ እርግጠኛ እውነት ነው፡፡ አላህም ከምትሠሩት ሥራ ዘንጊ አይደለም፡፡
ከየትም ከወጣህበት ስፍራ ፊትህን ወደ ተከለለው መስጊድ አግጣጫ አዙር፡፡ በየትም ስፍራ ብትኾኑ ለሰዎቹ እነዚያ ከነሱ የበደሉት ሲቀሩ (ሃይማኖታችንን ይክዳሉ ቂብላችንን ይከተላሉ በማለት) በናንተ ላይ መከራከሪያ እንዳይኖራቸው ፊቶቻችሁን ወደ አግጣጫው አዙሩ፡፡ አትፍሩዋቸውም፤ ፍሩኝም፤ (በዚህም ያዘዝኳችሁ መከራከሪያ እንዳይኖራቸው) በናንተም ላይ ጸጋየን እንድሞላላችሁና (ወደ እውነትም) እንድትመሩ ነው፡፡
በውስጣችሁ ከናንተው የኾነን በናንተ ላይ አንቀጾቻችንን የሚያነብላችሁና የሚያጠራችሁ፣ መጽሐፍንና ጥበብንም የሚያስተምራችሁ፣ ታውቁት ያልነበራችሁትንም ነገር የሚያሳውቃችሁ የኾነን መልክተኛ እንደላክን (ጸጋን ሞላንላችሁ)፡፡
አስታውሱኝም፤ አስታውሳችኋለሁና ለኔም አመስግኑ፤ አትካዱኝም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስና በሶላት ተረዱ፡፡ አላህ (በእርዳታው) ከታጋሾች ጋር ነውና፡፡
በአላህ መንገድ (ለሃይማኖቱ) የሚገደሉትን ሰዎችም «ሙታን ናቸው» አትበሉ፡፡ በእውነቱ ሕያዋን ናቸው፤ ግን አታውቁም፡፡
ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ታጋሾችንም (በገነት) አብስር፡፡
እነዚያን መከራ፤ በነካቻቸው ጊዜ «እኛ ለአላህ፤ ነን እኛም ወደርሱ ተመላሾች» ነን የሚሉትን (አብስር)፡፡
እነዚያ በእነርሱ ላይ ከጌታቸው የኾኑ ምሕረቶች ችሮታም አልሉ፡፡ እነርሱም (ወደ እውነት) ተመሪዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡
ሶፋና መርዋ ከአላህ (ትዕዛዝ መፈጸሚያ) ምልክቶች ናቸው፡፡ ቤቱን (ካዕባን) በሐጅ ወይም በዑምራህ ሥራ የጎበኘ ሰው በሁለቱ (መካከል) በመመላለሱ በርሱ ላይ ኃጢአት የለበትም፡፡ መልካምንም ሥራ በፈቃደኛነት የሠራ ሰው (አላህ ይመነዳዋል)፤ አላህ አመስጋኝ ዐዋቂ ነውና፡፡
እነዚያ ከአንቀጾችና ከቅን መምሪያ ያወረድነውን ለሰዎች በመጽሐፉ ከገለጽነው በኋላ የሚደብቁ፤ እነዚያ አላህ ይረግማቸዋል፤ ረጋሚዎችም ሁሉ ይረግሟቸዋል፡፡
እነዚያ (ከመደበቅ) የተጸጸቱና (ሥራቸውን) ያሳመሩም (የደበቁትን) የገለጹም ብቻ ሲቀሩ፡፡ እነዚህም በነሱ ላይ (ጸጸታቸውን) እቀበላለሁ፤ እኔም ጸጸትን በጣም ተቀባይ አዛኙ ነኝ፡፡
እነዚያ የካዱ እነርሱ ከሐዲዎች ኾነውም የሞቱ እነዚያ በነርሱ ላይ የአላህና የመላእክት የሰዎችም ሁሉ እርግማን አለባቸው፡፡
በውስጧ (በርግማንዋ ውስጥ) ሁልጊዜ ዘውታሪዎች ሲኾኑ ቅጣቱ ከነሱ አይቀለልም እነርሱም አይቅቆዩም (ጊዜ አይስሰጡም)፡፡
አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡
ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትንና ቀንንም በማተካካት፣ በዚያቸም ሰዎችን በሚጠቅም ነገር (ተጭና) በባህር ላይ በምትንሻለለው ታንኳ፣ አላህም ከሰማይ ባወረደው ውሃና በርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ሕያው በማድረጉ፣ በርሷም ውስጥ ከተንቀሳቃሽ ሁሉ በመበተኑ፣ ነፋሶችንም (በየአግጣጫው) በማገለባበጥ፣ በሰማይና በምድር መካከል በሚነዳውም ደመና ለሚያውቁ ሕዝቦች እርግጠኛ ምልክቶች አሉ፡፡
ከሰዎችም ከአላህ ሌላ ባለንጣዎችን (ጣዖታትን) አላህን እንደሚወዱ የሚወዷቸው ኾነው የሚይዙ አልሉ፡፡ እነዚያ ያመኑትም አላህን በመውደድ (ከነርሱ) ይበልጥ የበረቱ ናቸው፡፡ እነዚያም የበደሉት ሰዎች ቅጣትን (በትንሣኤ ቀን) ባዩ ጊዜ ኀይል ሁሉ ለአላህ ብቻ መኾኑንና አላህም ቅጣቱ ብርቱ መኾኑን (በአዱኛ ዓለም) ቢያውቁ ኖሮ (ባላንጣዎችን በመያዛቸው በተጸጸቱ ነበር)፡፡
እነዚያ አስከታዮቹ ቅጣትን ያዩ ሲኾኑ ከእነዚያ ከተከታዮች በተጥራሩና በእነርሱም (መካከል) ምክንያቶች በተቆረጡ ጊዜ (የሚኾኑትን ባወቁ ኖሮ በተጸጸቱ ነበር)፡፡
እነዚያም የተከተሉት «ለእኛ (ወደ ቅርቢቱ ዓለም) አንዲት ጊዜ መመለስ በኖረችንና ከእኛ እንደተጥራሩ ከእነርሱ በተጥራራን እንመኛለን» ይላሉ፡፡ እንደዚሁ አላህ ሥራዎቻቸውን በነርሱ ላይ ጸጸቶች አድርጎ ያሳያቸዋል፡፡ እነርሱም ከእሳት ወጪዎች አይደሉም፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! በምድር ካለው ነገር የተፈቀደ ጣፋጭ ሲኾን ብሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከታተሉ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡
(እርሱ) የሚያዛችሁ በኃጢኣትና በጸያፍ ነገር በአላህም ላይ የማታውቁትን እንድትናገሩ ብቻ ነው፡፡
ለእነርሱም «አላህ ያወረደውን ተከተሉ» በተባሉ ጊዜ «አይደለም አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበትን ነገር እንከተላለን» ይላሉ፡፡ አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና (ወደ እውነት) የማይመሩም ቢኾኑ (ይከተሉዋቸዋልን?)
