ترجمة سورة الدّخان

Sadiq and Sani - Amharic translation
ترجمة معاني سورة الدّخان باللغة الأمهرية من كتاب Sadiq and Sani - Amharic translation .


ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡

አብራሪ በኾነው መጽሐፍ እንምላለን፡፡

እኛ (ቁርኣኑን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው፡፡ እኛ አስፈራሪዎች ነበርንና፡፡

በውስጧ የተወሰነው ነገር ሁሉ ይልለያል፡፡

ከእኛ ዘንድ የኾነ ትእዛዝ ሲኾን (አወረድነው)፡፡ እኛ (መልክተኞችን) ላኪዎች ነበርን፡፡

ከጌታህ በኾነው ችሮታ (ተላኩ)፡፡ እነሆ እርሱ ሰሚው ዐዋቂው ነውና፡፡

የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ከኾነው (ተላኩ)፡፡ የምታረጋግጡ እንደኾናችሁ (ነገሩ እንዳልነው መኾኑን እወቁ)፡፡

ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ሕያው ያደርጋል፡፡ ይገድላልም፡፡ ጌታችሁ የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው፡፡

በእውነቱ እነርሱ የሚጫወቱ ሲኾኑ በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡

ሰማይም በግልጽ ጭስ የምትመጣበትን ቀን ተጠባበቅ፡፡

ሰዎችን የሚሸፍን (በኾነ ጭስ) ይህ አሳማሚ ቅጣት ነው፡፡

«ጌታችን ሆይ! ከእኛ ላይ ቅጣቱን ግለጥልን፡፡ እኛ አማኞች እንኾናለንና» (ይላሉም)፡፡

(ቅጣቱ በወረደ ጊዜ) ለእነርሱ መግገሰጽ እንዴት ይኖራቸዋል? አስረጅ መልክተኛ የመጣቸው ሲኾን (የካዱም ሲኾኑ)፡፡

ከዚያም ከእርሱ የዞሩ፤ (ከሰው) «የተሰተማረ ዕብድ ነው» ያሉም ሲኾኑ፡፡

እኛ ቅጣቱን ለጥቂት ጊዜ ገላጮች ነን፡፡ እናንተ (ወደ ክህደታችሁ) በእርግጥ ተመላሾች ናችሁ፡፡

ታላቂቱን ብርቱ አያያዝ በምንይዝበት ቀን፤ እኛ ተበቃዮች ነን፡፡

ከእነርሱም በፊት የፈርዖንን ሕዝቦች በእርግጥ ሞከርን፡፡ ክቡር መልእክተኛም መጣላቸው፡፡

«የአላህን ባሮች ወደኔ አድርሱ፡፡ እኔ ለእናንተ ታማኝ መልክተኛ ነኝና፡፡

«በአላህም ላይ አትኩሩ፡፡ እኔ ግልጽ የኾነን አስረጅ ያመጣሁላችሁ ነኝና (በማለት መጣላቸው)፡፡

«እኔም እንዳትወግሩኝ በጌታየና በጌታችሁ ተጠብቂያለሁ፡፡

«በእኔም ባታምኑ ራቁኝ» (ተዉኝ አለ)፡፡

ቀጥሎም (ስለ ዛቱበት) «እነዚህ አመጸኞች ሕዝቦች ናቸው» (አጥፋቸው) ሲል ጌታውን ለመነ፡፡

(ጌታው) «ባሮቼንም ይዘህ በሌሊት ኺድ፡፡ እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና፡፡

