ترجمة سورة القيامة

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة القيامة باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


(ነገሩ ከሓዲዎች እንደሚሉት) አይደለም፡፡ በትንሣኤ ቀን እምላለሁ፡፡

(ራሷን) ወቃሽ በኾነች ነፍስም እምላለሁ፡፡ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)፡፡

ሰው አጥንቶቹን አለመሰብሰባችንን ያስባልን?

አይደለም ጣቶቹን (ፊት እንደ ነበሩ) በማስተካከል ላይ ቻዮች ስንኾን (እንሰበስባቸዋለን)፡፡

ይልቁንም ሰው በፊቱ ባለው ነገር (በትንሣኤ) ሊያስተባብል ይፈልጋል፡፡

«የትንሣኤው ቀን መቼ ነው?» ሲል ይጠይቃል፡፡

ዓይንም በዋለለ ጊዜ፡፡

ጨረቃም በጨለመ ጊዜ፡፡

ፀሐይና ጨረቃም በተሰበሰቡ ጊዜ፡፡

«ሰው በዚያ ቀን መሸሻው የት ነው?» ይላል፡፡

ይከልከል፤ ምንም መጠጊያ የለም፡፡

በዚያ ቀን መርጊያው ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡

ሰው በዚያ ቀን ባስቀደመውና ባስቆየው ሁሉ ይነገራል፡፡

በእርግጥም ሰው በነፍሱ ላይ አስረጅ ነው፡፡ (አካሎቹ ይመሰክሩበታል)፡፡

ምክንያቶቹን ሁሉ ቢያመጣም እንኳ (አይሰማም)፡፡

በእርሱ (በቁርኣን ንባብ) ልትቸኩል ምላስህን በእርሱ አታላውስ፡፡

(በልብህ ውስጥ) መሰብሰቡና ማንበቡ በእኛ ላይ ነውና፡፡

ባነበብነውም ጊዜ (ካለቀ በኋላ) ንባቡን ተከተል፡፡

ከዚያም ማብራራቱ በእኛ ላይ ነው፡፡

(ከመጣደፍ) ተከልከል፡፡ ይልቁንም (ሰዎች) ፈጣኒቱን (ዓለም) ትወዳላችሁ፡፡

መጨረሻይቱንም (ዓለም) ትተዋላችሁ፡፡ (አትዘጋጁላትም)፡፡

ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው፡፡

ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው፡፡

ፊቶችም በዚያ ቀን ጨፍጋጊዎች ናቸው፡፡

በርሳቸውም ዐደጋ እንደሚሠራባቸው ያረጋግጣሉ፡፡

ንቁ (ነፍስ) ብሪዎችን በደረሰች ጊዜ፤

«አሻሪው ማነው?» በተባለም ጊዜ፡፡

(ሕመምተኛው) እርሱ (የሰፈረበት ነገር ከዚህ ዓለም) መልለየት መኾኑን ባረጋገጠም ጊዜ፡፡

ባትም በባት በተጣበቀች ጊዜ፡፡

በዚያ ቀን መነዳቱ ወደ ጌታህ (ፍርድ) ነው፡፡

አላመነምም አልሰገደምም፡፡

ግን አስተባበለ፤ (ከእምነት) ዞረም፡፡

ከዚያም እየተንጎባለለ ወደ ቤተሰቡ ኼደ፡፡

የምትጠላውን ነገር (አላህ) ያስከትልህ፡፡ ለአንተ ተገቢህም ነው፡፡

ከዚያም ጥፋት ይጠጋህ ለአንተ የተገባህም ነው፡፡

ሰው ስድ ኾኖ መትተውን ይጠረጥራልን?

የሚፈሰስ ከኾነ የፍትወት ጠብታ አልነበረምን?

ከዚያም የረጋ ደም ኾነ (አላህ ሰው አድርጎ) ፈጠረውም፡፡ አስተካከለውም፡፡

ከእርሱም ሁለት ዓይነቶችን ወንድና ሴትን አደረገ፡፡

ይህ (ጌታ) ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ አይደለምን?
Icon