ترجمة سورة الواقعة

الترجمة الأمهرية
ترجمة معاني سورة الواقعة باللغة الأمهرية من كتاب الترجمة الأمهرية .
من تأليف: محمد صادق ومحمد الثاني حبيب .

መከራይቱ በወደቀች ጊዜ፡፡
ለመውደቋ አስተባባይ (ነፍስ) የለችም፡፡
ዝቅ አድራጊና ከፍ አድራጊ ናት፡፡
ምድር መናወጥን በተናወጠች ጊዜ፡፡
ተራራዎችም መፍፈርፈርን በተፈረፈሩ ጊዜ (እንደተፈጨ ዱቄት በኾኑ ጊዜ)፡፡
የተበተነ ብናኝ በኾኑም ጊዜ
ሦስት ዓይነቶችም በኾናችሁ ጊዜ (ታዋርዳለች፤ ታነሳለችም)፡፡
የቀኝ ጓዶችም ምን (የተከበሩ) የቀኝ ጓዶች ናቸው፡፡
የግራ ጓዶችም ምን (የተዋረዱ) የግራ ጓዶች ናቸው፡፡
(ለበጎ ሥራ) ቀዳሚዎቹም (ለገነት) ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
እነዚያ ባለሟሎቹ ናቸው፡፡
በመጠቀሚያ ገነቶች ውስጥ ሲኾኑ፡፡
ከፊተኞቹ ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
ከኋለኞቹም ጥቂቶች ናቸው፡፡
በተታቱ አልጋዎች ላይ ይኾናሉ፡፡
በእርሷ ላይ የተመቻቹና ፊት ለፊት የተቅጣጩ ሲኾኑ፡፡
በእነርሱ ላይ ሁል ጊዜ የማያረጁ ወጣቶች ልጆች ይዘዋወራሉ፡፡
ከጠጅ ምንጭም በብርጭቆዎችና በኩስኩስቶች በጽዋም (በእነርሱ ላይ ይዝዞራሉ)፡፡
ከእርሷ የራስ ምታት አያገኛቸውም፤ አይሰክሩምም፡፡
ከሚመርጡትም ዓይነት በእሸቶች፡፡
ከሚሹትም በኾነ የበራሪ ሥጋ (ይዞሩባቸዋል)፡፡
ዓይናማዎች የኾኑ ነጫጭ ቆንጆዎችም አሏቸው፡፡
ልክ እንደተሸፈነ ሉል መሰሎች የኾኑ፡፡
በዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ዋጋ ይኾን ዘንድ (ይህንን አደረግንላቸው)፡፡
በውስጥዋ ውድቅ ንግግርንና መውወንጀልን አይሰሙም፡፡
ግን ሰላም መባባልን (ይሰማሉ)፡፡
የቀኝም ጓዶች ምንኛ (የከበሩ) የቀኝ ጓዶች!
በተቀፈቀፈ (እሾህ በሌለው) ቁርቁራ ውስጥ ናቸው፡፡
(ፍሬው) በተነባበረ በሙዝ ዛፍም፡፡
በተዘረጋ ጥላ ሥርም፡፡
በሚንቧቧ ውሃ አጠገብም፡፡
ብዙ (ዓይነት) በኾኑ ፍራፍሬዎችም፡፡
የማትቋረጥም የማትከለከልም የኾነች፡፡
ከፍ በተደረጉ ምንጣፎችም (ሴቶችም መካከል)፡፡
እኛ አዲስ ፍጥረት አድርገን (ለእነርሱ) ፈጠርናቸው፡፡
ደናግሎችም አደረግናቸው፡፡
ለባሎቻቸው ተሽሞርሟሪዎች እኩያዎች (አደረግናቸው)፡፡
ለቀኝ ጓዶች (አዘጋጀናቸው)፡፡
ከፊተኞቹ ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
ከኋለኞቹም ብዙ ጭፍሮች ናቸው፡፡
የግራ ጓደኞችም ምንኛ (የተዋረዱ) የግራ ጓዶች! ናቸው፡፡
በመርዛም ነፋስ በጣም በፈላ ውሃም ውስጥ ናቸው፡፡
ከጥቁር ጭስም በኾነ ጥላ ውስጥ፡፡
ቀዝቃዛም መልካምም ያልኾነ፡፡
እነርሱ ከዚህ በፊት ቅምጥሎች ነበሩና፡፡
በታላቅ ኀጢአትም ላይ ይዘወትሩ ነበሩና፡፡
ይሉም ነበሩ፡- «በሞትንና ዐፈር፣ ዐጥንቶችም በኾን ጊዜ እኛ በእርግጥ የምንቀሰቀስ ነን?
