ترجمة سورة يوسف

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة يوسف باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


አ.ለ.ረ (አሊፍ ላም ራ) እነዚህ የገላጩ መጽሐፍ አንቀጾች ናቸው፡፡

እኛ (ፍቹን) ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን ሲሆን በእርግጥ አወረድነው፡፡

እኛ ይህንን ቁርኣን ወደ አንተ በማውረዳችን በጣም መልካም ዜናዎችን በአንተ ላይ እንተርክልሃለን፡፡ እነሆ ከእርሱ በፊት (ካለፉት ሕዝቦች ታሪክ) በእርግጥ ከዘንጊዎቹ ነበርክ፡፡

ዩሱፍ ለአባቱ፡- «አባቴ ሆይ! እኔ ዐስራ አንድ ከዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃንም (በሕልሜ) አየሁ፡፡ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡

(አባቱም) አለ «ልጄ ሆይ! ሕልምህን ለወንድሞችህ አታውራ፡፡ ላንተ ተንኮልን ይሰሩብሃልና፡፡ ሰይጣን ለሰው ግልጽ ጠላት ነውና፡፡»

«እንደዚሁም (እንዳየኸው) ጌታህ ይመርጥሃል፡፡ ከንግግሮችም ፍች ያስተምርሃል፡፡ ጸጋውንም ከአሁን በፊት በሁለቱ አባቶችህ በኢብራሂምና በኢስሐቅ ላይ እንዳሟላት በአንተ ላይና በያዕቆብ ዘሮችም ላይ ይሞላታል፡፡ ጌታህ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና፡፡»

በዩሱፍና በወንድሞቹ (ታሪኮች) ውስጥ ለጠያቂዎች ሁሉ በእርግጥ አስደናቂ ምልክቶች ነበሩ፡፡

(ወንድሞቹ) ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «እኛ ጭፍሮች ስንሆን ዩሱፍና ወንድሙ (ብንያም) ወደ አባታችን ከእኛ ይበልጥ የተወደዱ ናቸው፡፡ አባታችን በግልጽ ስህተት ውስጥ ነው፡፡

«ዩሱፍን ግደሉ፡፡ ወይም በ(ሩቅ) ምድር ላይ ጣሉት፡፡ ያባታችሁ ፊት ለእናንተ የግል ይኾናልና፡፡ ከእርሱም በኋላ መልካም ሕዝቦች ትሆናላችሁና» (ተባባሉ)፡፡

ከእነሱ አንድ ተናጋሪ «ዩሱፍን አትግደሉ ግን በጉድጓድ አዘቅት ጨለማ ውስጥ ጣሉት፤ ከተጓዢዎች አንዱ ያነሳዋልና፡፡ ሠሪዎች ብትኾኑ (በዚሁ ተብቃቁ) አላቸው፡፡

(እነሱም) አሉ «አባታችን ሆይ! በዩሱፍ ላይ ለምን አታምነንም እኛም ለእርሱ በእርግጥ አዛኞች ነን፡፡»

«ነገ ከእኛ ጋር ላከውና ይደሰት፤ ይጫወትም፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎች ነን፡፡»

«እኔ እርሱን (ዩሱፍን) ይዛችሁ መሌዳችሁ በእርግጥ ያሳዝነኛል፡፡ እናንተም ከእርሱ ዘንጊዎች ስትሆኑ ተኩላ ይበላዋል ብዬ እፈራለሁ» አላቸው፡፡

«እኛ ጭፍራዎች ሆነን ሳለን ተኩላ ቢበላውማ እኛ ያን ጊዜ በእርግጥ ከሳሪዎች ነን» አሉት፡፡

እርሱንም ይዘውት በሌዱና በጉድጓዱ ጨለማ አዘቅት ውስጥ እንዲያደርጉት በቆረጡ ጊዜ (ሐሳባቸውን ፈጸሙበት)፡፡ ወደእርሱም እነሱ የማያውቁ ሲሆኑ ይህንን ሥራቸውን በእርግጥ ትነግራቸዋለህ ስንል ላክንበት፡፡

አባታቸውንም በምሽት እያለቀሱ መጡት፡፡

«አባታችን ሆይ! እኛ (ለሩጫና ለውርወራ) ልንሽቀዳደም ሌድን፡፡ ዩሱፍንም ዕቃችን ዘንድ ተውነው፡፡ ወዲያውም ተኩላ በላው፡፡ አንተም እውነተኞች ብንሆንም የምታምነን አይደለህም» አሉ፡፡

