ترجمة سورة النساء

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة النساء باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

እናንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን ከእርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን ከእነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶች የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ፡፡ ያንንም በርሱ የምትጠያየቁበትን አላህንና ዝምድናዎችንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና፡፡
የቲሞችንም ገንዘቦቻቸውን ስጡ፡፡ መጥፎውንም በመልካሙ አትለውጡ፡፡ ገንዘቦቻቸውንም ወደ ገንዘቦቻችሁ (በመቀላቀል) አትብሉ እርሱ ታላቅ ኃጢአት ነውና፡፡
በየቲሞችም (ማግባት) አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ (ዝሙትንና ከተወሰነላችሁ በላይ ማግባትንም ፍሩ)፡፡ ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፡፡ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡
ሴቶችንም መህሮቻቸውን በደስታ ስጡ፡፡ ለእናንተም ከእርሱ አንዳችን ነገር ነፍሶቻቸው ቢለግሱ መልካም ምስጉን ሲኾን ብሉት፡፡
ቂሎችንም ያችን አላህ ለእናንተ መተዳደሪያ ያደረጋትን ገንዘቦቻችውን (የያዛችሁላቸውን) አትስጡዋቸው፡፡ ከርሷም መግቡዋቸው አልብሱዋቸውም፡፡ ለእነሱም መልካምን ንግግር ተናገሩ፡፡
የቲሞችንም ጋብቻን እስከደረሱ ጊዜ ድረስ ፈትኑዋቸው፡፡ ከእነርሱም ቅንነትን ብታውቁ ገንዘቦቻቸውን ወደ እነርሱ ስጡ፡፡ በማባከንና ማደጋቸውንም በመሽቀዳደም አትብሏት፡፡ (ከዋቢዎች) ሀብታምም የኾነ ሰው ይከልከል፡፡ ድሃም የኾነ ሰው (ለድካሙ) በአግባብ ይብላ፡፡ ገንዘቦቻቸውንም ወደ እነርሱ በሰጣችሁ ጊዜ በእነርሱ ላይ አስመስክሩ፡፡ ተጠባባቂነትም በአላህ በቃ፡፡
ለወንዶች ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት (ንብረት) ፋንታ (ድርሻ) አላቸው፡፡ ለሴቶችም ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት ከእርሱ ካነሰው ወይም ከበዛው ፋንታ አላቸው፡፡ የተወሰነ ድርሻ (ተደርጓል)፡፡
ክፍያንም (ወራሽ ያልኾኑ) የዝምድና ባለቤቶችና የቲሞች፣ ምስኪኖችም በተገኙበት ጊዜ ከእርሱ ዳርጓቸው፡፡ መልካምንም ንግግር ተናገሩዋቸው፡፡
እነዚያም ከኋላቸው ደካሞችን ዝርያዎች ቢተው ኖሮ በእነርሱ ላይ የሚፈሩ (በየቲሞች ላይ) ይጠንቀቁ፡፡ አላህንም ይፍሩ፡፡ (ለተናዛዡ) ትክክለኛንም ቃል ይናገሩ፡፡
እነዚያ የየቲሞችን ገንዘብ በመበደል የሚበሉ በሆዶቻቸው ውስጥ የሚበሉት እሳትን ብቻ ነው፡፡ እሳትንም በእርግጥ ይገባሉ፡፡
አላህ በልጆቻችሁ (ውርስ በሚከተለው) ያዛችኋል፡፡ ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ (ሁለት ወይም) ከሁለት በላይም የኾኑ ሴቶች ብቻ ቢኾኑ ለእነሱ (ሟቹ) ከተወው ረጀት (ድርሻ) ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ አንዲትም ብትኾን ለርሷ ግማሹ አላት፡፡ ለአባትና ለእናቱም ለእርሱ ልጅ እንዳለው ከሁለቱ ለያንዳንዱ ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ለእርሱም ልጅ ባይኖረውና ወላጆቹ ቢወርሱት ለእናቱ ሲሶው አላት፡፡ ለእርሱም ወንድሞችና እኅቶች ቢኖሩት ለናቱ ከስድስት አንድ አላት፡፡ (ይህም የተባለው) በርሷ ከተናዘዘባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ አባቶቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ በመጥቀም ማንኛቸው ይበልጥ ቅርብ እንደኾኑ አታውቁም፡፡ (ይኽም) ከአላህ የተደነገገ ነው፤ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
ለእናንተም ሚስቶቻችሁ ከተዉት ንብረት ለእነርሱ ልጅ ባይኖራቸው ግማሹ አላችሁ፡፡ ለእነሱም ልጅ ቢኖራቸው ከተዉት ሀብት ከአራት አንድ አላችሁ፡፡ (ይህም) በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ለናንተም ልጅ ባይኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ (ለሚስቶች) ከአራት አንድ አላቸው፡፡ ለእናንተም ልጅ ቢኖራችሁ ከተዋችሁት ንብረት ለእነርሱ ከስምንት አንድ አላቸው (ይህም በርሷ ከምትናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡) ወላጅም ልጅም የሌለው በጎን ወራሾች የሚወርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ ለእርሱም (ለሟቹ) ወንድም ወይም እኅት (ከእናቱ በኩል ብቻ የኾነ) ቢኖር ከሁለቱ ለያንዳንዳቸው ከስድስት አንድ አላቸው፡፡ ከዚህም (ከአንድ) የበዙ ቢኾኑ እነርሱ በሲሶው ተጋሪዎች ናቸው፡፡ (ይህም ወራሾችን) የማይጎዳ ኾኖ በእርሷ ከሚናዘዙባት ኑዛዜ ወይም ከዕዳ በኋላ ነው፡፡ ከአላህም የኾነን ኑዛዜ (ያዛችኋል)፡፡ አላህም ዐዋቂ ቻይ ነው፡፡
እነዚህ የአላህ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዙ ሰዎች ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ ያገባቸዋል፡፡ ይህም ትልቅ ዕድል ነው፡፡
አላህንና መልክተኛውንም የሚያምጽ ወሰኖቹንም የሚተላለፍ በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን እሳትን ያገባዋል፡፡ ለርሱም አዋራጅ ቅጣት አለው፡፡
እነዚያም ከሴቶቻችሁ መጥፎን ሥራ (ዝሙትን) የሚሠሩ በእነርሱ ላይ ከናንተ አራትን (ወንዶች) አስመስክሩባቸው፡፡ ቢመሰክሩም ሞት እስከሚደርስባቸው ወይም አላህ ለእነርሱ መንገድን እስከሚያደርግ ድረስ በቤቶች ውሰጥ ያዙዋቸው (ጠብቁዋቸው)፡፡
እነዚያንም ከእናንተ ውስጥ (ዝሙትን) የሚሠሩዋትን አሰቃዩዋቸው፡፡ ቢጸጸቱና ሥራቸውንም ቢያሳምሩ ከእነርሱ ተገቱ (አታሰቃዩዋቸው)፡፡ አላህ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡
ጸጸትን መቀበል በአላህ ላይ የሚገባው ለእነዚያ ኀጢአትን በስህተት ለሚሠሩና ከዚያም ከቅርብ ጊዜ ለሚጸጸቱት ብቻ ነው፡፡ እነዚያንም አላህ በእነርሱ ላይ ጸጸትን ይቀበላል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ጸጸትንም መቀበል ለእነዚያ ኀጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ «እኔ አሁን ተጸጸትኩ» ለሚልና ለነዚያም እነርሱ ከሓዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለእነሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! ሴቶችን ያስገደዳችሁ ኾናችሁ ልትወርሱና ግልጽን መጥፎ ሥራ ካልሠሩ በስተቀር ከሰጣችኋቸው ከፊሉን ልትወስዱ ልታጉላሏቸውም ለእናንተ አይፈቀድም፡፡ በመልካምም ተኗኗሩዋቸው፡፡ ብትጠሉዋቸውም (ታገሱ)፡፡ አንዳችን ነገር ብትጠሉ አላህም በእርሱ ብዙ ደግ ነገርን ሊያደርግ ይቻላልና፡፡
በሚስትም ስፍራ ሚስትን ለመለወጥ ብትፈልጉ ለአንደኛይቱ (ለምትፈታው) ብዙን ገንዘብ የሰጣችኋት ስትኾኑ ከርሱ ምንንም አትውሰዱ፡፡ በመበደልና ግልጽ በኾነ ኀጢአት ትወስዱታላችሁን
ከፊላችሁ ወደ ከፊሉ በእርግጥ የደረሰ ሲኾንና ከእናንተ ላይም (ሴቶች) የጠበቀ ኪዳንን የያዙባችሁ ሲኾኑ እንዴት ትወስዱታላችሁ!
