ترجمة سورة الكهف

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة الكهف باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ምስጋና ለአላህ ለዚያ መጽሐፉን በውስጡ መጣመምን ያላደረገበት ሲሆን በባሪያው ላይ ላወረደው ይገባው፡፡

ቀጥተኛ ሲሆን ከእርሱ ዘንድ የኾነን ብርቱን ቅጣት ሊያስፈራራበት፣ እነዚያንም በጎ ሥራዎችን የሚሠሩትን ምእመናን ለነሱ መልካም ምንዳ ያላቸው መኾኑን ሊያበስርበት፤ (አወረደው)፡፡

በእርሱ ውስጥ ዘለዓለም የሚቆዩበት ሲኾኑ (ያላቸው መኾኑን)፡፡

እነዚያንም «አላህ ልጅን ይዟል» ያሉትን ሊያስፈራራበት (አወረደው)፡፡

ለእነሱም ለአባቶቻቸውም በርሱ ምንም እውቀት የላቸውም፡፡ ከአፎቻቸው የምትወጣውን ቃል ምን አከበዳት! ውሸትን እንጂ አይናገሩም፡፡

በዚህም ንግግር (በቁርኣን) ባያምኑ በፈለጎቻቸው ላይ በቁጭት ነፍስህን አጥፊ ልትሆን ይፈራልሃል፡፡

እኛ ማንኛቸው ሥራው ያማረ መኾኑን ልንፈትናቸው በምድር ላይ ያለን ሁሉ ለእርሷ ጌጥ አደረግን፤

እኛም በእርሷ ላይ ያለውን (በመጨረሻ) በእርግጥ በቃይ የሌለበት ምልጥ ዐፈር አድራጊዎች ነን፡፡

የዋሻውና የሰሌዳው ባለቤቶች ከተዓምራቶቻችን ሲሆኑ ግሩም መሆናቸውን አሰብክን

ጎበዞቹ ወደ ዋሻው በተጠጉና «ጌታችን ሆይ! ከአንተ ዘንድ እዝነትን ስጠን፤ ለእኛም ከነገራችን ቅንን አዘጋጅልን» ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

በዋሻውም ውስጥ የተቆጠሩን ዓመታት በጆሮዎቻቸው ላይ መታንባቸው፡፡

ከዚያም ከሁለቱ ክፍሎች ለቆዩት ጊዜ ልክ ያረጋገጠው ማንኛው መሆኑን ልናውቅ አስነሳናቸው፡፡

እኛ ወሬያቸውን በአንተ ላይ በእውነት እንተርካለን፡፡ እነሱ በጌታቸው ያመኑ ጎበዞች ናቸው፡፡ መመራትንም ጨመርንላቸው፡፡

(በንጉሣቸው ፊት) በቆሙና «ጌታችን የሰማያትና የምድር ጌታ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክን አንገዛም፡፡ ያን ጊዜ (ሌላን ብናመልክ) ወሰን ያለፈን (ንግግር) በእርግጥ ተናገርን፡፡» ባሉ ጊዜ ልቦቻቸውን አጠነከርን፡፡

«እነዚህ ሕዝቦቻችን ከእርሱ ሌላ አማልክትን ያዙ፤ (እውነተኞች ከኾኑ) በእነርሱ ላይ ግልጽ ማስረጃን ለምን አያመጡም በአላህም ላይ ውሸትን ከሚቀጣጥፍ ይበልጥ በዳይ ማነው» (አሉ)፡፡

«እነርሱንና ያንን ከአላህ ሌላ የሚግገዙትን በተለያችሁ ጊዜ ወደ ዋሻው ተጠጉ፡፡ ጌታችሁ ለእናንተ ከችሮታው ይዘረጋላችኋልና፤ ከነገራችሁም ለእናንተ መጠቃቀሚያን ያዘጋጅላችኋል» (ተባባሉ)፡፡

