ترجمة معاني سورة الأنعام باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation
ﰡ
آية رقم 1
ምስጋና ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው ጨለማዎችንና ብርሃንንም ላደረገው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ ከዚያም እነዚያ የካዱት (ጣዖታትን በጌታቸው) ያስተካክላሉ፡፡
آية رقم 2
እርሱ ያ ከጭቃ የፈጠራችሁ ከዚያም (የሞት) ጊዜን የወሰነ ነው፡፡ እርሱም ዘንድ (ለትንሣኤ) የተወሰነ ጊዜ አልለ፡፡ ከዚያም እናንተ (በመቀስቀሳችሁ) ትጠራጠራላችሁ፡፡
آية رقم 3
እርሱም ያ በሰማያትና በምድር (ሊግገዙት የሚገባው) አላህ ነው፡፡ ምስጢራችሁን ግልጻችሁንም ያውቃል፡፡ የምትሠሩትንም ሁሉ ያውቃል፡፡
آية رقم 4
ከጌታቸውም አንቀጾች አንዲትም አንቀጽ አትመጣቸውም ከርሷ የሚሸሹ ቢኾኑ እንጅ፡፡
آية رقم 5
በእውነቱም (ቁርኣን) በመጣላቸው ጊዜ በእርግጥ አስተባበሉ፡፡ በእርሱም ይሳለቁበት የነበሩት ነገር ዜናዎች (ቅጣት) በእርግጥ ይመጣባቸዋል፡፡
آية رقم 6
ከበፊታቸው ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን ማጥፋታችንን አላዩምን ለእናንተ ያላስመቸነውን (ለእነርሱ) በምድር ውስጥ አስመቸናቸው፡፡ በእነርሱም ላይ ዝናምን የተከታተለ ሲኾን ላክን፡፡ ወንዞችንም በሥራቸው እንዲፈሱ አደረግን፡፡ በኃጢአቶቻቸውም አጠፋናቸው፡፡ ከኋላቸውም ሌሎችን የክፍለ ዘመን ሰዎች አስገኘን፡፡
آية رقم 7
ባንተም ላይ በወረቀት የተጻፈን መጽሐፍ ባወረድንና በእጆቻቸው በነኩት ኖሮ እነዚያ የካዱት ሰዎች «ይህ ግልጽ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም» ባሉ ነበር፡፡
آية رقم 8
«በእርሱም (በሙሐመድ) ላይ መልአክ አይወረድለትም ኖሮአልን» አሉ፡፡ መልአክን ባወረድንም ኖሮ (ባያምኑ በጥፋታቸው) ነገሩ በተፈረደ ነበር፡፡ ከዚያም አይቆዩም ነበር፡፡
آية رقم 9
(መልክተኛውን) መልአክም ባደረግነው ኖሮ ወንድ (በሰው ምስል) ባደረግነው ነበር፡፡ በእነርሱም ላይ የሚያመሳስሉትን ነገር ባመሳሰልንባቸው ነበር፡፡
آية رقم 10
ካንተ በፊትም በመልክተኞች በእርግጥ ተላግጧል፡፡ በእነዚያም ከእነሱ ባላገጡት ላይ በእርሱ ያላግጡ የነበሩት ነገር (ቅጣት) ወረደባቸው፡፡
آية رقم 11
«በምድር ላይ ኺዱ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ» በላቸው፡፡
آية رقم 12
«በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የማን ነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «የአላህ ነው» በል፡፡ «በነፍሱ ላይ እዝነትን ጻፈ፡፡ በትንሣኤ ቀን በእርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲኾን በእርግጥ ይሰበስባችኋል፡፡ እነዚያ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩ ናቸው፤ እነርሱም አያምኑም፡፡
آية رقم 13
በሌሊትና በቀንም ጸጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂ ነው፡፡»
آية رقم 14
«ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ከኾነው አላህ እርሱ የሚመግብ የማይመገብም ሲኾን ሌላን አምላክ እይዛለሁን» በላቸው፡፡ «እኔ መጀመሪያ ትእዛዝን ከተቀበለ ሰው ልኾን ታዘዝኩ፡፡ ከአጋሪዎችም ፈጽሞ አትኹን (ተብያለሁ)» በላቸው፡፡
آية رقم 15
«እኔ በጌታዬ ባምጽ የታላቁን ቀን ቅጣት እፈራለሁ» በላቸው፡፡
آية رقم 16
በዚያ ቀን ከእርሱ ላይ (ቅጣት) የሚመለስለት ሰው (አላህ) በእርግጥ አዘነለት፡፡ ይህም ግልጽ ማግኘት ነው፡፡
آية رقم 17
አላህም በጉዳት ቢነካህ ለእርሱ (ለጉዳቱ) ከእርሱ በቀር ሌላ አስወጋጅ የለም፡፡ በበጎም ነገር ቢነካህ እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
آية رقم 18
እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን አሸናፊ ነው፡፡ እርሱም ጥበበኛው ውስጥ ዐዋቂው ነው፡፡
آية رقم 19
«በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «አላህ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፡፡ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላችሁን» በላቸው፡፡ «እኔ አልመሰክርም» በላቸው፡፡ «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡
آية رقم 20
እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ እነዚያ ከእነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡
آية رقم 21
በአላህም ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ወይም በአንቀጾቹ ካስተባበለ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው እነሆ በደለኞች አይድኑም፡፡
آية رقم 22
ሁላቸውንም የምንሰበስብበትንና ከዚያም ለእነዚያ (ጣዖታትን) ለአጋሩት እነዚያ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው ብላችሁ ታስቧቸው የነበራችሁት ተጋሪዎቻችሁ የት ናቸው የምንልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡
آية رقم 23
ከዚያም መልሳቸው «በጌታችን በአላህ ይኹንብን አጋሪዎች አልነበርንም» ማለት እንጅ ሌላ አትኾንም፡፡