የነዚያም የካዱት (እና ወደ ቅን መንገድ የሚጠራቸው ሰው) ምሳሌ እንደዚያ ድምጽንና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ (እንስሳ) ላይ እንደሚጮህ ብጤ ነው፡፡ (እነርሱ) ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከነዚያ ከሰጠናችሁ ጣፋጮች ብሉ፡፡ ለአላህም እርሱን ብቻ የምትገዙ እንደኾናችሁ አመስግኑ፡፡
በናንተ ላይ እርም ያደረገው በክትንና ደምን፣ የእሪያ ሥጋንም፣ በእርሱም (ማረድ) ከአላህ ስም ሌላ የተነሳበትን ነገር ብቻ ነው፡፡ ሽፍታና ወሰን አላፊ ሳይኾን (ለመብላት) የተገደደ ሰውም በርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
እነዚያ አላህ ከመጽሐፍ ያወረደውን የሚደብቁ በርሱም (በመደበቃቸው) ጥቂትን ዋጋ የሚገዙ እነዚያ በሆዶቻቸው ውስጥ እሳትን እንጂ አይበሉም፡፡ አላህም በትንሣኤ ቀን አያናግራቸውም፤ (ከኃጢኣት) አያጠራቸውምም፡፡ ለነርሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
እነዚያ ጥመትን በቅንነት ቅጣትንም በምሕረት የገዙ ናቸው፡፡ በእሳት ላይም ምን ታጋሽ አደረጋቸው!
ይህ (ቅጣት) አላህ መጽሐፍን በእውነት ያወረደ በመኾኑ ምክንያት (እና በርሱ በመካዳቸው) ነው፡፡ እነዚያም በመጽሐፉ የተለያዩት (ከእውነት) በራቀ ጭቅጭቅ ውስጥ ናቸው፡፡
መልካም ሥራ ፊቶቻችሁን ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም፡፡ ግን መልካም ሥራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነቢያትም፣ ያመነ ሰው ገንዘብንም ከመውደዱ ጋር ለዝምድና ባለቤቶችና ለየቲሞች ለምስኪኖችም፣ ለመንገደኞችም፣ ለለማኞችም፣ ለጫንቃዎችም (ማስለቀቅ) የሰጠ ሰውና ሶላትንም ደንቡን ጠብቆ የሰገደ፣ ዘካንም የሰጠ፣ ቃል ኪዳንም በገቡ ጊዜ በኪዳናቸው የሞሉ (ሰዎች ሥራ) ነው፡፡ በችግር በበሽታና በጦር ጊዜም ታጋሾችን (እናወድሳለን)፡፡ እነዚህ እነዚያ እውነትን የያዙ ናቸው፡፡ እነዚያም ተጠንቃቂዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በተገደሉ ሰዎች ማመሳሰል በናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ ነጻ በነጻ ባሪያም በባሪያ ሴትም በሴት (ይገደላሉ)፡፡ ለእርሱም (ለገዳዩ) ከወንድሙ (ደም) ትንሽ ነገር ምሕረት የተደረገለት ሰው (በመሓሪው ላይ ጉማውን) በመልካም መከታተል ወደርሱም (ወደ መሓሪው) ገዳዩ በመልካም አኳኋን መክፈል አለባቸው፡፡ ይህ ከጌታችሁ የኾነ ማቃለልና እዝነት ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕግን የተላለፈ ሰው ለርሱ አሳማሚ ቅጣት አለው፡፡
ለእናንተም ባለ አእምሮዎች ሆይ! በማመሳሰል (ሕግ) ውስጥ ሕይወት አላችሁ፡፡ ትጠነቀቁ ዘንድ (ገዳይን መግደል ተደነገገላችሁ)፡፡
አንዳችሁን ሞት በመጣበት ጊዜ ሀብትን ቢተው ለወላጆችና ለቅርብ ዘመዶች በበጎ መናዘዝ በናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ (ይህ) በጥንቁቆቹ ላይ እርግጠኛ ድንጋጌ ተደነገገ፡፡
(ኑዛዜውን) ከሰማውም በኋላ የለወጠው ሰው ኃጢአቱ በነዚያ በሚለውጡት ላይ ብቻ ነው፡፡ አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነውና፡፡
ከተናዛዢም በኩል (ከውነት) መዘንበልን ወይም (ከሢሶ በመጨመር) ኃጢኣትን ያወቀና በመካከላቸው ያስታረቀ ሰው በእርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም፡፡ አላህ በጣም መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡
የተቆጠሩን ቀኖች (ጹሙ)፡፡ ከእናንተም ውሰጥ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነ ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መጾም አለበት፡፡ በእነዚያም ጾምን በማይችሉት ላይ ቤዛ ድኻን ማብላት አለባቸው፡፡ (ቤዛን በመጨመር) መልካምንም ሥራ የፈቀደ ሰው እርሱ (ፈቅዶ መጨመሩ) ለርሱ በላጭ ነው፡፡ መጾማችሁም ለናንተ የበለጠ ነው፤ የምታውቁ ብትኾኑ (ትመርጡታላችሁ)፡፡
(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፡፡ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፡፡ አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡ ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)፡፡
ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡ ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና፡፡
በጾም ሌሊት ወደ ሴቶቻችሁ መድረስ ለናንተ ተፈቀደላችሁ፡፡ እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡ አላህ እናንተ ነፍሶቻችሁን የምትበድሉ መኾናችሁን ዐወቀ፡፡ በእናንተም ላይ ተመለሰላችሁ፡፡ ከእናንተም ይቅርታ አደረገ፡፡ አሁን ተገናኙዋቸው፡፡ አላህም ለናንተ የጻፈላችሁን ነገር (ልጅን) ፈልጉ፡፡ ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም፡፡ ከዚያም ጾምን እስከ ሌሊቱ ድረስ ሙሉ፡፡ እናንተም በመስጊዶች ተቀማጮች ስትኾኑ አትገናኙዋቸው፡፡ ይህች የአላህ ሕግጋት ናትና (ለመተላለፍ) አትቅረቧት፡፡ እንደዚሁ አላህ አንቀጾቹን ለሰዎች ያብራራል፡፡ እነርሱ (የተከለከሉትን) ሊጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡
ገንዘቦቻችሁንም በመካከላችሁ በከንቱ (ያለ አግባብ) አትብሉ፡፡ እናንተም የምታውቁ ስትኾኑ ከሰዎች ገንዘቦች ከፊልን በኃጢኣት ትበሉ ዘንድ ወደ ዳኞች አትጣሏት፡፡
(ሙሐመድ ሆይ!) ከለጋ ጨረቃዎች (መለዋወጥ) ይጠየቁሃል፡፡ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም ለሐጅም (ማወቂያ) ጊዜያቶች (ምልክቶች) ናቸው በላቸው፡፡ መልካም ሥራም ቤቶችን ከጀርባዎቻቸው በመምጣታችሁ አይደለም፡፡ ግን የመልካም ሥራ ባለቤት የተጠነቀቀ ሰው ነው፡፡ ቤቶችንም ከደጃፎቻቸው በኩል ግቡ፤ አላህንም ፍሩ ልትድኑ ይከጀላልና (በላቸው)፡፡
እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሓዲዎች) በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና፡፡
ባገኛችኋቸውም ስፍራ ሁሉ ግደሉዋቸው፡፡ ከአወጧችሁም ስፍራ አውጧቸው፡፡ መከራም ከመግደል ይበልጥ የበረታች ናት፡፡ በተከበረው መስጊድም ዘንድ በርሱ ውስጥ እስከሚጋደሉዋችሁ ድረስ አትጋደሉዋቸው፡፡ ቢጋደሉዋችሁም ግደሉዋቸው፤ የከሓዲዎች ቅጣት እንደዚህ ነው፡፡
ቢከለከሉም አላህ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
ሁከት እስከማይገኝና ሃይማኖት ለአላህ ብቻ እስከሚኾን ድረስ ተጋደሉዋቸው፡፡ ቢከለክሉም ወሰንን ማለፍ፤ በበዳዮች ላይ እንጂ የለም (ወሰን አትለፉባቸው)፡፡
የተከበረው ወር በተከበረው ወር አንጻር ነው፡፡ ክብሮችም ሁሉ ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ በእናንተም ላይ (በተከበረው ወር) ወሰን ያለፈባችሁን ሰው በናንተ ላይ ወሰን ባለፈው ብጤ በርሱ ላይ ወሰን እለፉበት፡፡ አላህንም ፍሩ አላህ ከሚፈሩት ጋር መኾኑንም ዕወቁ፡፡
በአላህም መንገድ ለግሱ፡፡ በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ፡፡ በጎ ሥራንም ሥሩ፤ አላህ በጎ ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡
ሐጅንና ዑምራንም ለአላህ ሙሉ፡፡ ብትታገዱም ከሀድይ (ከመሥዋእት) የተገራውን (መሰዋት) አለባችሁ፡፡ ሀድዩም እስፍራው እስከሚደርስ ድረስ ራሶቻችሁን አትላጩ፡፡ ከናንተም ውስጥ በሽተኛ ወይም በራሱ ሁከት ያለበት የኾነ ሰው (ቢላጭ) ከጾም ወይም ከምጽዋት ወይም ከመሥዋዕት ቤዛ አለበት፡፡ ጸጥታም ባገኛችሁ ጊዜ እስከ ሐጅ በዑምራ የተጣቀመ ሰው ከሀድይ የተገራውን (መሠዋት) አለበት፡፡ ያላገኘም ሰው ሶስትን ቀኖች በሐጅ ወራት፤ ሰባትም በተመለሳችሁ ጊዜ መጾም አለበት፡፡ ይህች ሙሉ ዐሥር (ቀናት) ናት፡፡ ይህም (ሕግ) ቤተሰቦቹ ከቅዱሱ መስጊድ አቅራቢያ ላልኾኑ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፤ አላህም ቅጣተ ብርቱ መኾኑን እወቁ፡፡
ሐጅ (ጊዜያቱ) የታወቁ ወሮች ናቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሠራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው በሐጅ ውስጥ ሴትን መገናኘት ማመጽም ክርክርም የለም፡፡ ከበጎም ሥራ የምትሠሩትን ሁሉ አላህ ያውቀዋል፡፡ ተሰነቁም፤ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህን መፍራት) ነው፡፡ የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ፡፡
(በሐጅ ጊዜ በንግድ ሥራ) ከጌታችሁ ትርፍን በመፈለጋችሁ በናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ ከዐረፋትም በጎረፋችሁ ጊዜ መሸዐረልሐራም ዘንድ አላህን አውሱ፡፡ (ለሐጅ) ስለመራችሁም አውሱት፡፡ ከመምራቱ በፊትም በእርግጥ ከተሳሳቾች ነበራችሁ፡፡
ከዚያም (ቁረይሾች ሆይ!) ሰዎቹ ከጎረፉበት ስፍራ ጉረፉ፤ (ተመለሱ)፡፡ አላህንም ምሕረትን ለምኑ፤ አላህ እጅግ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
የሐጅ ሥራዎቻችሁንም በፈጸማችሁ ጊዜ አባቶቻችሁን እንደምታወሱ ወይም ይበልጥ የበረታን ማውሳት አላህን አውሱ፡፡ ከሰዎችም ውስጥ፡- «ጌታችን ሆይ! በምድረዓለም መልካም ዕድልን ስጠን» የሚል ሰው አለ፡፡ ለርሱም በመጨረሻይቱ አገር ከዕድል ምንም የለውም፡፡
ከእነርሱም ውስጥ፡- «ጌታችን ሆይ! በምድረ ዓለም ደግን ነገር (ጸጋን) በመጨረሻይቱም አገር ደግን ነገር (ገነትን) ስጠን፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቀን» የሚሉ ሰዎች አልሉ፡፡
እነዚያከሠሩት በጎ ሥራ ለነርሱ እድል አላቸው፡፡ አላህም ምርመራው ፈጣን ነው፡፡
በተቆጠሩ ቀኖችም ውስጥ (በሚና ጠጠሮችን ስትወረውሩ) አላህን አውሱ፡፡ በሁለት ቀኖችም ውስጥ (በመኼድ) የተቻኮለ ሰው በርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም፡፡ የቆየም ሰው በርሱ ላይ ኃጢኣት የለበትም፡፡ (ይህም) አላህን ለፈራ ሰው ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ እናንተ ወደርሱ የምትሰበሰቡ መኾናችሁንም ዕወቁ፡፡
ከሰዎችም ውስጥ እርሱ ክርክረ ብርቱ ሲኾን በቅርቢቱ ሕይወት ንግግሩ የሚደንቅህና በልቡ ውስጥ ባለው ነገር ላይ አላህን የሚያስመሰክር ሰው አልለ፡፡
(ካንተ) በዞረም ጊዜ በምድር ላይ በውስጧ ሊያበላሽና አዝመራንና እንስሳዎችን ሊያጠፋ ይሮጣል፡፡ አላህም ማበላሸትን አይወድም፡፡
ለእርሱ «አላህን ፍራ» በተባለም ጊዜ፤ ትዕቢቱ በኃጢኣት (ሥራ) ላይ ትገፈፋዋለች፡፡ ገሀነምም በቂው ናት፤ (እርሷም) በእርግጥ የከፋች ምንጣፍ ናት፡፡
