ترجمة سورة الإسراء

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة الإسراء باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው፡፡ ከተዓምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው)፡፡ እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡

ሙሳንም መጽሐፉን ሰጠነው፡፡ ለእስራኤልም ልጆች መሪ አደረግነው፡፡ ከእኔ ሌላ መጠጊያን አትያዙ፤ (አልናቸውም)፡፡

እናንተ ከኑሕ ጋር (በመርከቢቱ) የጫናቸው ዘሮች ሆይ! (አላህን ተገዙ) እርሱ በብዙ አመስጋኝ ባሪያ ነበርና፡፡

ወደ እስራኤልም ልጆች በመጽሐፉ ውስጥ (እንዲህ በማለት) አወረድን፡፡ በምድር ላይ በእርግጥ ሁለት ጊዜ ታጠፋላችሁ፡፡ ትልቅንም ኩራት ትኮራላችሁ፡፡

ከሁለቱ (ጊዜያቶች) የመጀመሪያይቱ ቀጠሮ በመጣም ጊዜ ለእኛ የኾኑን ባሮች የብርቱ ኃይል ባለቤቶች የኾኑትን በእናንተ ላይ እንልካለን፡፡ በቤቶችም መካከል ይመላለሳሉ፤ (ይበረብሩታል፡፡) ይህ ተፈጻሚ ቀጠሮም ነበር፡፡

ከዚያም (በኋላ) ለእናንተ በእነሱ ላይ ድልን መለስንላችሁ፡፡ በገንዘቦችና በወንዶች ልጆችም ጨመርንላችሁ፡፡ በወገንም የበዛችሁ አደረግናችሁ፡፡

መልካም ብትሠሩ ለነፍሶቻችሁ መልካምን ሠራችሁ፡፡ መጥፎንም ብትሠሩ በነርሱ (በነፍሶቻችሁ) ላይ ነው፤ (አልን)፡፡ የኋለኛይቱም (ጊዜ) ቀጠሮ በመጣ ጊዜ ፊቶቻችሁን ሊያስከፉ፣ መስጊዱንም በመጀመሪያ ጊዜ እንደገቡት ሊገቡ፣ ያሸነፉትንም ሁሉ (ፈጽመው) ማጥፋትን እንዲያጠፉ (እንልካቸዋልን)፡፡

(በመጽሐፉም አልን) «ብትጸጸቱ፡- ጌታችሁ ሊያዝንላችሁ ይከጀላል፡፡ (ወደ ማጥፋት) ብትመለሱም እንመለሳለን፡፡ ገሀነምንም ለከሓዲዎች ማሰሪያ አደርገናል፡፡

ይህ ቁርኣን ወደዚያች እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፡፡ እነዚያንም በጎ የሚሠሩትን ምእመናን ለእነሱ ታላቅ ምንዳ ያላቸው መኾኑን ያበስራል፡፡

እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑት ለእነሱ አሳማሚ ቅጣትን አዘጋጅተንላቸዋል፤

ሰው መልካምን ነገር እንደሚለምን ሁሉ፤ መጥፎንም ነገር ይለምናል፡፡ ሰውም ቸኳላ ነው፡፡

ሌሊትንና ቀንንም (ለችሎታችን) ምልክቶች አደረግን፡፡ የሌሊትን ምልክትም አበስን፡፡ የቀንን ምልክትም የምታሳይ አደረግን፡፡ (ይህም የኾነበት) ከጌታችሁ ትርፍን ልትፈልጉ የዓመታትንም ቁጥርና ሒሳብንም ታውቁ ዘንድ ነው፡፡ ነገሩንም ሁሉ ለያይተን ዘረዘርነው፡፡

ሰውንም ሁሉ በራሪውን (ሥራውን) በአንገቱ አስያዝነው፡፡ ለእርሱም በትንሣኤ ቀን የተዘረጋ ኾኖ የሚያገኘው የኾነን መጽሐፍ እናወጣለታለን፡፡

«መጽሐፍህን አንብብ፡፡ ዛሬ ባንተ ላይ ተቆጣጣሪነት በነፍስህ በቃ» (ይባላል)፡፡

የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ የተሳሳተም ሰው የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በእርሷ ላይ ነው፡፡ ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ኃጢኣት አትሸከምም፡፡ መልዕክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡

ከተማንም ለማጥፋት በፈለግን ጊዜ ባለ ጸጋዎችዋን እናዛለን፡፡ በውስጧም ያምጻሉ፡፡ በእርሷም ላይ ቃሉ (ቅጣቱ) ይፈጸምባታል፡፡ ማጥፋትንም እናጠፋታለን፡፡

ከኑሕም በኋላ ከክፍለ ዘመናት ሰዎች ያጠፋናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ የባሮቹንም ኃጢኣቶች ውስጠ ዐዋቂ ተመልካች መኾን በጌታህ በቃ፡፡

ቸኳይቱን ዓለም (በሥራው) የሚፈልግ ሰው ለእርሱ በርሷ ውስጥ የሻነውን (ጸጋ) ለምንሻው ሰው እናስቸኩልለታለን፡፡ ከዚያም ለእርሱ ገሀነምን (መኖሪያ) አድርገንለታል፡፡ ተወቃሽ ብራሪ ኾኖ ይገባታል፡፡

መጨረሻይቱንም ዓለም የፈለገ ሰው እርሱ አማኝ ኾኖ ለርሷ (ተገቢ) ሥራዋን የሠራም ሰው እነዚህ ሥራቸው የተመሰገነ ይኾናል፡፡

ሁሉንም እነዚህንና እነዚያን ከጌታህ ስጦታ (በዚህ ዓለም) እንጨምርላቸዋለን፡፡ የጌታህም ስጦታ (በዚች ዓለም) ክልክል አይደለም፡፡

ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ እንዴት እንዳበለጥን ተመልከት፡፡ የመጨረሻያቱም አገር በማዕረጎች በጣም የከበረችና በመብለጥም የተለቀች ናት፡፡

ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ የተወቀስክ ረዳት የሌለህ ትኾናለህና፤

ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ፡፡ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፡፡ አትገላምጣቸውም፡፡ ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡

ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፡፡ «ጌታዬ ሆይ! በሕፃንነቴ (በርኅራኄ) እንዳሳደጉኝ እዘንልላቸውም» በል፡፡

ጌታችሁ በነፍሶቻችሁ ውስጥ ያለውን ሁሉ አዋቂ ነው፡፡ ታዛዦችም ብትኾኑ (በመሳሳትም ብታጠፉ) እርሱ ለተመላሾች መሓሪ ነው፡፡

ለዝምድና ባለቤትም መብቱን ስጥ፡፡ ለምስኪንና ለመንገደኛም (ስጥ)፡፡ ማባከንንም አታባክን፡፡

አባካኞች የሰይጣናት ወንድሞች ናቸውና፡፡ ሰይጣንም ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው፡፡

ከጌታህም የምትከጅላትን ጸጋ ለማጣት ከእነርሱ ብትዞር ለእነሱ ልዝብን ቃል ተናገራቸው፡፡

እጅህንም ወደ አንገትህ የታሰረች አታድርግ፡፡ መዘርጋትንም ሁሉ አትዘርጋት፤ የተወቀስክ የተቆጨኽ ትኾናለህና፡፡

ጌታህ ሲሳይን ለሚሻው ሰው ያሰፋል፤ ያጠባልም፡፡ እርሱ በባሮቹ ኹኔታ ውስጠ ዐዋቂ ተመልካች ነውና፡፡

ልጆቻችሁንም ድኽነትን ለመፍራት አትግደሉ፡፡ እኛ እንመግባቸዋለን፡፡ እናንተንም (እንመግባለን)፡፡ እነርሱን መግደል ታላቅ ኃጢኣት ነውና፡፡

ዝሙትንም አትቅረቡ፡፡ እርሱ በእርግጥ መጥፎ ሥራ ነውና፡፡ መንገድነቱም ከፋ!