آية رقم 24
በነፍሳቸው ላይ እንዴት እንደ ዋሹና ይቀጣጥፉት የነበሩት ነገር ከእነሱ እንዴት እንደ ተሰወረ ተመልከት፡፡
آية رقم 25
ከእነርሱም ወደ አንተ የሚያዳምጥ ሰው አልለ፡፡ በልቦቻቸውም ላይ እንዳያውቁት ሺፋኖችን በጆሮዎቻቸውም ላይ ድንቁርናን አደረግን፡፡ ተዓምርንም ሁሉ ቢያዩ በርሷ አያምኑም፡፡ በመጡህም ጊዜ የሚከራከሩህ ሲኾኑ እነዚያ የካዱት «ይህ (ቁርኣን) የቀድሞዎቹ ሰዎች ጽሑፍ ተረቶች እንጅ ሌላ አይደለም» ይላሉ፡፡
آية رقم 26
እነርሱም (ሰዎችን) ከእርሱ ይከለክላሉ፡፡ ከእርሱም ይርቃሉ፡፡ ነፍሶቻቸውንም እንጂ ሌላን አያጠፉም፤ ግን አያውቁም፡፡
آية رقم 27
በእሳትም ላይ በተቆሙ ጊዜ ምነው (ወደ ምድረ ዓለም) በተመለስን በጌታችንም አንቀጾች ባላስተባበልን ከምእምናንም በኾንን ዋ ምኞታችን! ባሉ ጊዜ ብታይ ኖሮ (የሚያሰደነግጥን ነገር ባየህ ነበር)፡፡
آية رقم 28
ይልቁንም ከዚህ በፊት ይደብቁት የነበሩት ሁሉ ለእነርሱ ተገለጸ፡፡ (ወደምድረ ዓለም) በተመለሱም ኖሮ ከእርሱ ወደ ተከለከሉት ነገር በተመለሱ ነበር፡፡ እነሱም በእርግጥ ውሸታሞች ናቸው፡፡
آية رقم 29
እርሷም (ሕይወት) «የቅርቢቱ ሕይወታችን እንጅ ሌላ አይደለችም እኛም ተቀስቀቃሾች አይደለንም» አሉ፡፡
آية رقم 30
በጌታቸውም ላይ (ለምርመራ) በተቆሙ ጊዜ ብታይ ኖሮ (አስደንጋጭን ነገር ባየህ ነበር)፡፡ «ይህ እውነት አይደለምን» ይላቸዋል፡፡ «በጌታችን ይኹንብን እውነት ነው» ይላሉ፡፡ «ትክዱት በነበራችሁት ምክንያት ቅጣቱን ቅመሱ» ይላቸዋል፡፡
آية رقم 31
እነዚያ በአላህ መገናኘት ያስተባበሉ በእርግጥ ከሰሩ፡፡ ሰዓቲቱም በድንገት በመጣቻቸው ጊዜ እነሱ ኃጢኣቶቻቸውን በጀርባዎቻቸው ላይ የሚሸከሙ ሲኾኑ «በርሷ (በምድረ ዓለም) ባጓደልነው ነገር ላይ ዋ ቁጪታችን» ይላሉ፡፡ ንቁ! የሚሸከሙት ነገር ከፋ፡፡
آية رقم 32
የቅርቢቱም ሕይወት ጨዋታና ላግጣ እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡ የመጨረሻይቱም አገር (ገነት) ለእነዚያ ለሚጠነቀቁት በጣም በላጭ ናት፡፡ አታውቁምን
آية رقم 33
እነሆ ያ የሚሉህ ነገር እንደሚያሳዝንህ በእርግጥ እናውቃለን፡፡ እነርሱም (በልቦቻቸው) አያስተባብሉህም፡፡ ግን በዳዮቹ በአላህ አንቀጾች ይክዳሉ፡፡
آية رقم 34
ከበፊትህም መልክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉበትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡ የአላህንም ንግግሮች ለዋጭ የለም፡፡ ከመልክተኞቹም ወሬ (የምትረጋጋበት) በእርግጥ መጣልህ፡፡
آية رقم 35
(ኢስላምን) መተዋቸውም ባንተ ላይ ከባድ ቢኾንብህ በምድር ውስጥ ቀዳዳን ወይም በሰማይ ውስጥ መሰላልን ልትፈልግና በተአምር ልትመጣቸው ብትችል (አድርግ)፡፡ አላህም በሻ ኖሮ በቅኑ መንገድ ላይ በሰበሳባቸው ነበር፡፡ ከተሳሳቱትም ሰዎች በፍጹም አትኹን፡፡
آية رقم 36
ጥሪህን የሚቀበሉት እነዚያ የሚሰሙት ብቻ ናቸው፡፡ ሙታንንም አላህ ይቀሰቅሳቸዋል፡፡ ከዚያም ወደርሱ ብቻ ይመለሳሉ፡፡
آية رقم 37
«ከጌታውም በእርሱ ላይ ለምን ተዓምር አልተወረደም» አሉ፡፡ «አላህ ተአምርን በማውረድ ላይ ቻይ ነው» በላቸው፡፡ ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡
آية رقم 38
ከተንቀሳቃሽም በምድር (የሚኼድ)፤ በሁለት ክንፎቹ የሚበርም በራሪ መሰሎቻችሁ ሕዝቦች እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ምንንም ነገር አልተውንም ከዚያም ወደ ጌታቸው ይሰበሰባሉ፡፡
آية رقم 39
እነዚያም በአንቀጾቻችን ያስዋሹ ደንቆሮች ድዳዎችም በጨለማዎች ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ አላህ ማጥመሙን የሚሻውን ሰው ያጠመዋል፡፡ መምራቱን የሚሻውንም ሰው በቀጥተኛ መንገድ ላይ ያደርገዋል፡፡
آية رقم 40
የአላህ ቅጣት ቢመጣባችሁ ወይም ሰዓቲቱ (ትንሣኤ) ብትመጣባችሁ ከአላህ ሌላን ትጠራላችሁን እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ንገሩኝ በላቸው፡፡
آية رقم 41
አይደለም እርሱን ብቻ ትጠራላችሁ፡፡ ቢሻም ወደርሱ የምትጠሩበትን ነገር ያስወግዳል፡፡ የምታጋሩትንም ነገር ትተዋላችሁ (በላቸው)፡፡
آية رقم 42
ከበፊትህም ወደ ነበሩት ሕዝቦች (መልክተኞችን) በእርግጥ ላክን፡፡ እንዲዋደቁም በድህነትና በበሽታ ያዝናቸው፡፡
آية رقم 43
ታዲያ ቅጣታችን በመጣባቸው ጊዜ አይዋደቁም ኖሯልን ግን ልቦቻቸው ደረቁ፡፡ ይሠሩት የነበሩትንም ነገር ሰይጣን ለነሱ አሳመረላቸው፡፡
آية رقم 44
በርሱም ይገሰጹበት የነበረውን ነገር በተው ጊዜ በእነሱ ላይ የነገርን ሁሉ ደጃፎች ከፈትን (አስመቸናቸው)፡፡ በተሰጡትም ነገር በተደሰቱ ጊዜ በድንገት ያዝናቸው፡፡ ወዲያውኑም እነርሱ ተስፋ ቆራጮች ኾኑ፡፡
آية رقم 45
የእነዚያም የበደሉት ሕዝቦች መጨረሻ ተቆረጠ፡፡ ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይገባው፡፡
آية رقم 46
ንገሩኝ አላህ መስሚያችሁንና ማያዎቻችሁን ቢወስድ በልቦቻችሁም ላይ ቢያትም ከአላህ ሌላ እሱን የሚያመጣላችሁ አምላክ ማነው በላቸው፡፡ አንቀጾችን እንዴት እንደምናብራራ ከዚያም እነሱ እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት፡፡
آية رقم 47
«ንገሩኝ የአላህ ቅጣት በድንገት ወይም በግልጽ ቢመጣባችሁ አመጠኞች ሕዝቦች እንጅ ሌላ ይጠፋልን» በላቸው፡፡
آية رقم 48
መልክተኞችንም አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን እንጅ አንልክም፡፡ ያመኑና መልካምን የሠሩ ሰዎችም በእነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም፡፡