«የፊተኞቹ አባቶቻችንም?»
በላቸው፡- «ፊተኞቹም ኋለኞቹም፡፡
«በተወሰነ ቀን ቀጠሮ በእርግጥ ተሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
«ከዚያም እናንተ ጠማሞች አስተባባዮች ሆይ!
« ከዘቁም ዛፍ በእርግጥ በይዎች ናችሁ፡፡
«ከእርሷም ሆዶቻችሁን ሞይዎች ናችሁ፡፡
«በእርሱ ላይም ከፈላ ውሃ ጠጪዎች ናችሁ፡፡
«የተጠሙንም ግመሎች አጠጣጥ ብጤ ጠጪዎች ናችሁ፡፡»
ይህ በፍርዱ ቀን መስተንግዷቸው ነው፡፡
እኛ ፈጠርናችሁ አታምኑምን?
(በማኅፀኖች) የምታፈሱትን አያችሁን?
እናንተ ትፈጥሩታላችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹን ነን?
እኛ ሞትን (ጊዜውን) በመካከላችሁ ወሰንን፡፡ እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም፡፡
ብጤዎቻችሁን በመለወጥና በዚያ በማታውቁትም (ቅርጽ) እናንተን በመፍጠር ላይ (አንሸነፍም)፡፡
የፊተኛይቱንም አፈጣጠር በእርግጥ ዐውቃችኋል፡፡ አትገነዘቡምን?
የምትዘሩትንም አያችሁን?
እናንተ ታበቅሉታላችሁን? ወይስ እኛ አብቃዮቹ ነን?
ብነሻ ኖሮ ደረቅ ስብርብር ባደረግነውና የምትደነቁም በኾናችሁ ነበር፡፡
«እኛ በዕዳ ተያዦች ነን፡፡
«በእርግጥም እኛ (ከመጠቀም) የተከለከልን ነን» (ትሉ ነበር)፡፡
ያንንም የምትጠጡትን ውሃ አየችሁን?
እናንተ ከደመናው አወረዳችሁትን? ወይስ እኛ አውራጆቹ ነን?
ብንሻ ኖሮ መርጋጋ ባደረግነው ነበር፡፡ አታመሰግኑምን?
ያቺንም የምትሰብቋትን እሳት አያችሁን?
እናንተ ዛፏን ፈጠራችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎችዋ ነን?
እኛ (ለገሀናም) ማስታወሻ ለመንገደኞችም መጠቀሚያ አደረግናት፡፡
የታላቁን ጌታህንም ስም አወድስ፡፡
በከዋክብትም መጥለቂያዎች እምላለሁ፡፡
እርሱም ብታወቁ ታላቅ መሓላ ነው፡፡
እርሱ የከበረ ቁርኣን ነው፡፡
በተጠበቀ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡
የተጥራሩት እንጅ ሌላ አይነካውም፡፡
ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡
በዚህ ንግግር እናንተ ቸልተኞች ናችሁን?
ሲሳያችሁንም (ዝናምን) እናንተ የምታስተባብሉት ታደርጋላችሁን?
(ነፍስ) ጉረሮንም በደረሰች ጊዜ፡፡
እናንተ ያን ጊዜ የምታዩ ስትኾኑ፡፡
እኛም ግን አታዩም እንጅ ከእናንተ ይልቅ ወደእርሱ የቀረብን ስንኾን፡፡
የማትዳኙም ከኾናችሁ፡፡
እውነተኞች እንደ ኾናችሁ (ነፍሲቱን ወደ አካሉ) ለምን አትመልሷትም፡፡
(ሟቹ) ከባለሟሎቹ ቢኾንማ፡፡
(ለእርሱ) ዕረፍት፣ መልካም ሲሳይም፣ የመጠቀሚያ ገነትም አልለው፡፡
ከቀኝ ጓዶችም ቢኾንማ፡፡
ከቀኝ ጓዶች ስለ ኾንክ ላንተ ሰላም አልለህ (ይባላል)፡፡
ከሚያስዋሹት ጠማማዎችም ቢኾንማ፡፡
ከፈላ ውሃ የኾነ መስተንግዶ አልለው፡፡
በገሀነም መቃጠልም (አልለው)፡፡
ይህ እርሱ እርግጠኛ እውነት ነው፡፡
የታላቁንም ጌታህን ስም አወድስ፡፡
Icon