ፀሐይንም በወጣች ጊዜ ከዋሻቸው ወደ ቀኝ ጎን ስታዘነብል ታያታለህ፡፡ በገባችም ጊዜ እነርሱ ከእርሱ በሰፊው ስፍራ ውስጥ ኾነው ሳሉ ወደ ግራ በኩል ትተዋቸዋለች፡፡ ይህ ከአላህ ተዓምራቶች ነው፡፡ አላህ የሚያቀናው ሰው ቅኑ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የሚያጠመውም ሰው ለርሱ አቅኝን ረዳት አታገኝለትም፡፡

እነሱም የተኙ ሆነው ሳሉ (ዓይኖቻቸው በመከፈታቸው) ንቁዎች ናቸው ብለህ ታስባቸዋለህ፡፡ ወደ ቀኝ ጎንና ወደ ግራ ጎንም እናገላብጣቸዋለን፡፡ ውሻቸውም ሁለት ክንዶቹን በዋሻው በር ላይ ዘርግቷል፡፡ በእነሱ ላይ ዘልቀህ ብታይ ኖሮ የምትሸሽ ኾነህ በዞርክ ነበር፡፡ ከእነሱም በእርግጥ ፍርሃትን በተመላህ ነበር፡፡

እንዲሁም በመካከላቸው እንዲጠያየቁ ቀሰቀስናቸው፡፡ ከእነሱ አንድ ተናጋሪ «ምን ያክል ቆያችሁ» አለ፡፡ «አንድን ቀን ወይም የቀንን ከፊል ቆየን» አሉ፡፡ «ጌታችሁ የቆያችሁትን ጊዜ ልክ ዐዋቂ ነው፡፡ ከዚህችም ብራችሁ ጋር አንዳችሁን ወደ ከተማይቱ ላኩ፡፡ ከምግቦቿ የትኛዋ ንጹሕ መሆኗንም ይመልከት፡፡ ከእርሱም (ከንጹሑ) ምግብን ያምጣላችሁ፡፡ ቀስም ይበል፡፡ በእናንተም አንድንም ሰው አያሳውቅ» አሉ፡፡

«እነሱ በእናንተ ላይ ቢዘልቁ ይቀጠቅጧችኋልና፡፡ ወይም ወደ ሃይማኖታቸው ይመልሷችኋል፡፡ ያንጊዜም በፍጹም ፍላጎታችሁን አታገኙም» (ተባባሉ)፡፡

እንደዚሁም የአላህ ቀጠሮ እርግጠኛ መሆኑን ሰዓቲቱም በርሷ ጥርጣሬ የሌለ መሆኑን ያውቁ ዘንድ በእነርሱ ላይ (ሰዎችን) አሳወቅን፡፡ (አማኞቹና ከሓዲዎቹ) ነገራቸውን በመካከላቸው ሲከራከሩ (የሆነውን አስታውስ፤ ከሓዲዎቹ)፡- «በእነሱ ላይም ግንብን ገንቡ» አሉ፡፡ ጌታቸው በእነሱ ይበልጥ ዐዋቂ ነው፡፡ እነዚያ በነገራቸው ላይ ያሸነፉት (ምእመናን) «በእነሱ ላይ በእርግጥ መስጊድን እንሠራለን» አሉ፡፡

በሩቅ ወርዋሪዎች ሆነው (በጥርጣሬ) «ሦስት ናቸው፤ አራተኛቸው ውሻቸው ነው» ይላሉ፡፡ «አምስት ናቸው፤ ስድስተኛቸው ውሻቸው ነውም» ይላሉ፡፡ «ሰባት ናቸው፤ ስምንተኛቸውም ውሻቸው ነው» ይላሉም፡፡ «ጌታዬ ቁጥራቸውን ዐዋቂ ነው፡፡ ጥቂት (ሰው) እንጂ አያውቃቸውም» በላቸው፡፡ በእነሱም ነገር ግልጽን ክርክር እንጂ (ጠልቀህ) አትከራከር፡፡ በእነሱም ጉዳይ ከነሱ (ከመጽሐፉ ሰዎች) አንድንም አትጠይቅ፡፡