በቀሚሱም ላይ የውሸትን ደም አመጡ፡፡ (አባታቸው) «አይደለም፤ ነፍሶቻችሁ (ውሸት) ነገርን ለእናንተ ሸለሙላችሁ፡፡ ስለዚህ መልካም ትዕግስት (ማድረግ አለብኝ) በምትሉትም ነገር ላይ መታገዣው አላህ ብቻ ነው» አለ፡፡

መንገደኞችም መጡ፡፡ ውሃ ቀጂያቸውንም ላኩ፡፡ አኮሊውንም (ወደ ጉድጓዱ) ሰደደ «የምስራች! ይህ ወጣት ልጅ ነው» አለ፡፡ ሸቀጥ አድርገውም ደበቁት፡፡ አላህም የሚሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡

በርካሽ ዋጋም በሚቆጠሩ ዲርሃሞች ሸጡት፡፡ በእርሱም ከቸልተኞቹ ነበሩ፡፡

ያም ከምስር የገዛው ሰው ለሚስቱ «መኖሪያውን አክብሪ፡፡ ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና» አላት፡፡ እንደዚሁም ለዩሱፍ (ገዥ ልናደርገውና) የሕልሞችንም ፍች ልናስተምረው በምድር ላይ አስመቸነው፡፡ አላህም በነገሩ ላይ አሸናፊ ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡

ጥንካሬውንም በደረሰ ጊዜ ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠነው፡፡ እንደዚሁም መልካም ሠሪዎችን ሁሉ እንመነዳለን፡፡

ያቺም እርሱ በቤቷ የነበረባት ሴት ከነፍሱ አባበለችው፡፡ ደጃፎቹንም ዘጋች፤ «ላንተ ተዘጋጅቼልሃለሁና ቶሎ ናም» አለችው፡፡ «በአላህ እጠበቃለሁ እርሱ (የገዛኝ) ጌታዬ ኑሮዬን ያሳመረልኝ ነውና፤ (አልከዳውም)፡፡ እነሆ! በደለኞች አይድኑም» አላት፡፡

በእርሱም በእርግጥ አሰበች፡፡ በእርሷም አሰበ፤ የጌታውን ማስረጃ ባላየ ኖሮ (የተፈጥሮ ፍላጎቱን ባረካ ነበር፤)፡፡ እንደዚሁ መጥፎ ነገርንና ኀጢአትን ከእርሱ ላይ ልንመልስለት (አስረጃችንን አሳየነው)፡፡ እርሱ ከተመረጡት ባሮቻችን ነውና፡፡

በሩንም ተሽቀዳደሙ ቀሚሱንም ከበስተኋላው ቀደደችው፡፡ ጌታዋንም (ባለቤቷን) እበሩ አጠገብ አገኙት፡፡ (ቀደም ብላ) «በባለቤትህ መጥፎን ያሰበ ሰው ቅጣቱ መታሰር ወይም አሳማሚ ስቃይ እንጂ ሌላ አይደለም» አለችው፡፡

(ዩሱፍም) «እርሷ ከነፍሴ አባበለችኝ» አለ፡፡ ከቤተሰቦቿም መስካሪ (እንዲህ ሲል) መሰከረ፡፡ «ቀሚሱ ከበስተፊት ተቀድዶ እንደሆነ እውነት ተናገረች፡፡ እርሱም ከውሸታሞቹ ነው፡፡

«ቀሚሱም ከበስተኋላ ተቀድዶ እንደሆነ ዋሸች፡፡ እርሱም ከእውነተኞቹ ነው፡፡»

ቀሚሱንም ከበስተኋላ ተቀድዶ ባየ ጊዜ «እርሱ (የተናገርሺው) ከተንኮላችሁ ነው (ሴቶች) ተንኮላችሁ በእርግጥ ብርቱ ነውና» አላት፡፡

«ዩሱፍ ሆይ! ከዚህ (ወሬ) ተከልከል፡፡ ለኃጢአትሽም ማርታን ለምኚ፡፡ አንቺ ከስህተተኞቹ ሆነሻልና» (አለ)፡፡

በከተማው ያሉ ሴቶችም «የዐዚዝ ሚስት ብላቴናዋን ከነፍሱ ታባብለዋለች፡፡ በእውነቱ ፍቅሩ ልቧን መቷታል፡፡ እኛ በግልጽ ስህተት ውስጥ ሆና በእርግጥ እናያታለን» አሉ፡፡