ከሴቶችም አባቶቻችሁ ያገቡዋቸውን አታግቡ፡፡ (ትቀጡበታላችሁ)፡፡ ያለፈው ሲቀር፡፡ እርሱ መጥፎና የተጠላ ሥራ ነውና፡፡ መንገድነቱም ከፋ!
እናቶቻችሁ፣ ሴት ልጆቻችሁም፣ እኅቶቻችሁም፣ አክስቶቻችሁም፣ የሹሜዎቻችሁም፣ የወንድም ሴቶች ልጆችም፣ የእኅት ሴቶች ልጆችም፣ እነዚያም ያጠቡዋችሁ እናቶቻችሁ፣ ከመጥባት የኾኑትም እኅቶቻችሁ፣ የሚስቶቻችሁም እናቶች፣ እነዚያም በጉያዎቻችሁ ያሉት የእነዚያ በእነርሱ የገባችሁባቸው ሚስቶቻችሁ ሴቶች ልጆች፣ (ልታገቧቸው) በእናንተ ላይ እርም ተደረጉባችሁ፡፡ በእነርሱም (በሚስቶቻችሁ) ያልገባችሁባቸው ብትኾኑ (በፈታችኋቸው ጊዜ ሴቶች ልጆቻቸውን ብታገቡ) በእናንተ ላይ ኀጢአት የለባችሁም፡፡ የእነዚያ ከጀርባዎቻችሁ የኾኑት ወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶችም በሁለት እኅትማማቾችም መካከል መሰብሰብ (እንደዚሁ እርም ነው)፡፡ ግን ከዚህ በፊት ያለፈው ሲቀር (እርሱንስ ተምራችኋል) አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
ከሴቶችም (በባል) ጥብቆቹ እጆቻቸሁ (በምርኮ) የያዙዋቸው ሲቀሩ በእናንተ ላይ እርም ናቸው፡፡ (ይህን) አላህ በናንተ ላይ ጻፈ፡፡ ከዚሃችሁም (ከተከለከሉት) ወዲያ ጥብቆች ኾናችሁ ዝሙተኞች ሳትኾኑ በገንዘቦቻችሁ ልትፈልጉ ለእናንተ ተፈቀደ፡፡ ከእነሱም በርሱ (በመገናኘት) የተጠቀማችሁባቸውን ሴቶች መህሮቻቸውን ግዴታ ሲኾን ስጧቸው፡፡ ከመወሰንም በኋላ በተዋደዳችሁበት ነገር በእናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ አላህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡
ከናንተም ውስጥ ጥብቆች ምእምናት የኾኑትን ለማግባት ሀብትን ያልቻለ ሰው እጆቻችሁ ንብረት ካደረጓቸው ከምእምናት ወጣቶቻችሁ (ባሪያን ያግባ)፡፡ አላህም እምነታችሁን ዐዋቂ ነው፡፡ ከፊላችሁ ከከፊሉ (የተራባ) ነው፡፡ (ባሮችን) በጌቶቻቸውም ፈቃድ አግቡዋቸው፡፡ መህሮቻቸውንም በመልካም መንገድ ስጧቸው፡፡ ጥብቆች ኾነው ዝሙተኞች ያልኾኑ የስርቆሽ ወዳጆችንም ያልያዙ ሲኾኑ (አግቧቸው)፡፡ በማግባት በተጠበቁም ጊዜ መጥፎን ሥራ ቢሠሩ በእነርሱ ላይ ከቅጣት በነጻዎቹ ላይ ያለው ግማሽ አለባቸው፡፡ ይኸ (ባሪያን ማግባት) ከናንተ ዝሙትን ለፈራ ሰው ነው፡፡
አላህ (የሃይማኖታችሁን ሕግጋት) ሊያብራራላችሁ ከእናንተ በፊትም የነበሩትን ነቢያት ደንቦች ሊመራችሁ በእናንተም ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
አላህም በእናንተ ላይ ጸጸትን ሊቀበል ይሻል፡፡ እነዚያም ፍላጎታቸውን የሚከተሉት (ከውነት) ትልቅን መዘንበል እንድትዘነበሉ ይፈልጋሉ፡፡
አላህ ከእናንተ ሊያቃልልላችሁ ይሻል፡፡ ሰውም ደካማ ኾኖ ተፈጠረ፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ገንዘቦቻችሁን በመካከላችሁ ያለ አግባብ አትብሉ፡፡ ግን ከእናንተ በመዋደድ የኾነችውን ንግድ (ብሉ)፡፡ ነፍሶቻችሁንም አትግደሉ፡፡ አላህ ለእናንተ አዛኝ ነውና፡፡
ወሰን በማለፍና በመበደልም ይህንን የሠራ ሰው እሳትን እናገባዋለን፡፡ ይኸም በአላህ ላይ ገር ነው፡፡
ከእርሱ ከተከለከላችሁት ታላላቆቹን (ኀጢአቶች) ብትርቁ (ትናንሾቹን) ኀጢአቶቻችሁን ከእናንተ እናብሳለን፡፡ የተከበረንም ስፍራ (ገነትን) እናገባችኋለን፡፡
አላህም ከፊላችሁን በከፊሉ ላይ በእርሱ ያበለጠበትን ጸጋ አትመኙ፡፡ ለወንዶች ከሠሩት ሥራ እድል አላቸው፡፡ ለሴቶችም ከሠሩት ሥራ ዕድል አላቸው፡፡ አላህንም ከችሮታው ለምኑት፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
ለሁሉም (ለወንዶችና ለሴቶች) ወላጆችና የቅርብ ዘመዶች ከተዉት ሀብት ጠቅላይ ወራሾችን አድርገናል፡፡ እነዚያንም (ለመረዳዳትና ለመዋረስ) በመሐላዎቻችሁ የተዋዋላችኋቸውን ድርሻቸውን (ከስድስት አንድ) ስጧቸው፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡
ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፡፡ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና (ወንዶች) ከገንዘቦቻቸው (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው፡፡ መልካሞቹም ሴቶች (ለባሎቻቸው) ታዛዦች አላህ ባስጠበቀው ነገር ሩቅን ጠባቂዎች ናቸው፡፡ እነዚያንም ማመጸቸውን የምትፈሩትን ገስጹዋቸው፡፡ በመኝታዎችም ተለዩዋቸው፡፡ (ሳካ ሳታደርሱ) ምቱዋቸውም፡፡ ቢታዘዟችሁም (ለመጨቆን) በእነርሱ ላይ መንገድን አትፈልጉ፤ አላህ የበላይ ታላቅ ነውና፡፡
(እናንተ ዋቢዎች) የመካከላቸውንም ጭቅጭቅ ብታውቁ ከቤተሰቦቹ ሽማግሌን ከቤተሰቦችዋም ሽማግሌን ላኩ፡፡ ማስታረቅን ቢሹ አላህ በመካከላቸው ያስማማል፡፡ አላህ ግልጽን ዐዋቂ ውስጥንም ዐዋቂ ነውና፡፡
አላህንም ተገዙ፡፡ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡ በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም፣ እጆቻችሁም ንብረት ባደረጓቸው (ባሮች)፣ መልካምን (ሥሩ)፤ አላህ ኩራተኛ ጉረኛ የኾነን ሰው አይወድም፡፡
እነዚያ የሚሰስቱ ሰዎችንም በመሰሰት የሚያዙ አላህም ከችሮታው የሰጣቸውን ጸጋ የሚደብቁ (ብርቱን ቅጣት ይቀጥጣሉ)፡፡ ለከሓዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
እነዚያም ለሰዎች ይውልኝ ሲሉ ገንዘቦቻቸውን የሚሰጡ በአላህና በመጨረሻውም ቀን የማያምኑ (ይቀጥጣሉ)፡፡ ሰይጣንም ለእርሱ ጓደኛው የኾነ ሰው ጓደኛነቱ ከፋ!