آية رقم 49
እነዚያም ባንቀጾቻችን ያስዋሹ ያምጹ በነበሩት ምክንያት ቅጣቱ ያገኛቸዋል፡፡
آية رقم 50
«ለእናንተ የአላህ ግምጃ ቤቶች እኔ ዘንድ ናቸው አልልም፡፡ ሩቅንም አላውቅም፡፡ ለእናንተም እኔ መልአክ ነኝ አልልም፡፡ ወደእኔ የሚወርድልኝን እንጅ ሌላን አልከተልም» በላቸው፡፡ «ዕውርና የሚያይ ይስተካከላሉን አታስተነትኑምን» በላቸው፡፡
آية رقم 51
እነዚያንም ከእርሱ ሌላ ረዳትና አማላጅ የሌላቸው ሲኾኑ ወደ ጌታቸው መስሰብሰብን የሚፈሩትን ይጠነቀቁ ዘንድ በርሱ (በቁርኣን) አስፈራራ፡፡
آية رقم 52
እነዚያን ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ የሚጠሩትን አታባር፡፡ ታባርራቸውና ከበደለኞችም ትኾን ዘንድ እነሱን መቆጣጠር ባንተ ላይ ምንም የለብህም፡፡ አንተንም መቆጣጠር በነሱ ላይ ምንም የለባቸውም፡፡
آية رقم 53
እንደዚሁም «ከመካከላችን አላህ የለገሰላቸው እነዚህ ናቸውን» ይሉ ዘንድ ከፊላቸውን በከፊሉ ሞከርን፡፡ አላህ አመስጋኞቹን ዐዋቂ አይደለምን
آية رقم 54
እነዚያም በተአምራታችን የሚያምኑት (ወደ አንተ) በመጡ ጊዜ «ሰላም በእናንተ ላይ ይኹን፡፡ ጌታችሁ በነፍሱ ላይ እዝነትን ጻፈ፡፡ እነሆ ከእናንተ ውስጥ በስሕተት ክፉን ሥራ የሠራ ሰው ከዚያም ከእርሱ በኋላ የተጸጸተና ሥራውን ያሳመረ እርሱ (አላህ) መሓሪ አዛኝ ነው» በላቸው፡፡
آية رقم 55
ﭿﮀﮁﮂﮃﮄ
ﮅ
እንደዚሁም (እውነቱ እንዲገለጽና) የወንጀለኞችም መንገድ ትብራራ ዘንድ አንቀጾችን እንገልጻለን፡፡
آية رقم 56
«እኔ እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትጠሩዋቸውን ከመገዛት ተከልክያለሁ» በላቸው፡፡ «ዝንባሌያችሁን አልከተልም፡፡ ያን ጊዜ በእርግጥ ተሳሳትኩ፡፡ እኔም ከተመሪዎቹ አይደለሁም» በላቸው፡፡
آية رقم 57
«እኔ ከጌታዬ በኾነች ግልጽ ማስረጃ ላይ ነኝ፡፡ በእርሱም አስተባበላችሁ፡፡ በርሱ የምትቻኮሉበት ቅጣት እኔ ዘንድ አይደለም፡፡ ፍርዱ ለአላህ ብቻ ነው፡፡ እውነትን ይፈርዳል፡፡ እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው» በላቸው፡፡
آية رقم 58
«በእርሱ የምትቻኮሉበት ቅጣት እኔ ዘንድ በኾነ ኖሮ በእኔና በእናንተ መካከል ነገሩ (ቅጣታችሁ) በተፈጸመ ነበር፡፡ አላህም በደለኞችን ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡
آية رقم 59
የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ፡፡ ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውሰጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ፡፡
آية رقم 60
እርሱም ያ በሌሊት የሚያስተኛችሁ በቀንም የሠራችሁትን ሁሉ የሚያውቅ ከዚያም የተወሰነው ጊዜ ይፈፀም ዘንድ በእርሱ (በቀን) ውስጥ የሚቀሰቅሳችሁ ነው፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደ እርሱ ነው፡፡ ከዚያም ትሠሩት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡
آية رقم 61
እርሱም ከባሮቹ በላይ ሲኾን ሁሉን አሸነፊ ነው፡፡ በናንተም ላይ ጠባቂዎችን (መላእክት) ይልካል፡፡ አንዳችሁንም ሞት በመጣበት ጊዜ (የሞት) መልእክተኞቻችን እነርሱ (ትእዛዛትን) የማያጓድሉ ሲኾኑ ይገድሉታል፡፡
آية رقم 62
ከዚያም እውነተኛ ወደ ኾነው ጌታቸው ወደ አላህ ይመለሳሉ፡፡ ንቁ! ፍርዱ ለእርሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ከተቆጣጣሪዎች ሁሉ ይበልጥ ፈጣን ነው፡፡
آية رقم 63
ከየብስና ከባሕር ጨለማዎች በግልጽና በምስጢር የምትጠሩት ስትኾኑ «ከነዚህ ቢያድነን በእርግጥ ከአመስጋኞች እንኾናለን (ስትሉ) የሚያድናችሁ ማነው» በላቸው፡፡
آية رقم 64
አላህ ከሷና ከጭንቅም ሁሉ ያድናችኋል፡፡ ከዚያም እናንተ ታጋራላችሁ በላቸው፡፡
آية رقم 65
«እርሱ (አላህ) ከበላያችሁ ወይም ከእግሮቻችሁ በታች ቅጣትን በእናንተ ላይ ሊልክ ወይም የተለያዩ ሕዝቦች ስትኾኑ ሊያደባልቃችሁና ከፊላችሁን የከፊሉን ጭካኔ ሊያቀምስ ቻይ ነው» በላቸው፡፡ ያውቁ ዘንድ አንቀጾችን እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት፡፡
آية رقم 66
በእርሱም (በቁርኣን) እሱ እውነት ሲኾን ሕዝቦችህ አስተባበሉ፡፡ በላቸው፡- «በናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም፡፡»
آية رقم 67
ﯰﯱﯲﯳﯴﯵ
ﯶ
ለትንቢት ሁሉ (የሚደርስበት) መርጊያ አለው፡፡ ወደፊትም ታውቁታላችሁ፡፡
آية رقم 68
እነዚያንም በአንቀጾቻችን የሚገቡትን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ሌላ በኾነ ወሬ እስከሚገቡ ድረስ ተዋቸው፡፡ ሰይጣንም (መከልከልህን) ቢያስረሳህ ከትውስታ በኋላ ከበደለኞች ሕዝቦች ጋር አትቀመጥ፡፡
آية رقم 69
በእነዚያም በሚጠነቀቁት ላይ ከሒሳባቸው ምንም የለባቸውም፡፡ ግን ይጠነቀቁ ዘንድ መገሰጽ (አለባቸው)፡፡
آية رقم 70
እነዚያንም ሃይማኖታቸውን ጨዋታና ላግጣ አድርገው የያዙትን ቅርቢቱም ሕይወት ያታለለቻቸውን ተዋቸው፡፡ በእርሱም (በቁርኣን) ነፍስ በሠራችው ሥራ እንዳትጠፋ አስታውስ፡፡ ለእርሷ ከአላህ ሌላ ረዳትና አማላጅ የላትም፡፡ በመበዢያም ሁሉ ብትበዥ ከርሷ አይወሰድም፡፡ እነዚህ እነዚያ በሠሩት ሥራ የተጠፉት ናቸው፡፡ ለነሱ ይክዱ በነበሩት ምክንያት ከፈላ ውሃ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡
آية رقم 71
«ከአላህ ሌላ የማይጠቅመንን እና የማይጎዳንን እንገዛለን አላህም ከመራን ጊዜ በኋላ የኋሊት እንመለሳለን እንደዚያ በምድር ላይ የዋለለ ሲኾን ሰይጣናት እንዳሳሳቱት ለእርሱ ወደኛ ና እያሉ ወደ ቅን መንገድ የሚጠሩ ወዳጆች እንዳሉት (እንደማይከተላቸውም) ሰው እንኾናለን» በላቸው፡፡ «የአላህ መንገድ እርሱ ቀጥተኛው መንገድ ነው፡፡ ለዓለማት ጌታ ልንገዛም ታዘዝን» በላቸው፡፡
آية رقم 72
ሶላትንም በደንቡ ስገዱ ፍሩትም፤ (በማለት ታዘዝን)፡፡ እርሱም ያ ወደርሱ ብቻ የምትሰበሰቡበት ነው፡፡
آية رقم 73
እርሱም ያ ሰማያትንና ምድርን በእውነት የፈጠረ ነው፡፡ «ኹን» የሚልበትንና ወዲያውም የሚኾንበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ ቃሉ እውነት ነው፡፡ በቀንዱም በሚነፋ ቀን ንግሥናው የርሱ ብቻ ነው፡፡ ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ጥበበኛው ውስጥ ዐዋቂው ነው፡፡
آية رقم 74
ኢብራሒምም ለአባቱ ለአዘር «ጣዖታትን አማልክት አድርገህ ትይዛለህን እኔ፤ አንተንም ሕዝቦችህንም በግልጽ መሳሳት ውስጥ ኾናችሁ አያችኋለሁ» ባለ ጊዜ (አስታውስ)
آية رقم 75
እንደዚሁም ኢብራሂምን (እንዲያውቅና) ከአረጋጋጮቹም ይኾን ዘንድ የሰማያትንና የምድርን መለኮት አሳየነው፡፡
آية رقم 76
ሌሊቱም በእርሱ ላይ ባጨለመ ጊዜ ኮከብን አየ፡፡ «ይህ ጌታዬ ነው» አለ፡፡ በጠለቀም ጊዜ፡- «ጠላቂዎችን አልወድም» አለ፡፡
آية رقم 77
ጨረቃንም ወጪ ኾኖ ባየ ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው» አለ፡፡ በገባም ጊዜ፡- «ጌታዬ (ቅኑን መንገድ) ባይመራኝ በእርግጥ ከተሳሳቱት ሕዝቦች እኾናለሁ» አለ፡፡
آية رقم 78
ፀሐይንም ጮራዋን ዘርግታ ባየ ጊዜ፡- «ይህ ጌታዬ ነው፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ነው» አለ፡፡ በገባችም ጊዜ፡- «ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩት ሁሉ ንጹሕ ነኝ» አለ፡፡
آية رقم 79
«እኔ ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው (አምላክ) ቀጥተኛ ስኾን ፊቴን አዞርኩ፡፡ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም» (አለ)፡፡
آية رقم 80
ወገኖቹም ተከራከሩት፡፡ «በአላህ (አንድነት) በእርግጥ የመራኝ ሲኾን ትከራከሩኛላችሁን በእርሱም የምታጋሩትን ነገር አልፈራም፡፡ ግን ጌታዬ ነገርን ቢሻ (ያገኘኛል)፡፡ ጌታዬም ነገሩን ሁሉ ዕውቀቱ ሰፋ፡፡ አትገነዘቡምን» አላቸው፡፡
آية رقم 81
«በእናንተ ላይ በእርሱ ማስረጃን ያላወረደበትን እናንተ ማጋራታችሁን የማትፈሩ ስትኾኑ የምታጋሩትን (ጣዖታት) እንዴት እፈራለሁ! የምታውቁም ብትኾኑ ከሁለቱ ክፍሎች በጸጥታ ይበልጥ ተገቢው ማንኛው ነው» (አለ)፡፡
آية رقم 82
እነዚያ ያመኑና እምነታቸውን በበደል ያልቀላቀሉ እነዚያ ለእነርሱ ጸጥታ አላቸው፡፡ እነሱም የተመሩ ናቸው፤
آية رقم 83
ይህችም ማስረጃችን ናት፡፡ ለኢብራሂም በሕዝቦቹ ላይ (አስረጅ እንድትኾን) ሰጠናት፡፡ የምንሻውን ሰው በደረጃዎች ከፍ እናደርጋለን፡፡ ጌታህ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
آية رقم 84
ለርሱም ኢስሐቅን (የልጅ ልጁን) ያዕቁብንም ሰጠነው፡፡ ሁሉንም መራን፡፡ ኑሕንም በፊት መራን፡፡ ከዘሮቹም ዳውድን፣ ሱለይማንንም፣ አዩብንም፣ ዩሱፍንም፣ ሙሳንም፣ ሃሩንንም (መራን)፡፡ እንደዚሁም በጎ ሰሪዎችን እንመነዳለን፡፡
آية رقم 85
ዘከሪያንም፣ የሕያንም፣ ዒሳንም፣ ኢልያስንም (መራን)፡፡ ሁሉም ከመልካሞቹ ናቸው፡፡
آية رقم 86
ኢስማዒልንም፣ አልየስዕንም፣ ዩኑስንም፣ ሉጥንም (መራን)፡፡ ሁሉንም በዓለማት ላይ አበለጥናቸውም፡፡
آية رقم 87
ከአባቶቻቸውም፣ ከዘሮቻቸውም፣ ከወንድሞቻቸውም (መራን)፡፡ መረጥናቸውም፤ ወደ ቀጥታውም መንገድ መራናቸው፡፡
آية رقم 88
ይህ የአላህ መምሪያ ነው፡፡ በእርሱ ከባሮቹ የሚሻውን ሰው ይመራል፡፡ ባጋሩም ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነሱ በታበሰ ነበር፡፡
آية رقم 89
እነዚህ እነዚያ መጻሕፍትንና ጥበብን፣ ነቢይነትንም የሰጠናቸው ናቸው፡፡ እነዚህ (የመካ ከሓዲዎች) በእርሷ ቢክዱም በእርሷ የማይክዱን ሕዝቦች ለእርሷ በእርግጥ አዘጋጅተናል፡፡
آية رقم 90
እነዚህ (ነቢያት)፤ እነዚያ አላህ የመራቸው ናቸው፡፡ በመንገዳቸውም ተከተል፡፡ «በእርሱ (በቁርአን) ላይ ምንም ዋጋ አልጠይቃችሁም፡፡ እርሱ ለዓለማት ግሣጼ እንጅ ሌላ አይደለም» በላቸው፡፡
آية رقم 91
«አላህ በሰው ላይ ምንም አላወረደም» ባሉም ጊዜ አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡ (እንዲህ) በላቸው፡- «ያንን ብርሃንና ለሰዎች መሪ ኾኖ ሙሳ ያመጣውን መጽሐፍ ክፍልፍሎች የምታደርጉት ስትኾኑ ማን አወረደው (የወደዳችኋትን) ትገልጿታላችሁ ብዙውንም ትደብቃላችሁ፡፡ እናንተም አባቶቻችሁም ያላወቃችሁትን ተስተማራችሁ፤»
آية رقم 92
«አላህ (አወረደው)» በላቸው፡፡ ከዚያም በውሸታቸው ውስጥ የሚጫወቱ ሲኾኑ ተዋቸው፡፡ ይህም ያወረድነው የኾነ ብሩክ ያንንም በፊቱ የነበረውን (መጽሐፍ) አረጋጋጭ መጽሐፍ ነው፡፡ የከተሞችን እናት (መካን) እና በዙሪያዋ ያሉትንም ሰዎች ልታስጠነቅቅበት (አወረድነው)፡፡ እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የሚያምኑት እነርሱ በሶላታቸው ላይ የሚጠባበቁ ሲኾኑ በርሱ ያምናሉ፡፡
