ترجمة سورة الفرقان

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة الفرقان باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ያወረደው (አምላክ) ክብርና ጥራት ተገባው፡፡

(እርሱ) ያ የሰማያትና የምድር ንግሥና የእርሱ ብቻ የኾነ፣ ልጅንም ያልያዘ፣ በንግሥናውም ተጋሪ የሌለው፣ ነገሩንም ሁሉ የፈጠረና በትክክልም ያዘጋጀው ነው፡፡

(ከሓዲዎች) ከእርሱም ሌላ ምንንም የማይፈጥሩን፣ እነርሱም የሚፈጠሩን፣ ለነፍሶቻቸውም ጉዳትን ለመከላከል ጥቅምንም ለማምጣት የማይችሉን ሞትንና ሕይወትንም መቀስቀስንም የማይችሉን፣ አማልክት ያዙ፡፡

እነዚያም የካዱት ይህ (ቁርኣን ሙሐመድ) የቀጠፈው በእርሱም ላይ ሌሎች ሕዝቦች ያገዙት የኾነ ውሸት እንጂ ሌላ አይደለም አሉ፡፡ በእርግጥም በደልንና እብለትን ሠሩ፡፡

አሉም «የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ተረቶች ናት፡፡ አስጻፋት፡፡ እርሷም በእርሱ ላይ ጧትና ማታ ትነበብለታለች፡፡»

«ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፡፡ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡

ለዚህም መልክተኛ ምግብን የሚበላ፣ በገበያዎችም የሚኼድ ሲኾን ምን (መልክተኛነት) አለው ከርሱ ጋር አስፈራሪ ይኾን ዘንድ ወደርሱ መልአክ (ገሃድ) አይወረድም ኖሯልን አሉ፡፡

«ወይም ወደእርሱ ድልብ አይጣልለትምን ወይም ከእርሷ የሚበላላት አትክልት ለእርሱ አትኖረውምን» (አሉ)፡፡ በዳዮቹም (ላመኑት) «የተደገመበትን ሰው እንጂ ሌላ አትከተሉም» አሉ፡፡

ላንተ ምሳሌዎችን እንዴት እንዳደረጉልህና እንደተሳሳቱ ተመልከት፡፡ (ወደ እውነት ለመድረስ) መንገድንም አይችሉም፡፡

ያ ቢሻ ከዚህ (ካሉት) የተሻለን ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን አትክልቶች ላንተ የሚያደርግልህ ሕንጻ ቤቶችንም ላንተ የሚያደርግልህ ጌታ ችሮታው በዛ፡፡

ይልቁንም በትንሣኤ አስተባበሉ፡፡ በትንሣኤ ላስተባበለም ሰው ሁሉ ነዳጅን እሳት አዘጋጅተናል፡፡

ከሩቅ ስፍራ ባየቻቸው ጊዜ ለእርሷ የቁጭት መገንፈልንና ማናፋትን ይሰማሉ፡፡

እጅ ከፍንጅ የታሠሩ ኾነውም ከእርሷ በጠባብ ስፍራ በተጣሉ ጊዜ በዚያ ስፍራ ጥፋትን ይጠራሉ፤ (ዋ ጥፋታችን ይላሉ)፡፡

፡-ዛሬ አንድን ጥፋት ብቻ አትጥሩ ብዙንም ጥፋት ጥሩ (ይባላሉ)፡፡

(እንዲህ) በላቸው «ይህ የተሻለ ነውን ወይስ ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጧት የዘለዓለሟ ገነት» ለእነርሱ ምንዳና መመለሻ ኾነች፡፡

ለእነሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ኾነው የሚፈልጉት ሁሉ አልላቸው፡፡ (ይህም) ተስፋ ከጌታህ ተለማኝ ተስፋ ነው፡፡

እነርሱንና ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸውንም የሚሰበስብባቸውንና «እናንተ እነዚህን ባሮቼን አሳሳታችሁን ወይስ እነሱው መንገድን ሳቱ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡

«ጥራት ይገባህ፤ ካንተ ሌላ ረዳቶችን ልንይዝ ለእኛ ተገቢያችን አልነበረም፡፡ ግን እነርሱንም አባቶቻቸውንም መገንዘብን እስከተዉ ድረስ አጣቀምካቸው፡፡ ጠፊ ሕዝቦችም ኾኑ» ይላሉ፡፡