በአላህና በመጨረሻውም ቀን ባመኑ አላህ ከሰጣቸውም (ሲሳይ) በለገሱ ኖሮ በነርሱ ላይ ምን (ጉዳት) ነበረ አላህም በነርሱ (ኹነታ) ዐዋቂ ነው፡፡
አላህ የብናኝን ክብደት ያህል አይበድልም፡፡ መልካም ሥራ ብትኾንም ይደራርባታል፡፡ ከእርሱም ዘንድ ታላቅን ምንዳ ይሰጣል፡፡
ከሕዝቦችም ሁሉ መስካሪን ባመጣን ጊዜ አንተንም በእነዚህ ላይ መስካሪ አድርገን በምናመጣህ ጊዜ (የከሓዲዎች ኹኔታ) እንዴት ይኾን
በዚያ ቀን እነዚያ የካዱትና መልክተኛውን ያልታዘዙት በእነሱ ምድር ብትደፋባቸው ይመኛሉ፡፡ ከአላህም ወሬን አይደብቁም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ኾናችሁ የምትሉትን ነገር እስከምታውቁ የረከሳችሁም ስትኾኑ መንገድን አላፊዎች ካልኾናችሁ በስተቀር (አካላታችሁን) እስከምትታጠቡ ድረስ ስግደትን አትቅረቡ፡፡ በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም፥ ወይንም ከእናንተ አንዱ ከዓይነምድር ቢመጣ፥ ወይንም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ፣ ንጹሕ የኾነን የምድር ገጽ አስቡ፡፡ ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁንም (በርሱ) አብሱ፡፡ አላህ ይቅር ባይ መሓሪ ነውና፡፡
ወደነዚያ ከመጽሐፉ (ዕውቀት) ዕድልን ወደ ተሰጡት አላየህምን ጥመትን (በቅንነት) ይገዛሉ፡፡ መንገድንም እንድትሳሳቱ ይፈልጋሉ፡፡
አላህም ጠላቶቻችሁን ዐዋቂ ነው፡፡ ጠባቂነትም በአላህ በቃ፡፡ ረዳትነትም በአላህ በቃ፡፡
ከነዚያ አይሁዳውያን ከኾኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አልሉ፡፡ «ሰማንም አመጽንም የማትሰማም ስትኾን ስማ» ይላሉ፡፡ በምላሶቻቸውም ለማጣመምና ሃይማኖትንም ለመዝለፍ ራዒና ይላሉ፡፡ እነሱም «ሰማን ታዘዝንም ስማም ተመልከተንም» ባሉ ኖሮ ለነሱ መልካምና ትክክለኛ በኾነ ነበር፡፡ ግን በክህደታቸው አላህ ረገማቸው፡፡ ጥቂትንም እንጅ አያምኑም፡፡
እናንተ መጽሐፉን የተሰጣችሁ ሆይ! ፊቶችን ሳናብስና በጀርባዎች ላይ ሳንመልሳቸው ወይም የሰንበትን ባለቤቶች (ያፈረሱትን) እንደረገምን ሳንረግማቸው በፊት ከእናንተ ጋር ያለውን የሚያረጋግጥ ኾኖ ባወረድነው (ቁርኣን) እመኑ፡፡ የአላህም ትዕዛዝ ተፈጻሚ ነው፡፡
አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም (ኀጢአት) ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኀጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡
ወደእነዚያ ነፍሶቻቸውን ወደ ሚያጠሩት (የሚያወድሱት) አላየህምን አይደለም፤ አላህ የሚፈልገውን ያጠራል፡፡ የተምር ፍሬ ክር ያህልም አይበደሉም፡፡
በአላህ ላይ ውሸትን እንዴት እንደሚቀጣጥፉ ተመልከት፡፡ ግልጽ ወንጀልም በርሱ (በመቅጠፍ) በቃ፡፡
ወደ እነዚያ ከመጽሐፉ ዕድልን ወደ ተሰጡት አላየኸምን በድግምትና በጣዖት ያምናሉ፡፡ ለእነዚያም ለካዱት፡- እናንተ በመንገድ (በሃይማኖት) ከእነዚያ ካመኑት ይበልጥ የቀናችሁ ናችሁ ይላሉ፡፡
እነዚያ አላህ የረገማቸው ናቸው፡፡ አላህም የረገመው ሰው ለእርሱ ፈጽሞ ረዳትን አታገኝለትም፡፡
በእውነቱ ለእነሱ ከንግሥናው ፋንታ አላቸውን ያን ጊዜ ለሰዎች በተምር ፍሬ ላይ ያለችውን ነጥብ ያህል አይሰጡም ነበር፡፡
ይልቁንም ሰዎችን (ሙሐመድን) አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ላይ ይመቀኛሉን ለኢብራሂምም ቤተሰቦች መጽሐፍንና ጥበብን በእርግጥ ሰጠን ታላቅንም ንግሥና ሰጠናቸው፡፡
ከእነሱም (ከይሁዶች) በእርሱ ያመነ አለ፡፡ ከእነርሱም ከእርሱ ያፈገፈ አለ፡፡ አቃጣይነትም በገሀነም በቃ፡፡
እነዚያን በተአምራታችን የካዱትን በእርግጥ እሳትን እናገባቸዋለን፡፡ ስቃይን እንዲቀምሱ ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡
እነዚያንም ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን ከስራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘልዓለም በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በእርግጥ እናገባቸዋለን፡፡ ለእነሱ በውስጥዋ ንጹሕ ሚስቶች አሉዋቸው፡፡ የምታስጠልልን ጥላም እናገባቸዋለን፡፡
አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡ በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ በትክክል እንድትፈርዱ (ያዛችኋል)፡፡ አላህ በርሱ የሚገሥጻችሁ ነገር ምን ያምር! አላህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፡፡ መልክተኛውንና ከእናንተም የስልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፡፡ በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፡፡ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡
ወደ እነዚያ እነርሱ በአንተ ላይ በተወረደውና ከአንተ በፊትም በተወረደው አምነናል ወደሚሉት፤ አላየህምን በእርሱ እንዲክዱ በእርግጥ የታዘዙ ሲኾኑ ወደ ጣዖት መፋረድን ይፈልጋሉ፡፡ ሰይጣንም (ከእውነት) የራቀን መሳሳት ሊያሳስታቸው ይፈልጋል፡፡
ለእነርሱም፡- «አላህ ወደ አወረደው (ቁርኣን)ና ወደ መልክተኛው ኑ» በተባሉ ጊዜ መናፍቃን ከአንተ መሸሽን ሲሸሹ ታያቸዋለህ፡፡
እጆቻቸውም ባስቀደሙት (ጥፋት) መከራ በደረሰችባቸውና ከዚያም «ደግን ሐሳብና ማስማማትን እንጅ ሌላ አልሻንም» በማለት በአላህ የሚምሉ ኾነው በመጡህ ጊዜ እንዴት ይኾናሉ
እነዚህ እነዚያ አላህ በልቦቻቸው ውስጥ ያለውን ሁሉ የሚያውቅባቸው ናቸው፡፡ እነርሱንም ተዋቸው ገሥጻቸውም፡፡ ለእነርሱም በነፍሶቻቸው ውስጥ ስሜት ያለውን ቃል ተናገራቸው፡፡
ማንንም መልክተኛ በአላህ ፈቃድ ሊታዘዙት እንጅ አልላክንም፡፡ እነሱም ነፍሶቻቸውን በበደሉ ጊዜ ወደ አንተ ቢመጡና አላህንም ምሕረትን በለመኑ መልክተኛውም ለነርሱ ምሕረትን በለመነላቸው ኖሮ አላህን ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ኾኖ ባገኙት ነበር፡፡
በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)፡፡
እኛም በእነርሱ ላይ፡- «ነፍሶቻችሁን ግደሉ ወይም ከአገሮቻችሁ ውጡ» ማለትን በጻፍን ኖሮ ከነሱ ጥቂቶቹ እንጅ ባልሠሩት ነበር፡፡ እነርሱም በእርሱ የሚገሰጹበትን ነገር በሠሩ ኖሮ ለነሱ መልካምና (በእምነታቸው ላይ) ለመርጋትም በጣም የበረታ በኾነ ነበር፡፡
ያን ጊዜም ከእኛ ዘንድ ታላቅን ምንዳ በሰጠናቸው ነበር፡፡
ቀጥተኛውንም መንገድ በእርግጥ በመራናቸው ነበር፡፡
አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዝ ሰው እነዚያ ከእነዚያ አላህ በእነርሱ ላይ ከለገሳቸው ከነቢያት፣ ከጻድቃንም፣ ከሰማዕታትም፣ ከመልካሞቹ ጋር ይኾናሉ፡፡ የእነዚያም ጓደኝነት አማረ፡፡
ይህ ችሮታ ከአላህ ነው፡፡ አዋቂነትም በአላህ በቃ፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጥንቃቄያችሁን ያዙ፡፡ ክፍልፍልም Ñድ ሆናችሁ (ለዘመቻ) ውጡ፡፡ ወይም ተሰብስባችሁ ውጡ፡፡
ከእናንተም ውስጥ በእርግጥ (ከዘመቻ) ወደ ኋላ የሚንጓደድ ሰው አልለ፡፡ አደጋም ብታገኛችሁ ከእነሱ ጋር ተጣጅ ባልኾንኩ ጊዜ አላህ በእኔ ላይ በእርግጥ ለገሰልኝ ይላል፡፡
ከአላህም የኾነ ችሮታ ቢያገኛችሁ በእናንተና በእርሱ መካከል ፍቅር እንዳልነበረች ሁሉ «ታላቅ ዕድልን አገኝ ዘንድ ከነሱ ጋር በኾንኩ ወይ ምኞቴ!» ይላል፡፡
እነዚያም ቅርቧን ሕይወት በመጨረሻይቱ ሕይወት የሚለውጡ በአላህ መንገድ ይጋደሉ፡፡ በአላህም መንገድ የሚጋደል፣ የሚገደልም ወይም የሚያሸንፍ ታላቅ ምንዳን በእርግጥ እንሰጠዋለን፡፡
በአላህ መንገድና ከወንዶች ከሴቶችና ከልጆችም የኾኑትን ደካሞች እነዚያን፡- «ጌታችን ሆይ! ከዚች ባለቤቶችዋ በዳይ ከኾኑት ከተማ አውጣን ከአንተም ዘንድ ለእኛ አሳዳሪን አድርግልን ከአንተ ዘንድም ለእኛ ረዳትን አድርግልን» የሚሉትን (ለማዳን) የማትጋደሉት ለእናንተ ምን አላችሁ
እነዚያ ያመኑት ሰዎች በአላህ መንገድ ይጋደላሉ፡፡ እነዚያ የካዱትም በጣዖት መንገድ ይጋደላሉ፡፡ የሰይጣንንም ጭፍሮች ተጋደሉ፡፡ የሰይጣን ተንኮል ደካማ ነውና፡፡
ወደእነዚያ ለእነርሱ፡- እጆቻችሁን (ከመጋደል) ሰብስቡ፣ ሶላትንም ደንቡን ጠብቃችሁ ስገዱ፣ ግዴታ ምጽዋትም ስጡ ወደ ተባሉት አላየህምን በእነርሱም ላይ መጋደል በተጻፈ ጊዜ ከእነሱ ከፊሎቹ ወዲያውኑ ሰዎችን አላህን እንደሚፈሩ ወይም የበለጠ ፍራቻን ይፈራሉ፡፡ «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መጋደልን ለምን ደነገግክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አታቆየንም ኖሮአልን» ይላሉም፡፡ «የቅርቢቱ ሕይወት ጥቅም አነስተኛ ነው፡፡ መጨረሻይቱም ዓለም አላህን ለሚፈራ ሰው በላጭ ናት፡፡ በተምር ፍሬ ውስጥ ያለን ክር ያህል እንኳ አትበደሉም» በላቸው፡፡
«የትም ስፍራ ብትኾኑ በጠነከሩ ሕንጻዎች ውስጥ ብትኾኑም እንኳ ሞት ያገኛችኋል፡፡ ደግም ነገር ብታገኛቸው ይህች ከአላህ ዘንድ ናት» ይላሉ፡፡ መከራም ብታገኛቸው «ይህቺ ከአንተ ዘንድ ናት» ይላሉ፡፡ «ሁሉም (ደጉም ክፉውም) ከአላህ ዘንድ ነው» በላቸው፡፡ ለእነዚህም ሰዎች ንግግርን ሊረዱ የማይቀርቡት ምን አላቸው
ከደግ ነገር የሚያገኝህ ከአላህ (ችሮታ) ነው፡፡ ከመከራም የሚደርስብህ ከራስህ (ጥፋት የተነሳ) ነው፡፡ ለሰዎችም ሁሉ መልክተኛ ኾነህ ላክንህ፡፡ መስካሪም በአላህ በቃ፡፡
መልክተኛውን የሚታዘዝ ሰው በእርግጥ አላህን ታዘዘ፡፡ ከትእዛዝም የሸሸ ሰው (አያሳስብህ)፡፡ በእነሱ ላይ ጠባቂ አድርገን አልላክንህምና፡፡
«(ነገራችን) መታዘዝ ነው» ይላሉም፤ ከአንተም ዘንድ በወጡ ጊዜ ከነርሱ ከፊሎቹ ከዚያ (በፊትህ) ከሚሉት ሌላን (በልቦቻቸው) ያሳድራሉ፡፡ አላህም የሚያሳድሩትን ነገር ይጽፋል፡፡ ስለዚህ ተዋቸው፡፡ በአላህም ላይ ተጠጋ፡፡ መጠጊያም በአላህ በቃ፡፡
ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡
ከጸጥታ ወይም ከፍርሃት አንዳች (ወሬ) በመጣላቸውም ጊዜ እርሱን ያጋንናሉ፡፡ ወደ መልክተኛውና ከእነርሱ ወደ ትዕዛዙ ባለቤቶች (ወደ ዐዋቂዎቹ) በመለሱት ኖሮ እነዚያ ከእነርሱ (ነገሩን) የሚያውጣጡት ባወቁት ነበር፡፡ በእናንተም ላይ የአላህ ችሮታና እዝነቱ ባልነበረ ኖሮ ከጥቂቶች በስተቀር ሰይጣንን በተከተላችሁ ነበር፡፡
በአላህም መንገድ ተጋደል፡፡ ራስህን እንጅ ሌላን አትገደድም፡፡ ምእምናንንም (በመጋደል ላይ) አደፋፍር፡፡ አላህ የእነዚያን የካዱትን ኀይል ሊከለክል ይከጀላል፡፡ አላህም በኀይል በመያዙ የበረታ ቅጣቱም የጠነከረ ነው፡፡
መልካም መታደግን የሚታደግ ሰው ለእርሱ ከርስዋ ዕድል ይኖረዋል፡፡ መጥፎ መታደግንም የሚታደግ ሰው ለእርሱ ከርስዋ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
በሰላምታ በተከበራችሁም ጊዜ ከእርሷ ይበልጥ ባማረ (ሰላምታ) አክብሩ፡፡ ወይም (እርሷኑ) መልሷት፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ ነውና፡፡
አላህ ከእርሱ በስተቀር አምላክ የለም፡፡ ወደ ትንሣኤ ቀን በርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲኾን በእርግጥ ይሰበስባችኋል፡፡ በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማነው
በመናፍቃንም (ነገር) አላህ በሥራዎቻቸው ወደ ክህደት የመለሳቸው ሲኾኑ ሁለት ክፍሎች የኾናችሁት ለናንተ ምን አላችሁ አላህ ያጠመመውን ሰው ልታቀኑ ታስባላችሁን አላህም ያሳሳተውን ሰው ለእርሱ መንገድን ፈጽሞ አታገኝለትም፡፡
(እነርሱ) እንደ ካዱ ብትክዱና እኩል ብትኾኑ ተመኙ! በአላህም ሃይማኖት እስከሚሰደዱ ድረስ ከነሱ ወዳጆችን አትያዙ፡፡ (ከእምነት) ቢያፈገፍጉም ያዙዋቸው፤ (ማርኩዋቸው)፡፡ ባገኛችሁበትም ስፍራ ግደሉዋቸው፡፡ ከእነሱም ወዳጅንና ረዳትን አትያዙ፡፡
እነዚያ በእናንተና በእነርሱ መካከል ቃል ኪዳን ወዳላቸው ሕዝቦች የሚጠጉና ወይም እናንተን ለመጋደል ወይም ወገኖቻቸውን ለመጋደል ልቦቻቸው የተጨነቁ ኾነው የመጧዋችሁ ሲቀሩ፤ (እነዚያንስ አትጋደሉዋቸው)፡፡ አላህም በሻ ኖሮ በእናንተ ላይ ኀይል በሰጣቸውና በተጋደሉዋችሁ ነበር፡፡ ቢተዋችሁና ባይጋደሉዋችሁም ወደ እናንተም እርቅን ቢያቀርቡ አላህ ለእናንተ በነሱ ላይ (የመጋደል) መንገድን አላደረገም፡፡
ሌሎች ከእናንተ ለመዳን ከወገኖቻቸውም ለመዳን የሚፈልጉን ታገኛላችሁ፡፡ ወደ እውከት እንዲመለሱ በተጠሩ ቁጥር በርሷ ውስጥ ይመለሳሉ፡፡ ባይተውዋችሁና እርቅንም ባያቀርቡላችሁ፣ እጆቻቸውንም ባይሰበስቡ፣ ባገኛችኋቸው ስፍራ ማርኩዋቸው፡፡ ግደሉዋቸውም፡፡ እነዚያንም ለእናንተ በነሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን አድርገናል፡፡
ለምእመንም በስሕተት ካልኾነ በቀር ምእመንን መግደል አይገባውም፡፡ ምእመንንም በስህተት የገደለ ሰው ያመነችን ጫንቃ (ባሪያ) ነጻ ማውጣትና ወደ ቤተሰቦቹም የምትሰጥ ጉማ ምሕረት ካላደረጉለት በስተቀር (መክፈል) አለበት፡፡ እርሱ (ተገዳዩ) ምእመን ሲኾን ለእናንተ ጠላት ከኾኑትም ሕዝቦች ቢኾን ያመነችን ጫንቃ ነጻ ማውጣት (ብቻ) አለበት፡፡ በእናንተና በእነሱ መካከል ቃል ኪዳን ካላቸውም ሕዝቦች ቢኾን ወደ ቤተሰቦቹ በእጅ የምትሰጥ ጉማና ያመነችን ጫንቃ ነጻ ማውጣት አለበት፡፡ ያላገኘ ሰውም ተከታታዮችን ሁለት ወሮች መጾም አለበት፡፡ አላህ መጸጸትን ለመቀበል (ደነገገላችሁ)፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
ምእመንንም አስቦ የሚገድል ሰው ቅጣቱ በውስጧ ዘውታሪ ሲኾን ገሀነም ናት፡፡ አላህም በርሱ ላይ ተቆጣ፡፡ ረገመውም፡፡ ለእርሱም ከባድ ቅጣትን አዘጋጀ፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህ መንገድ (ለመጋደል) በተጓዛችሁ ጊዜ አስረግጡ፡፡ ሰላምታንም ወደናንተ ላቀረበ ሰው የቅርቢቱን ሕይወት ጥቅም የምትፈልጉ ኾናችሁ ምእመን አይደለህም አትበሉ፡፡ አላህም ዘንድ ብዙ ዘረፋዎች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚሁ ነበራችሁ፡፡ አላህም በእናንተ ላይ ለገሰ ስለዚህ አስተውሉ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነውና፡፡
ከምእመናን የጉዳት ባለቤት ከኾኑት በቀር ተቀማጮቹና በአላህ መንገድ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉት አይተካከሉም፡፡ በገንዘቦቻቸውና በነፍሶቻቸው የሚታገሉትን አላህ በተቀማጮቹ ላይ በደረጃ አበለጠ፡፡ ለሁሉም አላህ መልካሚቱን (ገነት) ተስፋ ሰጠ፡፡ ታጋዮቹንም በተቀማጮቹ ላይ አላህ በታላቅ ምንዳ አበለጠ፡፡
ከእርሱ ዘንድ በኾኑ ደረጃዎች (አበለጠ)፡፡ ምሕረትንም አደረገ፡፡ እዝነትም አዘነላቸው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
እነዚያ (ለእምንት ባለመሰደድ) ነፍሶቻቸውን በዳዮች ኾነው መላእክት (በበድር) የገደሉዋቸው (መላእክት ለነርሱ) «በምን ነገር ላይ ነበራችሁ» አሏቸው፡፡ «በምድር ውስጥ ደካሞች ነበርን» አሉ፡፡ «የአላህ ምድር ትሰደዱባት ዘንድ ሰፊ አልነበረችምን» አሉዋቸው፡፡ እነዚያም መኖሪያቸው ገሀነም ናት፡፡ በመመለሻነትም ከፋች!