ያቺንም አላህ ያወገዛትን ነፍስ ያለ ሕግ አትግደሉ፡፡ የተበደለም ኾኖ የተገደለ ሰው ለዘመዱ (በገዳዩ ላይ) በእርግጥ ስልጣንን አድርገናል፡፡ በመግደልም ወሰንን አይለፍ፤ እርሱ የተረዳ ነውና፡፡

የየቲምንም ገንዘብ የብርታቱን ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በኾነች ኹኔታ እንጂ አትቅረቡ፡፡ በኪዳናችሁም ሙሉ፡፡ ኪዳን የሚጠየቁበት ነውና፡፡

በሰፈራችሁም ጊዜ ስፍርን ሙሉ፡፡ በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡

ለአንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር አትከተል፡፡ መስሚያ፣ ማያም፣ ልብም እነዚህ ሁሉ (ባለቤታቸው) ከእነሱ ተጠያቂ ነውና፡፡

በምድርም ላይ የተንበጣረረክ ሆነህ፤ አትሂድ፡፡ አንተ ፈጽሞ ምድርን አትሰረጉድምና በርዝመትም ፈጽሞ ጋራዎችን አትደርስምና፡፡

ይህ ሁሉ መጥፎው (አሥራ ሁለቱ ክልክሎች) እጌታህ ዘንድ የተጠላ ነው፡፡

ይህ ጌታህ ከጥበቡ ወደ አንተ ካወረደው ነገር ነው፡፡ ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አታድርግ የተወቀስክ የተባረርክ ኾነህ በገሀነም ውስጥ ትጣላለህና፡፡

ጌታችሁ በወንዶች ልጆች መረጣችሁና ከመላእክት ሴቶችን (ልጆች) ያዝን እናንተ ከባድን ቃል በእርግጥ ትናገራላችሁ፡፡

ይገሰጹም ዘንድ በዚህ ቁርኣን ውስጥ ደጋግመን በእርግጥ ገለጽን፡፡ መበርገግንም እንጂ ሌላን አይጨመርላቸውም፡፡

(ሙሐመድ ሆይ) በላቸው «እንደምትሉት ከእርሱ ጋር አማልክት በነበሩ ኖሮ ያን ጊዜ ወደ ዐርሹ ባለቤት መንገድን በፈለጉ ነበር፡፡»

ጥራት ይገባው፡፡ ከሚሉትም ነገር ሁሉ ከፍ ያለን ልቅና ላቀ፡፡

ሰባቱ ሰማያትና ምድርም በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ለእርሱ ያጠራሉ፡፡ ከነገርም ሁሉ ከማመስገን ጋር የሚያጠራው እንጂ አንድም የለም፡፡ ግን ማጥራታቸውን አታውቁትም፡፡ እርሱ ታጋሽ መሓሪ ነው፡፡

ቁርኣንንም ባነበብክ ጊዜ ባንተና በእነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም በማያምኑት ሰዎች መካከል የሚሸሸግን ግርዶሽ አድርገናል፡፡

እንዳያውቁትም በልቦቻቸው ላይ ሽፋንን በጆሮቻቸውም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን፡፡ ጌታህንም ብቻውን ኾኖ በቁርኣን ባወሳኸው ጊዜ የሚሸሹ ኾነው በጀርባዎቻቸው ላይ ይዞራሉ፡፡

እኛ ወደ አንተ በሚያዳምጡ ጊዜ እነሱም በሚንሾካሾኩ ጊዜ በዳዮች (እርስ በርሳቸው) የተደገመበትን ስው እንጂ አትከተሉም በሚሉ ጌዜ በእርሱ የሚያዳምጡበትን ምክንያት ዐዋቂ ነን፡፡

ምሳሌዎችን ለአንተ እንዴት እንዳደረጉልህና እንደ ተሳሳቱ ተመልከት፡፡ (ወደ እውነቱ ለመድረስ) መንገድንም አይችሉም፡፡

አሉም «እንዴት አጥንቶችና ብስብሶች በኾን ጊዜ እኛ አዲስ ፍጥረት ኾነን በእርግጥ ተቀስቃሾች ነን»

በላቸው «ድንጋዮችን ወይም ብረትን ሁኑ»

«ወይም በልቦቻችሁ ውስጥ የሚተልቅን ፍጥረት (ኹኑ መቀስቀሳችሁ አይቀርም)፡፡» «የሚመልሰንም ማነው» ይላሉ፡፡ ያ በመጀመሪያ ጊዜ የፈጠራችሁ ነው» በላቸው፡፡ ወደ አንተም ራሶቻቸውን ይነቀንቃሉ፡፡ «እርሱም መቼ ነው» ይላሉ፡፡ «(እርሱ) ቅርብ ሊኾነን ይቻላል በላቸው፡፡

