ﮛ
ترجمة معاني سورة الحجر
باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية
.
من تأليف:
محمد صادق ومحمد الثاني حبيب
.
ﰡ
አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) ይህች (አናቅጽ) ከመጽሐፉ አንቀጾችና ገላጭ ከኾነው ቁርኣን ናት፡፡
እነዚያ የካዱት (በትንሣኤ ቀን) ሙስሊሞች በኾኑ ኖሩ በብዛት ይመኛሉ፡፡
ተዋቸው ይብሉ፤ ይጠቀሙም፡፡ ተስፋም ያዘናጋቸው፡፡ በእርግጥም (መጥፎ ፍጻሜያቸውን) ያውቃሉ፡፡
ማንኛይቱንም ከተማ ለእርሷ የተወሰነ መጽሐፍ (ጊዜያት) ያላት ኾና እንጂ አላጠፋንም፡፡
ማንኛይቱም ሕዝብ ጊዜዋን ምንም አትቀድምም፡፡ (ከእርሱ) አይቆዩምም፡፡
«አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርኣን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ ዕብድ ነህ» አሉም፡፡
«ከእውነተኞቹ እንደ ኾንክ በመላእክት (መስካሪ) ለምን አትመጣንም» (አሉ)፡፡
መላእክትን በእውነት (በቅጣት) እንጂ አናወርድም፡፡ ያን ጊዜም የሚቆዩ አይደሉም፡፡
እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡
ከአንተም በፊት በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ሕዝቦች ውስጥ (መልክተኞችን) በእርግጥ ልከናል፡፡
ማንኛውም መልእክተኛ በእርሱ የሚያላግጡበት ኾነው እንጅ አይመጣቸውም ነበር፡፡
እንደዚሁ (ማስተባበልን) በአመጸኞቹ ልቦች ውስጥ እናገባዋለን፡፡
በእርሱ አያምኑበትም፡፡ የቀድሞዎቹም ድርጊት በእርግጥ አልፋለች፤ (እንደጠፉ ይጠፋሉ)፡፡
በእነርሱም ላይ ከሰማይ ደጃፍን በከፈትንላቸውና በእርሱ ሲወጡ በዋሉ ኖሮ፤
«የተዘጉት ዓይኖቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም እኛ የተደገመብን ሰዎች ነን» ባሉ ነበር፡፡
በሰማይም ላይ ቡርጆችን በእርግጥ አድርገናል፡፡ ለተመልካቾችም (በከዋክብት) አጊጠናታል፡፡
ከተባረረ ሰይጣንም ሁሉ ጠብቀናታል፡፡
ግን (ወሬ) መስማትን የሚሰርቅ ወዲየውኑ አብሪ ችቦ ይከተለዋል፡፡ (ያቃጥለዋል)፡፡
ምድርንም ዘረጋናት፡፡ በውስጧም ኮረብታዎችን ጣልናባት፡፡ በውስጧም (የተለካን) በቃይ ሁሉ አበቀልንባት፡፡
በእርሷም ውስጥ ለእናንተ መኖሪያዎችንና ለእርሱ መጋቢዎቹ ያልኾናችሁትንም (እንስሳትን) አደረግንላችሁ፡፡
መካዚኖቹም (መክፈቻቸው) እኛ ዘንድ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ በተወሰነም ልክ እንጂ አናወርደውም፡፡
ነፋሶችንም (ደመናን) ተሸካሚዎች አድርገን ላክን፡፡ ከሰማይም (ከደመና) ዝናብን አወረድን፡፡ እርሱንም አጠጣናችሁ፡፡ እናንተም ለእርሱ አድላቢዎች አይደላችሁም፡፡
እኛም ሕያው የምናደርግና የምንገድል እኛው ብቻ ነን፡፡ እኛም (ፍጡርን ሁሉ ) የምንወርስ (ቀሪ) ነን፡፡
ከእናንተም ተቀዳሚዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡ ወደ ኋላም ቀሪዎቹን በእርግጥ ዐውቀናል፡፡
ጌታህም እርሱ ይሰበስባችኋል፡፡ እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
ሰውንም ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጥቁር ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው፡፡
ጃንንም (ከሰው) በፊት ከእሳት ነበልባል ፈጠርነው፡፡