ለማንኛውም ነገር «እኔ ይህንን ነገ ሠሪ ነኝም» አትበል፡፡

«አላህ የሻ እንደ ሆነ (እሰራዋለሁ)» ብትል እንጂ፡፡ በረሳህም ጊዜ ጌታህን አውሳ፡፡ «ጌታዬም ከዚህ ይበልጥ ለቀጥታ የቀረበን ሊመራኝ ይከጀላል» በላቸው፡፡

በዋሻቸውም ውስጥ ሶስት መቶ ዓመታትን ቆዩ፡፡ ዘጠኝንም ጨመሩ፡፡

«አላህ የቆዩትን ልክ ዐዋቂ ነው» በላቸው፡፡ የሰማያትና የምድር ምስጢር የእሱ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ምን ያይ! ምን ይሰማም! ለእነርሱ ከእርሱ በቀር ምንም ረዳት የላቸውም፡፡ በፍርዱም አንድንም አያጋራም፡፡

ከጌታህም መጽሐፍ ወደ አንተ የተወረደውን አንብብ፡፡ ለቃላቶቹ ለዋጭ የላቸውም፡፡ ከእርሱም በቀር መጠጊያን በፍጹም አታገኝም፡፡

ነፍስህንም፤ ከእነዚያ ጌታቸውን ፊቱን (ውዴታውን) የሚሹ ኾነው በጧትና በማታ ከሚግገዙት ጋር አስታግስ፡፡ የቅርቢቱንም ሕይወት ሽልማት የምትሻ ሆነህ ዓይኖችህ ከእነሱ (ወደ ሌላ) አይለፉ፡፡ ልቡንም እኛን ከማስታወስ ያዘነጋነውን ፍላጎቱንም የተከተለውን ነገሩም ሁሉ ወሰን ማለፍ የሆነውን ሰው አትታዘዝ፡፡

«እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡ እኛ ለበደለኞች አጥሯ በእነሱ የከበበ የኾነችውን እሳት አዘጋጅተናል፡፡ (ከጥም) እርዳታንም ቢፈልጉ እንደ ዘይት ዝቃጭ ባለ ፊቶችን በሚጠብስ ውሃ ይረዳሉ፡፡ መጠጡ ከፋ! መደገፊያይቱም ምንኛ አስከፋች!

እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችንም የሠሩ እኛ ሥራን ያሳመረን ሰው ምንዳ አናጠፋም፡፡

እነዚያ ለእነሱ የመኖሪያ ገነቶች ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው አሏቸው፡፡ በእርሷ ውስጥ ከወርቅ የኾኑን አንባሮች ይሸለማሉ፡፡ ከቀጭን ሐርና ከወፍራም ሐርም አረንጓዴን ልብሶች ይለብሳሉ፡፡ በውስጧ በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ የተደገፉ ኾነው (ይቀመጣሉ)፡፡ ምንዳቸው ምን ያምር! መደገፊያይቱም ምንኛ አማረች!

ለእነሱም የሁለትን ሰዎች ምሳሌ ግለጽላቸው፡፡ ለአንደኛቸው (ለከሓዲው) ከወይኖች የኾኑን ሁለት አትክልቶች አደረግንለት፡፡ በዘምባባም አከበብናቸው፡፡ በመካከላቸውም አዝመራን አደረግን፡፡

ሁለቱም አትክልቶች ሰብላቸውን ሰጡ፡፡ ከእርሱም ምንም አላጎደሉም፡፡ በመካከላቸውም ወንዝን አፈሰስን፡፡

ለእርሱም (ከአትክልቶቹ ሌላ ፍሬያማ) ሀብት ነበረው፡፡ ለጓደኛውም (ለአማኙ) እርሱ የሚወዳደረው ሲኾን «እኔ ካንተ በገንዘብ ይበልጥ የበዛሁ በወገንም ይበልጥ የበረታሁ ነኝ» አለው፡፡