(እርሱም) የሚጠራችሁና (አላህን) አመስጋኞቹ ኾናችሁ ጥሪውን የምትቀበሉበት ጥቂትንም (ቀኖች) እንጂ ያልቆያችሁ መኾናችሁን የምትጠራጠሩበት ቀን ነው፤ (በላቸው)፡፡

ለባሮቼም በላቸው፡- ያችን እርሷ መልካም የኾነችውን (ቃል) ይናገሩ፡፡ ሰይጣን በመካከላቸው ያበላሻልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፡፡

ጌታችሁ በእናንተ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው፡፡ ቢሻ ያዝንላችኋል፤ ወይም ቢሻ ይቀጣችኋል፡፡ በእነሱም ላይ ኃላፊ ኾነህ አላክንህም፡፡ (አታስገድዳቸውም)፡፡

ጌታህም በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡ ከፊሉንም ነቢያት በከፊሉ ላይ በእርግጥ አብልጠናል፡፡ ዳውድንም ዘቡርን ሰጥተነዋል፡፡

«እነዚያን ከእርሱ ሌላ (አማልክት) የምትሏቸውን ጥሩ፡፡ ከእናንተም ላይ ጉዳትን ማስወገድን (ወደ ሌላ) ማዞርንም አይችሉም» በላቸው፡፤

እነዚያ እነርሱ የሚግገዟቸው ማንኛቸውም (ወደ አላህ) በጣም ቀራቢያቸው ወደ ጌታቸው መቃረቢያን (ሥራ) ይፈልጋሉ፡፡ እዝነቱንም ይከጅላሉ፡፡ ቅጣቱንም ይፈራሉ፡፡ የጌታህ ቅጣት የሚፈራ ነውና፡፡

አንዲትም ከተማ የለችም እኛ ከትንሣኤ ቀን በፊት አጥፊዎችዋ ወይም ብርቱን ቅጣት ቀጭዎችዋ ብንኾን እንጂ፡፡ ይህ በመጽሐፉ የተጻፈ ነው፡፡

ታምራቶችንም ከመላክ የቀድሞዎቹ ሰዎች በእርሷ ማስተባበልና (መጥፋት) እንጂ ሌላ አልከለከለንም፡፡ ለሰሙድም ግመልን ግልጽ ተዓምር ኾና ሰጠናቸው፡፡ በእርሷም በደሉ፡፡ ተዓምራቶችንም ለማስፈራራት እንጂ አንንልክም፡፡

ላንተም ጌታህ (ዕውቀቱ) በሰዎቹ ከበበ ባልንህ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ያችንም (በሌሊቱ ጉዞ በዓይንህ) ያሳየንህን ትርዕይት ለሰዎች ፈተና እንጂ አላደረግናትም፡፡ በቁርኣንም የተረገመችውን ዛፍ (እንደዚሁ ፈተና እንጂ አላደረግንም)፡፡ እናስፈራራቸዋለንም፤ ታላቅንም ጥመት እንጂ አይጨምርላቸውም፡፡

ለመላእክትም ለአደም ስገዱ ባልናቸው ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ «ከጭቃ ለፈጠርከው ሰው እሰግዳለሁን» አለ፡፡

«ንገረኝ ይህ ያ በእኔ ላይ ያበለጥከው ነውን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ብታቆየኝ ዘሮቹን ጥቂቶች ሲቀሩ ወደ ስህተት በእርግጥ እስባቸዋለሁ» አለ፡፡

(አላህም) አለው «ኺድ፤ ከእነሱም የተከተለህ ገሀነም የተሟላች ቅጣት ስትኾን ፍዳችሁ ናት፡፡

«ከእነሱ የቻልከውንም ሰው በድምጽህ አታል፡፡ በእነሱም ላይ በፈረሰኞችህ፣ በእግረኞችህም ኾነህ ለልብ፡፡ በገንዘቦቻቸውም፣ በልጆቻቸውም ተጋራቸው፣ ተስፋ ቃልም ግባላቸው፡፡ ሰይጣንም ማታለልን እንጂ ተስፋ ቃልን አይገባላቸውም፡፡

