ترجمة سورة مريم

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة مريم باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ከ.ሀ.የ.ዐ.ጸ (ካፍ ሃ ያ ዓይን ሷድ)

(ይህ) ጌታህ ባሪያውን ዘከሪያን በችሮታው ያወሳበት ነው፡፡

ጌታውን የምስጢርን ጥሪ በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ አጥንቴ ደከመ፤ ራሴም በሺበት ተንቀለቀለ፤ አንተም በመለመኔ ጌታዬ ሆይ! (ምንጊዜም) ዕድለ ቢስ አልሆንኩም፡፡

«እኔም ከበኋላዬ ዘመዶቼን በእርግጥ ፈራሁ፡፡ ሚስቴም መካን ነበረች ስለዚህ ከአንተ ዘንድ ለኔ ልጅን ስጠኝ፡፡

«የሚወርሰኝ ከያዕቆብ ቤተሰቦችም የሚወርስ የሆነን (ልጅ)፡፡ ጌታዬ ሆይ! ተወዳጅም አድርገው፡፡»

«ዘከሪያ ሆይ! እኛ በወንድ ልጅ ስሙ የሕያ በኾነ ከዚህ በፊት ሞክሼን ባላደረግንለት እናበስርሃለን» (አለው)፡፡

«ጌታዬ ሆይ! ሚስቴ መካን የነበረች ስትኾን እኔም ከእርጅና ድርቀትን በእርግጥ የደረስኩ ስኾን እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለ፡፡

(ጅብሪል) አለ «(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፡፡ ጌታህ፡- ከአሁን በፊት ምንም ያልነበርከውን የፈጠርኩህ ስኾን እርሱ በእኔ ላይ ቀላል ነው» አለ፡፡

«ጌታዬ ሆይ! (እንግዲያውስ) ለእኔ ምልክትን አድርግልኝ አለ፡፡ ምልክትህ ጤናማ ሆነህ ሳለህ ሦስት ሌሊትን (ከነቀናቸው) ሰዎችን ለማነጋገር አለመቻልህ ነው» አለው፡፡

ከምኩራቡም በሕዝቦቹ ላይ ወጣ፡፡ በ×ትና በማታ (ጌታችሁን) አወድሱ በማለትም ወደነሱ ጠቀሰ፡፡

«የሕያ ሆይ! መጽሐፉን በጥብቅ ያዝ!» (አልነው)፡፡ ጥበብንም በሕፃንነቱ ሰጠነው፡፡

ከእኛም የሆነን ርኅራኄ ንጽሕናንም (ሰጠነው)፡፡ ጥንቁቅም ነበር፡፡

ለወላጆቹም በጎ ሠሪ ነበር፡፡ ትዕቢተኛ አመጸኛም አልነበረም፡፡

በተወለደበት ቀንና በሚሞትበትም ቀን፣ ሕያው ሆኖ በሚነሳበትም ቀን ሰላም በእሱ ላይ ይሁን፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለይች ጊዜ (የሆነውን ታሪኳን) አውሳ፡፡

ከእነሱም መጋረጃን አደረገች፡፡ መንፈሳችንምም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን፡፡ ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት፡፡

«እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፡፡ ጌታህን ፈሪ እንደ ሆንክ (አትቅረበኝ)» አለች፡፡

«እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ» አላት፡፡

«(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራም ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለች፡፡

አላት «(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው፡፡» ጌታሽ «እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፡፡ ለሰዎችም ታምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው» አለ፤ (ነፋባትም)፡፡

ወዲያውኑም አረገዘችው፡፡ በእርሱም (በሆዷ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች፡፡

ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት፡፡ «ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ፡፡ ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ» አለች፡፡

ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት «አትዘኝ፡፡ ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል፡፡

«የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና፡፡

«ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም፡፡ እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም» በይ፡፡

በእርሱም የተሸከመቺው ሆና ወደ ዘመዶቿ መጣች፡፡ «መርየም ሆይ! ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ» አሏት፡፡

«የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፡፡ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት፡፡

ወደርሱም ጠቀሰች፡፡ «በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን!» አሉ፡፡

(ሕፃኑም) አለ «እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፡፡ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል፡፡»