እርሱም ነፍሱን በዳይ ኾኖ ወደ አትክልቱ ገባ፡፡ «ይህች ዘለዓለም ትጠፋለች ብዬ አልጠረጥርም» አለ፡፡

«ሰዓቲቱንም ቋሚ (ኋኝ) ናት ብዬ አልጠረጥርም፡፡ (እንደምትለው) ወደ ጌታዬም ብመለስ ከእርሷ የበለጠን መመለሻ በእርግጥ አገኛለሁ» (አለው)፡፡

ጓደኛው (አማኙ) እርሱ ለእርሱ የሚመላለሰው ሲኾን «በዚያ ከዐፈር፣ ከዚያም ከፍትወት ጠብታ ከፈጠረህ፣ ከዚያም ሰው ባደረገህ (አምላክ) ካድክን» አለው፡፡

«እኔ ግን እርሱ አላህ ጌታዬ ነው፤ (እላለሁ)፡፡ በጌታዬም አንድንም አላጋራም፡፡

«አትክልትህንም በገባህ ጊዜ አላህ የሻው ይኾናል፤ በአላህ ቢኾን እንጂ ኀይል የለም፤ አትልም ኖሯልን እኔን በገንዘብም በልጅም ካንተ በጣም ያነስኩ ሆኜ ብታየኝ፡፡

«ጌታዬ ከአትክልትህ የበለጠን ሊሰጠኝ በርሷም (በአትክልትህ) ላይ ከሰማይ መብረቆችን ሊልክባትና የምታንዳልጥ ምልጥ ምድር ልትኾን ይቻላል፡፡

ወይም ውሃው ሠራጊ ሊኾን (ይችላል)፡፡ ያን ጊዜ ለርሱ መፈለግን ፈጽሞ አትችልም» (አለው)፡፡

ሀብቱም ተጠፋ፡፡ እርሷ በዳሶቿ ላይ የወደቀች ኾና በእርሷ ባወጣው ገንዘብ ላይ (እየተጸጸተ) መዳፎቹን የሚያገላብጥና «ወይ ጸጸቴ! በጌታዬ አንድም ባላጋራሁ» የሚል ኾነ፡፡

ለእርሱም ከአላህ ሌላ የሚረዱት ጭፍሮች አልነበሩትም፡፡ ተረጂም አልነበረም፡፡

እዚያ ዘንድ (በትንሣኤ ቀን) ስልጣኑ እውነተኛ ለኾነው አላህ ብቻ ነው፡፡ እርሱ በመመንዳት የበለጠ ፍጻሜንም በማሳመር የበለጠ ነው፡፡

ለእነሱም የቅርቢቱን ሕይወት ምሳሌ አውሳላቸው፡፡ (እርሷ) ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ በእርሱም የምድር በቃይ እንደ ተቀላቀለበት (ከተዋበ በኋላ ደርቆ) ነፋሶችም የሚያበኑት ደቃቅ እንደ ኾነ ብጤ ናት፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

ገንዘብና ወንዶች ልጆች የቅርቢቱ ሕይወት ጌጦች ናቸው፡፡ መልካሞቹም ቀሪዎች (ሥራዎች) እጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው፡፡ በተስፋም በላጭ ናቸው፡፤

ተራራዎችንም የምናስኼድበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ ምድርንም ግልጽ ኾና ታያታለህ፡፡ እንሰበስባቸዋለንም፡፡ ከእነሱም አንድንም አንተውም፡፡

የተሰለፉም ኾነው በጌታህ ላይ ይቀረባሉ፡፡ (ይባላሉም) «በመጀመሪያ ጊዜ እንደ ፈጠርናችሁ (ራቁታችሁን) በእርግጥ መጣችሁን በእውነቱ ለእናንተ (ለመቀስቀሻ) ጊዜን አናደርግም መስሏችሁ ነበር፡፡»