ግን ከወንዶችና ከሴቶች ከሕፃኖችም ሲኾኑ (ለመውጣት) መላን የማይችሉና መንገድንም የማይምመሩ ደካሞች (ቅጣት የለባቸውም)
እነዚያም አላህ ከእነርሱ ይቅርታ ሊያደርግ ይሻል፡፡ አላህም ይቅር ባይ መሓሪ ነው፡፡
በአላህም መንገድ የሚሰደድ ሰው በምድር ውስጥ ብዙ መሰደጃንና ምቾትን ያገኛል፡፡ ወደ አላህና ወደ መልክተኛውም ስደተኛ ኾኖ ከቤቱ የሚወጣ ከዚያም (በመንገድ) ሞት የሚያገኘው ሰው ምንዳው በእርግጥ አላህ ዘንድ ተረጋገጠ፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
በምድርም ላይ በተጓዛችሁ ጊዜ እነዚያ የካዱት ያውኩናል ብላችሁ ብትፈሩ ከሶላት (ባለ አራት ረከዓት የኾኑትን) ብታሳጥሩ በናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ ከሓዲዎች ለእናንተ በእርግጥ ግልጽ ጠላቶች ናቸውና፡፡
በውስጣቸውም በኾንክና ሶላትን ለእነርሱ ባስገደድካቸው ጊዜ ከእነሱ አንዲት ጭፍራ ካንተ ጋር ትቁም፡፡ መሣሪያዎቻቸውንም ይያዙ፡፡ በግንባራቸውም በተደፉ ጊዜ ከስተኋላችሁ ይኹኑ፡፡ (እነዚህ ይኺዱና) ያልሰገዱትም ሌሎቹ ጭፍሮች ይምጡ፡፡ ከአንተም ጋር ይስገዱ፡፡ ጥንቃቄያቸውንና መሣሪያዎቻቸውንም ይያዙ፡፡ እነዚያ የካዱት ከመሣሪያዎቻችሁና ከጓዞቻችሁ ብትዘነጉና በእናንተ ላይ አንዲትን መዘንበል ቢዘነበሉ ተመኙ፡፡ ከዝናብም የኾነ ችግር በእናንተ ቢኖር ወይም ሕመምተኞች ብትኾኑ መሣሪያዎቻችሁን ብታስቀምጡ በናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ ጥንቃቄያችሁንም ያዙ፡፡ አላህ ለከሓዲዎች አዋራጅን ቅጣት አዘጋጀ፡፡
ሶላትንም በፈጸማችሁ ጊዜ ቆማችሁም ተቀምጣችሁም በጎኖቻችሁም ላይ ተጋድማችሁ አላህን አውሱ፡፡ በረጋችሁም ጊዜ ሶላትን (አሟልታችሁ) ስገዱ፡፡ ሶላት በምእምናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡
ሰዎቹንም በመፈለግ አትስነፉ፡፡ (ስትቆስሉ) የምትታመሙ ብትኾኑ እናንተ እንደምትታመሙ እነሱም ይታመማሉ፡፡ የማይከጅሉትንም ከአላህ ትከጅላላችሁ፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
እኛ በሰዎች መካከል አላህ ባሳወቀህ ልትፈርድ ወደ አንተ መጽሐፉን በእውነት አወረድን፡፡ ለከዳተኞችም ተከራካሪ አትኹን፡፡
አላህንም ምሕረትን ለምን፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡
ከእነዚያም ነፍሶቻቸውን ከሚበድሉት ላይ አትከራከር፡፡ አላህ ከዳተኛ ኃጢአተኛ የኾነን ሰው አይወድምና፡፡
ከሰው ይደበቃሉ፡፡ አላህም እርሱ (በዕውቀቱ) ከእነሱ ጋር ሲኾን ከንግግር የማይወደውን ነገር (በልቦቻቸው) በሚያሳድሩ ጊዜ (ከእርሱ) አይደበቁም፡፡ አላህም በሚሠሩት ሁሉ (በዕውቀቱ) ከባቢ ነው፡፡
እነሆ እናንተ እነዚያ በቅርቢቱ ሕይወት ከነሱ የተከራከራችሁ ናችሁ፡፡ በትንሣኤ ቀን አላህን ስለእነሱ የሚከራከር ማን ነው ወይስ ለእነሱ ኃላፊና መመኪያ የሚኾን ማን ነው
መጥፎም የሚሠራ ሰው ወይም ነፍሱን የሚበድል ከዚያም (ተጸጽቶ) አላህን ምሕረት የሚለምን አላህን መሓሪ አዛኝ ኾኖ ያገኘዋል፡፡
ኀጢአትንም የሚሠራ ሰው የሚሠራው ጥፋት በራሱ ላይ ነው፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፤
ኀጢአትን ወይም አበሳን የሚሠራም ሰው ከዚያም በእርሱ ንጹሕን ሰው የሚሰድብ ቅጥፈትንና ግልጽ አበሳን በቁርጥ ተሸከመ፡፡
የአላህም ችሮታና እዝነቱ ባንተ ላይ ባልነበረ ኖሮ ከእነሱ የኾኑ ጭፍሮች ሊያሳስቱህ ባሰቡ ነበር፡፡ ነፍሶቻቸውንም እንጅ ሌላን አያሳስቱም፡፡ በምንም አይጐዱህም፡፡ አላህም በአንተ ላይ መጽሐፍንና ጥበብን አወረደ፡፡ የማታውቀውንም ሁሉ አስተማረህ፡፡ የአላህም ችሮታ በአንተ ላይ ታላቅ ነው፡፡
ከውይይታቸው በምጽዋት ወይም በበጎ ሥራ ወይም በሰዎች መካከል በማስታረቅ ከሚያዙ ሰዎች ውይይት በስተቀር በብዙው ውስጥ ደግ ነገር የለበትም፡፡ ይኸንንም (የተባለውን) የአላህን ውዴታ ለመፈለግ የሚሠራ ሰው ታላቅ ምንዳን እንሰጠዋለን፡፡
ቅኑም መንገድ ለእርሱ ከተገለጸ በኋላ መልክተኛውን የሚጨቃጨቅና ከምእምኖቹ መንገድ ሌላ የኾነን የሚከተል ሰው (በዚህ ዓለም) በተሾመበት (ጥመት) ላይ እንሾመዋለን፤ ገሀነምንም እናገባዋለን፡፡ መመለሻይቱም ከፋች!