ሀሜታቸውንም በሰማች ጊዜ ወደነሱ ላከችባቸው፡፡ ምግብንም ለእነርሱ አዘጋጀችላቸው፡፡ ከእነሱ ለያንዳንዳቸውም ቢላዋን ሰጠች፡፡ በእነሱም ላይ «ውጣ» አለችው፡፡ ባዩትም ጊዜ አደነቁት፡፡ እጆቻቸውንም ቆረጡ፡፡ አላህም ጥራት ይገባው፡፡ ይህ ሰው አይደለም፡፡ ይህ ያማረ መልአክ እንጅ ሌላ አይደለም አሉ፡፡

«ታዲያ ይህ ያ በርሱ (ፍቅር) የዘለፋችሁኝ ነው፡፡ በእርግጥም ከነፍሱ አባበልኩት፡፡ እምቢ አለም፡፡ የማዘውንም ነገር ባይሠራ በእርግጥ ይታሰራል፡፡ ከወራዶቹም ይሆናል» አለች፡፡

«ጌታዬ ሆይ! ወደርሱ ከሚጠሩኝ ነገር (ከዝሙት) ይልቅ መታሰር ለእኔ የተወደደ ነው፡፡ ተንኮላቸውንም ከእኔ ላይ ባትመልስልኝ ወደነሱ እዘነበላለሁ፡፡ ከስህተተኞቹም እሆናለሁ» አለ፡፡

ጌታውም ጸሎቱን ተቀበለው፡፡ ተንኮላቸውንም ከእርሱ መለሰለት፡፡ እነሆ! እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡

ከዚያም ማስረጃዎቹን ካዩ በኋላ እስከጊዜ ድረስ እንዲያስሩት ለነሱ ታያቸው፡፡

ከእሱም ጋር ሁለት ጎበዞች እስር ቤቱ ገቡ፡፡ አንደኛቸው «እኔ በህልሜ የወይን ጠጅን ስጠምቅ አየሁ» አለ፡፡ ሌላውም፡- «እኔ በራሴ ላይ እንጀራን ተሸክሜ ከእሱ በራሪ (አሞራ) ስትበላ አየሁ፡፡ ፍቹን ንገረን፡፡ እኛ ከአሳማሪዎች ሆነህ እናይሃለንና» አሉት፡፡

(ዩሱፍም) አለ፡- «ማንኛውም የምትስሰጡት ምግብ ለናንተ ከመምጣቱ በፊት ፍቹን የምነግራችሁ ቢሆን እንጂ አይመጣላችሁም፡፡ ይኸ ጌታዬ ካሳወቀኝ ነገር ነው፤ እኔ በአላህ የማያምኑን እነርሱም መጨረሻይቱን ዓለም እነርሱ ከሓዲዎች የሆኑትን ሕዝቦች ሃይማኖት ትቻለሁ፡፡

«የአባቶቼንም የኢብራሂምንና የኢስሐቅን፣ የያዕቆብንም ሃይማኖት ተከትያለሁ፡፡ ለእኛ በአላህ ምንንም ማጋራት አይገባንም ያ (አለማጋራት) በእኛ ላይና በሰዎቹ ላይ የአላህ ችሮታ ነው፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያመሰግኑም፡፡

«የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! የተለያዩ አምላኮች ይሻላሉን ወይስ አሸናፊው አንዱ አላህ

«ከእርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዝዙም፡፡ አላህ በእርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም፡፡ ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም፡፡ እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትገዙ አዟል፡፡ ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡

«የወህኒ ቤት ጓደኞቼ ሆይ! አንደኛችሁማ ጌታውን (ንጉሡን) ጠጅ ያጠጣል፡፡ ሌላውማ ይሰቀላል፡፡ ከራሱም በራሪ (አሞራ) ትበላለች፡፡ ያ ፍቹን የምትጠይቁት ነገር ተፈጸመ፤» (አላቸው)፡፡

ለዚያም ከሁለቱ እርሱ የሚድን መሆኑን ለተጠራጠረው እጌታህ ዘንድ አስታውሰኝ አለው፡፡ ጌታውንም ከማስታወስ ሰይጣን አስረሳው፡፡ ለጥቂት ዓመታትም በወህኒ ቤቱ ውስጥ ቆየ፡፡