(ለሰው ሁሉ) መጽሐፉም ይቀርባል፡፡ ወዲያውም ከሓዲዎችን በውስጡ ካለው ነገር ፈሪዎች ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ «ዋ ጥፋታችን! ለዚህ መጽሐፍ (ከሥራ) ትንሽንም ትልቅንም የቆጠራት ቢኾን እንጂ የማይተወው ምን አለው» ይላሉም፡፡ የሰሩትንም ነገር ሁሉ ቀራቢ ኾኖ ያገኙታል፡፡ ጌታህም አንድንም አይበድልም፡፡

ለመላእክትም ለአደም ስገዱ ባልናቸው ጊዜ (የኾነውን አስታውስ)፡፡ ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ ከጋኔን (ጎሳ) ነበር፡፡ ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ፡፡ እርሱንና ዘሮቹን እነርሱ ለእናንተ ጠላቶች ሲኾኑ ከእኔ ላይ ረዳቶች አድርጋችሁ ትይዛላችሁን ለበዳዮች ልዋጭነቱ ከፋ!

የሰማያትንና የምድርን አፈጣጠር አላሳየኋቸውም፡፡ የነፍሶቻቸውንም አፈጣጠር (እንደዚሁ)፡፡ አሳሳቾችንም ረዳቶች አድርጌ የምይዝ አይደለሁም፡፡

«እነዚያንም (አምላክ) የምትሏቸውን ተጋሪዎቼን ጥሩ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ ይጠሯቸዋልም ግን አይመልሱላቸውም፡፡ በመካከላቸውም መጥፊያን ስፍራ (ገሀነምን) አደረግን፡፡

ከሓዲዎችም እሳትን ያያሉ፡፡ እነርሱም በውስጧ ወዳቂዎች መኾናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ከእርሷም መሸሻን አያገኙም፡፡

በዚህም ቁርኣን ውስጥ ከየምሳሌው ሁሉ ለሰዎች መላልሰን ገለጽን፡፡ ሰውም ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ክርክረ ብዙ ነው፡፡

ሰዎችንም መምሪያ በመጣላቸው ጊዜ ከማመንና ጌታቸውንም ምሕረትን ከመለመን የመጀመሪዎቹ (ሕዝቦች) ልማድ (መጥፋት) ልትመጣባቸው ወይም ቅጣቱ በያይነቱ ሊመጣባቸው (መጠባበቅ) እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም፡፡

መልክተኞችንም አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች ኾነው እንጂ አንልክም፡፡ እነዚያ የካዱትም በውሸት እውነቱን በእሱ ሊያበላሹ ይከራከራሉ፡፡ አንቀጾቼንና በእርሱ የተስፈራሩበትንም ነገር ማላገጫ አድርገው ያዙ፡፡

በጌታውም አንቀጾች ከተገሰጸና ከእርሷ ከዞረ እጆቹም ያስቀደሙትን ነገር ከረሳ ሰው ይበልጥ በዳይ ማነው እኛ በልቦቻቸው ላይ እንዳያውቁት ሺፋኖችን በጆሮዎቻቸውም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን፡፡ ወደ መመራትም ብትጠራቸው ያን ጊዜ ፈጽሞ አይምመሩም፡፡

ጌታህም በጣም መሃሪው የእዝነት ባለቤቱ ነው፡፡ በሠሩት ሥራ ቢይዛቸው ኖሮ ቅጣቱን ለእነሱ ባስቸኮለባቸው ነበር፡፡ ግን ለእነሱ ከእርሱ ሌላ መጠጊያን ፈጽሞ የማያገኙበት ቀጠሮ አላቸው፡፡