ከሰዎችም ውስጥ የአላህን ውዴታ ለመፈለግ ነፍሱን የሚሸጥ ሰው አልለ፡፡ አላህም ለባሮቹ በጣም ርኅሩህ ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሁላችሁም በመታዘዝ ውስጥ ግቡ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡
ግልጽ ማስረጃዎችም ከመጡላችሁ በኋላ ብትዘነበሉ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ መኾኑን እወቁ፡፡
አላህ (ቅጣቱ)ና መላእክቱ ከደመና በኾኑ ጥላዎች ውስጥ ሊመጡዋቸው እንጂ አይጠባበቁም፡፡ ነገሩም ተፈጸመ፤ ነገሮችም ሁሉ ወደ አላህ ይመለሳሉ፡፡
የእስራኤልን ልጆች ከግልጽ ተዓምር ስንትን እደሰጠናቸው ጠይቃቸው፡፡ የአላህንም ጸጋ ከመጣችለት በኋላ የሚለውጥ ሰው አላህ ቅጣተ ብርቱ ነው፡፡
ለእነዚያ ለካዱት ከእነዚያ ካመኑት የሚሳለቁ ሲኾኑ ቅርቢቱ ሕይወት ተሸለመችላችው፡፡ እነዚያም የተጠነቀቁት በትንሣኤ ቀን ከበላያቸው ናቸው፡፡ አላህም ለሚሻው ሰው ያለ ግምት ይሰጣል፡፡
ሰዎቹ ሁሉ አንድ ሕዝብ ነበሩ፤ (ተለያዩ)፡፡ አላህም ነቢያትን አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርጎ ላከ፡፡ ከእነርሱም ጋር መጻሕፍትን በሰዎቹ መካከል በዚያ በርሱ በተለያዩበት ነገር ይፈርድ ዘንድ በእውነት አወረደ፡፡ በእርሱም (በሃይማኖት) ግልጽ አስረጂዎች ከመጡላቸው በኋላ በመካከላቸው ለኾነው ምቀኝነት እነዚያው የተሰጡት እንጂ አልተለያዩበትም፡፡ አላህም እነዚያን ያመኑትን ሰዎች ለእዚያ ከእውነት በርሱ ለተለያዩበት በፍቃዱ መራቸው፡፡ አላህም የሚሻውን ሰው ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል፡፡
በእውነቱ የእነዚያ ከበፊታችሁ ያለፉት (ምእምናን መከራ) ብጤ ሳይመጣችሁ ገነትን ልትገቡ ታስባላችሁን? መልክተኛውና እነዚያ ከርሱ ጋር ያመኑት «የአላህ እርዳታ መቼ ነው?» እስከሚሉ ድረስ መከራና ጉዳት ነካቻቸው፤ ተርበደበዱም፡፡ ንቁ! የአላህ እርዳታ በእርግጥ ቅርብ ነው (ተባሉም)፡፡
ምንን (ለማንም) እንደሚለግሱ ይጠይቁሃል፡፡ ከመልካም ነገር የምትለግሱት፤ ለወላጆችና ለቅርብ ዘመዶች፣ ለየቲሞችም፣ ለድሆችም፣ ለመንገደኞችም ነው፡፡ ከበጎ ነገርም ማንኛውንም ብትሠሩ አላህ እርሱን ዐዋቂ ነው በላቸው፡፡
መጋደል እርሱ ለእናንተ የተጠላ ሲሆን በእናንተ ላይ ተጻፈ፡፡ አንዳች ነገርን እርሱ ለናንተ የበለጠ ሲሆን የምትጠሉት መኾናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አንዳችንም ነገር እርሱ ለናንተ መጥፎ ሲሆን የምትወዱት መሆናችሁ ተረጋገጠ፡፡ አላህም (የሚሻላችሁን) ያውቃል ግን እናንተ አታውቁም፡፡
ከተከበረው ወር (ከረጀብ) በርሱ ውስጥ ከመጋደል ይጠይቁሃል፡፡ በላቸው «በርሱ ውስጥ መጋደል ታላቅ (ኀጢአት) ነው፡፡ ግን ከአላህ መንገድ (ሰዎችን) መከላከል፣ በርሱም መካድ፣ ከተከበረውም መስጊድ (ማገድ) ባለቤቶቹንም ከርሱ ማውጣት አላህ ዘንድ ይበልጥ ታላቅ (ወንጀል) ነው፡፡ ፈተናም (ማጋራት) ከመግደል ይበልጥ ከባድ ነው፡፡ (ከሐዲዎች) ቢችሉ ከሃይማኖታችሁ እስከሚመልሳችሁ ድረስ የሚዋጉዋችሁ ከመሆን አይቦዝኑም፡፡ ከእናንተ ውስጥም ከሃይማኖቱ የሚመለስና እርሱም ከሐዲ ሆኖ የሚሞት ሰው እነዚያ (በጎ) ሥራቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም አገር ተበላሸች፡፡ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡»
እነዚያ ያመኑትና እነዚያም (ከአገራቸው) የተሰደዱት በአላህም መንገድ ላይ የተጋደሉት እነዚያ የአላህን እዝነት ይከጅላሉ፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
አእምሮን ከሚቃወም መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል፡፡ «በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢኣትና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው፡፡ ግን ኃጢኣታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው» በላቸው፡፡ ምንን እንደሚመጸውቱም (መጠኑን) ይጠይቁሃል፡፡ «ትርፍን (መጽውቱ)» በላቸው፡፡ እንደዚሁ ታስተነትኑ ዘንድ አላህ ለናንተ አንቀጾችን ይገልጽላችኋል፡፡
በቅርቢቱ ዓለምና በመጨረሻይቱ ታስተነትኑ ዘንድ (ይገለጽላችኋል)፡፡ ከየቲሞችም ይጠይቁሃል፡፡ «ለእነርሱ (ገንዘባቸውን በማራባት) ማሳመር በላጭ ነው፡፡ ብትቀላቀሏቸውም ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡ አላህም የሚያጠፋውን ከሚያበጀው (ለይቶ) ያውቃል፡፡ አላህም በሻ ኖሮ ባስቸገራችሁ ነበር፤ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና» በላቸው፡፡
(በአላህ) አጋሪ የሆኑ ሴቶች እስከሚያምኑ ድረስ አታግቡዋቸው፡፡ ከአጋሪይቱ ምንም ብትደንቃችሁም እንኳ ያመነችው ባሪያ በእርግጥ በላጭ ናት፡፡ ለአጋሪዎቹም እስከሚያምኑ ድረስ አትዳሩላቸው፡፡ ከአጋሪው (ጌታ) ምንም ቢደንቃችሁ ምእምኑ ባሪያ በላጭ ነው፡፡ እነዚያ (አጋሪዎች) ወደ እሳት ይጣራሉ፡፡ አላህም በፈቃዱ ወደ ገነትና ወደ ምሕረት ይጠራል፡፡ ሕግጋቱንም ለሰዎች ይገልጻል እነርሱ ሊገሰጹ ይከጀላልና፡፡
ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡
ሴቶቻችሁ ለናንተ እርሻ ናቸው፡፡ እርሻችሁንም በፈለጋችሁት ኹነታ ድረሱ፡፡ ለነፍሶቻችሁም (መልካም ሥራን) አስቀድሙ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ እናንተም ተገናኝዎቹ መኾናችሁን ዕወቁ፡፡ ምእመናንንም (በገነት) አብስር፡፡