ጌታህም ለመላእክት ባለጊዜ (አስታውስ)፡፡ እኔ ሰውን ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጭቃ እፈጥራለሁ፡፡
(ፍጥረቱን) ባስተካከልኩትና በውስጡ ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ለእርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ፡፡
መላእክትም መላውም ተሰብስበው ሰገዱ፡፡
ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር፡፡ ከሰጋጆቹ ጋር ከመኾን እንቢ አለ፡፡
(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! ከሰጋጆቹ ጋር የማትኾን ላንተ ምን ምክንያት አለህ» አለው፡፡
«ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከግም ጭቃ ለፈጠርከው ሰው ልሰግድ አይገባኝም» አለ፡፡
(አላህ) አለው «ከርሷም ውጣ፡፡ አንተ የተባረርክ እርጉም ነህና፡፡»
«ባንተ ላይም እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ እርግማን አለብህ፡፡»
«ጌታዬ ሆይ! እንግዲውያስ (ሰዎች) እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ አቆየኝ» አለ፡፡
(አላህም) አለ «አንተ ከሚቆዩት ነህ፡፡
«እስከታወቀው ወቅት ቀን ድረስ፡፡»
(ኢብሊስ) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔን በማጥመምህ ይኹንብኝ ለነርሱ በምድር ላይ (ኀጢአትን) እሸልምላቸዋለሁ፡፡ ሁሉንም አጠማቸዋለሁም፡፡»
«ከነርሱ ፍጹሞቹ ባሮችህ ብቻ ሲቀሩ፡፡»
(አላህም) አለ «ይህ በእኔ ላይ (መጠበቁ የተገባ) ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»
«እነሆ ባሮቼ በእነሱ ላይ ላንተ ስልጣን የለህም፡፡ ከጠማሞቹ የተከተለህ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡»
«ገሀነምም (ለርሱና ለተከተሉት) ለመላውም በእርግጥ ቀጠሯቸው ናት፡፡
«ለእርሷ ሰባት ደጃፎች አሏት፡፡ ለየደጀፉም ሁሉ ከእነሱ የተከፈለ ፋንታ አለ፡፡
«እነዚያ (ከኀጢአት) የተጠነቀቁት በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡
«ጸጥተኞች ኾናችሁ በሰላም ግቧት (ይባላሉ)፡፡
«ባልጋዎችም ላይ ፊት ለፊት የሚቅጣጩ ወንድማማቾች ኾነው በደረቶቻቸው ውስጥ ከቂም ያለውን ሁሉ እናስወግዳለን፡፡
«በእርሷም ውስጥ ድካም አይነካቸውም፡፡ እነሱም ከእርሷ የሚወጡ አይደሉም፡፡»
ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡
ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡
ከኢብራሂም እንግዶችም (ወሬ) ንገራቸው፡፡
በእርሱ ላይ በገቡና ሰላም ባሉት ጊዜ የኾነውን (አስታውስ)፡፡ (እርሱም) «እኛ ከእናንተ ፈሪዎች ነን» አላቸው፡፡
«አትፍራ፤ እኛ ዐዋቂ በኾነ ወንድ ልጅ እናበስርሃለን» አሉት፡፡
«እርጅና የደረሰብኝ ከመኾኔ ጋር አበሰራችሁኝን በምን ታበስሩኛላችሁ» አለ፡፡
«በእውነት አበሰርንህ፡፡ ከተሰፋ ቆራጮችም አትኹን» አሉ፡፡
«ከጠማማዎችም በስተቀር ከጌታው እዝነት ተስፋን የሚቆርጥ ማነው» አለ፡፡
«እናንተ መልክተኞች ሆይ! ኧረ ለመኾኑ ነገራችሁ ምንድን ነው» አለ፡፡
«እኛ አመጸኞች ወደ ኾኑ ሕዝቦች ተልከናል» አሉት፡፡