«ባሮቼ በእነሱ ላይ ፈጽሞ ላንተ ስልጣን የለህም፡፡ መጠጊያም በጌታህ በቃ፡፡»

ጌታችሁ ያ ከችሮታው ትፈልጉ ዘንድ መርከቦችን በባሕር ለይ ለእናንተ የሚነዳላችሁ ነው፡፡ እነሆ እርሱ ለናንተ አዛኝ ነውና፡፡

በባሕሩም ውስጥ ጉዳት ባገኛችሁ ጊዜ የምትጠሩዋቸው (አማልክት) ሁሉ ከእርሱ (ከአላህ) በቀር ይጠፋሉ፡፡ ወደ የብስም በማድረስ ባዳናችሁ ጊዜ (እምነትን) ትተዋላችሁ፡፡ ሰውም በጣም ከሓዲ ነው፡፡

የየብሱን በኩል (ምድርን) በእናንተ መገልበጡን ወይም ጠጠርን የያዘ ንፋስን በእናንተ ላይ መላኩን ከዚያም ለእናንተ ጠባቂ አለማግኘታችሁን አትፈሩምን

ወይስ ሌላ ጊዜ ወደ እርሱ (ወደ ባሕር) የሚመልሳችሁ ወዲያውም በእናንተ ላይ ብርቱን ነፋስ የሚልክ በክሕደታችሁም ምክንያት የሚያሰጥማችሁ መኾኑን ከዚያም በኛ ላይ በእርሱ ተከታይን (ረዳትን) ለእናንተ የማታገኙ መኾናችሁን አትፈሩምን

የአደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፡፡ በየብስና በባህርም አሳፈርናቸው፡፡ ከመልካሞችም (ሲሳዮች) ሰጠናቸው፡፡ ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው፡፡

ሰዎችን ሁሉ በመሪያቸው የምንጠራበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ መጽሐፉንም በቀኙ የተሰጠ ሰው እነዚያ መጽሐፋቸውን ያነባሉ፡፡ በተምር ፍሬ ስንጥቅ ላይ ያለውን ክር ያክል እንኳ አይበደሉም፡፡

በዚህችም ዓለም (ልበ) ዕውር የኾነ ሰው እርሱ በመጨረሻይቱም (ዓለም) ይበልጥ ዕውር ነው፡፡ መንገድንም በጣም የተሳሳተ ነው፡፤

እነሆ ከዚያም ወደ አንተ ካወረድነው ሌላን በእኛ ላይ ትዋሽ ዘንድ ሊፈትኑህ በእርግጥ ተቃረቡ፡፡ ያን ጊዜም ወዳጅ አድርገው በያዙህ ነበር፡፡

ባላረጋንህም ኖሮ ወደነሱ ጥቂትን (ዝንባሌ) ልትዘነበል በእርግጥ በተቃረብክ ነበር፡፡

ያን ጊዜ የሕይወትን ድርብ (ቅጣት) የሞትንም ድርብ (ቅጣት) ባቀመስንህ ነበር፡፡ ከዚያም ላንተ በኛ ላይ ረዳትን አታገኝም ነበር፡፡

ከምድሪቱም (ከዓረብ ምድር) ከርሷ ያወጡህ ዘንድ ሊያሸብሩህ በእርግጥ ተቃረቡ፡፡ ያን ጊዜም ከአንተ በኋላ ጥቂትን ጊዜ እንጂ አይቆዩም ነበር፡፡

ከመልክተኞቻችን ካንተ በፊት በእርግጥ እንደላክናቸው ሰዎች ልማድ ብጤ (ይጠፉ ነበር)፡፡ ለልማዳችንም መለወጥን አታገኝም፡፡

ሶላትን ከፀሐይ መዘንበል እስከ ሌሊት ጨለማ ድረስ ስገድ፡፡ የጎህንም ሶላት ስገድ፡፡ የጎህ ሶላት (መላእክት) የሚጣዱት ነውና፡፡