ንጉሡም «እኔ ሰባትን የሰቡ ላሞች ሰባት ከሲታዎች ሲበሏቸው ሰባትንም ለምለም ዘለላዎች ሌሎችንም ደረቆችን (ሲጠመጠሙባቸው በሕልሜ) አያለሁ፡፡ እናንተ ታላላቅ ሰዎች ሆይ! ሕልምን የምትፈቱ እንደሆናችሁ ሕልሜን ፍቱልኝ» አላቸው፡፡

«የሕልሞች ቅዠቶች ናቸው፡፡ እኛም የሕልሞችን ፍች ዐዋቂዎች አይደለንም» አሉት፡፡

ያም ከሁለቱ የዳነውና ከብዙ ጊዜ በኋላ (ዩሱፍን) ያስታወሰው ሰው «እኔ ፍቹን እነግራችኋለሁና ላኩኝ» አለ፤ (ወደ ዩሱፍ ሌደም)፡፡

«አንተ እውነተኛው ዩሱፍ ሆይ! ሰባትን የሰቡ ላሞች ሰባት ከሲታዎች ላሞች ሲበሉዋቸው ሰባትን ለምለም ዘለላዎችም ሌሎችንም ደረቆች (በነሱ ላይ ሲጠመጠሙባቸው ያየን ሰው ሕልም ፍች) ተችልን፡፡ ያውቁ ዘንድ ወደ ሰዎቹ ልመለስ እከጅላለሁና» (አለው)፡፡

(እርሱም) አለ፡- «ሰባትን የተከታተሉ ዓመታት ትዘራላችሁ፡፡ ያጨዳችሁትንም ሁሉ ከምትበሉት ጥቂት በስተቀር በዘለላው ውስጥ ተዉት፡፡

«ከዚያም ከእነዚያ በኋላ ካደለባችሁት ጥቂት ሲቀር ለእነሱ ያደለባችሁትን ሁሉ የሚበሉ ሰባት የችግር ዓመታት ይመጣሉ፡፡

«ከዚያም ከእነዚያ በኋላ ሰዎቹ በርሱ የሚዘነቡበት በርሱም (ወይንን) የሚጨምቁበት ዓመት ይመጣል፡፡»

ንጉሡም «እርሱን አምጡልኝ» አለ፡፡ መልክተኛውም (ዩሱፍን) በመጣው ጊዜ «ወደጌታህ ተመለስ፡፡ የዚያንም እጆቻቸውን የቆረጡትን ሴቶች ሁኔታ ጠይቀው፡፡ ጌታዬ ተንኮላቸውን ዐዋቂ ነውና» አለው፡፡

(ንጉሡም)፡- «ዩሱፍን ከነፍሱ ባባበላችሁት ጊዜ ነገራችሁ ምንድን ነው» አላቸው፡፡ «ለአላህ ጥራት ይገባው፡፡ በእርሱ ላይ ምንም መጥፎን ነገር አላወቅንም» አሉት፡፡ የዐዚዝ ሚስት፡-«አሁን እውነቱ ተገለጸ፡፡ እኔ ከነፍሱ አባበልኩት፡፡ እርሱም ከእውነተኞቹ ነው» አለች፡፡

(ዩሱፍ) «ይህ (ጌታዬ) ሩቅ ሆኖ ሳለ ያልከዳሁት መሆኔን አላህም የከዳተኞችን ተንኮል የማያቃና መሆኑን እንዲያውቅ ነው፤» (አለ)፡፡

«ነፍሴንም (ከስሕተት) አላጠራም፡፡ ነፍስ ሁሉ ጌታዬ የጠበቃት ካልሆነች በስተቀር በመጥፎ ነገር በእርግጥ አዛዥ ናትና፡፡ ጌታዬ በጣም መሓሪ አዛኝ ነው» (አለ)፡፡

ንጉሡም «እርሱን አምጡልኝ ለራሴ ግለኛ አደርገዋለሁና» አለ፡፡ ባናገረውም ጊዜ «አንተ ዛሬ እኛ ዘንድ ባለሟል ታማኝ ነህ» አለው፡፡

«በምድር ግምጃ ቤቶች ላይ (ሹም) አድርገኝ፡፡ እኔ ጠባቂ አዋቂ ነኝና» አለ፡፡

እንደዚሁም ለዩሱፍ በምድር ላይ ከእርሷ በፈለገው ስፍራ የሚሰፍር ሲሆን አስመቸነው፡፡ በችሮታችን የምንሻውን ሰው እንለያለን፡፡ የበጎ ሠሪዎችንም ዋጋ አናጠፋም፡፡