አላህ በርሱ የማጋራትን (ወንጀል) አይምርም፡፡ ከዚህም ወዲያ ያለውን ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው (ከእውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ፡፡
ከእርሱ ሌላ እንስታትን እንጅ አይገዙም፡፡ አመጸኛ ሰይጣንንም እንጅ ሌላን አይግገዙም፡፡
«አላህ የረገመውን ከባሮችህም የተወሰነን ድርሻ በእርግጥ እይዛለሁ» ያለውን (ሰይጣን እንጅ ሌላን አይከተሉም)፡፡
በእርግጥ አጠማቸዋለሁም፡፡ (ከንቱን) አስመኛቸዋለሁም፡፡ አዛቸውምና የእንስሶችን ጆሮዎች ይተለትላሉ፡፡ አዛቸውምና የአላህን ፍጥረት ይለውጣሉ፤ (ያለውን ይከተላሉ)፡፡ ከአላህም ሌላ ሰይጣንን ረዳት አድርጎ የሚይዝ ሰው ግልጽ ክስረትን በአርግጥ ከሰረ፡፡
(የማይፈጸመውን) ተስፋ ይሰጣቸዋል፡፡ ያስመኛቸዋልም፡፡ ሰይጣንም ለማታለል እንጅ አይቀጥራቸውም፡፡
እነዚያ መኖሪያቸው ገሀነም ናት፡፡ ከርስዋም መሸሻን አያገኙም፡፡
እነዚያም ያመኑና በጎ ሥራዎችን የሠሩ በሥራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘላለም በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ እናገባቸዋለን፡፡ አላህ እውነተኛን ተስፋ ሰጣቸው፡፡ በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማን ነው
(ነገሩ) በምኞታችሁና በመጽሐፉ ሰዎች ምኞት አይደለም፡፡ መጥፎን የሚሠራ ሰው በእርሱ ይቀጣል፡፡ ለእርሱም ከአላህ ሌላ ጠባቂንም ረዳትንም አያገኝም፡፡
ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡ በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያክል እንኳ አይበደሉም፡፡
እርሱ መልካም ሠሪ ኾኖ ፊቱን ለአላህ ከሰጠና የኢብራሂምንም መንገድ ቀጥተኛ ሲኾን ከተከተለ ሰው ይበልጥ ሃይማኖቱ ያማረ ማን ነው አላህም ኢብራሂምን ፍጹም ወዳጅ አድርጐ ያዘው፡፡
በሰማያት ያለውና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ በዕውቀት ከባቢ ነው፡፡
በሴቶችም ነገር ያስተቹሃል፡፡ አላህ በእነርሱ ይነግራችኋል፡፡ ያም በመጽሐፉ በእናንተ ላይ የሚነበበው በእነዚያ ለእነርሱ (ከውርስ) የተጻፈላቸውን በማትሰጧቸውና ልታገቧቸው በማትፈልጉት የቲሞች ሴቶች (ይህንን እንዳታደርጉ) ከሕፃናትም ለኾኑት ደካሞች መብታቸውን እንድትሰጡ ለየቲሞችም በትክክል አንድትቆሙ (ይነግራችኋል) በላቸው፡፡ ከበጎም ሥራ ማናቸውንም ብትሠሩ አላህ እርሱን ዐዋቂ ነው፡፡
ሴትም ከባልዋ ጥላቻን ወይም ፊቱን ማዞርን ብታውቅ በመካከላቸው መስማማትን ቢስማሙ በሁለቱ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ መታረቅም መልካም ነው፡፡ ነፍሶችም ንፍገት ተጣለባቸው፡፡ መልካምም ብትሠሩ ብትጠነቀቁም አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
በሴቶችም መካከል ምንም እንኳ ብትጓጉ (በፍቅር) ለማስተካከል አትችሉም፡፡ እንደ ተንጠለጠለችም አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ (ወደምትወዷት) መዘንበልን ሁሉ አትዘንበሉ፡፡ ብታበጁም ብትጠነቀቁም አላህ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
ቢለያዩም አላህ ሁሉንም በችሮታው ያብቃቃቸዋል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ጥበበኛ ነው፡፡
በሰማያት ያለውና በምድርም ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ እነዚያንም ከበፊታችሁ መጽሐፍን የተሰጡትን እናንተንም አላህን ፍሩ በማለት በእርግጥ አዘዝን፡፡ ብትክዱም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ (አትጐዱትም)፡፡ አላህም ተብቃቂ ምስጉን ነው፡፡
በሰማያት ያለውና በምድርም ያለው ሁሉ የአላህ ነው፡፡ መመከያም በአላህ በቃ፡፡
ሰዎች ሆይ!(አላህ) ቢሻ ያስወግዳችኋል፡፡ ሌሎችንም ያመጣል፡፡ አላህም በዚህ ላይ ቻይ ነው፡፡
የቅርቢቱን ዓለም ምንዳ የሚፈልግ የኾነ ሰው አላህ ዘንድ የቅርቢቱና የመጨረሻይቱ ምንዳ አልለ፡፡ አላህም ሰሚ ተመልካች ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቀዋሚዎች በነፈሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሀብታም ወይም ድኻ ቢኾን አላህ በእነርሱ (ከእናንተ) ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ፡፡ ብታጠምሙም ወይም (መመስከርን) ብትተው አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡ በአላህና በመላእክቱም፣ በመጽሐፎቹም፣ በመልክተኞቹም፣ በመጨረሻውም ቀን፣ የካደ ሰው (ከእውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ፡፡
እነዚያ (በሙሳ) ያመኑና ከዚያም (ወይፈንን በመገዛት) የካዱ ከዚያም (በእርሱ) ያመኑ ከዚያም (በዒሳ) የካዱ ከዚያም (በሙሐመድ) ክሕደትን የጨመሩ አላህ ለእነሱ የሚምራቸውና ቅኑን መንገድ የሚመራቸው አይደለም፡፡
መናፍቃንን ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣት ያላቸው መኾኑን አብስራቸው፡፡
እነዚያ ከምእምናን ሌላ ከሓዲዎችን ወዳጆች አድርገው የሚይዙ እነሱ ዘንድ ልቅናን ይፈልጋሉን ልቅናውም ሁሉ ለአላህ ብቻ ነው፡፡
በእናንተም ላይ በመጽሐፉ ውስጥ የአላህን አንቀጾች በርሷ ሲካድባትና በርሷም ሲላገጥባት በሰማችሁ ጊዜ በሌላ ወሬ ውስጥ እስከሚገቡ ድረስ ከእነሱ ጋር አትቀመጡ፡፡ ማለትን በእርግጥ አወረደ፡፡ እናንተ ያንጊዜ ብጤያቸው ናችሁና፡፡ አላህ መናፍቃንን እና ከሓዲዎችን በሙሉ በገሀነም ውስጥ ሰብሳቢ ነውና፡፡
እነዚያ በእናንተ (የጊዜን መዘዋወር) የሚጠባበቁ ናቸው፡፡ ለእናንተም ከአላህ የኾነ አሸናፊነት «ቢኖራችሁ ከእናንተ ጋር አልነበርንምን» ይላሉ፡፡ ለከሓዲዎችም ዕድል ቢኖር «(ከአሁን በፊት) በእናንተ ላይ አልተሾምንምን (እና አልተውናችሁምን) ከምእምናንም (አደጋ) አልከለከልናችሁምን» ይላሉ፡፡ አላህም በትንሣኤ ቀን በመካከላችሁ ይፈርዳል፡፡ አላህም ለከሓዲዎች በምእምናን ላይ መንገድን በፍጹም አያደርግም፡፡
መናፍቃን አላህን ያታልላሉ፡፡ እርሱም አታላያቸው ነው፡፡ (ይቀጣቸዋል)፡፡ ወደ ሶላትም በቆሙ ጊዜ ታካቾች ስዎችን የሚያሳዩ ኾነው ይቆማሉ፡፡ አላህንም ጥቂትን እንጅ አያወሱም፡፡
በዚህ መካከል ወላዋዮች ኾነው (ያሳያሉ)፡፡ ወደእነዚህም ወደእነዚያም አይደሉም፡፡ አላህም ያሳሳተውን ሰው ለእርሱ (የቅንነት) መንገድን በፍፁም አታገኝለትም፡፡
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከምእምናን ሌላ ከሓዲዎችን ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙ፤ ለአላህ በናንተ ላይ ግልጽ ማስረጃዎችን ልታደርጉ ትፈልጋላችሁን
መናፍቃን በእርግጥ ከእሳት በታችኛው አዘቅት ውስጥ ናቸው፡፡ ለእነሱም ረዳትን አታገኝላቸውም፡፡
እነዚያ የተመለሱ (ሥራቸውን) ያሳመሩም፤ በአላህም የተጠበቁ፤ ሃይማኖታቸውንም ለአላህ ፍጹም ያደረጉ ሲቀሩ፡፡ እነዚያስ ከምእምናን ጋር ናቸው፡፡ ለምእምናንም አላህ ታላቅን ምንዳ በእርግጥ ይሰጣል፡፡
ብታመሰግኑና ብታምኑ አላህ እናንተን በመቅጣት ምን ያደርጋል አላህም ወረታን መላሽ ዐዋቂ ነው፡፡
አላህ ከንግግር በክፉው መጮህን ከተበደለ ሰው (ጩኸት) በቀር አይወድም፡፡ አላህ ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡
ደግ ነገርን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት ወይም ከመጥፎ ነገር (ከበደል) ይቅርታ ብታደርጉ አላህ ይቅር ባይ ኃያል ነው፡፡
እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ የሚክዱ፣ በአላህና በመልክተኞቹም መካከል መለየትን የሚፈልጉ፣ «በከፊሉም እናምናለን በከፊሉም እንክዳለን» የሚሉ፣ በዚህም መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፤
እነዚያ በውነት ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ ለከሓዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
እነዚያም በአላህና በመልክተኞቹ ያመኑ ከነርሱም በአንድም መካከል ያልለዩ እነዚያ ምንዳዎቻቸውን በእርግጥ ይሰጣቸዋል፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡
የመጽሐፉ ሰዎች በነሱ ላይ ከሰማይ መጽሐፍን እንድታወርድ ይጠይቁሃል፡፡ ከዚያም የከበደን (ነገር) ሙሳን በእርግጥ ጠይቀዋል፡፡ «አላህንም በግልጽ አሳየን» ብለዋል፡፡ በበደላቸውም መብረቅ ያዘቻቸው፡፡ ከዚያም ተዓምራቶች ከመጡላቸው በኋላ ወይፈኑን (አምላክ አድርገው) ያዙ፡፡ ከዚያም ይቅር አልን፡፡ ሙሳንም ግልጽ ስልጣንን ሰጠነው፡፡
በቃል ኪዳናቸውም ምክንያት የጡርን ተራራ ከበላያቸው አነሳን፡፡ ለእነሱም «ደጃፉን አጎንባሾች ኾናችሁ ግቡ» አልን፡፡ ለእነርሱም «በሰንበት ቀን ትዕዛዝን አትተላልፉ» አልን፡፡ ከእነሱም ከባድን ቃል ኪዳን ያዝን፡፡
ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው፣ በአላህም አንቀጾች በመካዳቸው፣ ነቢያትንም ያለ አግባብ በመግደላቸውና «ልቦቻችን ሽፍኖች ናቸው» በማለታቸው ምክንያት (ረገምናቸው)፡፡ በእውነቱ በክህደታቸው ምክንያት አላህ በርሷ (በልቦቻቸወ) ላይ አተመ፡፡ ስለዚህ ጥቂትን እንጅ አያምኑም፡፡
በመካዳቸውም በመርየም ላይ ከባድ ቅጥፈትን በመናገራቸውም ምክንያት (ረገምናቸው)፡፡
«እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን» በማለታቸውም (ረገምናቸው)፡፡ አልገደሉትም አልሰቀሉትምም፡፡ ግን ለእነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፡፡ እነዚያም በእርሱ ነገር የተለያዩት ከእርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በእርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፡፡ በእርግጥም አልገደሉትም፡፡
ይልቁንስ አላህ (ኢሳን) ወደርሱ አነሳው፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፡፡ በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡
ከእነዚያ ይሁዳውያን ከኾኑትም በተገኘው በደል ሰዎችንም ከአላህ መንገድ በብዙ በመከልከላቸው ምክንያት ለእነሱ ተፈቅደው የነበሩትን ጣፋጮች ምግቦች በእነርሱ ላይ እርም አደረግንባቸው፡፡
ከእርሱ በቁርጥ የተከለከሉ ሲኾኑ አራጣንም በመያዛቸውና የሰዎችን ገንዘቦች ያለ አግባብ (በጉቦ) በመብላታቸውም ምክንያት (የተፈቀደላቸውን እርም አደረግንባቸው)፡፡ ከእነሱም ለከሓዲዎቹ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጀን፡፡
ግን ከነርሱ ውስጥ በዕውቀት የጠለቁትና ምእምናኖቹ በአንተ ላይ በተወረደውና ከአንተም በፊት በተወረደው መጽሐፍ የሚያምኑ ሲኾኑ ሶላትንም ደንቡን ጠብቀው ሰጋጆችን (እናመሰግናለን)፡፡ ዘካንም ሰጪዎቹ በአላህና በመጨረሻዎቹም ቀን አማኞቹ እነዚያ ታላቅ ምንዳን በእርግጥ እንሰጣቸዋለን፡፡
እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን ወደ አንተም አወረድን፡፡ ወደ ኢብራሂምም፣ ወደ ኢስማዒልም፣ ወደ ኢስሓቅም፣ ወደ ያዕቆብም፣ ወደ ነገዶቹም፣ ወደ ዒሳም፣ ወደ አዩብም፣ ወደ ዩኑስም፣ ወደ ሃሩንና፣ ወደ ሱለይማንም አወረድን፡፡ ለዳውድም ዘቡርን ሰጠነው፡፡
ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልክተኞች ባንተ ላይም ያልተረክናቸውን መልክተኞች (እንደላክን ላክንህ)፡፡ አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው፡፡
ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡
ግን አላህ ባንተ ላይ ባወረደው ይመሰክራል፡፡ በዕውቀቱ አወረደው፡፡ መላእክቱም ይመሰክራሉ፡፡ መስካሪም በአላህ በቃ፡፡
እነዚያ የካዱት ከአላህም መንገድ ያገዱት (ከእውነት) የራቀን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳቱ፡፡
እነዚያ የካዱ የበደሉም አላህ የሚምራቸውና (ቅን) መንገድን የሚመራቸው አይደለም፡፡
ግን በውስጧ ዘለዓለም ዘውታሪዎች ሲኾኑ የገሀነምን መንገድ (ይመራቸዋል)፡፡ ይህም በአላህ ላይ ገር ነው፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! መልክተኛው እውነትን ከጌታችሁ አመጣላችሁ፡፡ እመኑም ለናንተ የተሻለ (ይኾናል)፡፡ ብትክዱም (አትጐዱትም)፡፡ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነውና፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፡፡ በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ፡፡ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት «የኹን» ቃሉም ከእርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነው፡፡ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ፡፡ « (አማልክት) ሦስት ናቸው» አትበሉም፡፡ ተከልከሉ፤ ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና፡፡ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው፡፡ መመኪያም በአላህ በቃ፡፡
አልመሲሕ (ኢየሱስ) ለአላህ ባሪያ ከመኾን ፈጽሞ አይጠየፍም፡፡ ቀራቢዎች የኾኑት መላእክትም (አይጠየፉም)፡፡ እርሱን ከመገዛት የሚጠየፍና የሚኮራም ሰው (አላህ) ሁሉንም ወደ እርሱ በእርግጥ ይሰበስባቸዋል፡፡
እነዚያማ ያመኑት መልካሞችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ ከችሮታውም ይጨምርላቸዋል፡፡ እነዚያን የተጠየፉትንና የኮሩትንማ አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ከአላህም ሌላ ለእነሱ ዝምድንና ረዳትን አያገኙም፡፡
እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ዘንድ በእርግጥ አስረጅ መጣላችሁ፤ ወደእናንተም ገላጭ የኾነን ብርሃን (ቁርኣንን) አወረድን፡፡
እነዚያማ በአላህ ያመኑ በርሱም የተጠበቁ ከሱ በኾነው እዝነትና ችሮታ ውስጥ በእርግጥ ያስገባቸዋል፡፡ ወደእርሱም ቀጥተኛ መንገድን ይመራቸዋል፡፡
ይጠይቁሃል በላቸው፡- «ወላጅና ልጅ ሳይኖረው በሚወረስ ሰው አላህ ይነግራችኋል፡፡ ለእርሱ ልጅ የሌለው ሰው ቢሞት ለእርሱም እኅት ብትኖረው ለእርስዋ ከተወው ረጀት ግማሹ አላት፡፡ እርሱም ለርሷ ልጅ የሌላት እንደኾነች (በሙሉ) ይወርሳታል፡፡ ሁለት (እኅቶች ወይም ከሁለት በላይ) ቢኾኑም ከተወው ረጀት ከሦስት ሁለት እጁ አላቸው፡፡ ወንድሞች (ና እኅቶች) ወንዶችና ሴቶች ቢኾኑም ለወንዱ የሁለት ሴቶች ድርሻ ብጤ አለው፡፡ አላህ እንዳትሳሳቱ ለእናንተ ያብራራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡»
Icon