ከሌሊትም ላንተ ተጨማሪ የኾነችን ሶላት በእርሱ (በቁርኣን) ስገድ፡፡ ጌታህ ምስጉን በኾነ ስፍራ በእርግጥ ያቆምሃል፡፡

በልም ጌታዬ ሆይ! የተወደደን ማግባት አግባኝ፡፡ የተወደደንም ማውጣት አውጣኝ፡፡ ለእኔም ከአንተ ዘንድ የተረዳን ስልጣን አድርግልኝ፡፡

በልም «እውነት መጣ ውሸትም ተወገደ፤ እነሆ ውሸት ተወጋጅ ነውና፡፡»

ከቁርኣንም ለምእመናን መድኀኒትና እዝነት የኾነን እናወርዳለን፡፡ በዳዮችንም ከሳራን እንጂ ሌላ አይጨምርላቸውም፡፡

በሰውም ላይ ጸጋችንን በለገስን ጊዜ (ከምስጋና) ይዞራል፡፡ ጎኑንም (ከእውነት) ያርቃል፡፡ ችግርም በነካው ጊዜ ተስፋ ቆራጭ ይኾናል፡፡

«ሁሉም በሚመስለው መንገዱ ላይ ይሠራል፡፡ ጌታችሁም እርሱ መንገዱ ቀጥተኛ የኾነውን ሰው ዐዋቂ ነው በላቸው፡፡

ከሩሕም ይጠይቁሃል፡፡ «ሩሕ ከጌታዬ ነገር ነው ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም» በላቸው፡፡

ብንሻም ያንን ወዳንተ ያወረድነውን በእርግጥ እናስወግዳለን፡፡ ከዚያም ላንተ በእኛ ላይ በርሱ (ለማስመለስ) ተያዢን አታገኝም፡፡

ግን ከጌታህ በኾነው እዝነት (ጠበቅነው)፡፡ ችሮታው ባንተ ላይ ታላቅ ነውና፡፤

«ሰዎችም ጋኔኖችም የዚህን ቁርኣን ብጤ በማምጣት ላይ ቢሰበሰቡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆንም እንኳ ብጤውን አያመጡም» በላቸው፡፡

በዚህም ቁርኣን ውስጥ ከምሳሌው ሁሉ ለሰዎች በእርግጥ መላለስን፡፡ አብዛኞቹም ሰዎች ክህደትን እንጂ ሌላን እምቢ አሉ፡፡

አሉም «ለኛ ከምድር ምንጭን እስከምታፈነዳን ለአንተ አናምንም፡፡»

«ወይም ከዘምባባዎችና ከወይን የኾነች አትክልት ለአንተ እስከምትኖርህና በመካከልዋም ጂረቶችን በብዛት እስከምታንቧቧ፡፡

«ወይም እንደምትለው ከሰማይ ቁራጮችን በኛ ላይ እስከምታወድቅ፤ ወይም አላህንና መላእክትን በግልጽ እስከምታመጣ፡፡

«ወይም ከወርቅ የኾነ ቤት ላንተ እስከሚኖርህ፤ ወይም በሰማይ እስከምትወጣ፤ ለመውጣትህም በእኛ ላይ የምናነበው የኾነን መጽሐፍ እስከምታወርድልን ድረስ ፈጽሞ አናምንልህም» (አሉ)፡፡ «ጌታዬ ጥራት ይገባው፤ እኔ ሰው መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለሁም» በላቸው፡፡

ሰዎችንም መሪ (ቁርኣን) በመጣላቸው ጊዜ ከማመን «አላህ ሰውን መልክተኛ አድርጎ ላከን» ማለታቸው እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም፡፡

«በምድር ላይ ረግተው የሚኼዱ መላእክት በነበሩ ኖሮ በእነሱ ላይ (ከጎሳቸው) የመልአክን መልክተኛ ባወረድን ነበር» በላቸው፡፡

«በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአላህ በቃ፡፡ እርሱ በባሮቹ (ነገር) ውስጥ ዐዋቂ ተመልካች ነውና» በላቸው፡፡

አላህም ያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ያጠመማቸውም ሰዎች ከእርሱ ሌላ ለእነርሱ ፈጽሞ ረዳት አታገኝላቸውም፡፡ በትንሣኤ ቀንም ዕውሮች፣ ዲዳዎችም ደንቆሮዎችም ኾነው በፊቶቻቸው ላይ (እየተጎተቱ) እንሰበስባቸዋለን፡፡ መኖሪያቸው ገሀነም ናት፡፡ (ነዲድዋ) በደከመች ቁጥር መንቀልቀልን እንጨምርባቸዋለን፡፤