እነዚህ ከተሞችም በበደሉ ጊዜ አጠፋናቸው፡፡ ለመጥፊያቸውም የተወሰነ ጊዜን አደረግን፡፡

ሙሳም ለወጣቱ «የሁለቱን ባሕሮች መገናኛ እስከምደርስ ወይም ብዙን ጊዜ እስከምኼድ ድረስ (ከመጓዝ) አልወገድም» ያለውን (አስታውስ)፡፡

የሁለቱን መገናኛ በደረሱም ጊዜ ዐሣቸውን ረሱ፡፡ (ዐሣው) መንገዱንም በባህሩ ውስጥ ቀዳዳ አድርጎ ያዘ፡፡

ባለፉም ጊዜ ለወጣቱ «ምሳችንን ስጠን፡፡ ከዚህ ጉዟችን በእርግጥ ድካምን አግኝተናልና» አለ፡፡

«አየህን ወደ ቋጥኝዋ በተጠጋን ጊዜ እኔ ዐሣውን ረሳሁ፡፡ ማስታወሱንም ሰይጣን እንጂ ሌላ አላስረሳኝም፡፡ በባሕሩም ውስጥ መንገዱን አስደናቂ (መንገድ) አድርጎ ያዘ» አለ፡፡

(ሙሳም) ይህ እንፈልገው የነበርነው ነው አለው፡፡ በፈለጎቻቸውም ላይ እየተከተሉ ተመለሱ፡፡

ከባሮቻችንም ከእኛ ዘንድ ችሮታን የሰጠነውን ከእኛም ዘንድ ዕውቀትን ያስተማርነውን አንድን ባሪያ (ኸድርን) አገኙ፡፡

ሙሳ ለእርሱ «ከተማርከው ነገር ቀጥተኛን (ዕውቀት) ታስተምረኝ ዘንድ ልከተልህን» አለው፡፡

(ባሪያውም) አለ «አንተ ከእኔ ጋር መታገስን በጭራሽ አትችልም፡፡

«በዕውቀትም በእርሱ ባላዳረስከው ነገር ላይ እንዴት ትታገሳለህ»

(ሙሳ) «አላህ የሻ እንደ ኾነ ታጋሽና ላንተ ትዕዛዝን የማልጥስ ኾኜ ታገኘኛለህ» አለው፡፡

«ብትከተለኝም ለአንተ ከእርሱ ማውሳትን እስከምጀምርልህ ድረስ ከምንም ነገር አትጠይቀኝ» አለው፡፡

ኼዱም፡፡ በመርከቢቱም በተሳፈሩ ጊዜ ቀደዳት፡፡ «ባለ ቤቶቿን ልታሰጥም ቀደድካትን ትልቅ ነገርን በእርግጥ ሠራህ» አለው፡፡

«አንተ ከኔ ጋር ትእግሥትን ፈጽሞ አትችልም አላልኩምን» አለ፡፡

«በረሳሁት ነገር አትያዘኝ፡፡ ከነገሬም ችግርን አታሸክመኝ» አለው፡፡

(ወርደው) ተጓዙም፡፡ ወጣትንም ልጅ ባገኙና በገደለው፤ «ጊዜ ያለ ነፍስ (መግደል) ንጹሕን ነፍስ ገደልክን በእርግጥ መጥፎን ነገር ሥራህ» አለው፡፡

«አንተ ከኔ ጋር ትእግሥትን ፈጽሞ አትችልም አላልኩህምን» አለ፡፡

«ከርሷ (ከአሁኒቱ ጊዜ) በኋላ ከምንም ነገር ብጠይቅህ አትጎዳኘኝ፡፡ ከእኔ የይቅርታን መጨረሻ በእርግጥ ደርሰሃል» አለው፡፡

ኼዱም፡፡ ወደ አንዲት ከተማ ሰዎች በመጡም ጊዜ ነዋሪዎቿን ምግብን ጠየቁ፡፡ ከማስተናገዳቸውም እምቢ አሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ለመውደቅ የተቃረበን ግድግዳ አገኙ፡፡ (ኸድር) አቆመውም፡፡ (ሙሳም) «በሻህ ኖሮ በእርሱ ላይ ዋጋን በተቀበልክ ነበር» አለው፡፡