በአላህም ላይ እብለትን ከቀጣጠፈ ወይም ወደርሱ ምንም ያልተወረደለት ሲኾን «ወደኔ ተወረደልኝ» ካለና፡-«አላህም ያወረደውን ብጤ በእርግጥ አወርዳለሁ» ካለ ሰው ይበልጥ በዳይ ማን ነው በደለኞችንም በሞት መከራዎች ውስጥ በኾኑ ጊዜ መላእክት እጆቻቸውን ዘርጊዎች ኾነው « (ለቅጥጥብ) ነፍሶቻችሁን አውጡ፤ በአላህ ላይ እውነት ያልኾነን ነገር ትናገሩ በነበራችሁትና ከአንቀጾቹም ትኮሩ በነበራችሁት ምክንያት ዛሬ የውርደትን ቅጣት ትመነዳላችሁ» (የሚሏቸው ሲኾኑ) ብታይ ኖሮ (አስደናቂን ነገር ባየህ ነበር)፡፡
آية رقم 94
መጀመሪያም ጊዜ እንደ ፈጠርናችሁ ኾናችሁ የሰጠናችሁን ሁሉ በጀርባዎቻችሁ ኋላ የተዋችሁ ስትኾኑ የሰጠናችሁን ሁሉ በጀርባዎቻችሁ ኋላ የተዋችሁ ስትኾኑ ለየብቻችሁ ኾናችሁ በእርግጥ መጣችሁን እነዚያንም እነሱ በእናንተ ውስጥ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው የምትሉዋቸውን አማላጆቻችሁን ከእናንተ ጋር አናይም፡፡ ግንኙነታችሁ በእርግጥ ተቋረጠ፡፡ ከእናንተም ያ (ያማልደናል) የምትሉት ጠፋ (ይባላሉ)፡፡
آية رقم 95
አላህ ቅንጣትንና የፍሬን አጥንት ፈልቃቂ ነው፡፡ ሕያውን ከሙት ያወጣል፤ ሙትንም ከሕያው አውጪ ነው፡፡ እርሱ አላህ ነው፤ ታዲያ (ከእምነት) እንዴት ትመለሳላችሁ (ትርቃላችሁ)
آية رقم 96
እርሱም ጎህን (ከሌሊት ጨለማ) ፈልቃቂ ሌሊትንም ማረፊያ ፀሐይንና ጨረቃንም (ለጊዜ) መቁጠሪያ አድራጊ ነው፡፡ ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው (አላህ) ችሎታ ነው፡፡
آية رقم 97
እርሱም ያ ከዋክብትን በየብስና በባሕር ጨለማዎች ውስጥ በእርሷ ትመሩ ዘንድ ለእናንተ ያደረገ ነው፡፡ ለሚያውቁ ሕዝቦች አንቀጾችን በእርግጥ ዘረዘርን፡፡
آية رقم 98
እርሱም ያ ከአንዲት ነፍስ ያስገኛችሁ፤ ነው፡፡ (በማሕፀን) መርጊያና (በጀርባ) መቀመጫም (አላችሁ)፡፡ ለሚያወቁ ሕዝቦች አንቀጾችን በእርግጥ ዘረዘርን፡፡
آية رقم 99
እርሱም ያ ከሰማይ ውሃን ያወረደ ነው፡፡ በርሱም የነገሩን ሁሉ በቃይ አወጣን፡፡ የተደራረበንም ቅንጣት ከርሱ የምናወጣ የኾነን ለምለም (አዝመራ) ከርሱ አወጣን፡፡ ከዘንባባም ከእንቡጧ የተቀራረቡ የኾኑ ዘለላዎች አሉ፡፡ ከወይኖችም፣ ከወይራም፣ ከሩማንም (ቅጠላቸው) ተመሳሳይና (ፍሬያቸው) የማይመሳሰል ሲኾኑ አትክልቶችን (አወጣን)፡፡ ባፈራ ጊዜ ወደ ፍሬውና ወደ መብሰሉ ተመልከቱ፡፡ በእነዚህ ተዓምራት ለሚያምኑ ሕዝቦች ምልክቶች አሉ፡፡
آية رقم 100
ለአላህም አጋንንትን የፈጠራቸው ሲኾን (በመታዘዝ) ተጋሪዎች አደረጉ፡፡ ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችንም ያለ ዕውቀት ለእርሱ ቀጠፉ፡፡ (አላህ) ጥራት የተገባው ከሚሉት ነገር የላቀ ነው፡፡
آية رقم 101
(እርሱ) ሰማያትንና ምድርን ያለ ብጤ ፈጣሪ ነው፡፡ ለእርሱ ሚስት የሌለችው ሲኾን እንዴት ለእርሱ ልጅ ይኖረዋል ነገርንም ሁሉ ፈጠረ፡፡ እርሱም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
آية رقم 102
ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ ስለዚህ ተገዙት፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡
آية رقم 103
ዓይኖች አያገኙትም፤ (አያዩትም)፡፡ እርሱም ዓይኖችን ያያል፡፡ እርሱም ርኅራኄው ረቂቁ ውስጠ ዐዋቂው ነው፡፡
آية رقم 104
«ከጌታችሁ ዘንድ ብርሃኖች በእርግጥ መጡላችሁ፡፡ የተመለከተም ሰው (ጥቅሙ) ለነፍሱ ብቻ ነው፡፡ የታወረም ሰው (ጉዳቱ) በራሱ ላይ ብቻ ነው፡፡ እኔም በእናንተ ላይ ጠባቂ አይደለሁም» (በላቸው)፡፡
آية رقم 105
እንደዚሁም « (እንዲገመግሙና ያለፉትን መጻሕፍት) አጥንተሃልም» እንዲሉ ለሚያውቁ ሕዝቦችም (ቁርኣንን) እንድናብራራው አንቀጾችን እንገልጻለን፡፡
آية رقم 106
ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን ተከተል፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ አጋሪዎችንም ተዋቸው፡፡
آية رقم 107
አላህም በሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር፡፡ በእነሱም ላይ ጠባቂ አላደረግንህም፡፡ አንተም በእነሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም፡፡
آية رقم 108
እነዚያንም ከአላህ ሌላ የሚገዙዋቸውን (ጣዖታትን) አትስደቡ፡፡ ድንበርን በማለፍ ያለዕውቀት አላህን ይሰድባሉና፡፡ እንደዚሁ ለሕዝቦች ሁሉ ሥራቸውን ደግ አስመሰልንላቸው፡፡ ከዚያም መመለሻቸው ወደ ጌታቸው ነው፡፡ ይሠሩት የነበሩትንም ሁሉ ይነግራቸዋል፡፡
آية رقم 109
ተዓምርም ብትመጣላቸው በእርሷ በቁርጥ ሊያምኑ ጥብቅ መሐሎቻቸውን በአላህ ማሉ፡፡ «ተዓምራት ሁሉ አላህ ዘንድ ናት» በላቸው፡፡ እርሷ በመጣች ጊዜም አለማመናቸውን (ወይም ማመናቸውን) ምን አሳወቃችሁ
آية رقم 110
በመጀመሪያም ጊዜ በእርሱ እንዳላመኑ ሁሉ ልቦቻቸውንና ዓይኖቻቸውን እናገላብጣለን፡፡ በጥመታቸውም ውስጥ የሚዋልሉ ሲኾኑ እንተዋቸዋለን፡፡
آية رقم 111
እኛም ወደእነርሱ መላእክትን ባወረድን ሙታንም ባነጋገሩዋቸው ነገሩንም ሁሉ ጭፍራ ጭፍራ አድርገን በእነሱ ላይ በሰበሰብን ኖሮ አላህ ካልሻ በስተቀር የሚያምኑ ባልኾኑ ነበር፡፡ ግን አብዛኞቻቸው (ይህንን) ይስታሉ፡፡
آية رقم 112
እንደዚሁም ለነቢያት ሁሉ ከሰውና ከጋኔን የኾኑን ሰይጣናት ጠላት አደረግን፡፡ ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ለማታለል ልብስብስን ቃል ይጥላሉ፡፡ ጌታህም በሻ ኖሮ ባልሠሩት ነበር፡፡ ከቅጥፈታቸውም ጋር ተዋቸው፡፡
آية رقم 113