በምትሉትም (አማልክቶቻችሁ) አስዋሹዋችሁ፡፡ ቅጣቴን መገፍተርንም መርዳትንም አትችሉም፡፡ ከእናንተም የሚበድለውን ታላቅን ቅጣት እናቀምሰዋለን፤ (ይባላሉ)፡፡

ከአንተ በፊትም ከመልክተኞች እነሱ በእርግጥ ምግብን የሚበሉ በገበያዎችም የሚኼዱ ኾነው በስተቀር አልላክንም፡፡ ከፊላችሁንም ለከፊሉ ፈተና አድርገናል፡፡ ትታገሳላችሁን ጌታህም ተመልካች ነው፡፡

እነዚያም መገናኘታችንን የማይፈሩት በእኛ ላይ ለምን መላእክት አልወረደም፡፡ ወይም ጌታችንን ለምን አናይም አሉ፡ በነፍሶቻቸው ውስጥ በእርግጥ ኮሩ፡፡ ታላቅንም አመጽ አመፁ፡፡

መላእክትን በሚያዩበት ቀን በዚያ ጊዜ ለአመጸኞች ምስራች የላቸውም፡፡ «የተከለከለ ክልክልም አድርገን» ይላሉ፡፡

ከሥራም ወደ ሠሩት እናስባለን፡፡ የተበተነ ትቢያም እናደርገዋለን፡፡

የገነት ሰዎች በዚያ ቀን በመርጊያ የተሻሉ በማረፊያም በጣም ያማሩ ናቸው፡፡

ሰማይም በደመና የምትቀደድበትንና መላእክትም መወረድን የሚወርድበትን ቀን (አስታውስ)፡፡

እውነተኛው ንግሥና በዚያ ቀን ለአልራሕማን ብቻ ነው፡፡ በከሓዲዎችም ላይ አስቸጋሪ ቀን ነው፡፡

በዳይም «ከመልክተኛው ጋር ቀጥተኛን መንገድ ይዤ በኾነ ዋ ምኞቴ!» እያለ (በጸጸት) ሁለት እጆቹን የሚነክስበትን ቀን (አስታውስ)፡፡

«ዋ ጥፋቴ! እገሌን ወዳጅ ባልያዝኩ ኖሮ እመኛለሁ፡፡

(የእምነት ቃልን) ከመጣልኝ በኋላ ከማስታወስ በእርግጥ አሳሳተኝ» (ይላል)፡፡ ሰይጣንም ለሰው አጋላጭ ነው፡፡

መልክተኛውም «ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ ይህንን ቁርኣን የተተወ ነገር አድርገው ያዙት» አለ፡፡

እንደዚሁም ለነቢዩ ሁሉ ከአመጸኞች የኾነ ጠላትን አድርገናል፡፡ መሪና ረዳትም በጌታህ በቃ፡፡

እነዚያ የካዱትም «ቁርኣን በእርሱ ላይ ለምን በጠቅላላ አንድ ጊዜ አልተወረደም» አሉ፡፡ እንደዚሁ በእርሱ ልብህን ልናረጋ (ከፋፍለን አወረድነው)፡፡ ቀስ በቀስ መለያየትንም ለየነው፡፡

በጥያቄም አይመጡብህም እውነተኛውን (መልስ) መልካምን ፍችም የምናመጣልህ ብንኾን እንጅ፡፡

እነዚያ በፊቶቻቸው ለይ (እየተጎተቱ) ወደ ገሀነም የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ እነዚያ ስፍራቸው የከፋ መንገዳቸውም የጠመመ ናቸው፡፡

በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው፡፡ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን ረዳት አደረግንለት፡፡

«ወደእነዚያም በተዓምራቶቻችን ወደ አስተባበሉት ሕዝቦች ኺዱ» አልናቸው፡፡ (አስዋሿቸውም) ማጥፋትንም አጠፋናቸው፡፡

የኑሕን ሰዎችም መልክተኞችን ባስተባበሉ ጊዜ አሰጠምናቸው፡፡ ለሰዎችም መገሰጫ አደረግናለቸው፡፡ ለበደለኞችም አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡

ዓድንም ሰሙድንም የረስን ሰዎችም በዚህ መካከል የነበሩትንም ብዙን የክፍለ ዘመናት ሕዝቦች (አጠፋን)፡፡

ሁሉንም (ገሠጽን) ለእነሱ ምሳሌዎችን ገለጽን፡፡ ሁሉንም ማጥፋትን አጠፋናቸውም፡፡

በዚያችም ክፉ ዝናምን በተዘነመችው ከተማ ላይ (የመካ ከሐዲዎች) በእርግጥ መጥተዋል፡፡ የሚያዩዋት አልነበሩምን በእውነቱ መቀስቀስን የማይፈሩ ነበሩ፡፡

ባዩህም ጊዜ ያ አላህ መልእክተኛ አድርጎ የላከው ይህ ነውን እያሉ መሳለቂያ እንጂ ሌላ አያደርጉህም፡፡

«እነሆ በእርሷ ላይ መታገሳችን ባልነበረ ኖሮ ከአማልክቶቻችን ሊያሳስተን ቀርቦ ነበር» (ሲሉም ይሳለቃሉ)፡፡ ወደፊትም ቅጣቱን በሚያዩ ጊዜ መንገድን በጣም ተሰሳቹ ማን እንደኾነ በእርግጥ ያውቃሉ፡፡

ፍላጎቱን አምላኩ አድርጎ የያዘውን ሰው አየህን አንተ በእርሱ ላይ ጠባቂ ትኾናለህን

ይልቁንም አብዛኛዎቻቸው የሚሰሙ ወይም የሚያውቁ መኾናቸውን ታስባለህን እነርሱ እንደ እንስሳዎች እንጂ ሌላ አይደሉም፡፡ ከቶውንም እነሱ ይልቅ መንገድን የተሳሳቱ ናቸው፡፡

ወደ ጌታህ (ሥራ) ጥላን እንዴት እንደ ዘረጋ አላየህምን በሻም ኖሮ የረጋ ባደረገው ነበር፡፡ ከዚያም ፀሐይን በእርሱ ላይ ምልክት አደረግን፡፡

ከዚያም ቀስ በቀስ ወደእኛ ሰብሰብነው፡፡

እርሱም ያ ለእናንተ ሌሊትን ልብስ እንቅልፍንም ማረፊያ ያደረገ፤ ቀንንም መበተኛ ያደረገላችሁ ነው፡፡

እርሱም ያ ነፋሶችን አብሳሪዎች ሲኾኑ ከዝናሙ በስተፊት የላከ ነው፡፡ ከሰማይም አጥሪ ውሃን አወረድን፡፡

በእርሱ የሞተችን አገር ሕያው ልናደርግበት ከፈጠርነውም ፍጡር እንስሳዎችንና ብዙ ሰዎችንም ልናጠጣው (አወረድነው)፡፡

(ጸጋችንን) ይገነዘቡም ዘንድ በመካከላቸው ከፋፈልነው፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች ክህደትን እንጂ እንቢ አሉ፡፡

በሻንም ኖሮ በየከተማይቱ አስፈራሪን በላክን ነበር፡፡

ከሓዲዎችንም አትታዘዛቸው፡፡ በእርሱም (በቁርኣን) ታላቅን ትግል ታገላቸው፡፡

እርሱም ያ ሁለቱን ባሕሮች አጎራብቶ የለቀቀ ነው፡፡ ይህ ጥምን የሚቆርጥ ጣፋጭ ነው፡፡ ይህም የሚመረግግ ጨው ነው፡፡ በመካከላቸውም (ከመቀላቀል) መለያንና የተከለለን ክልል ያደረገ ነው፡፡

እርሱም ያ ከውሃ ሰውን የፈጠረ፣ የዝምድናና የአማችም ባለቤት ያደረገው ነው፡፡ ጌታህም ቻይ ነው፡፡

ከአላህም ሌላ የማይጠቅማቸውንና የማይጎዳቸውን ይግገዛሉ፤ ከሓዲም በጌታው ላይ (በማመጽ ለሰይጣን) ረዳት ነው፡፡

አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን እንጂ አልላክንህም፡፡

«በእርሱ ላይ ዋጋን በፍጹም አልጠይቃችሁም፡፡ ግን ወደ ጌታው (መልካም) መንገድን ለመያዝ የሻ ሰው (ይሥራ)» በላቸው፡፡

በዚያም በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ፡፡ ከማመስገንም ጋር አጥራው፡፡ በባሮቹ ኀጢኣቶችም ውስጠ ዐዋቂ በእርሱ በቃ፡፡