መልካም እንዳትሠሩ፣ አላህንም እንዳትፈሩ፣ በሰዎችም መካከል እንዳታስታርቁ አላህን ለመሐላዎቻችሁ ግርዶ አታድርጉ፡፡ አላህም ሰሚ አዋቂ ነው፡፡
በመሐላዎቻችሁ በውድቁ (ሳታስቡ በምትምሉት) አላህ አይዛችሁም፡፡ ግን ልቦቻችሁ ባሰቡት ይይዛችኋል፡፡ አላህም በጣም መሐሪ ታጋሽ ነው፡፡
ለእነዚያ ከሴቶቻቸው (ላይቀርቡ) ለሚምሉት አራትን ወሮች መጠበቅ አለባቸው፡፡ (ከመሐላቸው) ቢመለሱም አላህ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
መፍታትንም ቁርጥ አሳብ ቢያደርጉ (ይፍቱ)፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
የተፈቱ ሴቶችም ነፍሶቻቸውን (ከማግባት) ሦስትን ቁርእ ይጠብቁ፡፡ በአላህና በመጨረሻውም ቀን የሚያምኑ ቢኾኑ አላህ በማሕፀኖቻቸው ውስጥ የፈጠረውን ሊደብቁ ለነርሱ አይፈቀድላቸውም፡፡ ባሎቻቸውም በዚህ ውስጥ እርቅን ቢፈልጉ በመማለሳቸው ተገቢዎች ናቸው፡፡ ለእነርሱም (ለሴቶች) የዚያ በእነርሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኑዋኑዋር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፡፡ ለወንዶችም (ጣጣቸውን ስለሚሸከሙ) በእነሱ ላይ ብልጫ አላቸው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ፍች ሁለት ጊዜ ነው፤ (ከዚህ በኋላ) በመልካም መያዝ ወይም በበጎ አኳኋን ማሰናበት ነው፡፡ የአላህንም ሕግጋት አለመጠበቃቸውን ካላወቁ በስተቀር ከሰጣችኃቸው ነገር ምንንም ልትወስዱ ለእናንተ (ለባሎች) አይፈቀድላችሁም፡፡ የአላህንም ሕግጋት አለመጠበቃቸውን ብታውቁ በእርሱ (ነፍሷን) በተበዠችበት ነገር በሁለቱም ላይ ኃጢኣት የለም፡፡ ይህች የአላህ ሕግጋት ናት፤ አትተላለፏትም፡፡ የአላህንም ሕግጋት የሚተላለፉ እነዚያ እነርሱ በዳዮች ናቸው፡፡
(ሦስተኛ) ቢፈታትም ከዚህ በኋላ ሌላን ባል እስከምታገባ ድረስ ለርሱ አትፈቀድለትም፡፡ (ሁለተኛው ባል) ቢፈታትም የአላህን ሕግጋት መጠበቃቸውን ቢያውቁ በመማለሳቸው በሁለቱም ላይ ኃጢኣት የለባቸውም፡፡ ይህችም የአላህ ሕግጋት ናት ለሚያውቁ ሕዝቦች ያብራራታል፡፡
ሴቶችን በፈታችሁና (የዒዳ) ጊዜያቸውን በደረሱ ጊዜ በመልካም ያዙዋቸው፤ (ተማለሷቸው) ወይም በመልካም ኹኔታ አሰናብቱዋቸው፡፡ ለመጉዳትም ወሰን ታልፋባቸው ዘንድ አትያዙዋቸው፤ ይህንንም የሚሠራ ሰው ነፍሱን በእርግጥ በደለ፡፡ የአላህንም አንቀጾች ማላገጫ አድርጋችሁ አትያዙ፡፡ የአላህንም ጸጋ በናንተ ላይ ያደረገውን ከመጽሐፍና ከጥበብም በርሱ የሚገስጻችሁ ሲኾን በናንተ ላይ ያወረደውን አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፤ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ መኾኑን ዕወቁ፡፡
ሴቶችንም በፈታችሁና ጊዜያቸውን በደረሱ ጊዜ በመካከላቸው በሕግ በተዋደዱ ጊዜ ባሎቻቸውን ከማግባት አታስተጓጉሏቸው፡፡ ይህ (መከልከል) ከእናንተ በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው በርሱ ይገሰጽበታል፡፡ ይህ ሁኔታችሁ ለእናንተ በላጭ ነው፤ (ከመጠርጠር) አጥሪም ነው፡፡ አላህም ያውቃል፤ እናንተ ግን አታውቁም፡፡
እናቶችም ልጆቻቸውን ሙሉ የኾኑን ሁለት ዓመታት ያጥቡ፡፡ (ይህም) ማጥባትን መሙላት ለሻ ሰው ነው፡፡ ለእርሱም በተወለደለት (አባት) ላይ ምግባቸውና ልብሳቸው በችሎታው ልክ አለበት፡፡ ነፍስ ችሎታዋን እንጂ አትገደድም፡፡ ወላጂት (እናት) በልጅዋ ምክንያት ለርሱ የተወለደለትም (አባት) በልጁ ምክንያት አይጎዳዱ፡፡ በወራሽም ላይ እንደዚሁ ብጤ አለበት፡፡ (ወላጆቹ) ከሁለቱም በኾነ መዋደድና መመካከር (ልጁን ከጡት) መነጠልን ቢፈልጉ በሁለቱም ላይ ኃጢኣት የለባቸውም፡፡ ልጆቻችሁንም ለሌሎች አጥቢዎች ማስጠባትን ብትፈልጉ ልትሰጡ የሻችሁትን በመልካም ኹኔታ በሰጣችሁ ጊዜ (በማስጠባታችሁ) በእናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ አላህንም ፍሩ፤ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች መኾኑን ዕወቁ፡፡
እነዚያም ከናንተ ውስጥ የሚሞቱና ሚስቶችን የሚተዉ (ሚስቶቻቸው) በነፍሶቻቸው አራት ወሮች ከዐስር (ቀናት ከጋብቻ) ይታገሱ፡፡ ጊዜያቸውንም በጨረሱ ጊዜ በነፍሶቻቸው በታወቀ ሕግ በሠሩት ነገር በእናንተ ላይ ኃጢአት የለባችሁም፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው፡፡
ሴቶችንም ከማጨት በርሱ ባሸሞራችሁበት ወይም በነፍሶቻችሁ ውስጥ (ለማግባት) በደበቃችሁት በናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ አላህ እናንተ በእርግጥ የምታስታውሷቸው መኾናችሁን ዐወቀ፡፡ (ስለዚህ ማሸሞርንና ማሰብን ፈቀደላችሁ፡፡) ግን በሕግ የታወቀን ንግግር የምትነጋገሩ ካልኾናችሁ በስተቀር፤ ምስጢርን (ጋብቻን) አትቃጠሩዋቸው፡፡ የተጻፈውም (ዒዳህ) ጊዜውን እስከሚደርስ ድረስ ጋብቻን ለመዋዋል ቁርጥ ሐሳብ አታድርጉ፡፡ አላህም በነፍሶቻችሁ ያለውን ነገር የሚያውቅ መኾኑን ዕወቁ፤ ተጠንቀቁትም፡፡ አላህም መሓሪ ታጋሽ መኾኑን ዕወቁ፡፡
ሴቶችን ሳትነኳቸው (ሳትገናኙ)፤ ወይም ለነሱ መህርን ሳትወስኑላቸው ብትፈቷቸው በናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ (ዳረጎት በመስጠት መፍታት ትችላላችሁ፡፡) ጥቀሟቸውም፡፡ በሀብታም ላይ ችሎታው በድኀም ላይ ችሎታው (አቅሙ የሚፈቅደውን መስጠት) አለበት፡፡ መልካም የኾነን መጥቀም በበጎ ሠሪዎች ላይ የተረጋገጠን፤ (ጥቀሟቸው)፡፡