(የሚጥሉትም ሊያታልሉና) የእነዚያም በመጨረሻይቱ ሕይወት የማያምኑት ሰዎች ልቦች ወደእርሱ እንዲያዘነብሉ እንዲወዱትም እነርሱ ይቀጥፉ የነበሩትንም እንዲቀጣጥፉ ነው፡፡
آية رقم 114
እርሱ ያ መጽሐፉን የተብራራ ኾኖ ወደእናንተ ያወረደ ሲኾን «ከአላህ ሌላ ዳኛን እፈልጋለሁን» (በላቸው)፡፡ እነዚያም መጽሐፍን የሰጠናቸው እርሱ ከጌታህ ዘንድ በእውነት የተወረደ መኾኑን ያውቃሉ፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን፡፡
آية رقم 115
የጌታህም ቃላት እውነተኛና ትክክለኛ ስትኾን ተፈጸመች፡፡ ለቃላቱ ለዋጭ የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ዐዋቂው ነው፡፡
آية رقم 116
በምድርም ካሉት ሰዎች አብዛኞቹን ብትከተል ከአላህ መንገድ ያሳስቱሃል፡፡ ጥርጣሬን እንጅ ሌላን አይከተሉም፡፡ እነርሱም የሚዋሹ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡
آية رقم 117
ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የሚሳሳቱትን ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ተመሪዎቹን ዐዋቂ ነው፡፡
آية رقم 118
በአንቀጾቹም አማኞች እንደ ኾናችሁ (ሲታረድ) የአላህ ስም በእርሱ ላይ ከተወሳበት እንስሳ ብሉ፡፡
آية رقم 119
ወደርሱም (መብላት) ከተገደዳችሁበት በስተቀር በእናንተ ላይ እርም የተደረገውን ለእናንተ (አላህ) በእርግጥ የዘረዘረ ሲኾን ከዚያ በእርሱ ላይ የአላህ ስም ከተጠራበት የማትበሉት ለናንተ ምን (ምክንያት) አላችሁ ብዙዎቹም ያለ ዕውቀት በዝንባሌዎቻቸው ያሳስታሉ፡፡ ጌታህ እርሱ ወሰን አላፊዎቹን ዐዋቂ ነው፡፡
آية رقم 120
የኃጢአትንም ግልጹንም ድብቁንም ተውዉ፡፡ እነዚያ ኃጢአትን የሚሠሩ፤ ይሠሩት በነበሩት ነገር በእርግጥ ይቀጣሉ፡፡
آية رقم 121
በእርሱም ላይ የአላህ ስም ካልተጠራበት ነገር አትብሉ፡፡ እርሱም በእርግጥ አመጽ ነው፡፡ ሰይጣናትም ወደ ወዳጆቻቸው (በክትን በመብላት) ይከራከሯችሁ ዘንድ ያሾከሹካሉ፡፡ ብትታዘዙዋቸውም እናንተ በእርግጥ አጋሪዎች ናችሁ፡፡
آية رقم 122
ሙት የነበረና ሕያው ያደረግነው ለእርሱም በሰዎች መካከል በእርሱ የሚኼድበትን ብርሃን ያደረግንለት ሰው በጨለማዎች ውስጥ ከርሷ የማይወጣ ኾኖ እንዳልለ ሰው ብጤ ነውን እንደዚሁ ለከሓዲዎች ይሠሩት የነበሩት ነገር ተጌጠላቸው፡፡
آية رقم 123
እንደዚሁም በየከተማይቱ በውስጧ ያሴሩ ዘንድ የተንኮለኞችዋን ታላላቆች አደረግን፡፡ በነፍሶቻቸውም ላይ እንጅ በሌላ ላይ አያሴሩም፤ ግን አያውቁም፡፡
آية رقم 124
ተዓምርም በመጣቻቸው ጊዜ፡- «የአላህ መልክተኞች የተሰጡትን ብጤ እስክንሰጥ ድረስ በፍጹም አናምንም» አሉ፡፡ አላህ መልክቱን የሚያደርግበትን ስፍራ ዐዋቂ ነው፡፡ እነዚያን ያመጹትን ሰዎች ይዶልቱ በነበሩት ነገር አላህ ዘንድ ውርደትና ብርቱ ቅጣት ያገኛቸዋል፡፡
آية رقم 125
አላህም ሊመራው የሚሻውን ሰው ደረቱን (ልቡን) ለኢስላም ይከፍትለታል፡፡ ሊያጠመውም የሚሻውን ሰው ደረቱን ጠባብ ቸጋራ ወደ ሰማይ ለመውጣት አንደሚታገል ያደርገዋል፡፡ እንደዚሁ አላህ በእነዚያ በማያምኑት ላይ ርክሰትን ያደርጋል፡፡
آية رقم 126
ይህም (ያለህበት) ቀጥተኛ ሲኾን የጌታህ መንገድ ነው፡፡ ለሚያስታውሱ ሕዝቦች አንቀጾችን በእርግጥ ዘርዝረናል፡፡
آية رقم 127
ለእነርሱ በጌታቸው ዘንድ የሰላም አገር አላቸው፡፡ እርሱም (ጌታህ) ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ረዳታቸው ነው፡፡
آية رقم 128
ሁሉንም የሚሰበስብባቸውንም ቀን (አስታውስ)፡፡፡ የአጋንንት ጭፍሮች ሆይ! ከሰዎች (ጭፍራን በማጥመም) በእርግጥ አበዛችሁ (ይባላሉ)፡፡ ከሰዎችም የኾኑት ወዳጆቻቸው፡-«ጌታችን ሆይ! ከፊላችን በከፊሉ ተጠቀመ፡፡ ያንንም ለእኛ የወሰንክልንን ጊዜያችንን ደረስን» ይላሉ፡፡ እሳት አላህ የሻው ጊዜ ሲቀር በውስጧ ዘውታሪዎች ስትኾኑ መኖሪያችሁ ናት ይላቸዋል፡፡ ጌታህ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
آية رقم 129
እንደዚሁም የበደለኞችን ከፊል በከፊሉ ላይ ይሠሩት በነበሩት ጥፋት ምክንያት እንሾማለን፡፡
آية رقم 130
የጋኔንና የሰዎች ጭፍሮች ሆይ!፡- «አንቀጾቼን በእናንተ ላይ የሚተርኩ የዚህንም ቀናችሁን (ቅጣት) ማግኘትን የሚያስፈራሩዋችሁ ከእናንተው የኾኑ መልክተኞች አልመጧችሁምን» (ይባላሉ)፡፡ «በነፍሶቻችን ላይ መሰከርን፤ (መጥተውልናል)» ይላሉ፡፡ የቅርቢቱም ሕይወት አታለለቻቸው፡፡ በነፍሶቻቸውም ላይ እነርሱ ከሓዲዎች የነበሩ መኾናቸውን መሰከሩ፡፡
آية رقم 131
ይህ ጌታህ ከተሞችን ባለቤቶችዋ ዘንጊዎች ኾነው ሳሉ በበደል ምክንያት አጥፊ ባለመኾኑ ነው፡፡
آية رقم 132
ለሁሉም ከሠሩት ሥራ (የተበላለጡ) ደረጃዎች አልሏቸው፡፡ ጌታህም ከሚሠሩት ሁሉ ዘንጊ አይደለም፡፡
آية رقم 133
ጌታህም ተብቃቂ የእዝነት ባለቤት ነው፡፡ ቢሻ ያስወግዳችኋል፤ (ያጠፋችኋል)፡፡ ከሌሎች ሕዝቦችም ዘሮች እንዳስገኛችሁ ከበኋላችሁ የሚሻውን ይተካል፡፡
آية رقم 134
የምትቀጠሩት ሁሉ በእርግጥ መጪ ነው፡፡ እናንተም አምላጮች አይደላችሁም፡፡
آية رقم 135
«ሕዝቦቼ ሆይ! በችሎታችሁ ላይ ሥሩ፤ እኔ (በችሎታዬ ላይ) ሠሪ ነኝና፡፡ ምስጉኒቱም አገር (ገነት) ለእርሱ የምትኾንለት ሰው ማን እንደኾነ ወደ ፊት ታውቃላችሁ፡፡ እነሆ በደለኞች አይድኑም» በላቸው፡፡
آية رقم 136
ለአላህም ከፈጠረው ከአዝመራና ከግመል፣ ከከብት፣ ከፍየልም ድርሻን አደረጉ፡፡ በሐሳባቸውም «ይህ ለአላህ ነው፡፡ ይህም ለተጋሪዎቻችን ነው፡፡» ለተጋሪዎቻቸውም «(ለጣዖታት) የኾነው ነገር ወደ አላህ አይደርስም፡፡ ለአላህም የኾነው እርሱ ወደ ተጋሪዎቻቸው ይደርሳል» አሉ፡፡ የሚፈርዱት ፍርድ ከፋ!