ያ ሰማያትና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ፣ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ሥልጣኑ) የተደላደለ አልረሕማን ነው፡፡ ከእርሱም ዐዋቂን ጠይቅ፡፡

ለእነርሱም ለአልረሕማን ስገዱ በተባሉ ጊዜ አልረሕማን ማነው ለምታዘን (እና ለማናውቀው) እንሰግዳለን ይላሉ፡፡ (ይህ) መራቅንም ጨመራቸው፡፡

ያ በሰማይ ቡሩጆችን ያደረገና በእርሷም አንጸባራቂን (ፀሐይ) አብሪ ጨረቃንም ያደረገ ጌታ ክብሩ በጣም ላቀ፡፡

እርሱም ያ (ያመለጠውን ሥራ) ማስታወስን ለሚፈልግ ወይም ማመስገንን ለሚፈልግ ሰው ሌሊትንና ቀንን ተተካኪ ያደረገ ነው፡፡

የአልረሕማንም ባሮች እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚኼዱት፣ ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሩዋቸው ጊዜ ሰላም የሚሉት ናቸው፡፡

እነዚያም ለጌታቸው በግንባራቸው ተደፊዎችና ቋሚዎች ኾነው የሚያድሩት ናቸው፡፡

እነዚያም «ጌታችን ሆይ! የገሀነምን ቅጣት ከእኛ ላይ መልስልን ቅጣቷ የማይለቅ ነውና» የሚሉት ናቸው፡፡

እርሷ መርጊያና መቀመጫ በመኾን ከፋች! (ይላሉ)፡፡

እነዚያም በለገሱ ጊዜ የማያባክኑ የማይቆጥቡትም ናቸው፡፡ በዚህም መካከል (ልግስናቸው) ትክክለኛ የኾነ ነው፡፡

እነዚያም ከአላህ ጋር ሌላን አምላክ የማይገዙት፣ ያችንም አላህ እርም ያደረጋትን ነፍስ ያለ ሕግ የማይገድሉት፣ የማያመነዝሩትም ናቸው፡፡ ይህንንም የሚሠራ ሰው ቅጣትን ያገኛል፡፡

በትንሣኤ ቀን ቅጣቱ ለእርሱ ይደራረባል፡፡ በእርሱም ውስጥ የተዋረደ ኾኖ ይኖራል፡፡

ተጸጽቶ የተመለሰና ያመነ መልካምንም ሥራ የሠራ ሰው ብቻ ሲቀር፡፡ እነዚያም አላህ መጥፎ ሥራዎቻቸውን በመልካም ሥራዎች ይለውጣል፡፡ አላህም እጅግ መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

ተጸጽቶ የተመለሰም ሰው መልካምንም የሠራ እርሱ የተወደደን መመለስ ወደ አላህ ይመለሳል፡፡

እነዚያም እብለትን የማይመሰክሩ፤ በውድቅ ቃልም (ተናጋሪ አጠገብ) ባለፉ ጊዜ የከበሩ ኾነው የሚያልፉት ናቸው፡፡

እነዚያም በጌታቸው አንቀጾች በተገሰጹ ጊዜ (የተረዱ ተቀባዮች ኾነው እንጂ) ደንቆሮዎችና ዕውሮች ኾነው በእርሷ ላይ የማይደፉት ናቸው፡፡

እነዚያም «ጌታችን ሆይ! ከሚስቶቻችንና ከዘሮቻችን ለዓይኖች መርጊያን ለእኛ ስጠን፡፡ አላህን ለሚፈሩትም መሪ አድርገን» የሚሉት ናቸው፡፡

እነዚያ በመታገሳቸው የገነትን ሰገነቶች ይምመነዳሉ፡፡ በእርሷም ውስጥ ውዳሴንና ሰላምታን ይስሰጣሉ፡፡

በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ኾነው (ይስሰጣሉ)፡፡ መርጊያና መኖሪያይቱ አማረች፡፡

«ጸሎታችሁ ባልነበረ ኖሮ ጌታዬ እናንተን ከምንም አይቆጥራችሁም ነበር፡፡ በእርግጥም አስተባበላችሁ፤ ወደ ፊትም (ቅጣቱ) ያዣችሁ ይኾናል» በላቸው፡፡
Icon