ለእነርሱም መወሰንን በእርግጥ የወሰናችሁላቸው ስትኾኑ ሳትነኳቸው በፊት ብተፈቷቸው ካልማሩዋችሁ ወይም ያ የጋብቻው ውል በእጁ የኾነው (ባልየው) ካልማረ በስተቀር የወሰናችሁት ግማሹ አላቸው፡፡ ምሕረትም ማድረጋችሁ ወደ አላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ በመካከላችሁም ችሮታን አትርሱ፤ አላህ የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነውና፡፡
በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡
ብትፈሩም እግረኞች ወይም ጋላቢዎች ኾናችሁ (ስገዱ)፡፡ ጸጥተኞችም በኾናችሁ ጊዜ ታውቁት ያልነበራችሁትን እንደ አሳወቃችሁ አላህን አውሱ (ስገዱ)፡፡
እነዚያ ከናንተ ውስጥ የሚሞቱ ሚስቶችንም የሚተዉ፤ ለሚስቶቻቸው (ከቤታቸው) የማይወጡ ሲኾኑ ዓመት ድረስ መጠቀምን ኑዛዜን (ይናዘዙ)፡፡ በፈቃዳቸው ቢወጡም በሕግ ከታወቀው ነገር በነፍሶቻቸው በሠሩት በእናንተ (በሟቹ ዘመዶች) ላይ ኃጢኣት የለባችሁም አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ለተፈቱ ሴቶችም በችሎታ መጠን ዳረጎት አላቸው፡፡ አላህን በሚፈሩ ላይ ተደንግጓል፡፡
እንደዚሁ አላህ አንቀጾቹን ታውቁ ዘንድ ለናንተ ያብራራላችኋል፡፡
ወደ እነዚያ እነርሱ ብዙ ሺሕ ኾነው ሞትን ለመፍራት ከሀገሮቻቸው ወደ ወጡት ሰዎች ዕውቀትህ አልደረሰምን? አላህም ለነርሱ «ሙቱ» አላቸው፤ (ሞቱም)፡፡ ከዚያም ሕያው አደረጋቸው፡፡ አላህም በሰዎች ላይ ባለችሮታ ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያመሰግኑም፡፡
በአላህም መንገድ (ሃይማኖት) ተጋደሉ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ መኾኑን ዕወቁ፡፡
ያ ለአላህ መልካም ብድርን የሚያበድርና ለእርሱ (አላህ) ብዙ እጥፎች አድርጎ የሚያነባብርለት ማነው? አላህም ይጨብጣል፤ ይዘረጋልም፤ ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ፡፡
ከእስራኤል ልጆች ከሙሳ በኋላ ወደ ነበሩት ጭፍሮች ለነቢያቸው (ለሳሙኤል)፡- «ለእኛ ንጉሥን አስነሳልን በአላህ መንገድ እንዋጋለን፤» ባሉ ጊዜ አላየህምን? (አላወቅህምን?)፡-«መዋጋት ቢጻፍባችሁ አትዋጉም ይኾናል» አላቸው፡፡ «ከሀገሮቻችንና ከልጆቻችን የተባረርን ስንኾን በአላህ መንገድ የማንዋጋ ለእኛ ምን አለን?» አሉ፡፡ በእነርሱ ላይ መዋጋት በተጻፈባቸውም ጊዜ ከእነርሱ ጥቂቶች ሲቀሩ አፈገፈጉ፡፡ አላህም በዳዮቹን ዐዋቂ ነው፡፡
ነቢያቸውም ለእነርሱ፡- «አላህ ጧሉትን (ሳኦልን) ንጉሥ አድርጎ በእርግጥ ላከላችሁ» አላቸው፡፡ (እነርሱም)፡- «እኛ ከእርሱ ይልቅ በንግሥና ተገቢዎች ስንኾን ከሀብትም ስፋትን ያልተሰጠ ሲኾን ለእርሱ በኛ ላይ እንዴት ንግሥና ይኖረዋል?» አሉ፡፡ (ነቢያቸውም)፡-«አላህ በእናንተ ላይ መረጠው፡፡ በዕውቀትና በአካልም ስፋትን ጨመረለት፡፡ አላህም ንግሥናውን ለሚሻው ሰው ይሰጣል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው» አላቸው፡፡
ነቢያቸውም ለእነርሱ፡- «የንግሥናው ምልክት ከጌታችሁ የኾነ እርጋታ የሙሳ ቤተሰብና የሃሩን ቤተሰብ ከተውትም ቅርስ በውስጡ ያለበት መላእክት የሚሸከሙት ኾኖ ሳጥኑ ሊመጣላችሁ ነው፡፡ አማኞች ብትኾኑ በዚህ ለእናንተ እርግጠኛ ምልክት አልለ» አላቸው፡፡
ጧሉትም በሠራዊቱ (ታጅቦ) በወጣ ጊዜ፡- «አላህ በወንዝ (ውሃ) ፈታኛችሁ ነው ከርሱም የጠጣ ሰው ከእኔ አይደለም፡፡ ያልቀመሰውም ሰው በእጁ መዝገንን የዘገነ ሰው ብቻ ሲቀር እርሱ ከኔ ነው» አለ፡፡ ከእነርሱም ጥቂቶች ሲቀሩ ከርሱ ጠጡ፡፡ እርሱና እነዚያም ከእርሱ ጋር ያመኑት (ወንዙን) ባለፉት ጊዜ፡- «ጃሎትንና ሠራዊቱን በመዋጋት ለኛ ዛሬ ችሎታ የለንም» አሉት፡፡ እነዚያ እነርሱ አላህን ተገናኝዎች መኾናቸው የሚያረጋግጡት፡- «ከጥቂት ጭፍራ በአላህ ፈቃድ ብዙን ጭፍራ ያሸነፈች ብዙ ናት፤ አላህም ከታጋሾች ጋር ነው» አሉ፡፡
ለጃሎትና ለሠራዊቱ በተሰለፉም ጊዜ፡- «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ ትዕግስትን አንቧቧ፤ ጫማዎቻችንንም አደላድል፤ በከሓዲያን ሕዝቦችም ላይ እርዳን» አሉ፡፡
በአላህም ፈቃድ ድል መቷቸው፡፡ ዳውድም ጃሉትን (ዳዊት ጎልያድን) ገደለ፡፡ ንግሥናንና ጥበብንም (ነቢይነትን) አላህ ሰጠው፡፡ ከሚሻውም ነገር ሁሉ አሳወቀው፡፡ አላህም ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መመለሱ ባልነበረ ኖሮ ምድር በተበላሸች ነበር፤ ግን አላህ በዓለማት ላይ የችሮታ ባለቤት ነው፡፡
እነዚህ (አንቀጾች) በውነት በአንተ ላይ የምናነባቸው ሲኾኑ የአላህ አንቀጾች ናቸው፤ አንተም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነህ፡፡
እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ፡፡ ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ፡፡ የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው፡፡ አላህም በሻ ኖሮ እነዚያ ከእነርሱ (ከመልክተኞቹ) በኋላ የነበሩት ግልጽ ታምራቶች ከመጡላቸው በኋላ ባልተጋደሉ ነበር፡፡ ግን ተለያዩ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ያመነ ሰው አልለ፡፡ ከነርሱም ውስጥ የካደ ሰው አልለ፡፡ አላህም በሻ ኖሮ ባልተዋጉ (ባልተለያዩ) ነበር፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ይሠራል፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በርሱ ውስጥ ሽያጭ (መበዠት)፣ ወዳጅነትም፣ ምልጃም የሌለበት ቀን ከመምጣቱ በፊት ከሰጠናችሁ ነገር ለግሱ፡፡ ከሓዲዎችም በዳዮቹ እነርሱ ናቸው፡፡
አላህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፡፡ ማንገላጀትም እንቅልፍም አትይዘውም፡፡ በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፡፡ ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ ማነው? (ከፍጡሮች) በፊታቸው ያለውንና ከኋላቸው ያለውን ሁሉ ያውቃል፡፡ በሻውም ነገር እንጂ ከዕውቀቱ በምንም ነገር አያካብቡም (አያውቁም)፡፡ መንበሩ ሰማያትንና ምድርን ሰፋ፡፡ ጥበቃቸውም አያቅተውም፡፡ እርሱም የሁሉ በላይ ታላቅ ነው፡፡
በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
አላህ የእነዚያ ያመኑት ሰዎች ረዳት ነው፡፡ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል፡፡ እነዚያም የካዱት ረዳቶቻቸው ጣዖታት ናቸው፡፡ ከብርሃን ወደ ጨለማዎች ያወጧቸዋል፡፡ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፤ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
ወደዚያ አላህ ንግሥናን ስለሰጠው ኢብራሂምን በጌታው ነገር ወደ ተከራከረው ሰው አላየህምን ኢብራሂም «ጌታዬ ያ ሕያው የሚያደርግና የሚገድል ነው» ባለ ጊዜ «እኔ ሕያው አደርጋለሁ እገድላለሁም» አለ፡፡ ኢብራሂም፡- «አላህ ፀሐይን ከምሥራቅ በኩል ያመጣል (አንተ) ከምዕራብ በኩል አምጣት» አለው፡፡ ያም የካደው ሰው ዋለለ፤ (መልስ አጣ) አላህም በዳዮች ሕዝቦችን አይመራም፡፡
ወይም ያንን በከተማ ላይ እርሷ በጣራዎችዋ ላይ የወደቀች ስትኾን ያለፈውን ሰው ብጤ (አላየህምን)፡- «ይህችን (ከተማ) ከሞተች በኋላ አላህ እንዴት ሕያው ያደርጋታል» አለ፡፡ አላህም ገደለው መቶ ዓመትን (አቆየውም)፡፡ ከዚያም አስነሳው፡- «ምን ያህል ቆየህ» አለው፡፡ «አንድ ቀን ወይም የቀንን ከፊል ቆየሁ» አለ፡፡ «አይደለም መቶን ዓመት ቆየህ፡፡ ወደ ምግብህና ወደ መጠጥህም ያልተለወጠ ሲኾን ተመልከት፡፡ ወደ አህያህም ተመልከት፡፡ ለሰዎችም አስረጅ እናደርግህ ዘንድ (ይህንን ሠሰራን)፡፡ ወደ ዐፅሞቹም እንዴት እንደምናስነሳት ከዚያም ሥጋን እንደምናለብሳት ተመልከት» አለው፡፡ ለርሱም (በማየት) በተገለጸለት ጊዜ፡- «አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን ዐውቃለሁ» አለ፡፡
ኢብራሂምም «ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ፡፡) አላህ ፡- «አላመንክምን» አለው፡፡ «አይደለም (አምኛለሁ)፤ ግን ልቤ እንዲረጋ» ነው አለ፡፡ (አላህም)፡- «ከበራሪዎች (ከወፎች) አራትን ያዝ፡፡ ወደ አንተም ሰብስባቸው፡፡ (ቆራርጣቸውም)፤ ከዚያም በየኮረብታው ሁሉ ላይ ከነርሱ ቁራጭን አድርግ፡፡ ከዚያም ጥራቸው፤ ፈጥነው ይመጡሃልና፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ መኾኑን ዕወቅ» አለው፡፡
የእነዚያ ገንዘቦቻቸውን በአላህ መንገድ የሚለግሱ ሰዎች (ልግስና) ምሳሌ በየዘለላው ሁሉ መቶ ቅንጣት ያለባቸውን ሰባት ዘለላዎች እንደ አበቀለች አንዲት ቅንጣት ብጤ ነው፡፡ አላህም ለሚሻው ሰው (ከዚህ በላይ) ያነባብራል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡
እነዚያ ገንዘቦቻቸውን በአላህ መንገድ የሚለግሱ ከዚያም የሰጡትን ነገር መመጻደቅንና ማስከፋትን የማያስከትሉ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነርሱም አያዝኑም፡፡
መልካም ንግግርና ምሕረት ማድረግ ማስከፋት ከሚከተላት ምጽዋት በላጭ ነው፡፡ አላህም ተብቃቂ ታጋሽ ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እንደዚያ ገንዘቡን ለሰዎች ማሳየት ሲል እንደሚሰጠውና በአላህና በመጨረሻውም ቀን እንደማያምነው ሰው ምጽዋቶቻችሁን በመመጻደቅና በማስከፋት አታበላሹ፡፡ ምሳሌውም በላዩ ዐፈር እንዳለበት ለንጣ ድንጋይ ኃይለኛም ዝናብ እንዳገኘውና ምልጥ አድርጎ እንደተወው ብጤ ነው፡፡ ከሠሩት ነገር በምንም ላይ (ሊጠቀሙ) አይችሉም፡፡ አላህም ከሓዲያንን ሕዝቦች አይመራም፡፡
የእነዚያም የአላህን ውዴታ ለመፈለግና ለነፍሶቻቸው (እምነትን) ለማረጋገጥ ገንዘቦቻቸውን የሚለግሱ ሰዎች ምሳሌ በተስተካከለች ከፍተኛ ስፍራ ላይ እንዳለች አትክልት፣ ብዙ ዝናብ እንደነካት ፍሬዋንም እጥፍ ኾኖ እንደሰጠች፣ ዝናብም ባይነካት ካፊያ እንደሚበቃት ብጤ ነው፡፡ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡
(ከእናንተ) አንዳችሁ ለርሱ ከዘምባባና ከወይኖች በስርዋ ወንዞች የሚፈሱባት አትክልት ልትኖረው፣ በውስጧም ለርሱ ከየፍሬው ሁሉ ሊኖረው እርጅናም ሊነካውና ለርሱ ደካማዎች ዝርያዎች ያሉት ሲኾን በውስጡ እሳት ያለበት ውርጭ ሊያገኛትና ልትቃጠል ይወዳልን እንደዚሁ አላህ አንቀጾችን ለእናንተ ያብራራል፤ ልታስተነትኑ ይከጀላልና፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ካፈራችሁትና ከዚያም ለእናንተ ከምድር ካወጣንላችሁ ከመልካሙ ለግሱ፡፡ መጥፎውንም (ለመስጠት) አታስቡ፡፡ በእርሱ ዓይኖቻችሁን ጨፍናችሁ እንጂ የማትወስዱት ስትኾኑ ከእርሱ (ከመጥፎው) ትሰጣላችሁን አላህም ተብቃቂ ምስጉን መኾኑን ዕወቁ፡፡
ሰይጣን (እንዳትለግሱ) ድኽነትን ያስፈራራችኋል፡፡ በመጥፎም ያዛችኋል፡፡ አላህም ከርሱ የኾነን ምሕረትና ችሮታን ይቀጥራችኋል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡
ለሚሻው ሰው ጥበብን ይሰጣል፤ ጥበብንም የሚስሰጥ ሰው ብዙን መልካም ነገር በእርግጥ ተሰጠ፡፡ የአእምሮዎች ባለቤቶች እንጂ (ሌላው) አይገሰጽም፡፡