آية رقم 137
እንደዚሁም ከአጋሪዎቹ ለብዙዎቹ፤ ተጋሪዎቻቸው ሊያጠፉዋቸው ሃይማኖ ታቸውንም በእነሱ ላይ ሊያቀላቅሉባቸው (ሊያመሳስሉባቸው) ልጆቻቸውን መግደልን አሳመሩላቸው፡፡ አላህም በሻ ኖሮ ባልሠሩት ነበር፡፡ ከቅጥፈታቸውም ጋር ተዋቸው፡፡
آية رقم 138
በሐሳባቸውም ይህች እርም የኾነች ለማዳ እንስሳና አዝመራ ናት፡፡ የምንሻው ሰው እንጂ ሌላ አይበላትም፡፡ (ይህች) ጀርቦችዋ እርም የተደረገች ለማዳ እንስሳም ናት (አትጫንም)፡፡ ይህች በርሷ ላይ የአላህን ስም (ስትታረድ) የማይጠሩባትም እንስሳ ናት አሉ፡፡ በእርሱ ላይ ለመቅጠፍ (ነገሩን ወደ አላህ አስጠጉ)፡፡ ይቀጥፉት በነበሩት ነገር በእርግጥ ይቀጣቸዋል፡፡
آية رقم 139
«በነዚህም እንስሶች ሆዶች ውስጥ ያለው ለወንዶቻችን በተለይ የተፈቀደ ነው፡፡ በሚስቶቻችንም ላይ እርም የተደረገ ነው፡፡ ሙትም ቢኾን (ሙት ኾኖ ቢወለድ) እነርሱ (ወንዶቹም ሴቶቹም) በርሱ ተጋሪዎች ናቸው» አሉ፡፡ በመቅጠፋቸው አላህ በእርግጥ ይቀጣቸዋል፡፡ እርሱ ጥበበኛ ዐዋቂ ነውና፡፡
آية رقم 140
እነዚያ ያለ ዕውቀት በሞኝነት ልጆቻቸውን የገደሉና አላህም የሰጣቸውን (ሲሳይ) በአላህ ላይ በመቅጠፍ እርም ያደረጉ በእርግጥ ከሰሩ፡፡ በእርግጥ ተሳሳቱ፡፡ ተመሪዎችም አልነበሩም፡፡
آية رقم 141
እርሱም ያ ዳስ የሚደረግላቸውንና ዳስ የማይደረግላቸውን አትክልቶች የፈጠረ ነው፡፡ ዘምባባንም (የተምርን ዛፍ) አዝመራንም ፍሬዎቹ የተለያዩ ሲኾኑ ወይራንና ሩማንንም (ቅጠላቸው) ተመሳሳይና (ጣዕማቸው) የማይመሳሰል ሲኾኑ (ፈጠረ)፡፡ ባፈራ ጊዜ ከፍሬው ብሉ፡፡ በአጨዳውም ቀን ተገቢውን (ዘካ) ስጡ፡፡ አታባክኑም፡፡ እርሱ አባካኞችን አይወድምና፡፡
آية رقم 142
ከለማዳ እንስሳዎችም የሚጫኑትንና የማይጫኑትን (ፈጠረ)፡፡ አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ብሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡
آية رقم 143
ስምንትን ዓይነቶች ከበግ ሁለትን (ወንድና ሴትን) ከፍየልም ሁለትን (ፈጠረ)፡፡«ከሁለቱም ክፍሎች አላህ ወንዶቹን እርም አደረገን ወይስ ሴቶቹን ወይስ በርሱ ላይ የሁለቱ ሴቶች ማሕፀኖች ያጠቃለሉትን እውነተኞች እንደሆናችሁ በዕውቀት (በአስረጅ) ንገሩኝ» በላቸው፡፡
آية رقم 144
ከግመልም ሁለትን ከከብትም ሁለትን (ፈጠረ)፡፡«አላህ (ከሁለቱ) ወንዶቹን እርም አደረገን ወይስ ሴቶቹን ወይስ የሁለቱ ሴቶች ማሕፀኖች በእርሱ ላይ ያጠቃለሉትን በእውነቱ አላህ በዚህ ባዘዛችሁ ጊዜ የተጣዳችሁ ነበራችሁን ሰዎችንም ያለ ዕውቀት ሊያጠም በአላህ ላይ ውሸትንም ከቀጠፈ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማን ነው አላህ በደለኞችን ሕዝቦች (ቅኑን መንገድ) አይመራም፡፡»
آية رقم 145
(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው፡- «ወደእኔ በተወረደው ውስጥ በክት ወይም ፈሳሽ ደም ወይም የአሳማ ስጋ እርሱ ርኩስ ነውና ወይም በአመጽ ከአላህ ስም ሌላ በእርሱ ላይ የተወሳበት ካልኾነ በስተቀር በሚመገበው ተመጋቢ ላይ እርም የኾነን ነገር አላገኝም፡፡ አመጸኛና ወሰን ያለፈ ሳይኾንም የተገደደ ሰው (ከተወሱት ቢበላ ኃጢአት የለበትም)፡፡ ጌታህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡»
آية رقم 146
በእነዚያም አይሁዳውያን በኾኑት ላይ ባለ ጥፍርን ሁሉ እርም አደረግን፡፡ ከከብት፣ ከፍየልና ከበግም ሞራዎቻቸውን ጀርባዎቻቸው ወይም አንጀቶቻቸው የተሸከሙት ወይም በአጥንት የተቀላቀለው (ስብ) ሲቀር በነርሱ ላይ እርም አደረግን፡፡ ይህንን በአመጻቸው ምክንያት ቀጣናቸው፡፡ እኛ እውነተኞች ነን፡፡
آية رقم 147
ቢያስተባብሉህም፡- «ጌታችሁ የሰፊ ችሮታ ባለቤት ነው፡፡ ብርቱ ቅጣቱም ከአመጸኞች ሕዝቦች ላይ አይመለስም» በላቸው፡፡
آية رقم 148
እነዚያ ያጋሩት «አላህ በሻ ኖሮ እኛም አባቶቻቸንም ባላገራን ነበር፡፡ አንዳችንም ነገር እርም ባላደረግን ነበር ይላሉ፡፡ እንደዚሁ (እነዚህን እንደዋሹ) እነዚያ ከበፊታቸው የነበሩት ብርቱ ቅጣታችንን እስከቀመሱ ድረስ አስተባባሉ፡፡ ለእኛ ታዘልቁልን ዘንድ (ማጋራታችሁን ለመውደዱ) እናንተ ዘንድ ዕውቀት አለን ጥርጣሬን እንጅ ሌላ አትከተሉም፡፡ እናንተ ዋሾዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም» በላቸው፡፡
آية رقم 149
«የተሟላው ማስረጃ የአላህ ነው፡፡ በሻም ኖሮ ሁላችሁንም ባቀናችሁ ነበር» በላቸው፡፡
آية رقم 150
«እነዚያን አላህ ይህን እርም ማድረጉን የሚመሰክሩትን ምስክሮቻችሁን አምጡ» በላቸው፡፡ ቢመሰክሩም ከእነርሱ ጋር አትመስክር፡፡ የነዚያንም በአንቀጾቻችን ያስተባበሉትን የነዚያንም እነርሱ በጌታቸው (ሌላን) የሚያስተካክሉ ሲኾኑ በመጨረሻይቱ ዓለም የማያምኑትን ሰዎች ዝንባሌዎች አትከተል፡፡