(ኸድር) አለ «ይህ በእኔና በአንተ መካከል መለያያ ነው፡፡ በእርሱ ላይ መታገስን ያልቻልክበትን ፍች እነግርሃለሁ፡፡

«መርከቢቱማ በባሕር ለሚሠሩ ምስኪኖች ነበረች፡፡ ከኋላቸውም መርከብን ሁሉ በቅሚያ የሚይዝ ንጉሥ ነበረና፤ (እንዳይቀማቸው) ላነውራት ፈቀድኩ፡፡

«ወጣቱም ልጅማ ወላጆቹ ምእመናን ነበሩ፡፡ (ቢያድግ) ትእቢትንና ክህደትንም የሚያስገድዳቸው መኾኑን ፈራን፡፡

«ጌታቸውም በንጹሕነት ከእርሱ በላጭን በእዝነትም ከእርሱ በጣም ቀራቢን ልጅ ሊለውጥላቸው ፈለግን፡፡

«ግድግዳውማ በከተማይቱ ውስጥ የነበሩ የሁለት የቲሞች ወጣቶች ነበር፡፡ በሥሩም ለእነርሱ የኾነ (የተቀበረ) ድልብ ነበረ፡፡ አባታቸውም መልካም ሰው ነበር፡፡ ጌታህም ለአካለ መጠን እንዲደርሱና ከጌታህ ችሮታ ድልባቸውን እንዲያወጡ ፈቀደ፡፡ በፈቃዴም አልሠራሁትም፡፡ ይህ በእርሱ ላይ መታገስን ያልቻልከው ነገር ፍች ነው» (አለው)፡፡

ከዙልቀርነይንም ይጠይቁሃል፡፡ «በእናንተ ላይ ከእርሱ ወሬን አነባለሁ፤» በላቸው፡፡

እኛ ለእርሱ በምድር አስመቸነው፡፡ ከነገሩም ሁሉ (መዳረሻ) መንገድን ሰጠነው፡፡

መንገድንም (ወደ ምዕራብ) ተከተለ፡፡

ወደ ፀሐይ መግቢያም በደረሰ ጊዜ ጥቁር ጭቃ ባላት ምንጭ ውስጥ ስትጠልቅ አገኛት፡፡ ባጠገቧም ሕዝቦችን አገኘ፡፡ «ዙልቀርነይን ሆይ! ወይም (በመግደል) ትቀጣለህ ወይም በእነርሱ መልካም ነገርን (መማረክን) ትሠራለህ» አልነው፡፤

«የበደለውን ሰውማ ወደፊት እንቀጣዋለን፡፡ ከዚያም ወደ ጌታው ይመለሳል፡፡ ብርቱንም ቅጣት ይቀጣዋል» አለ፡፡

«ያመነም ሰውማ መልካምንም ሥራ የሠራ ለእርሱ ከምንዳ በኩል መልካሚቱ (ገነት) አለችው፡፡ ለእርሱም ከትእዛዛችን ገርን ነገር እናዘዋለን» (አለ)፡፡

ከዚያም መንገድን (ወደ ምሥራቅ) ቀጠለ፡፡

ወደ ፀሐይ መውጫ በደረሰም ጊዜ ለእነሱ ከበታችዋ መከለያን ባላደረግንላቸው ሕዝቦች ላይ ስትወጣ አገኛት፡፡

(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፡፡ እርሱም ዘንድ ባለው ነገር ሁሉ በእርግጥ በዕውቀት ከበብን፡፡

ከዚያም (ወደ ሰሜን አቅጣጫ) መንገድን ቀጠለ፡፡

በሁለቱ ጋራዎችም መካከል በደረሰ ጊዜ በአቅራቢያቸው ንግግርን ለማወቅ የማይቃረቡ ሕዝቦችን አገኘ፡፡

«ዙልቀርነይን ሆይ! የእጁጅና መእጁጅ በምድር ላይ አበላሺዎች ናቸውና በእኛና በእነሱ መካከል ግድብን ታደርግልን ዘንድ ግብርን እናድርግልህን» አሉ፡፡