«በየትም ስፍራ ብሆን ብሩክ አድርጎኛል፡፡ በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል፡፡»

«ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)፡፡ ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም፡፡

«ሰላምም በእኔ ላይ ነው፡፡ በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፡፡»

ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡ ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡

ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም፡፡ (ከጉድለት ሁሉ) ጠራ፡፡ ነገርን በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል፡፡

(ዒሳ አለ) «አላህም ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት፡፡ ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው፡፡»

ከመካከላቸውም አሕዛቦቹ በእርሱ ነገር ተለያዩ፡፡ ለእነዚያም ለካዱት ሰዎች ከታላቁ ቀን መጋፈጥ ወዮላቸው፡፡

በሚመጡን ቀን ምን ሰሚ ምንስ ተመልካች አደረጋቸው! ግን አመጸኞች ዛሬ (በዚህ ዓለም) በግልጽ ስህተት ውስጥ ናቸው፡፤

እነሱም (አሁን) በዝንጋቴ ላይ ኾነው ሳሉ እነሱም የማያምኑ ሲኾኑ ነገሩ በሚፈረድበት ጊዜ የቁልጭቱን ቀን አስፈራራቸው፡፡

እኛ ምድርን በእርሷም ላይ ያለውን ሁሉ እኛ እንወርሳለን፡፡ ወደኛም ይመለሳሉ፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ ኢብራሂምንም አውሳ፡፡ እርሱ በጣም እውነተኛ ነቢይ ነበርና፡፡

ለአባቱ ባለ ጊዜ (አስታውስ) «አባቴ ሆይ! የማይሰማንና የማያይን ከአንተም ምንንም የማይጠቅምህን (ጣዖት) ለምን ትግገዛለህ

«አባቴ ሆይ! እኔ ከዕውቀት ያልመጣልህ ነገር በእርግጥ መጥቶልኛልና ተከተለኝ፡፡ ቀጥተኛውን መንገድ እመራሃለሁና፡፡

«አባቴ ሆይ! ሰይጣንን አትግገዛ፡፡ ሰይጣን ለአልረሕማን አመጸኛ ነውና፡፡

«አባቴ ሆይ! እኔ ከአልረሕማን ቅጣት ሊያገኝህ ለሰይጣንም ጓደኛ ልትኾን እፈራለሁ፡፡»

(አባቱም) «ኢብራሂም ሆይ! አንተ አምላኮቼን ትተህ የምትዞር ነህን ባትከለከል በእርግጥ እወግርሃለሁ፡፡ ረዥም ጊዜንም ተወኝ» አለ፡፡

«ደህና ኹን፡፡ ወደፊት ከጌታዬ ምሕረትን እለምንልሃለሁ፡፡ እርሱ ለኔ በጣም ርኅሩኅ ነውና» አለ፡፡

«እናንተንም ከአላህ ሌላ የምትግገዙትንም እርቃለሁ፡፡ ጌታዬንም እግገዛለሁ፡፡ ጌታዬን በመገዛት የማፍር አለመኾኔን እከጅላለሁ፡፡»

እነርሱንም ከአላህ ሌላ የሚግገዙትንም በራቀ ጊዜ ለእርሱ ኢስሐቅንና ያዕቆብን ሰጠነው፡፡ ሁሉንም ነቢይ አደረግንም፡፡

ለእነሱም ከችሮታችን ሰጠናቸው፡፡ ለእነርሱም ከፍ ያለ ምስጉን ዝናን አደረግንላቸው፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ ሙሳንም አውሳ፡፡ እርሱ ምርጥ ነበርና፡፡ መልክተኛ ነቢይም ነበር፡፡

ከጡር ቀኝ ጎን በኩልም ጠራነው፡፡ ያነጋገርነውም ሲኾን አቀረብነው፡፡

ከችሮታችንም ወንድሙን ሃሩንን ነቢይ አድርገን ሰጠነው፡፡

በመጽሐፉ ኢስማዒልንም አውሳ፡፡ እርሱ ቀጠሮን አክባሪ ነበረና፡፡ መልክተኛ ነቢይም ነበር፡፡

ቤተሰቦቹንም በሶላትና በዘካ ያዝ ነበር፡፡ እጌታውም ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡

በመጽሐፉ ኢድሪስንም (ሄኖክን) አውሳ፡፡ እርሱ እውነተኛ ነቢይ ነበርና፡፡

ወደ ከፍተኛም ስፍራ አነሳነው፡፡

እነዚህ (ዐሥሩ) እነዚያ አላህ በእነሱ ላይ የለገሰላቸው ከነቢያት ከአዳም ዘር ከኑሕ ጋር (በመርከቢቱ ላይ) ከጫናቸውም (ዘሮች) ከኢብራሂምና ከእስራኤልም ዘሮች ከመራናቸውና ከመረጥናቸውም የኾኑት የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ፡፡

ከእነሱም በኋላ ሶላትን ያጓደሉ (የተዉ) ፍላጎቶችንም የተከተሉ መጥፎ ምትኮች ተተኩ! የገሀነምንም ሸለቆ በእርግጥ ያገኛሉ፡፡

ግን የተጸጸተና ያመነም በጎንም ሥራ የሠራ ሰው እነዚህ ገነትን ይገባሉ፡፡ አንዳችንም አይበደሉም፡፡

የመኖሪያን ገነቶች ያችን አልረሕማን ለባሮቹ በሩቅ ኾነው ሳሉ ተስፋ ቃል የገባላቸውን (ይገባሉ)፡፡ እርሱ ተስፋው ተፈጻሚ ነውና፤

በእርሷ ሰላምን እንጂ ውድቅን ነገር አይሰሙም፡፡ ለእነሱም በርሷ ውስጥ ጧትም ማታም ሲሳያቸው አላቸው፡፡

ይህች ያቺ ከባሮቻችን ጥንቁቆች ለኾኑት የምናወርሳት ገነት ናት፡፡

(ጂብሪል አለ) «በጌታህም ትእዛዝ እንጅ አንወርድም፡፡ በፊታችን ያለው፣ በኋላችንም ያለው በዚህም መካከል ያለው ሁሉ የርሱ ነው፡፡ ጌታህም ረሺ አይደለም፡፡

(እርሱ) የሰማያትና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው፡፡ እርሱን በመገዛትም ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን

ሰውም «በሞትኩ ጊዜ ወደፊት ሕያው ኾኜ (ከመቃብር) እወጣለሁን» ይላል፡፡

ሰው ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን እኛ የፈጠርነው መኾኑን አያስታውስምን

በጌታህ እንምላለን ሰይጣናት ጋር በእርግጥ እንሰበስባቸዋለን፡፡ ከዚያም በገሀነም ዙሪያ የተንበረከኩ ኾነው፤ በእርግጥ እናቀርባቸዋለን፡፡

ከዚያም ከየጭፍሮቹ ሁሉ ከእነርሱ ያንን (እርሱ) በአልረሕማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የኾነውን እናወጣለን፡፡

ከዚያም እኛ እነዚያን እነርሱ በእርሷ ለመግባት ተገቢ የኾኑትን እናውቃለን፡፡

ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም፡፡ (መውረዱም) ጌታህ የፈረደው ግዴታ ነው፡፡

ከዚያም እነዚያን የተጠነቀቁትን እናድናለን፡፡ አመጸኞቹንም የተንበረከኩ ኾነው በውስጧ እንተዋቸዋለን፡፡

በእነሱም ላይ አንቀጾቻችን ግልጽ መስረጃዎች ኾነው በተነበቡ ጊዜ እነዚያ የካዱት ለእነዚያ ላመኑት «ከሁለቱ ክፍሎች መኖሪያው የሚበልጠውና ሸንጎውም ይበልጥ የሚያምረው ማንኛው ነው» ይላሉ፡፡

ከእነሱም በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች እነሱ በቁሳቁስና በትርኢትም በጣም ያማሩትን ብዙዎችን አጥፍተናል፡፡