آية رقم 151
«ኑ፤ ጌታችሁ በእናንተ ላይ እርም ያደርገውን ነገር (በእርሱም ያዘዛችሁን) ላንብብላችሁ» በላቸው፡፡ «በእርሱ (በአላህ) ምንንም ነገር አታጋሩ፡፡ ለወላጆችም በጎን ሥራ (ሥሩ)፡፡ ልጆቻችሁንም ከድህንት (ፍራቻ) አትግደሉ፡፡ እኛ እናንተንም እነርሱንም እንመግባችኋለንና፡፡ መጥፎ ሥራዎችንም ከእርሷ የተገለጸውንም የተደበቀውንም ሁሉ አትቅረቡ፡፡ ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ በሕግ ቢኾን እንጅ አትግደሉ፡፡ ይህን ታውቁ ዘንድ (አላህ) በእርሱ አዘዛችሁ፡፡»
آية رقم 152
«የየቲምንም ገንዘብ ብርታቱን (አካለ መጠን) እስኪደርስ ድረስ በዚያች እርሷ መልካም በኾነች ኹኔታ እንጅ አትቅረቡ፡፡ ስፍርንና ሚዛንንም በትክክሉ ሙሉ፡፡ ነፍስን ችሎታዋን እንጂ አናስገድድም፡፡ በተናገራችሁም ጊዜ በዘመዶቻችሁ ላይ ቢኾንም እንኳ (እውነትን በመናገር) አስተካክሉ፡፡ በአላህም ቃል ኪዳን ሙሉ፡፡ እነሆ ትገሰጹ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡»
آية رقم 153
«ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም፡፡ (የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፡፡ ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡»
آية رقم 154
ከዚያም ለሙሳ በዚያ መልካም በሠራው ላይ (ጸጋችንን) ለማሟላት ነገርንም ሁሉ ለመዘርዘር መጽሐፉን (ለእስራኤል ልጆች) መሪና እዝነት ይኾን ዘንድ ሰጠነው፡፡ እነርሱ በጌታቸው መገናኘት ሊያምኑ ይከጀላልና፡፡
آية رقم 155
ይህም ያወረድነው የኾነ የተባረከ መጽሐፍ ነው፡፡ ተከተሉትም፡፡ ይታዘንላችሁም ዘንድ (ከክህደት) ተጠንቀቁ፡፡
آية رقم 156
«(ያወረድነውም) መጽሐፍ የተወረደው ከፊታችን በሁለቱ ጭፍሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ እኛም ከንባባቸው ዘንጊዎች ነበርን» እንዳትሉ ነው፡፡
آية رقم 157
ወይም «እኛ መጽሐፍ በእኛ ላይ በተወረደ ኖሮ ከእነሱ ይበልጥ የተመራን እንኾን ነበር» እንዳትሉ ነው፡፡ ስለዚህ ከጌታችሁ ግልጽ ማስረጃ፣ መምሪያም፣ እዝነትም በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ በአላህም አንቀጾች ካስተባበለና ከእርሷም ከዞረ ሰው ይበልጥ በዳይ ማን ነው እነዚያን አንቀጾቻችንን የሚተውትን ይተውት በነበሩት ምክንያት ብርቱን ቅጣት በእርግጥ እንቀጣቸዋለን፡፡
آية رقم 158
መላእክት ልትመጣላቸው ወይም ጌታህ (ቅጣቱ) ሊመጣ ወይም ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ ሊመጣ እንጂ ይጠባበቃሉን ከጌታህ ምልክቶች ከፊሉ በሚመጣ ቀን ከዚህ በፊት አማኝ ያልኾነችን ነፍስ እምነትዋ ወይም በእምነትዋ (ጊዜ) በጎ ያልሠራችን (ነፍስ ጸጸትዋ) አይጠቅማትም፡፡ ተጠባበቁ እኛ ተጠባባቂዎች ነንና በላቸው፡፡
آية رقم 159
እነዚያ ሃይማኖታቸውን የለያዩ አሕዛብም የኾኑ በምንም ከእነሱ አይደለህም፡፡ ነገራቸው ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡ ከዚያም ይሠሩት የነበሩትን ሁሉ ይነገራቸዋል፡፡
آية رقم 160
በመልካም ሥራ የመጣ ሰው ለእርሱ ዐሥር ብጤዎችዋ አሉት፡፡ በክፉ ሥራም የመጣ ሰው ብጤዋን እንጅ አይመነዳም፡፡ እነርሱም አይበደሉም፡፡
آية رقم 161
«እኔ ጌታዬ ወደ ቀጥተኛው መንገድ ትክክለኛን ሃይማኖት ወደ እውነት አዘንባይ ሲኾን የአብርሃምን መንገድ መራኝ፡፡ እርሱም ከአጋሪዎቹ አልነበረም» በል፡፡
آية رقم 162
«ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው» በል፡፡
آية رقم 163
«ለእርሱ ተጋሪ የለውም፡፡ በዚህም (በማጥራት) ታዘዝኩ፡፡ እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» (በል)፡፡
آية رقم 164
በላቸው «እርሱ (አላህ) የሁሉ ጌታ ሲኾን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ (ክፉን) አትሠራም፡፡ ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ሸክም (ኃጢአት) አትሸከምም፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው፡፡ ወዲያውም በእርሱ ትለያዩበት የነበራችሁትን ሁሉ ይነገራችኋል፡፡»
آية رقم 165
እርሱም ያ በምድር ምትኮች ያደረጋችሁ በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ ከፊላችሁን ከከፊሉ በላይ በደረጃዎች ከፍ ያደረገ ነው፡፡ ጌታህ ቅጣቱ ፈጣን ነው፡፡ እርሱም እጅግ መሓሪ ሩኅሩኅ ነው፡፡
تقدم القراءة