ከምጽዋትም ማንኛውንም የለገሳችሁትን ወይም ከስለት የተሳላችሁትን አላህ ያውቀዋል፡፡ ለበዳዮችም ከረዳቶች ምንም የላቸውም፡፡
ምጽዋቶችን ብትገልጹ እርሷ ምንኛ መልካም ናት፡፡ ብትደብቋትና ለድኾች ብትሰጧትም እርሱ ለናንተ በላጭ ነው፡፡ ከኃጢአቶቻችሁም ከእናንተ ያብሳል፡፡ አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
እነርሱን ማቅናት በአንተ ላይ የለብህም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት (ምንዳው) ለነፍሶቻችሁ ነው፡፡ የአላህንም ፊት (ውዴታውን) ለመፈለግ እንጂ አትለግሱም፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት ሁሉ (ምንዳው) ወደናንተ ይሞላል፡፡ እናንተም አትበደሉም፡፡
(የምትመጸውቱት) ለእነዚያ በአላህ መንገድ (ለመታገል ሲሉ) ለታገዱት ድኾች ነው፡፡ በምድር መኼድን አይችሉም፡፡ (ልመናን) ከመጥጠበቃቸው (የተነሳ) የማያውቅ ሰው ሀብታሞች ናቸው ብሎ ይጠረጥራቸዋል፡፡ በምልክታቸው ታውቃቸዋለህ፡፡ ሰዎችን በችክታ አይለምኑም፡፡ ከገንዘብም የምትለግሱት አላህ እርሱን ዐዋቂ ነው፡፡
እነዚያ ገንዘቦቻቸውን በሌሊትና በቀን በድብቅም በግልጽም የሚለግሱ ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም፡፡
እነዚያ አራጣን የሚበሉ ያ ሰይጣን ከመንካቱ የተነሳ የሚጥለው ሰው (ከአውድቁ) እንደሚነሳ ብጤ እንጅ (ከመቃብራቸው) አይነሱም፡፡ ይህ እነርሱ መሸጥ የአራጣ ብጤ ብቻ ነው በማለታቸው ነው፡፡ ግን መሸጥን አላህ ፈቅዷል፡፡ አራጣንም እርም አድርጓል፡፡ ከጌታውም ግሳጼ የመጣለትና የተከለከለ ሰው ለርሱ (ከመከልከሉ በፊት) ያለፈው አለው፡፡ ነገሩም ወደ አላህ ነው፤ (አራጣን ወደ መብላት) የተመለሰም ሰው እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡
አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል፡፡ ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡ አላህም ኃጠኢተኛ ከሓዲን ሁሉ አይወድም፡፡
እነዚያ ያመኑ፡፡ መልካም ሥራዎችንም የሠሩ፡፡ ሶላትንም ያስተካከሉ፡፡ ዘካንም የሰጡ ለነርሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፡፡ ከአራጣም የቀረውን ተዉ፡፡ አማኞች እንደኾናችሁ (ተጠንቀቁ)፡፡
(የታዘዛችሁትን) ባትሠሩም ከአላህና ከመልክተኛው በኾነች ጦር (መወጋታችሁን) ዕወቁ፡፡ ብትጸጸቱም ለእናንተ የገንዘቦቻችሁ ዋናዎች አሏችሁ፡፡ አትበድሉም አትበደሉምም፡፡
የድኽነት ባለቤት የኾነም (ባለዕዳ) ሰው ቢኖር እማግኘት ድረስ ማቆየት ነው፡፡ (በመማር) መመጽወታችሁም ለእናንተ በላጭ ነው፡፡ የምታውቁ ብትኾኑ (ትሠሩታላችሁ)፡፡
በእርሱም ውስጥ ወደ አላህ የምትመለሱበትንና ከዚያም እነርሱ የማይበደሉ ሲሆኑ ነፍስ ሁሉ የሠራችውን ሥራ የምትሞላበትን ቀን ተጠንቀቁ፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ በዕዳ በተዋዋላችሁ ጊዜ ጻፉት፡፡ ጸሐፊም በመካከላችሁ በትክክል ይጻፍ፡፡ ጸሐፊም አላህ እንደ አሳወቀው መጻፍን እንቢ አይበል፡፡ ይጻፍም፡፡ ያም በርሱ ላይ ዕዳው ያለበት ሰው በቃሉ ያስጽፍ፡፡ አላህንም ጌታውን ይፍራ፡፡ ከእርሱም (ካለበት ዕዳ) ምንንም አያጉድል፡፡ ያም በርሱ ላይ ዕዳው ያለበት ቂል፣ ወይም ደካማ፣ ወይም በቃሉ ማስጻፍን የማይችል ቢኾን ዋቢው በትክክል ያስጽፍለት፡፡ ከወንዶቻችሁም ሁለትን ምስክሮች አስመስክሩ፡፡ ሁለትም ወንዶች ባይኾኑ ከምስክሮች ሲኾኑ ከምትወዱዋቸው የኾኑን አንድ ወንድና አንደኛዋ ስትረሳ አንደኛይቱ ሌላዋን ታስታውሳት ዘንድ ሁለት ሴቶች (ይመስክሩ)፡፡ ምስክሮችም በተጠሩ ጊዜ እንቢ አይበሉ፡፡ (ዕዳው) ትንሽ ወይም ትልቅ ቢኾንም እስከ ጊዜው ድረስ የምትጽፉት ከመኾን አትሰልቹ፡፡ እንዲህ ማድረጋችሁ አላህ ዘንድ በጣም ትክክል ለምስክርነትም አረጋጋጭ ላለመጠራጠራችሁም በጣም ቅርብ ነው፡፡ ግን በመካከላችሁ እጅ በጅ የምትቀባበሏት ንግድ ብትኾን ባትጽፉዋት በናንተ ላይ ኃጢኣት የለባችሁም፡፡ በተሻሻጣችሁም ጊዜ አስመስክሩ፡፡ ጸሐፊም ምስክርም (ባለ ጉዳዩ ጋር) አይጎዳዱ፡፡ (ይህንን) ብትሠሩም እርሱ በእናንተ (የሚጠጋ) አመጽ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህም ያሳውቃችኋል፡፡ አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
በጉዞም ላይ ብትኾኑና ጸሐፊን ባታገኙ የተጨበጡ መተማመኛዎችን ያዙ፡፡ ከፊላችሁም ከፊሉን ቢያምን ያ የታመነው ሰው አደራውን ያድርስ፡፡ አላህንም ጌታውን ይፍራ፡፡ ምስክርነትንም አትደብቁ፡፡ የሚደብቃትም ሰው እርሱ ልቡ ኃጢኣተኛ ነው፡፡ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
በሰማያት ውስጥና በምድርም ውስጥ ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት አላህ በርሱ ይቆጣጠራችኋል፡፡ ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡:
አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡ ለርስዋ የሠራችው አላት፡፡ በርስዋም ላይ ያፈራችው (ኀጢአት) አለባት፡፡ (በሉ)፡- ጌታችን ሆይ! ብንረሳ ወይም ብንስት አትያዘን፤ (አትቅጣን)፡፡ ጌታችን ሆይ! ከባድ ሸክምን ከእኛ በፊት በነበሩት ላይ እንደጫንከው በእኛ ላይ አትጫንብን፡፡ ጌታችን ሆይ! ለኛም በርሱ ችሎታ የሌለንን ነገር አታሸክመን፡፡ ከእኛም ይቅርታ አድርግ ለእኛም ምሕረት አድርግ፡፡ እዘንልንም፤ ዋቢያችን አንተ ነህና፡፡ በከሓዲዎች ሕዝቦች ላይም እርዳን፡፡
Icon