ይህ (ቅጣት)፤ እነርሱ በአንቀጾቻችን ስለ ካዱና «አጥንቶችና ብስብሶች በኾን ጊዜ እኛ አዲስ ፍጥረት ኾነን ተቀስቃሾች ነን» ስላሉም ፍዳቸው ነው፡፡

ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ አላህ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ መኾኑን በእርሱ ጥርጣሬ የሌለበትም ጊዜ (ለሞትም ለትንሣኤም) ለእነርሱ የወሰነ መኾኑን አላወቁምን በደለኞችም ከክህደት በቀር እምቢ አሉ፡፡

«እናንተ የጌታዬን የችሮታ መካዚኖች ብትይዙ ኖሮ ያን ጊዜ በማውጣታችሁ ማለቋን በመፍራት በጨበጣችሁ ነበር፡፡ ሰውም በጣም ቆጣቢ ነው፡፡»

ለሙሳም ግልጽ የኾኑን ዘጠኝ ተዓምራቶች በእርግጥ ሰጠነው፡፡ በመጣቸውም ጊዜ የእስራኤልን ልጆች (ከፈርዖን እንዲለቀቁ) ጠይቅ (አልነው)፡፡ ፈርዖንም «ሙሳ ሆይ! እኔ የተደገመብህ መኾንህን በእርግጥ እጠረጥራለሁ» አለው፡፡

(ሙሳም) «እነዚህን (ተዓምራቶች) መገሰጫዎች ሲኾኑ የሰማያትና የምድር ጌታ እንጂ ሌላ እንዳላወረዳቸው በእርግጥ ዐውቀሃል፡፡ እኔም ፈርዖን ሆይ! የምትጠፋ መኾንህን በእርግጥ እጠረጥርሃለሁ» አለው፡፡

ከምድርም ሊቀሰቅሳቸው አሰበ፡፡ እርሱንና ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ሰዎች ሁሉንም አሰጠምናቸው፡፡

ከእርሱም በኋላ ለእሰራኤል ልጆች «ምድሪቱን ተቀመጡባት የኋለኛይቱም (ሰዓት) ቀጠሮ በመጣ ጊዜ እናንተን የተከማቻችሁ ስትኾኑ እናመጣችኋለን» አልናቸው፡፡

(ቁርኣንን) በውነትም አወረድነው፡፡ በእውነትም ወረደ፡፡ አንተንም አብሳሪና አስጠንቃቂ አድርገን እንጂ አልላክንህም፡፡

ቁርኣንንም በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ኾነህ ታነበው ዘንድ ከፋፈልነው፡፡ ቀስ በቀስ ማውረድንም አወረድነው፡፡

«በእርሱ እመኑ ወይም አትመኑ» በላቸው፤ እነዚያ ከእርሱ በፊት ዕውቀትን የተሰጡት በእነሱ ላይ በተነበበ ጊዜ ሰጋጆች ኾነው በሸንጎበቶቻቸው ላይ ይወድቃሉ፤

ይላሉም «ጌታችን ጥራት ይገባው! እነሆ የጌታችን ተስፋ ተፈጻሚ ነው፡፡»

እያለቀሱም በሸንጎበቶቻቸው ላይ ይወድቃሉ (አላህን) መፍራትንም ይጨምራላቸዋል፡፡

«አላህን ጥሩ፤ ወይም አልረሕማንን ጥሩ፤ (ከሁለቱ) ማንኛውንም ብትጠሩ (መልካም ነው)፡፡ ለእርሱ መልካም ስሞች አሉትና» በላቸው፡፡ በስግደትህም (ስታነብ) አትጩህ፡፡ በእርሷም ድምጽህን ዝቅ አታድርግ በዚህም መካከል መንገድን ፈልግ፡፡

«ምስጋና ለአላህ ለዚያ ልጅን ላልያዘው፣ ለእርሱም በንግሥናው ተጋሪ ለሌለው፣ ለእርሱም ከውርደት ረዳት ለሌለው ይገባው በልም፡፡ ማክበርንም አክብረው፡፡»
Icon