«የሉጥ ቤተሰቦች ብቻ ሲቀሩ፡፡ (እነርሱን) እኛ ሁላቸውንም በእርግጥ የምናድናቸው ነን፡፡
«ሚስቱ ብቻ ስትቀር፡፡ እርሷን (በቅጣቱ ውስጥ) ከሚቀሩት መኾኗን ወሰነናል» (አሉ)፡፡
መልክተኞቹም የሉጥን ቤተሰቦች በመጡባቸው ጊዜ፤
(ሉጥ) «እናንተ የተሳታችሁ ሕዝቦች ናችሁ» አላቸው፡፡
«አይደለም እኛ ሕዝቦችህ በርሱ ይጠራጠሩበት በነበሩት ቅጣት መጣንህ» አሉት፡፡
«እውነትንም ይዘን መጣንህ፡፡ እኛም በእርግጥ እውነተኞች ነን፡፡
ከቤተሰብህም ጋር በሌሊቱ ከፊል ኺድ፡፡ ከኋላቸውም ተከተል፡፡ ከእናንተም አንድም ሰው ወደ ኋላው አይገላመጥ፡፡ ወደ ታዘዛችሁበትም ስፍራ እለፉ» (አሉት)፡፡
ወደርሱም ያንን ትእዛዝ አወረድን፡፡ (እርሱም) የእነዚህ (ሕዝቦች) መጨረሻ ያነጉ ሲኾኑ (ሥራቸው) መቆረጥ ነው፡፡
የከተማይቱም ሰዎች የሚበሳሰሩ ኾነው መጡ፡፡
(ሉጥም) አለ «እነዚህ እንግዶቼ ናቸውና አታጋልጡኝ፡፡
«አላህንም ፍሩ፤ አታሳፍሩኝም፡፡»
«ከዓለማት (ማንንም እንዳታስተናግድ) አልከለከልንህምን» አሉት፡፡
(ሉጥም) «እነኝህ ሴቶች ልጆቼ ናቸው፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (አግቧቸው)» አለ፡፡
በዕድሜህ እንምላለን እነሱ በእርግጥ በስከራቸው ውስጥ ይዋልላሉ፡፡
ጩኸቲቱም ፀሐይ የወጣችባቸው ሲኾኑ ያዘቻቸው፡፡
ላይዋንም ከታችዋ አደረግን፡፡ በእነሱም ላይ የሸክላ ደንጊያዎችን አዘነብንባቸው፡፡
በዚህ ውስጥ ለተመልካቾች በእርግጥ መገምገሚያዎች አሉበት፡፡
እሷም (ከተማይቱ) በቀጥታ መንገድ ላይ ናት፡፡
በዚህ ውስጥ በእርግጥ ለምእምናን መገሰጫ አለ፡፡
እነሆ የአይከት ሰዎችም በእርግጥ በዳዮች ነበሩ፤
ከነሱም ተበቀልን ሁለቱም (የሉጥና የአይከት ሕዝቦች ከተሞች) በእርግጥ በግልጽ መንገድ ላይ ናቸው፡፡
የሒጅርም ሰዎች መልክተኞቹን በእርግጥ አስተባበሉ፡፡
ተዓምራታችንንም ሰጠናቸው፡፡ ከእርሷም ዘንጊዎች ነበሩ፡፡
ከኮረብታዎችም ቤቶችን ጸጥተኞች ኾነው ይጠርቡ ነበር፡፡
ያነጉም ሲኾኑ ጩኸት ያዘቻቸው፤ (ወደሙ)፡፡
ይሠሩትም የነበሩት ሕንጻ ምንም አልጠቀማቸውም፡፡
ሰማያትንና ምድርንም በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በእውነት እንጂ (በላግጣ) አልፈጠርንም፡፡ ሰዓቲቱም በእርግጥ መጪ ናት፡፡ መልካምንም ይቅርታ አድርግላቸው፡፡
ጌታህ እርሱ (ያልነበረን) ፈጣሪው ዐዋቂው ነው፡፡
ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትንና ታላቁንም ቁርኣን (በሙሉ) በእርግጥ ሰጠንህ፡፡
ከእነርሱ (ከከሓዲዎች) ብዙዎችን ወገኖች በእርሱ ወደ አጣቀምንበት ጸጋ ዓይኖችህን አትዘርጋ፡፡ በእነሱም ላይ (ባያምኑ) አትዘን፡፡ ክንፍህንም ለምእምናን አለዝብ፡፡
በልም «እኔ ግልጽ አስፈራሪው እኔ ነኝ፡፡»
(ሰዎችን ለማገድ የመካን በሮች) በተከፋፈሉት ላይ እንደ አወረድነው (በኾነ ቅጣት አሰፈራሪያችሁ ነኝ በል)፡፡
(እነርሱም) እነዚያ ቁርኣንንን ክፍልፍሎች ያደረጉ ናቸው፡፡
በጌታህም እንምላለን፡፡ ሁላቸውንም እንጠይቃቸዋለን፤
ይሠሩት ከነበሩት ነገር ሁሉ፡፡
የታዘዝክበትንም ነገር በይፋ ግለጽ፡፡ አጋሪዎችንም ተዋቸው፡፡
ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንሃል፡፡
(እነሱም) እነዚያ ከአላህ ጋር ሌላ አምላክን ያደረጉ ናቸው፡፡ በእርግጥም (ፍጻሜያቸውን) ወደፊት ያውቃሉ፡፡
አንተም በሚሉት ነገር ልብህ የሚጠብ መኾኑን በእርግጥ እናውቃለን፡፡
ጌታህንም ከማመስገን ጋር አጥራው ከሰጋጆቹም ኹን፡፡
እውነቱም (ሞት) እስኪመጣህ ድረስ ጌታህን ተገዛ፡፡