«ባሕሩንም የተከፈተ ኾኖ ተወው፡፡ እነርሱ የሚሰጥጠሙ ሰራዊት ናቸውና» (አለው)፡፡

ከአትክልቶችና ከምንጮችም ብዙ ነገሮችን ተዉ፡፡

ከአዝመራዎችም ከመልካም መቀመጫም፡፡

በእርሷ ተደሳቾች ከነበሩባትም ድሎት (ብዙን ነገር ተዉ)፡፡

(ነገሩ) እንደዚሁ ኾነ፡፡ ሌሎችንም ሕዝቦች አወረስናት፡፡

ሰማይና ምድርም በእነርሱ ላይ አላለቀሱም፡፡ የሚቆዩም አልነበሩም፡፡

የእስራኤልንም ልጆች አዋራጅ ከኾነ ስቃይ በእርግጥ አዳንናቸው፡፡

ከፈርዖን፤ እርሱ የኮራ ከወሰን አላፊዎቹ ነበርና፡፡

ከማወቅም ጋር በዓለማት ላይ በእርግጥ መረጥናቸው፡፡

ከታምራቶችም በውስጡ ግልጽ የኾነ ፈተና ያለበትን ሰጠናቸው፡፡

እነዚህ (የመካ ከሓዲዎች) በእርግጥ ይላሉ፡-

እርሷ የፊተኛይቱ ሞታችን እንጅ አይደለችም፡፡ እኛም የምንቀሰቀስ አይደለንም፡፡

እውነተኞችም እንደ ኾናችሁ አባቶቻችንን አምጡልን፡፡

እነርሱ በላጮች ናቸውን ወይስ የቱብበዕ ሕዝቦችና እነዚያ ከእነርሱ በፊት የነበሩት? አጠፋናቸው፡፡ እነርሱ አመጸኞች ነበሩና፡፡

ሰማያትንና ምድርንም በሁለቱ መካከል ያለውንም ሁሉ ቀላጆች ኾነን አልፈጠርንም፡፡

ሁለቱንም በምር እንጅ አልፈጠርናቸውም፡፡ ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም፡፡

የመለያው ቀን ለሁሉም ቀጠሯቸው ነው፡፡

ዘመድ ከዘመዱ ምንንም የማይጠቅምበት እነርሱም የማይርረዱበት ቀን ነው፡፡

አላህ ያዘነለት ሰውና ያመነ ብቻ ሲቀር፡፡ (እርሱስ ይርረዳል)፡፡ እርሱ አሸናፊው አዛኙ ነውና፡፡

የዘቁመ ዛፍ

የኀጢኣተኛው ምግብ ነው፡፡

እንደ ዘይት አተላ ነው፡፡ በሆዶች ውስጥ የሚፈላ ሲኾን፡፡

እንደ ገነፈለ ውሃ አፈላል (የሚፈላ ሲኾን)፡፡

ያዙት፤ ወደ ገሀነም መካከልም በኀይል ጎትቱት፡፡

ከዚያም «ከራሱ በላይ ከፈላ ውሃ ስቃይ አንቧቡበት፡፡»

«ቅመስ፤ አንተ አሸናፊው ክብሩ ነህና» (ይባላል)፡፡

«ይህ ያ በእርሱ ትጠራጠሩበት የነበራችሁት ነው» (ይባላሉ)፡፡

ጥንቁቆቹ በእርግጥ በጸጥተኛ መኖሪያ ውስጥ ናቸው፡፡

በአትክልቶችና በምንጮች ውስጥ ናቸው፡፡

ፊት ለፊት የተቅጣጩ ኾነው ከስስ ሐርና ከወፍራም ሐር ይለብሳሉ፡፡

(ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ ዓይናማዎች የኾኑን ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን፡፡

በእርሷም ውስጥ የተማመኑ ኾነው፤ ከፍራፍሬ ሁሉ ያዝዛሉ፡፡

የፊተኛይቱን ሞት እንጅ (ዳግመኛ) በእርሷ ውስጥ ሞትን አይቀምሱም፡፡ የገሀነምንም ቅጣት (አላህ) ጠበቃቸው፡፡

ከጌታህ በኾነ ችሮታ (ጠበቃቸው)፡፡ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው፡፡

(ቁርኣኑን) በቋንቋህም ያገራነው (ሕዝቦችህ) ይገነዘቡ ዘንድ ብቻ ነው፡፡

ተጠባበቅም እነርሱ ተጠባባቂዎች ናቸውና፡፡
Icon