«በስሕተት ውስጥ የኾነ ሰው አልረሕማን ለእርሱ ማዘግየትን ያዘገየዋል፡፡ የሚዛትባቸውንም ወይም ቅጣቱን ወይም ሰዓቲቱን ባዩ ጊዜ እርሱ ስፍራው መጥፎና ሰራዊቱ ደካማ የኾነው ሰው ማን እንደኾነ በእርግጥ ያውቃሉ» በላቸው፡፡

እነዚያንም የቀኑትን ሰዎች አላህ ቅንነትን ይጨምርላቸዋል፡፡ መልካሞቹ ቀሪዎች (ሥራዎች) እጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው፡፡ በመመለሻም የተሻሉ ናቸው፡፡

ያንንም በአንቀጾቻችን የካደውን «(በትንሣኤ ቀን) ገንዘብም ልጅም በእርግጥ እስሰጣለሁ ያለውንም አየህን»

ሩቁን ምስጢር ዐወቀን ወይስ አልረሕማን ዘንድ ቃል ኪዳንን ያዘ

ይከልከል (አይሰጠውም)፡፡ የሚለውን ሁሉ በእርግጥ እንጽፋለን፡፡ ለእርሱም ከቅጣት ጭማሬን እንጨምርለታለን፡፡

(አልለኝ) የሚለውንም ሁሉ እንወርሰዋለን፡፡ ብቻውንም ኾኖ ይመጣናል፡፡

ከአላህም ሌላ አማልክትን ለእነሱ መከበሪያ (አማላጅ) እንዲኾኑዋቸው ያዙ፡፡

ይከልከሉ፤ መገዛታቸውን በእርግጥ ይክዷቸዋል፡፡ በእነሱም ላይ ተቃራኒ ይኾኑባቸዋል፡፡

እኛ ሰይጣናትን በከሓዲዎች ላይ (በመጥፎ ሥራ) ማወባራትን የሚያወባሩዋቸው ሲኾኑ የላክን መኾናችንን አለየህምን

በእነሱም (መቀጣት) ላይ አትቻኮል፡፡ ለእነሱ (ቀንን) መቁጠርን እንቆጥርላቸዋለንና፡፡

ምእምናንን የተከበሩ ጭፍሮች ኾነው ወደ አልረሕማን የምንሰበስብበትን ቀን (አስታውስ)፡፡

ከሓዲዎችንም የተጠሙ ኾነው ወደ ገሀነም የምንነዳበትን (ቀን አስታውስ)፡፡

አልረሕማን ዘንድ ቃል ኪዳንን የያዘ ሰው ቢኾን እንጂ ማማለድን አይችሉም፡፡

«አልረሕማንም ልጅን ያዘ (ወለደ)» አሉ፡፡

ከባድ መጥፎን ነገር በእርግጥ አመጣችሁ፡፡

ከእርሱ (ከንግግራቸው) ሰማያት ሊቀደዱ፣ ምድርም ልትሰነጠቅ፣ ጋራዎችም ተንደው ሊወድቁ ይቃረባሉ፡፡

ለአልረሕማን ልጅ አልለው ስለአሉ፡፡

ለአልረሕማን ልጅን መያዝ አይገባውም፡፡

በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ (በትንሣኤ ቀን) ለአልራሕማን ባሪያ ኾነው የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡

በእርግጥ (በዕውቀቱ) ከቧቸዋል፡፡ መቁጠርንም ቆጥሯቸዋል፡፡

ሁሉም በትንሣኤ ቀን ለየብቻ ኾነው ወደርሱ መጪዎች ናቸው፡፡

እነዚያ ያመኑና በጎ ሥራዎችን የሠሩ አልረሕማን ለእነሱ ውዴታን ይሰጣቸዋል፡፡

በምላስህም (ቁርኣንን) ያገራነው በእርሱ ጥንቁቆቹን ልታበስርበት በእርሱም ተከራካሪዎችን ሕዝቦች ልታስፈራራበት ነው፡፡

ከእነሱም በፊት ከክፍለ ዘመናት ሕዝቦች ብዙዎችን አጥፍተናል፡፡ ከእነሱ አንድን እንኳ ታያለህን ወይስ ለእነሱ ሹክሹክታን ትሰማለህን
Icon