የመጨረሻይቱም ዓለም ምንዳ ለእነዚያ ላመኑትና ይጠነቀቁ ለነበሩት የበለጠ ነው፡፡

የዩሱፍ ወንድሞችም መጡ፡፡ በእርሱም ላይ ገቡ፡፡ እነሱም እርሱን የሳቱት ሲሆኑ ዐወቃቸው፡፡

(ጉዳያቸውን ፈጽሞ) ስንቃቸውንም ባዘጋጀላቸው ጊዜ አለ፡- «ከአባታችሁ በኩል የሆነውን ወንድማችሁን አምጡልኝ፡፡ እኔ ከአስተናጋጆች ሁሉ በላጭ ስሆን፤ ስፍርን የምሞላ መሆኔን አታዩምን

እርሱንም ባታመጡልኝ እኔ ዘንድ ለእናንተ ስፍር የላችሁም፤ አትቀርቡኝምም፡፡»

«ስለእርሱ አባቱን በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡ እኛም (ይህንን) በእርግጥ ሠሪዎች ነን» አሉት፡፡

ለአሽከሮቹም «ሸቀጣቸውን ወደ ቤተሰቦቻቸው በተመለሱ ጊዜ ያውቋት ዘንድ በየጓዞቻቸው ውስጥ አድርጉላቸው፡፡ ሊመለሱ ይከጀላልና» አላቸው፡፡

ወደ አባታቸውም በተመሰሉ ጊዜ፡- «አባታችን ሆይ! (ወንድማችንን እስከምንወስድ) ስፍር ከእኛ ተከልክሏል፡፡ ስለዚህ ወንድማችንን ከእኛ ጋር ላከው፡፡ ይሰፍርልናልና እኛም ለርሱ ጠባቂዎች ነን» አሉ፡፡

«ከአሁን በፊት በወንድሙ ላይ እንዳመንኳችሁ እንጂ በእርሱ ላይ አምናችኋለሁን አላህም በጠባቂነት (ከሁሉ) የበለጠ ነው፡፡ እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው፤» አላቸው፡፡

ዕቃቸውንም በከፈቱ ጊዜ ሸቀጣቸው ወደእነርሱ ተመልሳ አገኙ፡፡ ፡-«አባታችን ሆይ! ምን እንፈልጋለን ይህቺ ሸቀጣችን ናት፡፡ ወደኛ ተመልሳልናለች፤ (እንረዳባታለን)፡፡ ለቤተሰቦቻችንም እንሸምታለን፡፡ ወንድማችንንም እንጠብቃለን፡፡ የግመልንም ጭነት እንጨምራለን፡፡ ይህ (በንጉሡ ላይ) ቀላል ስፍር ነው» አሉ፡፡

«ካልተከበባችሁ በስተቀር እርሱን በእርግጥ የምታመጡልኝ ለመሆናችሁ ከአላህ የሆነን ቃል ኪዳን መተማመኛ እስከምትሰጡኝ ድረስ ከእናንተ ጋር ፈጽሞ አልልከውም» አላቸው፡፡ መተማመኛቸውንም በሰጡት ጊዜ «አላህ በምንለው ሁሉ ላይ ምስክር ነው» አላቸው፡፡

አለም «ልጆቼ ሆይ! በአንድ በር አትግቡ፡፡ ግን በተለዩ በሮች ግቡ፡፡ ከአላህም (ፍርድ) በምንም አልጠቅማችሁም፤ (አልመልስላችሁም)፡፡ ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም፡፡ በእርሱ ላይ ተመካሁ፡፡ ተመኪዎችም ሁሉ በእርሱ ብቻ ይመኩ፡፡»

አባታቸውም ካዘዛቸው ስፍራ በገቡ ጊዜ ከአላህ (ፍርድ) ምንም ነገር ከነርሱ የሚከለክልላቸው አልነበረም፡፡ ግን በያዕቆብም ነፍስ ውስጥ የነበረች ጉዳይ ናት፡፡ ፈጸማት፡፡ እርሱም ስላሳወቅነው የዕውቀት ባለቤት ነው፤ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡

በዩሱፍ ላይ በገቡ ጊዜም ወንድሙን ወደርሱ አስጠጋው፡፡ «እነሆ እኔ ወንድምህ ነኝ፡፡ ይሠሩት በነበሩትም ሁሉ አትቆላጭ» አለው፡፡

ዕቃቸውንም ባዘጋጀላቸው ጊዜ፤ ዋንጫይቱን በወንድሙ ዕቃ ውስጥ አደረገ፡፡ ከዚያም «እናንተ ባለ ግመሎች ሆይ! እናንተ በእርግጥ ሌቦች ናችሁ ሲል ጠሪ ተጣራ፡፡»

ወደነሱ ዞረውም «ምንድን ጠፋችሁ» አሉ፡፡

«የንጉሡ መስፈሪያ ጠፍቶናል፡፡ እርሱንም ላመጣ ሰው የግመል ጭነት አለው፡፡ እኔም በእርሱ ተያዥ ነኝ» አለ፡፡

«በአላህ እንምላለን በምድር ላይ ለማጥፋት እንዳልመጣን በእርግጥ ዐውቃችኋል፡፡ ሌቦችም አልነበርንም» አሉ፡፡

«ውሸታሞች ብትሆኑ ቅጣቱ ምንድን ነው» አሏቸው፡፡

«ቅጣቱ (በያዕቆብ ሕግ) ዕቃው በጓዙ ውስጥ የተገኘበት ሰው (ራሱ መወሰድ) ነው፡፡ እርሱም ቅጣቱ ነው፡፡ እንደዚሁ በደለኞችን እንቀጣለን» አሉ፡፡

(ምርመራውን) ከወንድሙም ዕቃ በፊት በዕቃዎቻቸው ጀመረ፡፡ ከዚያም (ዋንጫይቱን) ከወንድሙ ዕቃ ውስጥ አወጣት፡፡ እንደዚሁ ለዩሱፍ ብልሃትን አስተማርነው፡፡ አላህ ባልሻ ኖሮ በንጉሡ ሕግ ወንድሙን ሊይዝ አይገባውም ነበር፡፡ የምንሻውን ሰው በደረጃዎች ከፍ እናደርጋለን፡፡ ከዕውቀት ባለቤቶች ሁሉ በላይም ዐዋቂ አልለ፡፡

«ቢሰርቅ ከአሁን በፊት የርሱው ወንድም በእርግጥ ሰርቋል» አሉ፡፡ ዩሱፍም (ይህችን ንግግር) በነፍሱ ውስጥ ደበቃት፡፡ ለእነሱም አልገለጣትም፡፡ (በልቡ) «እናንተ ሥራችሁ የከፋ ነው፡፡ አላህም የምትሉትን ሁሉ ይበልጥ ዐዋቂ ነው» አለ፡፡

አንተ የተከበርከው ሆይ! «ለእርሱ በእርግጥ ታላቅ ሽማግሌ አባት አለው፡፡ ስለዚህ በእርሱ ስፍራ አንደኛችንን ያዝ፡፡ እኛ ከመልካም ሠሪዎች ሆነህ እናይሃለንና» አሉት፡፡

«ዕቃችንን እርሱ ዘንድ ያገኘንበትን ሰው እንጂ ሌላን ከመያዝ በአላህ እንጠብቃለን፡፡ እኛ ያን ጊዜ በእርግጥ በዳዮች ነን» አለ፡፡

ከርሱም ተስፋን በቆረጡ ጊዜ የሚመካከሩ ሆነው ገለል አሉ፡፡ ታላቃቸው አለ «አባታቸሁ በናንተ ላይ ከአላህ የሆነን መታመኛ ኪዳን በእርግጥ የያዘባችሁ መሆኑን ከዚህም በፊት በዩሱፍ ላይ ግፍ የሠራችሁትን አታውቁምን ስለዚህ አባቴ ለእኔ እስከሚፈቅድልኝ ወይም አላህ ለኔ እስከሚፈርድልኝ ድረስ የምስርን ምድር አልለይም፡፡ እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው፡፡

«ወደ አባታችሁ ተመለሱ በሉትም፡- አባታችን ሆይ! ልጅህ ሰረቀ፡፡ ባወቅነውም ነገር እንጂ አልመሰከርንም፡፡ ሩቁንም ነገር (ምስጢሩን) ዐዋቂዎች አልነበርንም፡፡

«ያችንም በውስጧ የነበርንባትን ከተማ ያችንም በውስጧ የመጣነውን ባለ ግመል ጓድ ጠይቅ፡፡ እኛም በእርግጥ እውነተኞች ነን፡፡»