አለ «ጌታዬ በእርሱ ያስመቸኝ ሀብት (ከናንተ ግብር) በላጭ ነው፡፡ ስለዚህ በጉልበት እገዙኝ፡፡ በእናንተና በእነሱ መካከል ብርቱን ግድብ አደርጋለሁና፡፡

«የብረትን ታላላቅ ቁራጮች ስጡኝ» (አላቸው)፡፡ በሁለቱ ኮረብታዎች (ጫፍ) መካከልም ባስተካከለ ጊዜ አናፉ አላቸው፡፡ (ብረቱን) እሳትም ባደረገው ጊዜ «የቀለጠውን ነሐስ ስጡኝ፤ በርሱ ላይ አፈስበታለሁና» አላቸው፡፡

(የእጁጅና መእጁጅ) ሊወጡትም አልቻሉም፡፡ ለእርሱ መሸንቆርንም አልቻሉም፡፡

«ይህ (ግድብ) ከጌታዬ ችሮታ ነው፡፡ የጌታየም ቀጠሮ በመጣ ጊዜ ትክክል ምድር ያደርገዋል፡፡ የጌታዬም ቀጠሮ ተረጋገጠ ነው» አለ፡፡

በዚያም ቀን ከፊላቸውን በከፊሉ የሚቀላቀሉ አድርገን እንተዋቸዋለን፡፡ በቀንዱም ይነፋል መሰብሰብንም እንሰበስባቸዋለን፡፤

ገሀነምንም በዚያ ቀን ለከሓዲዎች በጣም ማቅረብን እናቀርባታለን፡፡

ለዚያ ዓይኖቻቸው ከግሳጼዬ በሺፋን ውስጥ ለነበሩትና መስማትንም የማይችሉ ለነበሩት (እናቀርባታለን)፡፡

እነዚያ የካዱት ባሮቼን ከእኔ ሌላ አማልክት አድርገው መያዛቸውን (የማያስቆጣኝ አድርገው) አሰቡን እኛ ገሀነምን ለከሓዲዎች መስተንግዶ አዘጋጅተናል፡፡

«በሥራዎች በጣም ከሳሪዎቹን እንንገራችሁን» በላቸው፡፡

እነዚያ እነሱ ሥራን የሚያሳምሩ የሚመስላቸው ሲሆኑ በቅርቢቱ ሕይወት ሥራቸው የጠፋባቸው ናቸው፡፡

እነዚያ እነርሱ በጌታቸው ማስረጃዎችና በመገናኘቱ የካዱት ናቸው፡፡ ሥራዎቻቸውም ተበላሹ፡፡ ለእነሱም በትንሣኤ ቀን (ጠቃሚ) ሚዛንን አናቆምላቸውም፡፡

(ነገሩ) ይህ ነው፡፡ በክህደታቸው አንቀጾቼንና መልክተኞቼንም መሳለቂያ አድርገው በመያዛቸው ፍዳቸው ገሀነም ነው፡፡

እነዚያ ያመኑና መልካም ሥራዎችን የሠሩ የፊርደውስ ገነቶች ለእነሱ መስፈሪያ ናቸው፡፡

በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ከእርሷ መዛወርን የማይፈልጉ ሲኾኑ፤ (መስፈሪያቸው ነው)፡፡

«ባሕሩ ለጌታዬ ቃላት (መጻፊያ) ቀለሞችን በሆነ ኖሮ ብጤውን ጭማሪ ብናመጣም እንኳን የጌታዬ ቃላት ከማለቋ በፊት ባሕሩ ባለቀ ነበር» በላቸው፡፡

«እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደኔ የሚወረድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፡፡ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፡፡ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ» በላቸው፡፡
Icon