(ያዕቆብ) «አይደለም ነፍሶቻችሁ አንዳች ነገርን ለእናንተ ሸለሙላችሁ፡፡ (ሠራችሁትም)፡፡ መልካምም ትእግስት (ማድረግ) አለብኝ፡፡ እነርሱን (ሦስቱንም) የተሰበሰቡ ሆነው አላህ ሊያመጣልኝ ይከጀላል፡፡ እነሆ እርሱ ዐዋቂ ጥበበኛ ነውና» አላቸው፡፡

ከእነሱም ዘወር አለናኣ«በዩሱፍ ላይ ዋ ሐዘኔ!» አለ፡፡ ዓይኖቹም ከሐዘን (ለቅሶ) የተነሳ ነጡ፡፡ እርሱም በትካዜ የተመላ ነው፡፡

(እነርሱም) «በአላህ እንምላለን፡፡ ለጥፋት የቀረብክ እስከምትሆን ወይም ከጠፊዎቹ እስከምትሆን ድረስ ዩሱፍን ከማውሳት አትወገድም» አሉ፡፡

«ጭንቀቴንና ሐዘኔንና የማሰሙተው ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡ ከአላህም በኩል የማታውቁትን ነገር ዐውቃለሁ» አላቸው፡፡

«ልጆቼ ሆይ! ሊዱ፤ ከዩሱፍና ከወንድሙም (ወሬ) ተመራመሩ፡፡ ከአላህም እዝነት ተስፋ አትቁረጡ፡፡ እነሆ ከአላህ እዝነት ከሓዲዎች ሕዝቦች እንጂ ተስፋ አይቆርጥም» (አለ)፡፡

በእርሱም ላይ በገቡ ጊዜ «አንተ የተከበርከው ሆይ! እኛንም ቤተሰቦቻችንንም ጉዳት ደረሰብን፡፡ ርካሽ ሸቀጥም ይዘን መጥተናል፡፡ ስፍርንም ለኛ ሙላልን፡፡ በኛም ላይ መጽውት አላህ መጽዋቾችን ይመነዳልና» አሉት፡፡

«እናንተ የማታውቁ በነበራችሁ ጊዜ በዩሱፍና በወንድሙ ላይ የሰራችሁትን ግፍ ዐወቃችሁን» አላቸው፡፡

«አንተ በእርግጥ አንተ ዩሱፍ ነህን» አሉት፡፡ «እኔ ዩሱፍ ነኝ፡፡ ይህም ወንድሜ ነው፡፡ አላህ በኛ ላይ በእርግጥ ለገሰልን፡፡ እነሆ! የሚጠነቀቅና የሚታገስ ሰው (አላህ ይክሰዋል)፡፡ አላህ የበጎ አድራጊዎችን ዋጋ አያጠፋምና» አለ፡፡

«በአላህ እንምላለን፡፡ አላህ በኛ ላይ በእርግጥ አበለጠህ፡፡ እኛም በእርግጥ አጥፊዎች ነበርን» አሉ፡፡

«ዛሬ በናንተ ላይ ወቀሳ የለባችሁም፡፡ አላህ ለእናንተ ይምራል፡፡ እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው» አላቸው፡፤

«ይህንን ቀሚሴን ይዛችሁ ሊዱ፡፡ በአባቴ ፊትም ጣሉት የሚያይ ሆኖ ይመጣልና፡፡ ቤተሰቦቻችሁንም ሰብስባችሁ አምጡልኝ» (አላቸው)፡፡

ግመል ጫኞቹም (ምስርን) በተለዩ ጊዜ አባታቸው «እኔ የዩሱፍን ሽታ በእርግጥ አገኛለሁ፡፡ ባታቄሉኝ ኖሮ (ታምኑኝ ነበር)» አለ፡፡

«በአላህ እንምላለን፡፡ አንተ በእርግጥ በቀድሞው ስህተትህ ውስጥ ነህ» አሉት፡፡

አብሳሪውም በመጣ ጊዜ (ቀሚሱን) በፊቱ ላይ ጣለው፡፡ ወዲውም የሚያይ ኾነ፡፡ «እኔ ለእናንተ፡- ከአላህ በኩል የማታውቁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን» አላቸው፡፡

«አባታችን ሆይ! ለኀጢአቶቻችን ምሕረትን ለምንልን እኛ ጥፋተኞች ነበርንና» አሉ፡፡

«ወደፊት ለእናንተ ጌታዬን ምሕረትን እለምንላችኋለሁ፡፡ እነሆ! እርሱ መሓሪው አዛኙ ነውና» አላቸው፡፤

በዩሱፍ ላይም በገቡ ጊዜ ወላጆቹን ወደርሱ አስጠጋቸው፡፡ «በአላህም ፈቃድ ጥብቆች ስትኾኑ ምስርን ግቡ» አላቸው፡፡

ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፡፡ ለእርሱም ሰጋጆች ኾነው ወረዱለት፡፡ «አባቴም ሆይ! ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፡፡ ጌታ በእርግጥ እውነት አደረጋት፡፡ ከወህኒ ቤትም ባወጣኝና ሰይጣንም በእኔና በወንድሞቼ መካከል ከአበላሸ በኋላ እናንተን ከገጠር ባመጣችሁ ጊዜ በእርግጥ ለኔ መልካም ዋለልኝ፡፡ ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው፡፡ እነሆ እሱ ዐዋቂው ጥበበኛው ነው» አለ፡፡

«ጌታዬ ሆይ! ከንግሥና በእርግጥ ሰጠኸኝ፡፡ ከሕልሞችም ፍች አስተማርከኝ፡፡ የሰማያትና የምድር ፈጣሪ ሆይ! አንተ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም ረዳቴ ነህ፡፡ ሙስሊም ሆኘ ግደለኝ፡፡ በመልካሞቹም አስጠጋኝ» (አለ)፡፡

(ሙሐመድ ሆይ) ይህ ወዳንተ የምናወርደው ሲኾን፤ ከሩቅ ወሬዎች ነው፡፡ አንተም እነርሱ (በዩሱፍ) የሚመክሩ ኾነው ነገራቸውን በቆረጡ ጊዜ እነሱ ዘንድ አልነበርክም፡፡

አብዛኛዎቹም ሰዎች (ለማመናቸው) ብትጓጓም የሚያምኑ አይደሉም፡፡

በእርሱም (በቁርአን) ላይ ምንም ዋጋ አትጠይቃቸውም፡፡ እርሱ ለዓለማት ግሳጼ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

በሰማያትና በምድርም ካለችው ምልክት ብዙይቱ እነሱ ከርሷ ዘንጊዎች ኾነው በርሷ ላይ ያልፋሉ፡፡

አብዛኞቻቸውም፤ እነሱ አጋሪዎች ኾነው እንጂ በአላህ አያምኑም፡፡

ከአላህ ቅጣት ሸፋኝ አደጋ የምትመጣባቸው ወይም ሰዓቲቱ እነሱ የማያውቁ ሲኾኑ በድንገት የምትመጣባቸው መኾኑዋን አይፈሩምን

«ይህች መንገዴ ናት፡፡ ወደ አላህ እጠራለሁ፡፡ እኔም የተከተለኝም ሰው በግልጽ ማስረጃ ላይ ነን፡፡ ጥራትም ለአላህ ይገባው፡፡ እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም» በል፡፡

ካንተ በፊትም ከከተሞች ሰዎች ወደነርሱ ራእይ የምናወርድላቸው የኾኑን ወንዶችን እንጂ አልላክንም፡፡ በምድር ላይ አይኼዱምና የእነዚያን ከእነሱ በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ አይመለከቱምን የመጨረሻይቱም አገር ለእነዚያ ለተጠነቀቁት በእርግጥ የተሻለች ናት፤ አታውቁምን

መልክተኞቹም ተስፋ በቆረጡና እነርሱ በእርግጥ የተዋሹ መኾናቸውን በተጠራጠሩ ጊዜ እርዳታችን መጣላቸው፡፡ (እኛ) የምንሻውም ሰው እንዲድን ተደረገ፡፡ ቅጣታችንም ከአጋሪዎቹ ሕዝቦች ላይ አይመለስም፡፡

በታሪካቸው ውስጥ ለአእምሮ ባለ ቤቶች በእርግጥ መገሰጫ ነበረ፡፡ (ይህ ቁርኣን) የሚቀጣጠፍ ወሬ አይደለም፡፡ ግን ያንን በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ለነገርም ሁሉ ገላጭ ለሚያምኑ ሕዝቦችም መሪና ችሮታ ነው፡፡
Icon